በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በክቡር ደም’ ተዋጅተናል

‘በክቡር ደም’ ተዋጅተናል

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

‘በክቡር ደም’ ተዋጅተናል

ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸበት ከሁሉ የላቀው ተግባር የአንድያ ልጁን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ነው። የሰው ልጆች ኃጢአተኛ እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ያለው ቤዛ የግድ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም” ይላል። ፍጹም ያልሆነ ሰው ‘ለዘላለም እንዲኖር’ ቤዛ ያስፈልገዋል። (መዝሙር 49:6-9) “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን” በመስጠቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ዮሐንስ 3:16

ሆኖም ቤዛው የሚያድነን እንዴት ነው? ይሖዋ አምላክ ባሳየው ታላቅ ፍቅር አማካኝነት ነጻ መውጣት የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።

በቤዛው ነጻ ወጥተናል

በመጀመሪያ፣ የኢየሱስ መሥዋዕት ከአዳም ከወረስነው ኃጢአት ነጻ ያወጣናል። ሁላችንም የተወለድነው በኃጢአት ነው። የይሖዋን ሕግ ባንጥስም እንኳ ኃጢአተኞች ነን። እንዴት? ሮሜ 5:12 እንዲህ ይላል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል።” የኃጢአተኛው አዳም ልጆች እንደመሆናችን መጠን አለፍጽምናውንም ወርሰናል። ይሁን እንጂ ቤዛ ስለተከፈለልን ከወረስነው ኃጢአት ነጻ መሆን እንችላለን። (ሮሜ 5:16) ኢየሱስ ኃጢአት በአዳም ልጆች ላይ ያስከተለውን መዘዝ በመሸከም ‘ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ቀምሷል።’—ዕብራውያን 2:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:24

በሁለተኛ ደረጃ ቤዛው ወደ ሞት ከሚመሩ የኃጢአት ውጤቶች ነጻ ያወጣናል። መጽሐፍ ቅዱስ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” ይላል። (ሮሜ 6:23) ኃጢአት የሚያስከትለው ቅጣት ሞት ነው። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ የአምላክ ልጅ መሥዋዕታዊ ሞት ሞቷል። በእርግጥም “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን . . . ሕይወትን አያይም።”—ዮሐንስ 3:36

ኃጢአት ከሚያስከትላቸው መዘዞች ነጻ ልንወጣ የምንችለው በአምላክ ልጅ ካመንን ብቻ እንደሆነ ልብ ማለት ይገባናል። ይህ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ለውጦች ማድረግን እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተን መኖርን ይጨምራል። ማንኛውንም የስህተት አካሄድ መተውና አምላክን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ኀጢአታችን እንዲደመሰስ ንስሓ መግባትና ከመንገዳችን መመለስ’ እንዳለብን ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 3:19

በሦስተኛ ደረጃ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሕሊና ወቀሳ ነጻ ያደርገናል። ለይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑና ተጠምቀው የልጁ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሰዎች በሙሉ እረፍት ያገኛሉ። (ማቴዎስ 11:28-30) ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ በንጹሕ ሕሊና አምላክን ማገልገላችን ጥልቅ እርካታ ይሰጠናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) ኃጢአታችንን በመናዘዝና ኃጢአቱን በድጋሚ ባለመሥራት ምሕረት እናገኛለን፤ እንዲሁም ከሕሊና ወቀሳ ነጻ እንሆናለን።—ምሳሌ 28:13

ቤዛው እርዳታና ተስፋ ይሰጣል

በመጨረሻም፣ በቤዛው ላይ ያለን እምነት በአምላክ ፊት ያለንን አቋም በተመለከተ ከመሥጋት ያሳርፈናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:1) ኢየሱስ እኛን በመርዳት ረገድ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 7:25) ኃጢአተኞች እስከሆንን ድረስ በአምላክ ዘንድ ትክክለኛ አቋም እንዲኖረን የኢየሱስ ክርስቶስ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ያስፈልገናል። ኢየሱስ ለእኛ እንደ ሊቀ ካህን የሆነው እንዴት ነው?

ኢየሱስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ትንሣኤ ካገኘ ከአርባ ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ በማረግ ‘ክቡር ደሙን’ ለአምላክ አቅርቧል። በዚህም ምክንያት በቅርቡ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነጻ ያወጣቸዋል። a (1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስን ልንወደውና ልንታዘዘው ይገባል ቢባል አትስማማም?

ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ አምላክንም ልንወደውና ልንታዘዘው ይገባል። በፍቅር ተነሳስቶ ‘የቤዛውን’ ዝግጅት አድርጎልናል። (1 ቆሮንቶስ 1:30) አሁን ያለውን ሕይወታችንን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰጠን እሱ ነው። ስለዚህ ‘ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር እንድንታዘዝ’ የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ መጋቢት/ሚያዝያ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ያውቁ ኖሯል?

• ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው ከደብረ ዘይት ተራራ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 1:9, 12

• ኢየሱስ ሲያርግ የተመለከቱት ታማኝ ሐዋርያቱ ብቻ ነበሩ።—የሐዋርያት ሥራ 1:2, 11-13