በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት

ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት

ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት

“ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።”​—⁠ኤፌሶን 4:27 የ1954 ትርጉም

1. ብዙዎች የዲያብሎስን ሕልውና የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?

 ለበርካታ ዘመናት ብዙዎች ዲያብሎስ ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ክፉ ሰዎችን በመንሽ ወደ እሳታማ ሲኦል የሚወረውር፣ ቀይ ልብስ የለበሰ፣ ቀንድ ያለውና ሰኮናው የተሰነጠቀ ፍጡር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሐሳብ አይደግፍም። ሆኖም እንዲህ ያለው የተሳሳተ ሐሳብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዲያብሎስን ሕልውና እንዲጠራጠሩ ወይም ይህ ቃል የሚያመለክተው የክፋት ሐሳብን ብቻ እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጓል።

2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዲያብሎስ ምን ይላል?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ መኖሩን የሚያረጋግጥ በዓይን ምሥክር የተደገፈና ግልጽ የሆነ ማስረጃ ይሰጠናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ እያለ የተመለከተው ከመሆኑም በላይ ምድር በነበረበት ወቅት አነጋግሮታል። (ኢዮብ 1:6፤ ማቴዎስ 4:4-11) ቅዱሳን ጽሑፎች የዚህን መንፈሳዊ ፍጡር የመጀመሪያ ስም ባይገልጹም የአምላክን ስም በማጥፋቱ ዲያብሎስ (“ስም አጥፊ” ማለት ነው) እንዲሁም ይሖዋን በመቃወሙ ሰይጣን (“ተቃዋሚ” ማለት ነው) ብለው ይጠሩታል። ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ሔዋንን ለማሳት በእባብ ስለተጠቀመ ሳይሆን አይቀርም “የጥንቱ እባብ” ተብሏል። (ራእይ 12:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14) ከዚህም በተጨማሪ “ክፉው” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።​—⁠ማቴዎስ 6:​13 a

3. የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?

3 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የእርሱ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ሰይጣንን መምሰል እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ስለዚህ “ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 4:27 የ1954 ትርጉም ) ይህ ከሆነ ታዲያ ልንርቃቸው የሚገቡን አንዳንዶቹ የሰይጣን ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

ታላቁን ስም አጥፊ አትምሰሉ

4. “ክፉው” የአምላክን ስም ያጠፋው እንዴት ነው?

4 “ክፉው” ተብሎ የተጠራው ሰይጣን ስም አጥፊ በመሆኑ ዲያብሎስ የሚል ስያሜ ማግኘቱ ተገቢ ነው። ስም ማጥፋት ሲባል የሌላውን ሰው ስም ማጉደፍና ተንኰል ያዘለ የሐሰት ወሬ መንዛት ማለት ነው። አምላክ ለአዳም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” የሚል መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ሔዋንም ይህንን ትእዛዝ ታውቅ ነበር፤ ሆኖም ዲያብሎስ በእባብ አማካኝነት እንዲህ አላት:- “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍጥረት 3:4, 5) ይህ የይሖዋ አምላክን ስም የሚያጎድፍ ተንኰል አዘል ንግግር ነበር!

5. ዲዮጥራጢስ በስም አጥፊነት ሊጠየቅ የሚገባው ለምን ነበር?

5 እስራኤላውያን “በሕዝብህ መካከል እየዞርህ የስም አጥፊነት ወሬ አታሰራጭ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:16 የ1980 ትርጉም ) ሐዋርያው ዮሐንስም በዘመኑ ስለነበረ አንድ ስም አጥፊ ሰው ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ መሆን የሚወደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ።” (3 ዮሐንስ 9, 10) ዲዮጥራጢስ የዮሐንስን ስም እያጠፋ ስለነበረ ለፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። ከታማኝ ክርስቲያኖች መካከል እንደ ዲዮጥራጢስ መሆንና ታላቁን ስም አጥፊ ሰይጣንን መምሰል የሚፈልግ ማን ይኖራል?

6, 7. የሌሎችን ስም ማጥፋት የማንፈልገው ለምንድን ነው?

6 ብዙውን ጊዜ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ስም ለማጥፋት የታቀዱ ትችቶችና የሐሰት ውንጀላዎች ይሰነዘሩባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው [ኢየሱስን] በብርቱ ይወነጅሉት ነበር” ይላል። (ሉቃስ 23:10) ጳውሎስም፣ በሊቀ ካህናቱ በሐናንያና በሌሎች ሰዎች በሐሰት ተከስሶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 24:1-8) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ” በማለት ጠርቶታል። (ራእይ 12:10) እዚህ ላይ በሐሰት እንደተከሰሱ የተገለጹት ወንድሞች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በምድር ላይ የሚኖሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ናቸው።

7 ማንኛውም ክርስቲያን የሌሎችን ስም ማጥፋትም ሆነ በሐሰት መወንጀል አይፈልግም። ያም ሆኖ ግን የተሟላ መረጃ ሳይኖረን በሌሎች ላይ ከመሰከርን እንዲህ ልናደርግ እንችላለን። በሙሴ ሕግ መሠረት ሆን ብሎ በሌሎች ላይ በሐሰት የመሰከረ ሰው በሞት ሊቀጣ ይችል ነበር። (ዘፀአት 20:16፤ ዘዳግም 19:15-19) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ከሚጸየፋቸው ነገሮች አንዱ “በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር” ነው። (ምሳሌ 6:16-19) እንግዲያው ቀንደኛውን ስም አጥፊና ሐሰተኛ ከሳሽ መምሰል እንደማንፈልግ ግልጽ ነው።

የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ራቁ

8. ዲያብሎስ “ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ” የነበረው በምን መንገድ ነው?

8 ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይ ነው። ኢየሱስ “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር” ብሏል። (ዮሐንስ 8:44) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ እንዲያምጹ ካደረገበት የመጀመሪያ ድርጊቱ ጀምሮ ሰይጣን ነፍሰ ገዳይ ሆኗል። በመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስትም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ሞትን አምጥቷል። (ሮሜ 5:12) ይህንን ማድረግ የሚችለው ደግሞ በሰው ውስጥ ያለ ክፉ ሐሳብ ሳይሆን አንድ ግለሰብ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል።

9. በ1 ዮሐንስ 3:​15 ላይ እንደተገለጸው ነፍሰ ገዳይ ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

9 ለእስራኤላውያን ከተሰጡት አሥር ትእዛዛት አንዱ “አትግደል” ይላል። (ዘዳግም 5:17) ሐዋርያው ጴጥሮስም ለክርስቲያኖች ሲጽፍ “ማንም . . . ነፍሰ ገዳይ . . . ሆኖ መከራን አይቀበል” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 4:15) ስለዚህ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የሰው ሕይወት አናጠፋም። ሆኖም አንድን ክርስቲያን የምንጠላውና እንዲሞት የምንመኝ ከሆነ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንሆናለን። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 3:15) እስራኤላውያን “ወንድምህን በልብህ አትጥላው” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:17) እንግዲያው፣ ነፍሰ ገዳዩ ሰይጣን ክርስቲያናዊ አንድነታችንን እንዳያጠፋው በእኛና በእምነት ባልንጀራችን መካከል ችግር ሲፈጠር ጊዜ ሳንሰጥ እንፍታው።​—⁠ሉቃስ 17:3, 4

የሐሰትን አባት ተቃወሙት

10, 11. የሐሰት አባት የሆነውን ሰይጣንን ለመቃወም ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 ዲያብሎስ ውሸታም ነው። ኢየሱስ “እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 8:​44) ሰይጣን ሔዋንን የዋሻት ሲሆን ኢየሱስ ግን ወደ ምድር የመጣው ስለ እውነት ለመመስከር ነበር። (ዮሐንስ 18:37) የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ዲያብሎስን በመቃወም ለመጽናት ከፈለግን ከውሸትና ከማታለል መራቅ እንዲሁም ‘እውነት መናገር’ ይኖርብናል። (ዘካርያስ 8:16፤ ኤፌሶን 4:25) “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ የሚባርከው እውነተኛ የሆኑ ምሥክሮቹን ብቻ ነው። ክፉዎች እርሱን የመወከል መብት የላቸውም።​—⁠መዝሙር 31:5፤ 50:16፤ ኢሳይያስ 43:​10

11 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማወቃችን ምክንያት ከሰይጣን ውሸቶች ነጻ መውጣታችንን የምናደንቅ ከሆነ “የእውነት መንገድ” የሆነውን ክርስትናን አጥብቀን እንይዛለን። (2 ጴጥሮስ 2:2፤ ዮሐንስ 8:32) አጠቃላዩ የክርስትና ትምህርት “የወንጌል እውነት” ነው። (ገላትያ 2:5, 14) መዳናችን፣ ‘በእውነት በመመላለሳችን’ ማለትም ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖራችንና ‘የሐሰትን አባት’ በመቃወማችን ላይ የተመካ ነው።​—⁠3 ዮሐንስ 3, 4, 8

ቀንደኛውን ከሃዲ ተቃወሙት

12, 13. ለከሃዲዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

12 ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ የሆነው መንፈሳዊ ፍጡር በአንድ ወቅት በእውነት ውስጥ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው “በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም።” (ዮሐንስ 8:44) ይህ ቀንደኛ ከሃዲ “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ያለማቋረጥ ሲቃወመው ቆይቷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተታልለው ከእውነት በመራቃቸው ‘በዲያብሎስ ወጥመድ’ ተይዘው የጥቃቱ ሰለባዎች ሆነው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ፣ እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ ማገገምና ከሰይጣን ወጥመድ ነጻ መውጣት እንዲችሉ በየዋህነት እንዲመራቸው የሥራ ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:23-26) እርግጥ ነው፣ መጀመሪያውኑም ቢሆን እውነትን አጥብቆ መያዙና በክህደት አመለካከት አለመጠመዱ በጣም የተሻለ ነው።

13 የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ዲያብሎስን በመስማታቸውና የውሸት ሐሳቦቹን በመቀበላቸው ከሃዲዎች ሆነዋል። እኛስ ከሃዲዎችን መስማት፣ ጽሑፎቻቸውን ማንበብ ወይም የኢንተርኔት ድረ ገጻቸውን መመልከት ይኖርብናል? አምላክንና እውነትን የምንወድ ከሆነ እንዲህ አናደርግም። ‘የክፉ ሥራቸው ተባባሪ’ መሆን ስለማንፈልግ ከሃዲዎች ወደ ቤታችን እንዲመጡ መፍቀድ አይኖርብንም፤ ሌላው ቀርቶ ሰላምም እንኳ አንላቸውም። (2 ዮሐንስ 9-11) “ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት” የሚያስገቡና ‘በፈጠራ ታሪካቸው ሊበዘብዙን’ የሚሞክሩ ሐሰተኛ መምህራንን በመከተል የክርስትናን “የእውነት መንገድ” ትተን በዲያብሎስ የተንኰል ወጥመድ ፈጽሞ መውደቅ የለብንም።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​1-3

14, 15. ጳውሎስ ከኤፌሶን ለመጡ ሽማግሌዎችና የአገልግሎት ባልደረባው ለሆነው ለጢሞቴዎስ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?

14 ጳውሎስ ከኤፌሶን የመጡ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ። እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 20:28-30) ከጊዜ በኋላ እንዲህ ያለው ክህደት የተነሳ ሲሆን ‘እውነትንም አጣሞታል።’

15 በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእውነትን ቃል በትክክል እንዲያስረዳ’ ለጢሞቴዎስ ማሳሰቢያ ሰጥቶት ነበር። ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከንቱ ልፍለፋ ራቅ፤ በዚህ ነገር የተጠመዱ ሰዎች ከእግዚአብሔር እየራቁ ይሄዳሉና። ትምህርታቸው እንደማይሽር ቍስል ይሠራጫል፤ ከእነዚህም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ፤ እነዚህም ከእውነት ርቀው የሚባዝኑ ናቸው። እነርሱም ትንሣኤ ሙታን ከዚህ በፊት ሆኖአል እያሉ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣሉ።” ክህደት ጀምሮ ነበር! ጳውሎስ አክሎም “ይሁን እንጂ . . . የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል” ብሏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:15-19

16. ቀንደኛው ከሃዲ ሰይጣን የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን ቢጠቀምም ለአምላክና ለቃሉ ታማኝ ሆነን ለመመላለስ የቻልነው እንዴት ነው?

16 ሰይጣን በከሃዲዎች በመጠቀም እውነተኛውን አምልኮ ለመበረዝ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሙከራው ፍሬ ቢስ ሆኗል። በ1868 አካባቢ ቻርልስ ቴዝ ራስል፣ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ተቀባይነት አግኝተው የነበሩ መሠረተ ትምህርቶችን በጥንቃቄ ሲመረምር የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚያዛቡ ትምህርቶች እንዳሉ ተገነዘበ። ራስል እውነትን ከተጠሙ ሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋር በመሆን በፒተርስበርግ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋመ። ከዚያን ጊዜ በኋላ ባለፉት ወደ 140 የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ የይሖዋ አገልጋዮች እውቀታቸው እንዲሁም ለአምላክና ለቃሉ ያላቸው ፍቅር ጨምሯል። ቀንደኛው ከሃዲ የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን የሚጠቀም ቢሆንም ታማኝና ልባም ባሪያ በመንፈሳዊ ንቁ መሆኑ እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለይሖዋም ሆነ ለቃሉ ታማኝ ሆነው እንዲመላለሱ አስችሏቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​45 የ1954 ትርጉም 

የዚህ ዓለም ገዥ እንዲቆጣጠራችሁ ፈጽሞ አትፍቀዱ

17-19. በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ምንድን ነው? ይህንን ዓለም መውደድ የሌለብንስ ለምንድን ነው?

17 ሰይጣን እኛን ለማጥመድ የሚጠቀምበት ሌላው ዘዴ ይህን ዓለም ማለትም ከአምላክ የራቀውንና የክፋት ጎዳና የሚከተለውን የሰው ዘር ኅብረተሰብ እንድንወድ ማድረግ ነው። ኢየሱስ፣ ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት የጠራው ሲሆን “በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:​30) እኛም ሰይጣን እንዲቆጣጠረን ፈጽሞ አንፍቀድለት! ‘ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን።’ (1 ዮሐንስ 5:​19) ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ወድቆ ቢሰግድለት “የዓለምን መንግሥታት” ሁሉ እንደሚሰጠው ቃል የገባለት ዓለም በእርሱ ቁጥጥር ሥር ስላለ ነው፤ የአምላክ ልጅ ግን ይህንን ግብዣ እንደማይቀበል ቁርጥ ባለ መንገድ ነግሮታል። (ማቴዎስ 4:​8-10) በሰይጣን የሚገዛው ይህ ዓለም የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላቸዋል። (ዮሐንስ 15:​18-21) ሐዋርያው ዮሐንስ ዓለምን እንዳንወድ ያሳሰበን መሆኑ ምንም አያስገርምም!

18 ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:15-17) በዓለም ላይ የሚታየው የአኗኗር ዘይቤ ኃጢአተኛ ለሆነው ሥጋችን ማራኪ በመሆኑና ከይሖዋ አምላክ መሥፈርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ስለሚጋጭ ዓለምን መውደድ የለብንም።

19 ሆኖም በልባችን ውስጥ ዓለምን የመውደድ ዝንባሌ እንዳለ ብንገነዘብስ? አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሥጋዊ ፍላጎቶችን ማስወገድ እንድንችል እንዲረዳን እንጸልይ። (ገላትያ 5:16-21) ከጽድቅ የራቀውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ በማይታይ ሁኔታ ‘የሚገዙት የርኩሳን መናፍስት ሰራዊት’ መሆናቸውን ካስታወስን ራሳችንን “ከዓለም ርኩሰት” ለመጠበቅ ጥረት እንደምናደርግ ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠ያዕቆብ 1:27፤ ኤፌሶን 6:11, 12፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4

20. ክርስቲያኖች “ከዓለም አይደሉም” ሊባልልን የሚችለው ለም​ንድን ነው?

20 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ “እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችና ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አጋሮቻቸው በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ ለመሆንና ራሳቸውን ከዓለም ለመለየት ይጥራሉ። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14፤ ያዕቆብ 4:4) ከዓለም በመለየታችንና “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆናችን ከጽድቅ የራቀው ይህ ዓለም ይጠላናል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ሴሰኞች፣ አመንዝሮች፣ ቀማኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ሌቦች፣ ውሸታሞችና ሰካራሞች በሚገኙበት ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ እንደምንኖር አይካድም። (1 ቆሮንቶስ 5:9-11፤ 6:9-11፤ ራእይ 21:8) ያም ሆኖ ግን ዓለምን የተቆጣጠረው የኃጢአት ዝንባሌ ስለማይመራን “የዓለምን መንፈስ” አንተነፍስም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​12

ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት

21, 22. በኤፌሶን 4:​26, 27 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

21 ‘የዓለም መንፈስ’ እንዲቆጣጠረን ከመፍቀድ ይልቅ በአምላክ መንፈስ እንመራለን፤ ይህ መንፈስ ደግሞ እንደ ፍቅርና ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት እንድናፈራ ያደርገናል። (ገላትያ 5:22, 23) እነዚህ ባሕርያት ዲያብሎስ በእምነታችን ላይ የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች ለመቋቋም ያስችሉናል። እርሱ ቁጣ ‘ወደ እኩይ ተግባር’ እንዲመራን ማድረግ ይፈልጋል፤ የአምላክ መንፈስ ግን ‘ከንዴት እንድንቆጠብና ቍጣን እንድንተው’ ይረዳናል። (መዝሙር 37:​8) እውነት ነው፣ አልፎ አልፎ እንድንቆጣ የሚያደርገን በቂ ምክንያት ይኖረን ይሆናል፤ ሆኖም ጳውሎስ “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት” የሚል ምክር ሰጥቶናል።​—⁠ኤፌሶን 4:26, 27

22 ተቆጥተን ከቆየን ቁጣችን ኃጢአት እንድንሠራ ሊያደርገን ይችላል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ መቆየታችን ዲያብሎስ በጉባኤው ውስጥ አለመግባባት ለመፍጠር የሚያስችል አሊያም ደግሞ መጥፎ ነገር እንድንሠራ ለማነሳሳት የሚያመች አጋጣሚ ይከፍትለታል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ ችግሩን ጊዜ ሳናጠፋ አምላካዊ በሆነ መንገድ ልንፈታው ይገባል። (ዘሌዋውያን 19:17, 18፤ ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15, 16) እንግዲያው በአምላክ መንፈስ በመመራት ራስን የመግዛት ባሕርይ እናዳብር፤ ለመቆጣት የሚያበቃን ምክንያት ቢኖረንም እንኳ ቁጣችን ወደ ምሬት፣ ክፋትና ጥላቻ እንዳይመራን እንጠንቀቅ።

23. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

23 በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ልንኮርጃቸው የማይገቡንን አንዳንድ የዲያብሎስ ባሕርያት ተመልክተናል። ሆኖም አንዳንድ አንባቢያን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያነሱ ይሆናል:- ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል? በክርስቲያኖች ላይ ስደት እንዲቀሰቀስ የሚያደርገው ለምንድን ነው? ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “ዲያብሎስ በእርግጥ አለ?” የሚል ርዕስ ያለውን የኅዳር 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የሰው ስም ማጥፋት የሌለብን ለምንድን ነው?

በ1 ዮሐንስ 3:​15 ላይ እንደተገለጸው ነፍሰ ገዳይ እንዳንሆን ምን ማድረግ አለብን?

• ለከሃዲዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

• ዓለምን መውደድ የሌለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዲያብሎስ ክርስቲያናዊ አንድነታችንን እንዲያጠፋ ፈጽሞ አንፈቅድም

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሐንስ ዓለምን እንዳንወድ አጥብቆ ያሳሰበን ለምንድን ነው?