በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል”

“እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል”

“እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል”

“እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።”—ሮሜ 14:12

1. ሦስቱ ዕብራውያን የትኛውን ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል?

 በባቢሎን የሚኖሩ ሦስት ወጣት ዕብራውያን ውሳኔ የሚያሻው ሁኔታ ተደቅኖባቸዋል፤ የገጠማቸው ሁኔታ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ምን ማድረግ ይኖርባቸው ይሆን? የአገሪቱ ሕግ በሚያዘው መሠረት ለግዙፉ ምስል መስገድ? ወይስ ለምስሉ አምልኮ ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆን ወደሚንበለበለው እቶን እሳት መጣል? ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ስለ ጉዳዩ ማንንም ለማማከር ጊዜ አልነበራቸውም፤ እነርሱም ቢሆኑ እንዲህ ማድረግ አላስፈለጋቸውም። አለ አንዳች ማመንታት “ንጉሥ ሆይ፤ . . . አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ” በማለት መለሱ። (ዳንኤል 3:1-18) እነዚህ ሦስት ዕብራውያን ኃላፊነታቸውን ተሸክመዋል።

2. ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ለጲላጦስ ውሳኔ ያደረገለት ማን ነው ለማለት ይቻላል? ይህ ሮማዊውን አገረ ገዥ ከተጠያቂነት ነጻ ያደርገዋል?

2 ይህ ሁኔታ ከተከናወነ ከስድስት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ አንድ አገረ ገዢ በተከሳሹ ላይ የቀረቡትን ክሶች ለማየት ተቀምጧል። አገረ ገዢው ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ተከሳሹ ንጹሕ ሰው እንደሆነ አመነ። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ሰውየው እንዲገደል እየጠየቀ ነበር። አገረ ገዢው ሐሳባቸውን ላለመቀበል ጥረት ቢያደርግም ኃላፊነቱን መሸከም ስላልቻለ በሕዝቡ ተጽዕኖ ተሸነፈ። ውኃ አስመጥቶ እጆቹን በመታጠብ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ” አለ። ከዚያም ሰውየውን እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነቱን ከመሸከም ይልቅ ሌሎች በእርሱ ቦታ እንዲወስኑለት ፈቅዷል። ምንም ያህል ቢታጠብ ግን በኢየሱስ ላይ ባሳለፈው ፍትሕ የጎደለው ብያኔ ተጠያቂ ከመሆን ሊነጻ አይችልም።—ማቴዎስ 27:11-26፤ ሉቃስ 23:13-25

3. ሌሎች በእኛ ቦታ ሆነው እንዲወስኑልን ማድረግ የሌለብን ለምንድን ነው?

3 አንተስ? ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲገጥምህ እንደ ሦስቱ ዕብራውያን ታደርጋለህ? ወይስ ሌሎች እንዲወስኑልህ ትፈቅዳለህ? ውሳኔ ማድረግ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ ብስለት ይጠይቃል። ለአብነት ያህል፣ ወላጆች ለትንንሽ ልጆቻቸው ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እርግጥ፣ ጉዳዩ ውስብስብና የተለያዩ ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባትን የሚጠይቅ በሚሆንበት ጊዜ ውሳኔ ማድረግ በጣም ከባድ እንደሚሆን አይካድም። ያም ቢሆን ግን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት፣ ‘መንፈሳውያን የሆኑ’ ወንድሞች ከሚሸከሙልን “ከባድ ሸክም” መካከል የሚቆጠር አይደለም። (ገላትያ 6:1, 2) ከዚህ ይልቅ ‘እያንዳንዳችን ለእግዚአብሔር መልስ የምንሰጥበት’ ቀለል ያለ ሸክም ነው። (ሮሜ 14:12) መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል” ይላል። (ገላትያ 6:5) ይህ ከሆነ ታዲያ በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ሰዎች በመሆናችን ያሉብንን የአቅም ገደቦች መገንዘብና ይህንን ለማካካስ ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል።

ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?

4. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አለመታዘዝ ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ ምን ትልቅ ቁም ነገር ሊያስተምረን ይገባል?

4 በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን አስከፊ መዘዞች ያስከተለ ውሳኔ አደረጉ። እነዚህ ባልና ሚስት መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ ፍሬ ለመብላት መረጡ። (ዘፍጥረት 2:16, 17) እንዲህ ያለ ውሳኔ እንዲያደርጉ ምክንያት የሆናቸው ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ።” (ዘፍጥረት 3:6) ሔዋን እንዲህ ያለ ውሳኔ እንድታደርግ የገፋፋት ራስ ወዳድነት ነበር። እርሷ የወሰደችው እርምጃ አዳምንም እንዲተባበራት አድርጎታል። በዚህም የተነሳ ኃጢአትና ሞት “ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ።” (ሮሜ 5:12) የአዳምና የሔዋን አለመታዘዝ የሰው ልጆች ያለባቸውን የአቅም ገደብ በተመለከተ ትልቅ ቁም ነገር ሊያስተምረን ይገባል:- የሰው ልጅ የአምላክን መመሪያ እስካልተከተለ ድረስ የተሳሳተ ውሳኔ ማድረጉ አይቀርም።

5. ይሖዋ ምን መመሪያ ሰጥቶናል? ከዚህስ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?

5 ይሖዋ አምላክ ያለ መመሪያ እንዳልተወን ማወቁ በጣም ያስደስታል! መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል” ይላል። (ኢሳይያስ 30:21) ይሖዋ በመንፈሱ አመራር በተጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያነጋግረናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናትና እውቀት ማካበት ይኖርብናል። ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ ‘የበሰሉ ሰዎች የሚመገቡትን ጠንካራ ምግብ’ መመገብ አለብን። በተጨማሪም ‘መልካምና ክፉውን ለመለየት ራሳችንን ማስለመድ’ ወይም የማሰብ ችሎታችንን ማሠልጠን እንችላለን። (ዕብራውያን 5:14) ከአምላክ ቃል የተማርነውን ተግባራዊ በማድረግ የማስተዋል ችሎታችንን ማዳበር እንችላለን።

6. ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ምን ያስፈልገዋል?

6 በተፈጥሮ ያገኘነው ሕሊናችን ውሳኔ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ቦታ አለው። ሕሊናችን ፍርድ የመስጠት ችሎታ ያለው ሲሆን ‘ሊከስሰን ወይም ሊከላከልልን’ ይችላል። (ሮሜ 2:14, 15) ይሁን እንጂ ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ከተፈለገ ከአምላክ ቃል በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ልናሠለጥነውና ያወቅነውን ተግባራዊ በማድረግ ንቁ እንዲሆን ልንረዳው ይገባል። ሕሊናችን ካልሠለጠነ በአካባቢው ባሕልና ልማድ በቀላሉ ሊሸነፍ ይችላል። አካባቢያችን እንዲሁም የሌሎች ሰዎች አመለካከትም ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ሕሊናችን የሚሰጠንን ማሳሰቢያ በተደጋጋሚ ችላ የምንልና የአምላክን መመሪያዎች የምንጥስ ከሆነ እያደር ምን ይሆናል? “በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል” ምንም የማይሰማውና ምላሽ የማይሰጥ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) በሌላ በኩል ግን በአምላክ ቃል የሠለጠነ ሕሊና አስተማማኝ መሪ ይሆናል።

7. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?

7 እንግዲያው፣ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነታችንን ለመሸከም ቁልፉ ከቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ ነው። ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲገጥሙን አስቀድመን ሳናስብበት ቸኩለን ውሳኔ ላይ ከመድረስ ይልቅ ጊዜ ወስደን አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት መጣርና እነዚህንም በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። እንደ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ወዲያውኑ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ በሚገጥመን ጊዜም እንኳ ከአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ካካበትንና ሕሊናችንን በዚህ መሠረት ካሠለጠንነው ውሳኔ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ማለት ነው። ብስለት ለማግኘት መጣራችን ውሳኔ የማድረግ ችሎታችንን እንዴት ሊያሳድግልን እንደሚችል ለመረዳት እስቲ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሁለት ጉዳዮች እንመልከት።

ወዳጆች አድርገን መምረጥ ያለብን እነማንን ነው?

8, 9. (ሀ) መጥፎ ጓደኝነትን ማስወገድ እንዳለብን የሚያሳዩት መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) መጥፎ ጓደኝነት መመሥረት ሲባል ጥሩ ሥነ ምግባር ከሌላቸው ሰዎች ጋር በቀጥታ መወዳጀትን ብቻ የሚያመለክት ነው? አብራራ።

8 ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ “የዓለም አይደላችሁም” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ካወቅን በኋላ ከሴሰኞች፣ ከአመንዝሮች፣ ከሌቦች፣ ከሰካራሞችና እንደነዚህ የመሳሰሉ ድርጊቶች ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር መወዳጀት እንደሌለብን መገንዘብ አይከብደንም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ ደግሞ እንዲህ ያሉ ሰዎችን በፊልምና በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒውተር አማካኝነት በማየት አሊያም ስለ እነርሱ በማንበብ አብረናቸው ጊዜ ማሳለፍም ከእነርሱ ጋር ከመወዳጀት ያልተናነሰ ጉዳት እንዳለው እንገነዘባለን። በኢንተርኔት ቻት ሩም “ከግብዞች” ወይም እውነተኛ ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች ጋር ማውራትን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—መዝሙር 26:4

9 በሥነ ምግባር ረገድ ጥሩ አቋም ቢኖራቸውም በእውነተኛው አምላክ ከማያምኑ ሰዎች ጋር የቀረበ ወዳጅነት ስለ መመሥረትስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 5:19) መጥፎ ባልንጀርነት መመሥረት ሲባል ብልሹ ሥነ ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር መወዳጀትን ብቻ እንደማያመለክት እንገነዘባለን። በመሆኑም ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ብቻ የቅርብ ወዳጅነት መመሥረታችን የጥበብ እርምጃ ነው።

10. ከዓለም ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ብስለት የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

10 በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን ማድረግ የማይቻል ከመሆኑም በላይ አስፈላጊም አይደለም። (ዮሐንስ 17:15) በክርስቲያናዊው አገልግሎት፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ የይሖዋ አምላኪ ካልሆኑ ሰዎች ጋር መገናኘታችን አይቀርም። የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ ከሌሎች የበለጠ እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸው ይሆናል። ሆኖም የማመዛዘን ችሎታችን ከሠለጠነ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ከዓለም ሰዎች ጋር በተወሰነ መጠን መገናኘት፣ የቀረበ ግንኙነት ከመመሥረት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን እንገነዘባለን። (ያዕቆብ 4:4) ስለዚህ በትምህርት ቤት ከትምህርት ሰዓት ውጪ በሚዘጋጁ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና የዳንስ ፕሮግራሞች እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻችን በሚያዘጋጅዋቸው ፓርቲዎችና ግብዣዎች ላይ መገኘትን በተመለከተ ብስለት የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።

የሥራ ምርጫ

11. ሥራን በተመለከተ ውሳኔ ስናደርግ ግምት ውስጥ ልናስገባ የሚገባን ተቀዳሚው ጉዳይ ምንድን ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ብስለት በሚታይበት መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ‘ቤተሰባችንን የመርዳት’ ግዴታችንን ከሟሟላት ጋር በተያያዘ በምናደርገው ውሳኔ ረገድም ይረዳናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) በመጀመሪያ ደረጃ ልናስብበት የሚገባው ነገር የሥራው ዓይነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ተግባራትን የሚደግፍ ሥራ መምረጥ ስህተት እንደሆነ ግልጽ ነው። በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከጣዖት አምልኮ፣ ከስርቆት፣ ደምን አለ አግባብ ከመጠቀም ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወግዛቸው ሌሎች ድርጊቶች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አይሠሩም። ከዚህም በላይ አሠሪያችን ቢያዘንም እንኳ ውሸት አንናገርም ወይም አናጭበረብርም።—የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ ራእይ 21:8

12, 13. ከሥራ ጋር የተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ልብ ልንላቸው የሚገቡት ሌሎች ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

12 ሥራው በራሱ መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የማያስጥስ ቢሆንስ? ስለ እውነት ያለን እውቀት እያደገ ሲሄድና የማመዛዘን ችሎታችን ሲሻሻል ልብ ልንላቸው የሚገቡ ሌሎች ነጥቦችንም እናስተውላለን። ሥራው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወግዛቸው ድርጊቶች ጋር የተያያዘ ነገር እንድናከናውን የሚያደርገን ቢሆንስ? ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ቁማር በሚያጫውት ድርጅት ውስጥ የስልክ ጥሪዎችን ለመቀበል መቀጠር ይችላል? የደመወዙ ምንጭና የሥራው ቦታም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል። ለአብነት ያህል፣ የሕንጻ ተቋራጭ የሆነ ክርስቲያን ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አንዱን ቀለም እንደ መቀባት ያለ የሐሰት ሃይማኖትን ለማስፋፋት የሚረዳ ሥራ ለማግኘት በጨረታ ይካፈላል?—2 ቆሮንቶስ 6:14-16

13 አሠሪያችን የሐሰት አምልኮ የሚካሄድበትን ቦታ የማስዋብ ሥራ ቢቀበልስ? በዚህ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ሥልጣን እንዳለንና በሥራው የምንካፈለው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። መጥፎ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ቦታዎች ጨምሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ በሁሉም ቦታዎች ፖስታ እንደማድረስ ያሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የማይጋጩ ሥራዎችንስ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? በማቴዎስ 5:45 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ አይሆንም? ልብ ልንለው የሚገባው ነጥብ፣ ሁልጊዜ በዚህ ሥራ መካፈላችን በሕሊናችን ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚለው ነው። (ዕብራውያን 13:18) በእርግጥም ከሥራ ምርጫ ጋር በተያያዘ ብስለት የሚንጸባረቅበት ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነታችንን ለመሸከም፣ የማመዛዘን ችሎታችንንና ከአምላክ ያገኘነውን ሕሊናችንን ማሠልጠን ይኖርብናል።

“በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ”

14. ምንም ዓይነት ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባን ነጥብ ምንድን ነው?

14 ሰብዓዊ ትምህርት መከታተልን አሊያም አንድ ዓይነት ሕክምና መቀበልን ወይም አለመቀበልን የመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የምናደርጋቸው ውሳኔዎችስ? ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ምንም ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመርመርና እነዚህንም በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” ብሏል።—ምሳሌ 3:5, 6

15. ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች ምን እንማራለን?

15 አብዛኛውን ጊዜ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሌሎች ሰዎችንም ስለሚነኩ ልናስብባቸው ይገባል። ለአብነት ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ውስጥ ምግብን በተመለከተ የተሰጡት አብዛኞቹ ገደቦች ቀርተውላቸው ነበር። በሕጉ መሠረት ርኩስ እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ተቀባይነት ያላቸውን አንዳንድ ምግቦች መብላት ይችሉ ነበር። ያም ሆኖ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ከጣዖት አምልኮ ጋር ግንኙነት ሊኖረው የሚችል የእንስሳ ሥጋን በተመለከተ “እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 8:11-13) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሌሎችን ላለማሰናከል ሲሉ ለሰዎች ሕሊና እንዲጠነቀቁ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ለሌሎች ሰዎች “መሰናክል” መሆን የለባቸውም።—1 ቆሮንቶስ 10:29, 32

አምላካዊ ጥበብን ፈልጉ

16. ውሳኔ በማድረግ ረገድ ጸሎት የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ውሳኔ በማድረግ ረገድ ጸሎት ታላቅ እርዳታ ያበረክታል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል” ብሏል። (ያዕቆብ 1:5) በይሖዋ በመተማመን ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ጥበብ እንዲሰጠን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። ስለሚያሳስቡን ነገሮች ለእውነተኛው አምላክ ስንነግረውና መመሪያውን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ፣ መንፈስ ቅዱስ የምናነባቸው ጥቅሶች ይበልጥ እንዲገቡን እንዲሁም ሳናስተውላቸው ያለፍናቸውን እንድናስታውስ ይረዳናል።

17. ውሳኔ በማድረግ ረገድ ሌሎች ሰዎች ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሊረዱን ይችላሉ? አዎን፣ ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ የጎለመሱ ወንድሞች ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:11, 12) በተለይ ከባድ ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ እነዚህን ወንድሞች ልናማክራቸው እንችላለን። ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋል ያላቸውና ተሞክሮ ያካበቱ ግለሰቦች ከምናደርገው ውሳኔ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሊነግሩንና ‘ከሁሉ የሚሻለውን እንድንለይ’ ሊረዱን ይችላሉ። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ይሁን እንጂ ልንጠነቀቅበት የሚገባ ጉዳይ አለ:- ሌሎች ለእኛ እንዲወስኑልን መፍቀድ አይኖርብንም። ኃላፊነቱን መሸከም ያለብን እኛ ራሳችን ነን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተን የምናደርገው ውሳኔ ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል?

18. ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ስለሚኖረው ውጤት ምን ማለት ይቻላል?

18 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተንና ጉዳዩን በጥንቃቄ አስበንበት የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛሉ? ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት መገኘቱ አይቀርም። ሆኖም ለጊዜው መጥፎ ነገር ሊደርስብን ይችላል። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ግዙፉን ምስል ላለማምለክ ሲወስኑ ሞት ሊከተል እንደሚችል ያውቁ ነበር። (ዳንኤል 3:16-19) በተመሳሳይም ሐዋርያት ለአይሁድ የሳንሄድሪን ሸንጎ ከሰው ይልቅ ለአምላክ እንደሚታዘዙ በተናገሩ ጊዜ ነጻ ከመለቀቃቸው በፊት ተገርፈዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:27-29, 40) ከዚህም በላይ “ጊዜና አጋጣሚ” ማንኛውንም ውሳኔ ቢሆን እንዳይሳካ ሊያደርገው ይችላል። (መክብብ 9:11 NW) ትክክለኛ ውሳኔ አድርገንም እንኳ በሆነ መንገድ ችግር ቢገጥመን ይሖዋ ችግሩን ለመቋቋም እንደሚረዳንና ወደፊት እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7

19. ውሳኔ በማድረግ ረገድ ያለብንን ኃላፊነት መሸከም የምንችለው እንዴት ነው?

19 እንግዲያው ውሳኔ ስናደርግ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመርመርና በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ያወቅነውን በተግባር ማዋል ይኖርብናል። ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱና በጉባኤ ውስጥ ባሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች አማካኝነት ለሚሰጠን እርዳታ በጣም ልናመሰግነው ይገባል! እንዲህ ባለው መመሪያና በተደረገልን ዝግጅት በመጠቀም ትክክለኛ ውሳኔ በማድረግ ረገድ ያለብንን ኃላፊነት እንሸከም!

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?

• ብስለት ማግኘታችን በጓደኛ ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ የሚኖረው እንዴት ነው?

• ከሥራ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ልብ ልንላቸው የሚገቡ አስፈላጊ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

• ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ምን ዓይነት እርዳታ ማግኘት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአዳምና የሔዋን አለመታዘዝ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ያስተምረናል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከበድ ያለ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መርምር