በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ስለ ኢየሱስ ከመናገር ወደ ኋላ አንልም’

‘ስለ ኢየሱስ ከመናገር ወደ ኋላ አንልም’

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

‘ስለ ኢየሱስ ከመናገር ወደ ኋላ አንልም’

ወቅቱ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን ቦታውም በኢየሩሳሌም የሚገኘው ከፍተኛው የአይሁድ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ነው። በዚህ ወቅት የሳንሄድሪን ሸንጎ የ12ቱን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ጉዳይ ለመመርመር ተሰይሟል። ለፍርድ የቀረቡት ለምንድን ነው? ስለ ኢየሱስ በመስበካቸው ምክንያት ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ በዚህ ፍርድ ቤት ፊት ሲቀርቡ ሁለተኛ ጊዜያቸው ሲሆን ለቀሩት አሥር ሐዋርያት ግን ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

ሊቀ ካህኑ፣ ለ12ቱ ሐዋርያት ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ያወጣውን ትእዛዝ ነገራቸው። በዚያን ወቅት ስለ ኢየሱስ ማስተማራቸውን እንዲያቆሙ ሲነገራቸው ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም” በማለት መልሰው ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ድፍረት ማግኘት እንዲችሉ ከጸለዩ በኋላ ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጠሉ።—የሐዋርያት ሥራ 4:18-31

ሊቀ ካህኑ ከዚህ ቀደም ዝቶባቸው የነበረ ቢሆንም ማስፈራሪያው ምንም ውጤት አለማስገኘቱን ስላወቀ ለሁለተኛ ጊዜ ችሎቱ ፊት በቀረቡበት በዚህ ወቅት እንዲህ በማለት ተናገረ:- “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ!”—የሐዋርያት ሥራ 5:28

ቆራጥ አቋም

ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያትም በድፍረት እንዲህ ሲሉ መለሱ:- “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” (የሐዋርያት ሥራ 5:29) በእርግጥም የሰዎች ትእዛዝና የአምላክ ሕግ በሚጋጭበት ጊዜ ከቁጥር የማይገቡትን ሰዎችን ከመታዘዝ ይልቅ ይሖዋን መታዘዝ አለብን። a

ሐዋርያት ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተናገሯቸው ቃላት ለሳንሄድሪን አባላት አጥጋቢ ምላሽ ሊሆኗቸው በተገባ ነበር። እነዚህ የአይሁድ ኅብረተሰብ መሪዎች መታዘዝ የሚገባው ለአምላክ ነው ወይስ ለሰው? ተብለው ቢጠየቁ “አምላክን ታዘዙ” ብለው በአንድ ድምጽ መመለስ ነበረባቸው። ደግሞስ አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ መሆኑን ያምኑ የለም?

ጴጥሮስ ሐዋርያቱን በሙሉ በመወከል ሳይሆን አይቀርም፣ ከአገልግሎታቸው ጋር በተያያዘ ከሰዎች ይልቅ አምላክን እንደሚታዘዙ ተናግሯል። በመሆኑም ሐዋርያት ታዛዥ አይደላችሁም በሚል የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርጎታል። የሳንሄድሪን አባላት ከሰው ይልቅ ለአምላክ ታዛዥ መሆን ትክክል የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ ብሔራቸው ካሳለፈው ታሪክ መረዳት ይችላሉ። በግብጽ የሚገኙ ሁለት አዋላጆች፣ የዕብራውያን ሴቶች የወለዷቸውን ወንዶች ልጆች በሕይወት በመተው ፈርዖንን ሳይሆን አምላክን እንደፈሩ አሳይተዋል። (ዘፀአት 1:15-17) ንጉሥ ሕዝቅያስ እጁን እንዲሰጥ ግፊት ቢደረግበትም ከንጉሥ ሰናክሬም ይልቅ ይሖዋን ታዟል። (2 ነገሥት 19:14-37) የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ጠንቅቀው የሚያውቋቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ ሕዝቦቹ ለእርሱ ታዛዥ እንዲሆኑ እንደሚጠብቅባቸው ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ።—1 ሳሙኤል 15:22, 23

ታዛዥነት ይክሳል

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” የሚሉት ቃላት ከከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አባላት መካከል ቢያንስ የአንዱን ሰው ልብ ነክተዋል። በሳንሄድሪን ሸንጎ ላቅ ያለ ግምት ይሰጠው የነበረው ገማልያል የተባለ ዳኛ በወቅቱ በተካሄደው ዝግ ችሎት ላይ ጥበብ ያዘለውን ሐሳቡን እንዲያዳምጡ የፍርድ ቤቱን አባላት አግባባቸው። ገማልያል የጥንት ምሳሌዎችን በመጥቀስ ሐዋርያቱ በሚያከናውኑት ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት ጥበብ የጎደለው አካሄድ እንደሆነ ነገራቸው። በመጨረሻም “እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ አትንኳቸው፤ . . . እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል” በማለት ንግግሩን ደመደመ።—የሐዋርያት ሥራ 5:34-39

ምክንያታዊ የሆኑት የገማልያል ቃላት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሐዋርያቱን እንዲለቅ አሳመኑት። ሐዋርያቱ የተገረፉ ቢሆንም የገጠማቸው ነገር በፍርሃት እንዲሸበሩ አላደረጋቸውም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 5:42

ሐዋርያት፣ የአምላክ ሥልጣን ከሁሉ የላቀ መሆኑን በመግለጻቸው ምንኛ ተባርከዋል! በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ይህን የመሰለ አመለካከት አላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋን ከሁሉ በላይ እንደሆነ ገዢያቸው አድርገው መመልከታቸውን ቀጥለዋል። ከአምላክ መመሪያ ተቃራኒ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ቢታዘዙ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” በማለት ልክ እንደ ሐዋርያት ዓይነት መልስ ይሰጣሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ መስከረም/ጥቅምት የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ፣ ገማልያል በሳንሄድሪን በተካሄደው ዝግ ችሎት ላይ የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? አምላክ በቀጥታ ለሉቃስ የገማልያልን ቃላት ገልጾለት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የገማልያል የቀድሞ ተማሪ የነበረው ጳውሎስ ገማልያል የተናገራቸውን ቃላት ለሉቃስ ነግሮት ይሆናል። አሊያም ደግሞ ሉቃስ፣ በሐዋርያቱ ሐሳብ የሚስማማ የከፍተኛው ፍርድ ቤት አባል የሆነ ሰው አማክሮ ሊሆን ይችላል።