በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ያህ ድነቴ ሆነልኝ’

‘ያህ ድነቴ ሆነልኝ’

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

‘ያህ ድነቴ ሆነልኝ’

የይሖዋ ሕዝቦች ከፊታቸው ምርጫ ተደቅኖባቸዋል። ክፉ ለሆነው ለጥንቱ የግብጽ ገዢ ይታዘዙ ይሆን? ወይስ ይሖዋ አምላክን በመታዘዝ በባርነት ይማቅቁ የነበሩበትን ቦታ ለቅቀው ተስፋይቱን ምድር ይወርሱ ይሆን?

እብሪተኛ የነበረው የግብጹ ንጉሥ ፈርዖን የይሖዋን ሕዝቦች አልለቅም በማለቱ አምላክ አሥር መቅሰፍቶችን በምድሩ ላይ አመጣበት። ይህ የይሖዋን ኃይል የሚያሳይ ድርጊት ነበር! የግብጻውያን አማልክት እነዚህን መቅሰፍቶች ለመቋቋም ምንም ነገር ማድረግ አልቻሉም።

ፈርዖን የአምላክን ሕዝቦች እንዲለቅ በተነገረው ጊዜ “‘እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር ማነው?’ እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” በማለት በንቀት ተናገረ። (ዘፀአት 5:​2) በዚህም ምክንያት ይሖዋ በግብጻውያን ላይ የሚከተሉትን መቅሰፍቶች አወረደባቸው:- (1) የውኃ ወደ ደም መለወጥ፣ (2) ጓጉንቸሮች፣ (3) ተባዮች፣ (4) የዝንብ መንጋ፣ (5) የእንስሳት እልቂት፣ (6) በሰዎችና በእንስሳት ላይ የሚወጣ እባጭ፣ (7) በረዶ፣ (8) የአንበጣ መንጋ፣ (9) ጨለማ እንዲሁም (10) የፈርዖንን ልጅ ጨምሮ የግብጽ በኩሮች በሙሉ መሞት። በመጨረሻም ፈርዖን ዕብራውያኑን ለቀቃቸው። እንዲያውም አገሩን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላለፈ!​—⁠ዘፀአት 12:​31, 32

ብዙ ድብልቅ ሕዝቦችን ጨምሮ በጠቅላላ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ እስራኤላውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ወዲያውኑ ወጡ። (ዘፀአት 12:​37, 38) ብዙም ሳይቆይ ግን ፈርዖን ኃይለኛ የሆነውን ሠራዊቱን አስከትሎ ያሳድዳቸው ጀመር። እስራኤላውያን ከፊታቸው ባለው በቀይ ባሕር፣ ከኋላቸው በሚከተላቸው የፈርዖን ሠራዊትና ጭው ባለው በረሃ የተነሣ መውጫ መንገድ ያጡ ይመስላል። እንደዛም ሆኖ ሙሴ ለሕዝቡ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ” አላቸው።​—⁠ዘፀአት 14:​8-14

ይሖዋ እስራኤላውያን መሸሽ እንዲችሉ በተአምራዊ መንገድ ቀይ ባሕርን ለሁለት ከፈለው። ሆኖም ግብጻውያን ተከትለዋቸው መግባት ሲጀምሩ አምላክ ውኃውን ወደ ቦታው መለሰው። “የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣ [ይሖዋ] ባሕር ውስጥ ጣላቸው።” (ዘፀአት 14:​26-28፤ 15:​4) ትዕቢተኛው ፈርዖን ይሖዋን ለማክበር አሻፈረኝ ማለቱ ለጥፋት ዳረገው።

ይሖዋ በቀይ ባሕር “ተዋጊ” መሆኑን አስመስክሯል። (ዘፀአት 15:​3) ቅዱስ ጽሑፉ “እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔር . . . አመኑ” በማለት ይዘግባል። (ዘፀአት 14:​31፤ መዝሙር 136:​10-15) ወንዶቹ ከሙሴ ጋር የድል መዝሙር የዘመሩ ሲሆን ማርያምና ሌሎች ሴቶችም በጭፈራ በማጀብ ለአምላክ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል። a

ይሖዋ አሁንም ነጻ አውጪ አምላክ ነው

በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ከወሰደው ታላቅ እርምጃ እምነት የሚገነቡ ትምህርቶችን ሊያገኙ ይችላሉ። ልናውቀው የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ይሖዋ ገደብ የሌለው ኃይል ያለው እና ሕዝቦቹን ሙሉ በሙሉ ሊረዳ የሚችል አምላክ መሆኑን ነው። ሙሴና እስራኤላውያን በድል አድራጊነት መንፈስ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ” በማለት በደስታ ዘምረዋል።​—⁠ዘፀአት 15:​6

ሌላው የምንማረው ነገር ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ጥልቅ ፍላጎት ያለው መሆኑን ነው። እስራኤላውያን “እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ ድነቴም ሆነልኝ፤ እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ” እያሉ ዘምረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አምላክን ፈቃድ በመቃወም ረገድ የሚሳካለት እንደማይኖር ትምህርት እናገኛለን። አምላክ ነጻ ያወጣቸው ሕዝቦች በድል መዝሙራቸው ላይ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ?” በማለት ዘምረዋል።​—⁠ዘፀአት 15:​2, 11

የጥንቷ ግብጽ ንጉሥ እንደነበረው እንደ ፈርዖን በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ገዢዎችም የይሖዋን ሕዝቦች ያሳድዳሉ። እብሪተኛ መሪዎች ‘በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ሊናገሩና የልዑልንም ቅዱሳን ሊያስጨንቁ’ ይችላሉ። (ዳንኤል 7:​25፤ 11:​36) ሆኖም ይሖዋ ለሕዝቦቹ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል።​—⁠ኢሳይያስ 54:​17

ፈርዖንና ሠራዊቱ እንዳልተሳካላቸው ሁሉ የአምላክ ተቃዋሚዎች የሆኑ ሁሉ አይሳካላቸውም። ይሖዋ ሕዝቦቹን ከግብጽ ነጻ ለማውጣት እንደወሰደው ያሉ እርምጃዎች፣ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” በማለት የተናገሩትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መከተል ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 5:​29

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ጥር/የካቲት የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ያውቁ ኖሯል?

• ይሖዋ ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ ነፋስ እንዲነፍስ በማድረግ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን በደረቅ መሬት እንዲሻገሩ አስችሏቸዋል።​—⁠ዘፀአት 14:​21, 22

• በሚሊዮን የሚቆጠሩት እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን በዚያ አጭር ጊዜ ለማቋረጥ 1.5 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ስፋት ያለው መተላለፊያ ያስፈልጋቸው ነበር።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግብጽ ሐሰተኛ አማልክት ከይሖዋ የመጡትን አሥሩን መቅሰፍቶች ለማቆም አልቻሉም

[ምንጭ]

ሦስቱም ምስሎች:- Photograph taken by courtesy of the British Museum