በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰይጣንን ተቃወሙት፣ ከእናንተም ይሸሻል!

ሰይጣንን ተቃወሙት፣ ከእናንተም ይሸሻል!

ሰይጣንን ተቃወሙት፣ ከእናንተም ይሸሻል!

“ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል።”​—⁠ያዕቆብ 4:7

1, 2. (ሀ) በኢሳይያስ ምዕራፍ 14 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ዘገባ ውስጥ የተገለጸው የትኛው የዲያብሎስ ባሕርይ ነው? (ለ) በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ እንወያያለን?

 በእብሪተኝነት ረገድ ዲያብሎስን የሚተካከለው የለም። የአምላክ ነቢይ የሆነው ኢሳይያስ የዲያብሎስን የትዕቢት ዝንባሌ አስመልክቶ ያሰፈረው ዘገባ አለ። ባቢሎን የዓለም ታላቅ ኃይል ለመሆን ከአንድ ምዕተ ዓመት የበለጠ ጊዜ ሲቀራት፣ የይሖዋ ሕዝቦች “በባቢሎን ንጉሥ ላይ” እንደሚከተለው ብለው እንደተናገሩ ተደርጎ ተገልጾ ነበር:- “በልብህም እንዲህ አልህ፤ ‘ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት [በዳዊት መሥመር የመጡ ነገሥታት] በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤ . . . ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።’ ” (ኢሳይያስ 14:3, 4, 12-15፤ ዘኍልቍ 24:17) ‘የባቢሎን ንጉሥ’ ትዕቢት “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ካንጸባረቀው መንፈስ ጋር ተመሳሳይ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የባቢሎን ሥርወ መንግሥት አሳፋሪ ውድቀት እንደደረሰበት ሁሉ የሰይጣን እብሪተኝነትም መጨረሻው ጥፋት ይሆናል።

2 ያም ቢሆን ግን ሰይጣን በሕይወት እስካለ ድረስ የሚከተሉት ጥያቄዎች ያሳስቡን ይሆናል:- ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል? በክርስቲያኖች ላይ ስደት እንዲያደርሱባቸው ሰዎችን የሚያነሳሳቸው ለምንድን ነው? ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

ዲያብሎስን ልንፈራው ይገባል?

3, 4. በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችም ሆኑ አጋሮቻቸው ዲያብሎስን የማይፈሩት ለምንድን ነው?

3 “ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ። እነሆ፤ ዲያብሎስ ሊፈትናችሁ አንዳንዶቻችሁን ወደ እስር ቤት ይጥላል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።” ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በመንፈስ ለተቀቡት ክርስቲያኖች እንዴት የሚያበረታቱ ናቸው! (ራእይ 2:10) በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ተባባሪዎቻቸው ዲያብሎስን አይፈሩትም። ይህ የሆነው በተፈጥሯቸው ደፋሮች በመሆናቸው ሳይሆን ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ስላላቸውና ‘በክንፎቹ ጥላ ሥር መጠጊያ ስለሚያገኙ’ ነው።​—⁠መዝሙር 34:​9፤ 36:​7

4 ደፋር የነበሩት የጥንቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ያውቁ ስለነበር ሰይጣን ዲያብሎስ ሊሰነዝርባቸው የሚችለውን ጥቃት በመፍራት አልተሸበሩም። በተመሳሳይ ዛሬም በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችም ሆኑ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አጋሮቻቸው ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ላለማጉደል ቆርጠዋል። ያም ቢሆን ግን ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዲያብሎስ ሕይወታችንን እንድናጣ ሊያደርገን እንደሚችል ተናግሯል። ታዲያ ይህ ሊያስፈራን አይገባም?

5. በዕብራውያን 2:​14, 15 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ሥጋና ደም ያለው ሰው ሆኖ እንደመጣ ከገለጸ በኋላ ይህንን ያደረገው “በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው” ብሏል። (ዕብራውያን 2:14, 15) ሰይጣን “በሞት ላይ ኀይል ያለው” በመሆኑ የአስቆሮቱ ይሁዳን ከተቆጣጠረው በኋላ በአይሁድ መሪዎችና በሮማውያን በመጠቀም ኢየሱስን አስገድሎታል። (ሉቃስ 22:3፤ ዮሐንስ 13:26, 27) ሆኖም ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ መሞቱ ኃጢአተኛ የሆነውን የሰው ዘር ከሰይጣን ቁጥጥር ነጻ ያወጣው ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል።​—⁠ዮሐንስ 3:16

6, 7. ሰይጣን በሞት ላይ ኃይል ያለው እስከ ምን ድረስ ነው?

6 ዲያብሎስ በሞት ላይ ኃይል ያለው እስከ ምን ድረስ ነው? ሰይጣን የክፋት ድርጊቶችን መፈጸም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተናገራቸው ውሸቶችና የሰጣቸው መመሪያዎች የሰው ልጆችን ለሞት ዳርገዋል። ይህም የሆነው አዳም ኃጢአት በመሥራቱና በዚህም የተነሳ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ኃጢአትንና ሞትን በማውረሱ ነው። (ሮሜ 5:​12) ከዚህም በተጨማሪ የሰይጣን ምድራዊ አገልጋዮች በይሖዋ አምላኪዎች ላይ ስደት ሲያደርሱ ኖረዋል፤ አንዳንድ ጊዜም ልክ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዳደረጉት ገድለዋቸዋል።

7 ያም ሆኖ ግን፣ ዲያብሎስ መግደል የፈለገውን ማንኛውንም ሰው መግደል እንደሚችል አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። አምላክ የእርሱ ለሆኑት ጥበቃ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሰይጣን በምድር ላይ ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎች በሙሉ እንዲያጠፋ ፈጽሞ አይፈቅድለትም። (ሮሜ 14:8) ይሖዋ ሕዝቦቹ በሙሉ ስደት እንዲደርስባቸው እንዲሁም አንዳንዶቻችን በዲያብሎስ ጥቃት ምክንያት ሕይወታችንን እንድናጣ የሚፈቅድ መሆኑ እውነት ነው። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ስማቸው በአምላክ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ውስጥ የተጻፈ ሰዎች ድንቅ የሆነው የትንሣኤ ተስፋ እንደተዘረጋላቸው ይናገራል፤ ዲያብሎስ ይህንን ማስቀረት ፈጽሞ አይችልም።​—⁠ሚልክያስ 3:16፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

ሰይጣን ስደት የሚያደርስብን ለምንድን ነው?

8. ዲያብሎስ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ስደት የሚያመጣው ለምንድን ነው?

8 ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከሆንን ዲያብሎስ በእኛ ላይ ስደት ለማነሳሳት ትልቅ ምክንያት ያገኛል። ዓላማው እምነታችንን እንድንክድ ማድረግ ነው። በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ውድ የሆነ ዝምድና አለን፤ ሰይጣን ደግሞ ይህን ዝምድና ማበላሸት ይፈልጋል። ይህም ሊያስገርመን አይገባም። ይሖዋ፣ ምሳሌያዊ በሆነችው የእርሱ ‘ሴት’ እና ‘በእባቡ’ እንዲሁም ‘በዘሮቻቸው’ መካከል ጠላትነት እንደሚኖር በዔድን ውስጥ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:14, 15) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዲያብሎስን “የጥንቱ እባብ” ብሎ የሚጠራው ከመሆኑም በላይ የቀረው ዘመን አጭር እንደሆነና በታላቅ ቁጣ እንደተሞላ ይናገራል። (ራእይ 12:9, 12) በሁለቱ ‘ዘሮች’ መካከል ያለው ጠላትነት እስከቀጠለ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ሰይጣን እንዲህ ያለ ስደት የሚያመጣበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

9, 10. ዲያብሎስ ምን ጥያቄ አስነስቷል? ይህስ ከሰው ልጆች ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

9 ዲያብሎስ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት ያለው ማን መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ አስነስቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የሰው ልጆች ለፈጣሪያቸው ያላቸው ታማኝነት አጠያያቂ እንደሆነ ገልጿል። ሰይጣን ቅን በነበረው በኢዮብ ላይ ስደት አድርሶበት ነበር። ለምን? ኢዮብ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት እንዲያጎድል ለማድረግ ነበር። የኢዮብ ሚስትና “የምታስጨንቁ አጽናኞች” በማለት የጠራቸው ሦስቱ ወዳጆቹ በወቅቱ የዲያብሎስን ዓላማ ለመፈጸም አገልግለዋል። በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፣ ሰይጣን በሰዎች ላይ ፈተና እንዲያደርስ ከተፈቀደለት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ የሚቀጥል ማንም እንደማይኖር በመናገር ይሖዋን ተገዳድሮታል። ይሁን እንጂ ኢዮብ በአቋሙ በመጽናት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። (ኢዮብ 1:8 እስከ 2:9፤ 16:2፤ 27:5፤ 31:6) በዛሬው ጊዜ ዲያብሎስ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት የሚያደርሰው ታማኝነታቸውን እንዲያጎድሉ ለማድረግና ያነሳው ጥያቄ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ስለሚፈልግ ነው።

10 ዲያብሎስ ስደት የሚያመጣብን ለአምላክ ያለንን ታማኝነት እንድናጎድል አጥብቆ ስለሚፈልግ መሆኑን ማወቃችን ብርቱዎችና ደፋሮች እንድንሆን ያስችለናል። (ዘዳግም 31:​16) አምላካችን የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ በመሆኑ ታማኝነታችንን መጠበቅ እንድንችል ይረዳናል። በአቋማችን በመጽናት ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት እንጣር፤ በዚህም ይሖዋ ለዋነኛው ተሳዳቢ፣ ለሰይጣን ዲያብሎስ መልስ መስጠት እንዲችል እናደርጋለን።​—⁠ምሳሌ 27:​11

“ከክፉው አድነን”

11. “ወደ ፈተናም አታግባን” የሚለው ጸሎት ምን ትርጉም አለው?

11 ታማኝነታችንን መጠበቅ ቀላል ነገር አይደለም፤ ይህን ለማድረግ አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል። በተለይም በናሙና ጸሎቱ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በዚህ ረገድ ጠቃሚ ናቸው። ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት የተወሰነው ክፍል “ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ” ይላል። (ማቴዎስ 6:13) ይሖዋ ኃጢአት እንድንሠራ አይፈትነንም። (ያዕቆብ 1:13) ሆኖም በአንዳንድ አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አንድ ነገር እንዲሆን ስለፈቀደ ብቻ እርሱ እንደፈጸመው አድርጎ ይናገራል። (ሩት 1:20, 21) እንግዲያው ኢየሱስ እንደተናገረው በማለት ስንጸልይ ይሖዋ በፈተና እንድንወድቅ እንዳይፈቅድ መጠየቃችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” በማለት ማረጋገጫ ስለሰጠን ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:13

12. “ከክፉው አድነን” ብለን የምንጸልየው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ስለ ፈተና ከገለጸ በኋላ “ከክፉው አድነን እንጂ” በማለት ተናግሯል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ከክፉም አድነን” (የ1954 ትርጉም ) ወይም “ከክፉ አድነን” (የ1980 ትርጉም ) ይላሉ። ይሁን እንጂ “አድነን” የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በዋነኝነት የተሠራበት ከሰዎች ጋር በተያያዘ ነው፤ ከዚህም በላይ የማቴዎስ ወንጌል ዲያብሎስን “ፈታኙ” ብሎ ስለሚጠራው አንድ አካል መሆኑን ያሳያል። (ማቴዎስ 4:3, 11) እንግዲያው “ከክፉው” ከሰይጣን ዲያብሎስ እንዲያድነን ወደ አምላክ መጸለያችን ተገቢ ነው። ሰይጣን በአምላክ ላይ ኃጢአት እንድንሠራ ሊያስተን ይሞክራል። (1 ተሰሎንቄ 3:5) “ከክፉው አድነን” የሚል ልመና ስናቀርብ፣ ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝብን በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንዲመራንና እንዲረዳን መጠየቃችን ነው።

ለዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ አትስጡት

13, 14. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሥነ ምግባር ብልግና ፈጽሞ ለነበረ በጉባኤው ውስጥ ለሚገኝ አንድ ግለሰብ የነበራቸውን አመለካከት መለወጥ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

13 ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩት ክርስቲያኖች ይቅር ባዮች እንዲሆኑ ለማሳሰብ እንዲህ በማለት ጽፎላቸው ነበር:- “እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በእርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው። ይህንንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የእርሱን ዕቅድ አንስተውምና።” (2 ቆሮንቶስ 2:10, 11) ዲያብሎስ በተለያዩ መንገዶች መግቢያ ቀዳዳ ሊያገኝ ይችላል፤ ሆኖም ጳውሎስ ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ የተናገረው ለምን ነበር?

14 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመ ሰው በጉባኤው ውስጥ እንዲመላለስ በመፍቀዳቸው ጳውሎስ ተግሣጽ ሰጥቷቸው ነበር። ጉባኤው “በአረማውያን ዘንድ እንኳ ታይቶ የማይታወቅ” ዝሙት ሲፈጸም በቸልታ በመመልከቱ ነቀፋ ስለደረሰበት ሰይጣን ሳይደሰት አልቀረም። ውሎ አድሮ ግን ኃጢአተኛው ሰው ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። (1 ቆሮንቶስ 5:1-5, 11-13) ከጊዜ በኋላ፣ ግለሰቡ ንስሐ ገባ። የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት ይህንን ሰው ይቅር ለማለትና እንደገና ወደ ጉባኤው እንዲመለስ ለማድረግ ፈቃደኞች ካልሆኑ ዲያብሎስ ሌላ መግቢያ ቀዳዳ ያገኛል። እንዴት? እንዲህ ካደረጉ ልክ እንደራሱ እንደ ሰይጣን ደግነት የጎደላቸውና ምሕረት የለሾች መሆናቸው ነው። ንስሐ የገባው ሰው “ከልክ በላይ አዝኖ” ይሖዋን ማምለኩን ከተወ፣ በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች መሐሪ አምላክ በሆነው በይሖዋ ፊት በዚህ ጉዳይ ይጠየቁበታል። (2 ቆሮንቶስ 2:7፤ ያዕቆብ 2:13፤ 3:1) ማንኛውም ክርስቲያን ቢሆን እንደ ሰይጣን ጨካኝ፣ ደግነት የጎደለውና ምሕረት የለሽ መሆን እንደማይፈልግ ግልጽ ነው።

የአምላክ የጦር ትጥቅ የሚያስገኘው ጥበቃ

15. ምን ዓይነት ጦርነት እያካሄድን ነው? ድል ማድረጋችንስ በምን ላይ የተመካ ነው?

15 ከዲያብሎስ ጥቃት ጥበቃ ማግኘት ከፈለግን በክፉ መንፈሳውያን ኃይሎች ላይ መንፈሳዊ ጦርነት ማካሄድ ይኖርብናል። እንደነዚህ ባሉት ኃያላን ክፉ መናፍስት ላይ ድል መቀዳጀታችን “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” በመልበሳችን ላይ የተመካ ነው። (ኤፌሶን 6:​11-18) ይህ የጦር ትጥቅ ‘የጽድቅ ጥሩርንም’ ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:​14) የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል አምላክን ባለመታዘዙ መንፈስ ቅዱስን አጥቷል። (1 ሳሙኤል 15:22, 23) እኛ ግን በጽድቅ ጎዳና መመላለሳችንን ከቀጠልንና መንፈሳዊውን የጦር ትጥቅ በሙሉ ከለበስን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ የምናገኝ ከመሆኑም በላይ ሰይጣንና ክፉ መላእክቱ ማለትም አጋንንት እንዳያጠቁን የሚያስፈልገንን ጥበቃ እናገኛለን።​—⁠ምሳሌ 18:​10

16. ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች የሚሰነዘርብንን ጥቃት ለመመከት የሚያስችለንን ያልተቋረጠ ጥበቃ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች የሚሰነዘርብንን ጥቃት ለመመከት የሚያስችለንን ያልተቋረጠ ጥበቃ ለማግኘት ከሚያስፈልጉን ነገሮች መካከል የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብና ማጥናት እንዲሁም ‘ታማኙ መጋቢ’ በሚያቀርብልን ጽሑፎች ጥሩ አድርጎ መጠቀም ይገኙበታል። (ሉቃስ 12:42) እንዲህ ካደረግን ከሚከተለው የጳውሎስ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ አእምሯችንን ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች እንሞላዋለን:- “ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:8

17. ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማወጅ ምን ይረዳናል?

17 ይሖዋ ‘እግሮቻችን በሰላም ወንጌል ተጫምተው እንዲቆሙ’ ይረዳናል። (ኤፌሶን 6:15) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ተሳትፎ ማድረጋችን የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንድናውጅ ያስታጥቀናል። ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲማሩና መንፈሳዊ ነፃነት እንዲያገኙ በመርዳት ታላቅ ደስታ እናገኛለን! (ዮሐንስ 8:​32) ‘የመንፈስ ሰይፍ’ የሆነው ‘የአምላክ ቃል’ ራሳችንን ከሐሰት ትምህርቶች ለመጠበቅም ሆነ “ምሽግን ለመደምሰስ” በጣም አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 6:17፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገን ከተጠቀምንበት እውነትን ለማስተማር የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በሰይጣን ማታለያዎች እንዳንሸነፍ ጥበቃ ይሆነናል።

18. “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም” የምንችለው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ የጦር ዕቃችን መናገር የጀመረው እንደሚከተለው በማለት ነበር:- “በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ።” (ኤፌሶን 6:10, 11) “መቋቋም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቦታውን ይዞ የቆመን ወታደር ያመለክታል። ሰይጣን አንድነታችንን ለማናጋት፣ ትምህርታችንን ለመበከል ወይም ለአምላክ ያለንን ታማኝነት እንድናጎድል ለማድረግ የተለያዩ የተንኰል ዘዴዎችን ቢጠቀምም በመንፈሳዊው ውጊያ ጸንተን እንቆማለን። ዲያብሎስ የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች እስከዛሬ እንዳላሸነፉን ሁሉ ወደፊትም አያሸንፉንም! a

ዲያብሎስን ተቃወሙት፣ ከእናንተም ይሸሻል

19. ዲያብሎስን መቃወም የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

19 ከዲያብሎስና በእርሱ አመራር ሥር ካሉት ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር የምናደርገውን መንፈሳዊ ውጊያ በድል መወጣት እንችላለን። ሰይጣን በፍርሃት እንድንርድ ሊያደርገን አይገባም፤ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” ብሎናል። (ያዕቆብ 4:7) ሰይጣንንና የእርሱ ተባባሪዎች የሆኑትን ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን በመቃወም ረገድ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከምትሃታዊ ወይም ከአስማታዊ ድርጊቶች እንዲሁም ከእነዚህ ነገሮች ጋር ግንኙነት ካላቸው ሰዎች በመራቅ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋ አገልጋዮች ከመተት መራቅ እንዳለባቸው እንዲሁም በኮከብ ቆጠራ፣ በሟርትና በመናፍስታዊ ድርጊቶች ፈጽሞ መካፈል እንደሌለባቸው ይገልጻሉ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከተጠመድንና ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ካለን ማንም ሰው መተት ያደርግብናል ብለን መፍራት አይኖርብንም።​—⁠ዘኍልቍ 23:23፤ ዘዳግም 18:10-12፤ ኢሳይያስ 47:12-15፤ የሐዋርያት ሥራ 19:18-20

20. ዲያብሎስን መቃወም የምንችለው እንዴት ነው?

20 ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችና እውነቶች ጋር ተስማምተን በመኖርና ጠንካራ አቋም በመውሰድ ‘ዲያብሎስን መቃወም’ እንችላለን። ይህ ዓለም ሰይጣን አምላኩ በመሆኑ ከእርሱ ጋር ተስማምቶ ይኖራል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንግዲያው እንደ ትዕቢት፣ ራስ ወዳድነት፣ የሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመጽ እና ፍቅረ ንዋይ የመሳሰሉትን የዓለም ዝንባሌዎች ልናስወግድ ይገባል። ኢየሱስ፣ ሰይጣን በምድረ በዳ በፈተነው ወቅት ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም መልስ ሲሰጠው ዲያብሎስ እንደሸሸ እናውቃለን። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10, 11) በተመሳሳይ እኛም ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የምንገዛና በጸሎት አማካኝነት በእርሱ የምንታመን ከሆነ ሰይጣን ሽንፈት ተከናንቦ ‘ከእኛ ይሸሻል።’ (ኤፌሶን 6:18) ይሖዋ አምላክና ውድ ልጁ ከእኛ ጎን ስለሆኑ ማንኛውም ግለሰብ፣ ሌላው ቀርቶ ዲያብሎስም እንኳ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትልብን አይችልም!​—⁠መዝሙር 91:​9-11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ አምላክ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግንቦት 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21-23ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሰይጣን ዲያብሎስን ልንፈራው ይገባል?

• ሰይጣን በክርስቲያኖች ላይ ስደት የሚያመጣው ለምንድን ነው?

• “ከክፉው አድነን” ብለን የምንጸልየው ለምንድን ነው?

• በመንፈሳዊው ውጊያ ድል መቀዳጀት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደፋር የነበሩት የጥንቶቹ የክርስቶስ ተከታዮች እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዲያብሎስ በይሖዋ የመታሰቢያ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉት ሰዎች ትንሣኤ እንዳያገኙ ማድረግ አይችልም

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ “ከክፉው” እንዲያድንህ ትጸልያለህ?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” ለብሰሃል?