በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ‘ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናግሯል።’ (1 ነገሥት 4:32) እነዚህን ጥበብ ያለባቸው አባባሎች ማግኘት የምንችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? አዎን፣ ይኖራል። የምሳሌ መጽሐፍ ተጽፎ የተጠናቀቀው በ717 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ ሲሆን ሰሎሞን የተናገራቸውን በርካታ ምሳሌዎች ይዟል። በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ከሚገኙት የያቄ ልጅ አጉርና ንጉሥ ልሙኤል ከጻፏቸው ሁለት ምዕራፎች በቀር መላውን የምሳሌ መጽሐፍ የጻፈው ሰሎሞን ነው። ያም ሆኖ አንዳንዶች ልሙኤል የሰሎሞን ሌላ ስም ነው የሚል እምነት አላቸው።

በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ምሳሌዎች ጥምር የሆነ ዓላማ አላቸው፤ ይኸውም “ጥበብንና ተግሣጽን” እንድናውቅ መርዳት ነው። (ምሳሌ 1:2) እነዚህ ምሳሌዎች ጥበብን ማለትም ነገሮችን በግልጽ የመረዳትና ባለን እውቀት ተጠቅመን ችግሮችን የመፍታት ችሎታን ለማዳበር ይረዱናል። ከዚህም በላይ ተግሣጽን ወይም የሥነ ምግባር ሥልጠናም ይሰጡናል። ምሳሌዎቹን በትኩረት ማንበባችንና የሚሰጡንን ምክር በተግባር ላይ ማዋላችን መልካም ልብ እንዲኖረን ሊረዳን እንዲሁም ደስታና ስኬት ሊያስገኝልን ይችላል።—ዕብራውያን 4:12

‘ጥበብን አግኝ፤ ምክርን አጥብቀህ ያዝ’

(ምሳሌ 1:1 እስከ 9:18)

ሰሎሞን “ጥበብ በጐዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች” ብሏል። (ምሳሌ 1:20) ጥርት ብሎ የሚሰማውን የጥበብን የጎላ ድምጽ ማዳመጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ምዕራፍ 2 ጥበብ የምታስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች ይዘረዝራል። ምዕራፍ 3 ደግሞ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ከዚያም ሰሎሞን እንደሚከተለው ይላል:- “ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት። ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት።”—ምሳሌ 4:7, 13

ዓለም የሚያስፋፋው ሥነ ምግባር የጎደለው አካሄድ የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ ተቋቁመን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል? አምስተኛው ምዕራፍ ይህን ለማድረግ የሚረዳን የማሰብ ችሎታችንን ማዳበርና የዓለምን ማባበያዎች ለይተን ማወቅ መሆኑን ይገልጻል። የሥነ ምግባር ርኩሰት መፈጸም ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያስከትል መገንዘባችንም ጠቃሚ ነው። ቀጣዩ ምዕራፍ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ድርጊቶችና ዝንባሌዎች እንድንርቅ ያሳስበናል። ሰባተኛው ምዕራፍ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው የሚጠቀምበትን ዘዴ በማጋለጥ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ትምህርት ይሰጠናል። በምዕራፍ 8 ላይ የጥበብ ዋጋማነትና ማራኪነት ግሩም በሆነ መንገድ ተገልጿል። ቀደም ባሉት ምዕራፎች ውስጥ የተብራሩትን ነጥቦች ጠቅለል አድርጎ የሚገልጸው 9ኛው ምዕራፍ ጥበብን እንድንሻ የሚያነሳሱ ስሜት ቀስቃሽ ምሳሌዎችን ይዟል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:7፤ 9:10—ይሖዋን መፍራት “የዕውቀት መጀመሪያ” እና “የጥበብ መጀመሪያ” የሆነው በምን መንገድ ነው? ይሖዋ፣ የሁሉ ነገር ፈጣሪና የቅዱሳን መጻሕፍት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን እርሱን የማንፈራ ከሆነ ምንም ዓይነት እውቀት አናገኝም። (ሮሜ 1:20፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እርሱ የትክክለኛ እውቀት ሁሉ ምንጭ ነው። በመሆኑም እውቀት የሚጀምረው ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት በማሳየት ነው። በተጨማሪም እውቀት ከሌለ ጥበበኛ መሆን ስለማይቻል አምላካዊ ፍርሃት የጥበብም መጀመሪያ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋን የማይፈራ ሰው የቱንም ያህል እውቀት ቢኖረው እውቀቱን ፈጣሪውን ለማክበር አይጠቀምበትም።

5:3 NW—አመንዝራ ሴት “እንግዳ ሴት” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው? ምሳሌ 2:16, 17 (NW) ይህቺ “እንግዳ ሴት” ‘በአምላኳ ፊት የገባችውን ኪዳን እንዳቃለለች’ ይገልጻል። አመንዝሮችን ጨምሮ የሐሰት አማልክትን የሚያመልክ ወይም የሙሴን ሕግ የሚያቃልል ማንኛውም ሰው እንግዳ ወይም ባዕድ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።—ኤርምያስ 2:25፤ 3:13

7:1, 2—“ቃሌ” እና “ትእዛዜ” በሚሉት አባባሎች ውስጥ ምን ይካተታል? እነዚህ አባባሎች ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚሰጧቸው ትምህርቶች በተጨማሪ ወላጆች ለቤተሰቡ ጥቅም ሲሉ የሚያወጧቸውን ሕግጋትና ደንቦች ይጨምራሉ። ልጆች ለእነዚህ ሕጎች መገዛትና ወላጆች የሚሰጧቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች መቀበል ይኖርባቸዋል።

8:30—“ዋና ባለሙያ” የተባለው ማን ነው? በሰው የተመሰለችው ጥበብ ራሷን ዋና ባለሙያ በማለት ጠርታለች። በሰውኛ ዘይቤ የቀረበው ይህ አነጋገር፣ የጥበብን ባሕርይ ከመግለጽ ያለፈ ቁም ነገር ይዟል። ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር የአምላክ የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረበትን ሁኔታ ይጠቁማል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ አስቀድሞ “እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት” አድርጎታል። (ምሳሌ 8:22) “ዋና ባለሙያ” እንደመሆኑ መጠን አባቱ ሁሉን ነገር ሲፈጥር እርሱም በሥራው ተካፍሏል።—ቈላስይስ 1:15-17

9:17—“የስርቆት ውሃ” የተባለው ምንድን ነው? ‘ጣፋጭ’ የሆነውስ በምን መልኩ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት የሚያስገኘውን ደስታ ከምንጭ የተቀዳ የሚያረካ ውኃ ከመጠጣት ጋር ያመሳስለዋል። በመሆኑም የስርቆት ውኃ የተባለው በድብቅ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ነው። (ምሳሌ 5:15-17) ግለሰቡ፣ ድርጊቱ በሌሎች ዘንድ እንደማይታወቅበት ማሰቡ እንዲህ ያለው ውኃ ጣፋጭ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:10-14 ኃጢአተኞች በቁሳዊ ሀብት ደልለው የክፋት ጎዳናቸውን እንድንከተል እንዳያደርጉን መጠንቀቅ አለብን።

3:3 NW:- ፍቅራዊ ደግነትንና እውነትን ከፍ አድርገን ልንመለከታቸውና ልክ እንደ ውድ ሐብል በግልጽ ልናሳያቸው ይገባል። እነዚህ ባሕርያት በልባችን ላይ መቀረጽና ከእኛ ጋር ሙሉ በሙሉ መዋሃድ ይኖርባቸዋል።

4:18 መንፈሳዊ እውቀት ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ነገር ነው። በመንፈሳዊ ብርሃን ውስጥ ጸንተን ለመኖር ከፈለግን ትሑትና ገር እንደሆንን መቀጠል ይኖርብናል።

5:8 በሙዚቃ፣ በመዝናኛ፣ በኢንተርኔት ወይም በመጻሕፍትና በጋዜጦች ከሚተላለፉት ከሁሉም ጎጂ የሆኑ የሥነ ምግባር ተጽዕኖዎች መራቅ ይኖርብናል።

5:21 ይሖዋን የሚወድ ሰው ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ጥሩ ዝምድና ለጥቂት ጊዜ በሚቆይ ደስታ ይለውጠዋል? በጭራሽ! የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚገፋፋን ከሁሉ የላቀው ጠንካራ ምክንያት ይሖዋ መንገዳችንን ሁሉ እንደሚመለከትና የምናደርጋቸው ነገሮች በእርሱ ዘንድ እንደሚያስጠይቁን ማወቃችን ነው።

6:1-5 እነዚህ ቁጥሮች ‘ለጎረቤት ዋስ ከመሆን’ ወይም ሌሎችን ለመርዳት ስንል ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባን የሚገልጹ እጅግ ጠቃሚ ምክሮችን ይዘዋል! ስላደረግነው ነገር በጥሞና ስናስብ ጥበብ የጎደለው አካሄድ መሆኑን ካስተዋልን፣ ሳንዘገይ ‘ጎረቤታችንን አጥብቀን መነዝነዝ’ እንዲሁም ጉዳዩን ለማስተካከል የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።

6:16-19 ማንኛውም የክፋት ድርጊት በእነዚህ ሰባት ዋና ዋና ክፍሎች ውስጥ ይካተታል ለማለት ይቻላል። በመሆኑም አጥብቀን ልንጠላቸው ይገባል።

6:20-24 ከልጅነት ጀምሮ የተሰጠ መንፈሳዊ ሥልጠና አንድን ሰው በሥነ ምግባር ብልግና ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ ይረዳዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ከመስጠት ቸል ማለት የለባቸውም።

7:4 ማስተዋልንና ጥበብን አጥብቀን መውደድ ይኖርብናል።

መመሪያ ሊሆኑን የሚችሉ አጫጭር አባባሎች

(ምሳሌ 10:1 እስከ 29:27)

ቀሪዎቹ የሰሎሞን ምሳሌዎች አጫጭር አባባሎችን ይዘዋል። እነዚህ አባባሎች ብዙውን ጊዜ የቀረቡት አንድን ነገር ከሌላው ጋር በማነጻጸር፣ በማመሳሰልና በማወዳደር ሲሆን ባሕርይን፣ አነጋገርንና አመለካከትን የሚዳስሱ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይዘዋል።

ከምዕራፍ 10 እስከ ምዕራፍ 24 ያሉት ምዕራፎች ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ዋጋ እንዳለው ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። ከምዕራፍ 25 እስከ ምዕራፍ 29 ድረስ ያሉትን ምሳሌዎች የገለበጡት “የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች” ናቸው። (ምሳሌ 25:1) እነዚህ ምሳሌዎች በይሖዋ መታመን እንዳለብን የሚገልጹትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችንም ይዘዋል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

10:6—‘መዓት የክፉዎችን አፍ የሚዘጋው’ እንዴት ነው? ይህ አባባል በአጠቃላይ ሲታይ ክፉ አድራጊዎች በሌሎች ዘንድ ጥላቻን እንደሚያተርፉና ይህም ዝም እንዲሉ ምክንያት እንደሚሆናቸው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ወይም በግርጌ ማስታወሻው መሠረት፣ ክፉዎች ጣፋጭ በሚመስል አንደበት ሌሎችን የሚጎዳ ተንኮል ያዘለ ድርጊታቸውን እንደሚሸፍኑ ለማመልከት ታስቦም ይሆናል።

10:10—‘በዐይኑ የሚጠቅስ’ ሐዘን የሚያስከትለው እንዴት ነው? “ወሮበላና ጨካኝ [“ምናምንቴ፣” የ1954 ትርጉም] ሰው” ‘በነውረኛ አንደበቱ’ ብቻ ሳይሆን ‘ጥቅሻን’ የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን በማሳየት የክፋት ሐሳቡን ለመሸፋፈን ይሞክራል። (ምሳሌ 6:12, 13) ይህ ዓይነቱ የማታለል ድርጊት ተጠቂውን ለከፍተኛ ሐዘን ሊዳርገው ይችላል።

10:29—“የእግዚአብሔር መንገድ” ምንድን ነው? ይህ ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያመለክት እንጂ ልንከተለው የሚገባንን የአኗኗር ዘይቤ የሚጠቁም አይደለም። አምላክ የሰው ልጆችን የያዘበት መንገድ ለጻድቃን መጠጊያቸው ለክፉዎች ደግሞ መጥፊያቸው መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

11:31—ኃጢአተኞች ከጻድቃን የባሰ የሚቀበሉት ለምንድን ነው? እዚህ ላይ እየተነገረ ያለው ጻድቃንም ሆኑ ኃጥአን ስለሚቀበሉት የቅጣት መጠን ነው። ጻድቅ ሲሳሳት እርማት ይሰጠዋል። ክፉ ሰው ግን ሆነ ብሎ ኃጢአት ከመሥራቱም ባሻገር ወደ መልካም ጎዳና ለመመለስ አሻፈረኝ ይላል። በመሆኑም ይህ ሰው የባሰ ቅጣት ሊቀበል ይገባዋል።

12:23—አንድ ሰው ‘ዕውቀትን የሚሰውረው’ እንዴት ነው? አንድ ሰው እውቀትን ይሰውራል ሲባል የሚያውቀውን ሁሉ ከሌሎች ይደብቃል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውቀቱን ጉራ በመንዛት ሳይሆን በማስተዋል ለሌሎች ያካፍላል ማለት ነው።

14:17—‘መሠሪ ሰው የማይወደደው’ ለምንድን ነው? “መሠሪ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሁለት ትርጉም አለው። አስተዋይ የሆነን ሰው አሊያም ደግሞ ተንኮለኛን ሰው ያመለክታል። ተንኮል የሚያውጠነጥን ሰው ለምን እንደሚጠላ መረዳት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ‘ከዓለም ላለመሆን’ የሚመርጡ አስተዋይ ሰዎችም መጠላታቸው አይቀርም።—ዮሐንስ 15:19

18:19—“የተበደለ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይበልጥ የማይበገር” የሚሆነው አንዴት ነው? እንዲህ ዓይነቱ ሰው ልክ በጠላት እንደተወረረ የተመሸገ ከተማ የደረሰበትን በደል ይቅር ከማለት ይልቅ ግትር አቋም ይይዝ ይሆናል። በእርሱና በበዳዩ መካከል የተነሳው ቅራኔ ሊከፈት እንደማይችል “እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ” በመካከላቸው ገደብ ሊፈጥር ይችላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

10:11-14 አነጋገራችን ሌሎችን የሚያንጽ እንዲሆን ከተፈለገ አእምሯችን በትክክለኛው እውቀት መሞላትና ልባችንም በፍቅር መገፋፋት አለበት። እንዲሁም ከአፋችን የሚወጡትን ቃላት በጥበብ መምረጥ ይኖርብናል።

10:19፤ 12:18፤ 13:3፤ 15:28፤ 17:28 የምንናገራቸው ቃላት ቀደም ተብሎ የታሰበባቸው ሊሆኑ ይገባል፤ ብዙ ከመናገር መቆጠብም ይኖርብናል።

11:1፤ 16:11፤ 20:10, 23 ይሖዋ ከሌሎች ጋር በምናደርገው የንግድ ግንኙነት ረገድ ሐቀኞች እንድንሆን ይፈልጋል።

11:4 የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን፣ የጉባኤ ስብሰባን፣ ጸሎትንና አገልግሎትን የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን ችላ ብሎ ቁሳዊ ሀብትን በማሳደድ መጠመድ ሞኝነት ነው።

13:4 የጉባኤ ኃላፊነትን ለመሸከም ወይም በመጪው አዲስ ዓለም የሚገኘውን ሕይወት ለመውረስ ‘መመኘት’ ብቻውን በቂ አይደለም። ታታሪ መሆንና ብቃቶቹን ለማሟላት ጠንክሮ መሥራት ይገባል።

13:24፤ 29:15, 21 አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ልጁን መረን አይለቅም ወይም ደግሞ ሲያጠፋ በቸልታ አያልፈውም። ከዚህ ይልቅ አባት ወይም እናት የልጃቸውን መጥፎ ዝንባሌ ለማስወገድ ሲሉ ችግሩ ሥር ከመስደዱ በፊት ተገቢውን እርማት መስጠት ይኖርባቸዋል።

14:10 አንዳንዴ ያሰብነውን ያህል የውስጥ ስሜታችንን አውጥተን መግለጽ ሊሳነን ወይም ደግሞ የሚመለከቱን ሰዎች ስሜታችንን ሙሉ በሙሉ ላይረዱልን ይችላሉ። በመሆኑም ከሌሎች የምንፈልገውን ያህል ማጽናኛ ሳናገኝ ልንቀር እንችላለን። በዚህ ጊዜ በይሖዋ ላይ ብቻ ታምነን የሚገጥሙንን ችግሮች ለመወጣት መጣር ሊኖርብን ይችላል።

15:7 የ1954 ትርጉም:- አንድ ገበሬ የሚዘራውን ዘር በአንድ በተወሰነ መሬት ላይ እንደማይገለብጠው ሁሉ እኛም የምናውቀውን በሙሉ በሌሎች ላይ ከመዘርገፍ መቆጠብ ይኖርብናል። ጠቢብ የሆነ ሰው እውቀቱን እንደ አስፈላጊነቱ ቀስ በቀስ ይዘራል።

15:15፤ 18:14 አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን አስጨናቂ ነገሮች ቢደርሱብንም እንኳ ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል።

17:24 አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ከሚያተኩሩና ዓይኖቻቸው ከወዲያ ወዲህ ከሚንከራተቱ “ተላሎች” በተለየ መልኩ በጥበብ መመላለስ እንችል ዘንድ ማስተዋልን ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።

23:6-8 ሌሎችን በእንግድነት ስንቀበል ግብዞች ከመሆን መራቅ ይኖርብናል።

27:21 የሚቀርብልን ምስጋና ማንነታችን ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል። ስንመሰገን ምሥጋናውን ያገኘነው በራሳችን ጥረት ሳይሆን በይሖዋ እርዳታ መሆኑን በማመን እርሱን ይበልጥ ለማገልገል የምንነሳሳ ከሆነ ትሑት መሆናችን ይታያል። ሆኖም ምሥጋና ሲቀርብልን ከሌሎች እንደበለጥን ሆኖ የሚሰማን ከሆነ ትሕትና እንደሚጎድለን ይጠቁማል።

27:23-27 እነዚህ ምሳሌዎች የአንድን ከብት አርቢ ሕይወት በናሙና መልክ በመጥቀስ በትጋት እየሠሩ ቀላል ኑሮ መምራት እርካታ እንደሚያስገኝ ያሳያሉ። ከዚህም በላይ በይሖዋ ላይ የመታመንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ። a

28:5 የ1954 ትርጉም:- ወደ ይሖዋ በመጸለይና ቃሉን በትጋት በማጥናት ‘አምላክን የምንሻ’ ከሆነ እርሱን በተገቢው መንገድ ለማገልገል የሚያስፈልገንን ‘ማስተዋል ሁሉ’ እናገኛለን።

‘በጥሞና የተነገረ ንግግር’

(ምሳሌ 30:1 እስከ 31:31)

የምሳሌ መጽሐፍ ‘በጥሞና በተነገሩ’ ሁለት መልእክቶች ይደመደማል። (ምሳሌ 30:1 የ1980 ትርጉም፤ 31:1 NW) በንጽጽር ዘይቤ የቀረቡት የአጉር አመራማሪ ምሳሌዎች ስግብግብነት እርካታ እንደማያስገኝ ይገልጻሉ። ከዚህም በተጨማሪ አሳሳች ወንዶች ወጣት ሴቶችን ለማጥመድ የሚጠቀሙባቸው መሠሪ ዘዴዎች ለመረዳት እንኳ አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳያሉ። b ከኩራትና ከቁጣ መራቅ እንዳለብንም ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ።

የልሙኤል እናት ለልጅዋ ያስተላለፈችው መልእክት፣ የወይን ጠጅን ጨምሮ የሚያሰክሩ መጠጦችን በአግባቡ ስለ መጠቀምና በጽድቅ ስለ መፍረድ የሚገልጹ ጠቃሚ ምክሮችን ይዘዋል። መልካም ሚስትን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ የሚቋጨው በሚከተለው አባባል ነው:- “የሚገባትን ሽልማት ስጧት፤ ሥራዋም በየአደባባዩ ያስመስግናት።”—ምሳሌ 31:31

ጥበብን አግኝ፣ ተግሣጽን ተቀበል፣ አምላካዊ ፍርሃትን አዳብር እንዲሁም በይሖዋ ታመን። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የምሳሌ መጽሐፍ እንዴት ያሉ ግሩም ትምህርቶችን ያስጨብጠናል! እንግዲያው ምክሮቹን ተግባራዊ በማድረግ “እግዚአብሔርን የሚፈራ” ሰው የሚያገኘውን ደስታ እናጣጥም።—መዝሙር 112:1

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የነሐሴ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31⁠ን ተመልከት።

b የሐምሌ 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የትክክለኛ እውቀት ሁሉ ምንጭ ነው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘እውቀትን መዝራት’ ሲባል ምን ማለት ነው?