በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነትና አምላካዊ ፍርሃት የሚያስገኘው ድፍረት

እምነትና አምላካዊ ፍርሃት የሚያስገኘው ድፍረት

እምነትና አምላካዊ ፍርሃት የሚያስገኘው ድፍረት

“እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ [“ደፋር ሁን፣” NW]፤ በርታ።”—ኢያሱ 1:9

1, 2. (ሀ) በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ እስራኤላውያን ከነዓናውያንን የማሸነፍ አጋጣሚያቸው ምን ያህል ነበር? (ለ) ይሖዋ ለኢያሱ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶታል?

 በ1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ሙሴ ሊገጥሟቸው ስለሚችሉ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስመልክቶ ለሕዝቡ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጣቸው:- “ሰማይ ጠቀስ ቅጥር ያላቸው ታላላቅ ከተሞች ያሏቸውን፣ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ አስለቅቀህ ለመግባት ዮርዳኖስን አሁን ትሻገራለህ። ዔናቃውያን ብርቱና ቁመተ ረጃጅም ሕዝቦች ናቸው፤ . . . ‘ዔናቃውያንን ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?’ ሲባልም ሰምተሃል።” (ዘዳግም 9:1, 2) አዎን፣ እነዚህ ግዙፍ ጦረኞች ስማቸው የገነነ ነበር! ከዚህም በላይ አንዳንድ ከነዓናውያን በሚገባ የታጠቀ ሠራዊት ያላቸው ሲሆን ከጦር ትጥቆቻቸው መካከል ፈረሶችና ጎማዎቻቸው ላይ ረጅም ስለታም ማጭድ የተገጠመላቸው ሰረገሎች ይገኙበታል።—መሳፍንት 4:13

2 በሌላ በኩል እስራኤላውያን በባርነት ቀንበር ሥር ሲማቅቁ የኖሩ ሲሆን ለ40 ዓመታትም በምድረ በዳ ሲንከራተቱ ቆይተዋል። በመሆኑም በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ የማሸነፍ አጋጣሚያቸው እጅግ የመነመነ ነበር። ያም ሆኖ ሙሴ እምነት ነበረው፤ ይሖዋ እየመራቸው እንዳለ ‘ይታየው’ ነበር። (ዕብራውያን 11:27) ስለሆነም ሕዝቡን “ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህ እግዚአብሔር . . . እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል” አላቸው። (ዘዳግም 9:3፤ መዝሙር 33:16, 17) ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ የእርሱ ድጋፍ እንደማይለየው ለኢያሱ ሲያረጋግጥለት እንደሚከተለው ብሎታል:- “አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእሥራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ።”—ኢያሱ 1:2, 5

3. ኢያሱ እምነትና ድፍረት እንዲኖረው የረዳው ምንድን ነው?

3 ኢያሱ የይሖዋን እርዳታና መመሪያ ማግኘት ከፈለገ የአምላክን ሕግ ማንበብና ማሰላሰል እንዲሁም በሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅበት ነበር። ይሖዋ እንዲህ ብሎታል:- “ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤ በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ [“ደፋር ሁን፣” NW]፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?” (ኢያሱ 1:8, 9) ኢያሱ አምላክን በመስማቱ ደፋር፣ ብርቱና ስኬታማ ሊሆን ችሏል። ይሁንና በእርሱ ትውልድ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን አልሰሙም። በዚህም ምክንያት ስኬታማ ለመሆን ያልቻሉ ከመሆኑም በላይ በምድረ በዳ ሞተዋል።

እምነት የለሹ ሕዝብ ድፍረት አጣ

4, 5. (ሀ) አሥሩ ሰላዮች የነበራቸው አመለካከት ኢያሱና ካሌብ ከነበራቸው አስተሳሰብ ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡ እምነት በማጣቱ ምን ተሰማው?

4 ከአርባ ዓመት በፊት ማለትም እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ሊገቡ በተቃረቡበት ጊዜ፣ ሙሴ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ለማድረግ 12 ሰዎችን ልኮ ነበር። ከእነዚህ መካከል አሥሩ በፍርሃት ርደው ተመለሱ። “እዚያ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ግዙፎች ናቸው፤ ኔፊሊምንም በዚያ አይተናል፤ የዔናቅ ዝርያዎች የመጡት ከኔፊሊም ነው። ራሳችንን ስናየው እንደ አንበጣ ነበርን” በማለትም ጮኹ። በእርግጥ ከዔናቅ ዝርያዎች ሌላ በዚያ የተመለከቷቸው “ሰዎች ሁሉ” ግዙፎች ነበሩ? በጭራሽ። የዔናቅ ሰዎችስ ከጥፋት ውኃ በፊት ከነበሩት ከኔፊሊሞች የመጡ ናቸው? በፍጹም አይደሉም! ያም ሆኖ በዚህ የተጋነነ ወሬ ሳቢያ ማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ሽብር ተፈጠረ። እንዲያውም በባርነት ሲኖሩበት ወደነበረው ወደ ግብጽ ለመመለስ እስከመፈለግ ደረሱ!—ዘኍልቍ 13:31 እስከ 14:4

5 ይሁን እንጂ ከሰላዮቹ መካከል ሁለቱ ማለትም ኢያሱና ካሌብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። በመሆኑም ከነዓናውያንን “እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለን . . . ጥላቸው ተገፎአል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው” ሲሉ ተናገሩ። (ዘኍልቍ 14:9) ኢያሱና ካሌብ እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት የያዙት ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ነበር? በጭራሽ አልነበረም። እንደማንኛውም እስራኤላዊ ይሖዋ አሥሩን መቅሰፍት በማምጣት ኃያሏን ግብጽንና አማልክቶቿን እንዴት አድርጎ እንዳዋረዳቸው ተመልክተዋል። በኋላም ይሖዋ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ሲያሰጥማቸው እማኞች ነበሩ። (መዝሙር 136:15) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አሥሩ ሰላዮችም ሆኑ ወሬያቸውን አምነው የተቀበሉት ሰዎች መፍራታቸው ተገቢ አልነበረም። ስለሆነም ይሖዋ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው?” በማለት በሁኔታው በጥልቅ ማዘኑን ገልጿል።—ዘኍልቍ 14:11

6. ድፍረትና እምነት የሚያያዙት እንዴት ነው? ይህ ሁኔታስ በዘመናችን የታየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምን እንደነበር በግልጽ ተናግሯል፤ ሕዝቡ በፍርሃት መርበድበዳቸው እምነት ማጣታቸውን የሚያጋልጥ ነበር። አዎን፣ እምነትና ድፍረት በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ዮሐንስ የክርስቲያን ጉባኤንና የሚያደርገውን መንፈሳዊ ውጊያ አስመልክቶ “ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:4) በዛሬው ጊዜ፣ ወጣት አረጋዊ፣ ብርቱ ደካማ ሳይባል ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ የገፋፋቸው የኢያሱና የካሌብ ዓይነት እምነት ነው። ይህን ኃያልና ደፋር ሠራዊት ማንኛውም ዓይነት ጠላት ዝም ሊያሰኘው አይችልም።—ሮሜ 8:31

‘ወደ ኋላ አታፈግፍጉ’

7. ‘ወደ ኋላ ማፈግፈግ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

7 በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ምሥራቹን በድፍረት የሚሰብኩት “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም” በማለት ከጻፈው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የሚመሳሰል አስተሳሰብ ስላላቸው ነው። (ዕብራውያን 10:39) ጳውሎስ የገለጸው ‘ወደ ኋላ ማፈግፈግ’ የሚለው ሐሳብ አንዳንድ ጊዜ ሊያጋጥም የሚችለውን ጊዜያዊ የፍርሃት ስሜት የሚያመለክት አይደለም፤ ምክንያቱም ብዙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ፍርሃት የተሰማቸው ጊዜ አለ። (1 ሳሙኤል 21:12፤ 1 ነገሥት 19:1-4) ከዚህ ይልቅ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው “ወደኋላ መመለስን፣ መሸሽንና እውነትን ችላ ማለትን” ያመለክታል። አክሎም ‘ወደ ኋላ ማፈግፈግ’ ከአምላክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ “የመርከብን ሸራ አውርዶ ፍጥነቱ እንዲቀንስ ማድረግን” የሚያሳይ ምሳሌያዊ አነጋገር ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። እርግጥ ነው፣ ጠንካራ እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች ስደት፣ የጤና መታወክ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸው እንኳ ‘ፍጥነታቸው እንዲቀንስ’ አይፈቅዱም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብላቸውና ድካማቸውን እንደሚረዳላቸው ስለሚገነዘቡ እርሱን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ። (መዝሙር 55:22፤ 103:14) አንተስ ይህን የመሰለ እምነት አለህ?

8, 9. (ሀ) ይሖዋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች እምነት ያጠናከረው እንዴት ነው? (ለ) እምነታችንን ለመገንባት ምን ማድረግ እንችላለን?

8 በአንድ ወቅት ሐዋርያት እምነታቸው እንዳነሰ ሆኖ ስለተሰማቸው ኢየሱስን “እምነታችንን ጨምርልን” ብለውት ነበር። (ሉቃስ 17:5) ከልብ ያቀረቡት ይህ ጥያቄ በተለይ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ በተቀበሉና የአምላክን ቃልና ዓላማ በጥልቀት ለመረዳት በቻሉ ጊዜ ምላሽ አግኝቷል። (ዮሐንስ 14:26፤ የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚህ ወቅት እምነታቸው የተጠናከረ ሲሆን ተቃውሞ ቢኖርባቸውም ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ለማዳረስ ያስቻላቸውን የስብከት ዘመቻ ጀመሩ።—ቈላስይስ 1:23፤ የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 28:22

9 እኛም እምነታችንን ለመገንባትና በአገልግሎታችን ለመቀጠል ከፈለግን ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናት፣ ማሰላሰልና መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ኢያሱ፣ ካሌብና የጥንት ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉት ሁሉ የአምላክ እውነት በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲቀረጽ በማድረግ ያለብንን መንፈሳዊ ውጊያ በጽናት ለመዋጋትና አሸናፊዎች ለመሆን የሚያስፈልገንን ድፍረት ማግኘት እንችላለን።—ሮሜ 10:17

አምላክ መኖሩን ማመን ብቻ በቂ አይደለም

10. ትክክለኛ እምነት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

10 በጥንት ዘመን በነበሩት ታማኝ ሰዎች ላይ እንደታየው ድፍረትና ጽናት የሚያስገኘው እምነት አምላክ መኖሩን አምኖ ከመቀበል ያለፈ ነገርን ይጨምራል። (ያዕቆብ 2:19) እምነት ይሖዋን በሚገባ ማወቅና በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ይጠይቃል። (መዝሙር 78:5-8፤ ምሳሌ 3:5, 6) ይህም የአምላክን ሕግና መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ ለራሳችን መሆኑን በሙሉ ልብ አምነን መቀበል አለብን ማለት ነው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እምነት ይሖዋ ቃል የገባውን ነገር በሙሉ እንደሚፈጽምና “ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ” ማመንን ይጨምራል።—ዕብራውያን 11:1, 6፤ ኢሳይያስ 55:11

11. ኢያሱና ካሌብ እምነትና ድፍረት በማሳየታቸው የተባረኩት እንዴት ነው?

11 እንዲህ ዓይነቱ እምነት ባለበት የሚቆም አይደለም። እውነትን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ባደረግን፣ የዚህንም ጥቅም ‘በቀመስን’ እንዲሁም ለምናቀርባቸው ጸሎቶች የሚሰጡንን ምላሾች ‘ባየን’ ቁጥር በሌላ አነጋገር በእርግጥ ይሖዋ እየመራን መሆኑን በተገነዘብን መጠን እምነታችን እያደገ ይሄዳል። (መዝሙር 34:8፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15) ኢያሱና ካሌብ የአምላክን ጥሩነት መቅመሳቸው ጥልቅ እምነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ እሙን ነው። (ኢያሱ 23:14) የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል:- አምላክ ቃል በገባላቸው መሠረት ከ40 ዓመቱ የምድረ በዳ ጉዞ በሕይወት ተርፈዋል። (ዘኍልቍ 14:27-30፤ 32:11, 12) ከነዓንን ለመያዝ በተደረገው የስድስት ዓመት ጦርነት በትጋት ተካፍለዋል። በመጨረሻም ረጅም ዕድሜና ጥሩ ጤንነት እንዲሁም የራሳቸው ርስት አግኝተዋል። በእርግጥም ይሖዋ በታማኝነትና በድፍረት የሚያገለግሉትን አብዝቶ ይባርካቸዋል!—ኢያሱ 14:6, 9-14፤ 19:49, 50፤ 24:29

12. ይሖዋ ‘ቃሉን ከፍ ከፍ’ የሚያደርገው እንዴት ነው?

12 አምላክ ለኢያሱና ለካሌብ ያሳያቸው ፍቅራዊ ደግነት መዝሙራዊው “ቃልህን፣ ከሁሉ [“ከስምህ ሁሉ፣” የ1879 ትርጉም] በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሱናል። (መዝሙር 138:2) ይሖዋ አንድ ነገር በስሙ ቃል ሲገባ፣ የገባው ቃል ፍጻሜ እጅግ “ከፍ ከፍ” ያለ ይኸውም እኛ ከምናስበው በላይ የተረጋገጠ ይሆናል። (ኤፌሶን 3:20) አዎን፣ ይሖዋ በእርሱ ‘ደስ ለሚላቸው’ ሰዎች ተስፋ የገባላቸውን ሳይፈጽም ቀርቶ አያሳፍራቸውም።—መዝሙር 37:3, 4

‘እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ’ ሰው

13, 14. ሄኖክ እምነትና ድፍረት ያስፈለገው ለምን ነበር?

13 በቅድመ ክርስትና ዘመን ከነበሩት ምሥክሮች መካከል አንዱ የሆነውን የሄኖክን ምሳሌ በመመርመር ስለ እምነትና ስለ ድፍረት ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሄኖክ ገና ትንቢት መናገር ከመጀመሩ በፊት እምነትና ድፍረት ማሳየቱ ለፈተና እንደሚዳርገው ሳይገነዘብ አልቀረም። እንዴት? ምክንያቱም ይሖዋ በእርሱ አገልጋዮችና በሰይጣን ዲያብሎስ አገልጋዮች መካከል ጠላትነት ወይም ጥላቻ እንደሚኖር በዔድን ገልጾ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15) በተጨማሪም ሄኖክ ይህ ጥላቻ በሰው ዘር የመጀመሪያ ታሪክ ላይ ቃየን ወንድሙን አቤልን በገደለ ጊዜ በገሃድ መታየት መጀመሩን ያውቃል። ምክንያቱም አባታቸው አዳም፣ ሄኖክ ከተወለደ በኋላ ወደ 310 ለሚጠጉ ዓመታት በሕይወት ኖሯል።—ዘፍጥረት 5:3-18

14 ሄኖክ ይህን ሁሉ የሚያውቅ ቢሆንም በድፍረት ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ’ ሲሆን ክፉ ሰዎች በይሖዋ ላይ የሚናገሩትን “የስድብ ቃል” ያወግዝ ነበር። (ዘፍጥረት 5:22፤ ይሁዳ 14, 15) ሄኖክ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ የወሰደው ድፍረት የተሞላበት አቋም በርካታ ጠላቶችን እንዲያፈራና ሕይወቱ ለአደጋ እንዲጋለጥ ሳያደርገው አልቀረም። በዚህ ጊዜ ይሖዋ የእርሱ ነቢይ የሆነውን ይህን ሰው ተሠቃይቶ እንዳይሞት ጠብቆታል። ይሖዋ እርሱን “ደስ እንዳሰኘ” ለሄኖክ ከገለጠለት በኋላ ከሕይወት ወደ ሞት ‘ወስዶታል፤’ ምናልባትም ይህን ያደረገው ሄኖክ ተመስጦ ራእይ በመመልከት ላይ እያለ ሊሆን ይችላል።—ዕብራውያን 11:5, 13፤ ዘፍጥረት 5:24

15. ሄኖክ በዘመናችን ለሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?

15 ጳውሎስ የሄኖክን መወሰድ ከተናገረ በኋላ ቀጠል አድርጎ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት የእምነትን አስፈላጊነት በድጋሚ አጽንዖት ሰጥቶታል። (ዕብራውያን 11:6) አዎን፣ ሄኖክ የነበረው እምነት አካሄዱን ከይሖዋ ጋር እንዲያደርግና አምላክ የለሽ ለሆነው ዓለም የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ድፍረት ሰጥቶታል። በዚህ ረገድ ሄኖክ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። እኛም ብንሆን እውነተኛውን አምልኮ በሚቃወመውና በክፋት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ልናከናውነው የሚገባን ተመሳሳይ ሥራ ተሰጥቶናል።—መዝሙር 92:7፤ ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 12:17

አምላካዊ ፍርሃት ድፍረት ያስገኛል

16, 17. አብድዩ ማን ነው? በምንስ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር?

16 ከእምነት በተጨማሪ ድፍረትን ለማግኘት የሚረዳን ሌላም ባሕርይ አለ። ይኸውም ለአምላክ ያለን አክብሮታዊ ፍርሃት ነው። በነቢዩ ኤልያስና በሰሜናዊው የእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ዘመን ስለኖረውና አምላክን በመፍራት ረገድ የላቀ ምሳሌ ስለሆነ አንድ ሰው እንመልከት። በአክዓብ የግዛት ዘመን ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በበኣል አምልኮ ተበክሎ ነበር። እንዲያውም የአክዓብ ሚስት ከነበረችው ‘ከኤልዛቤል ማእድ’ የሚመገቡ 450 የበኣልና 400 የአሼራ ነቢያት ነበሩ።—1 ነገሥት 16:30-33፤ 18:19

17 የይሖዋ ጠላት የሆነችው ጨካኟ ኤልዛቤል እውነተኛውን አምልኮ ከምድር ላይ ለማጥፋት ጥራለች። አንዳንድ የይሖዋ ነቢያትን ያስገደለች ከመሆኑም ባሻገር ኤልያስን ለመግደል ትፈልግ ነበር፤ ይሁንና ኤልያስ በይሖዋ መመሪያ መሠረት ዮርዳኖስን አቋርጦ ሸሸ። (1 ነገሥት 17:1-3፤ 18:13) በዚህ ጊዜ በሰሜናዊው መንግሥት ውስጥ ትክክለኛውን አምልኮ ይዞ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትህም። በወቅቱ በቤተ መንግሥት ውስጥ የምትሠራ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ሁኔታው ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስብ። ፈሪሃ አምላክ የነበረው የአክዓብ ቤት አዛዥ አብድዩ a በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበር።—1 ነገሥት 18:3

18. የይሖዋ አምላኪ የነበረውን አብድዩን ልዩ ያደረገው ምንድን ነው?

18 አብድዩ የይሖዋን አምልኮ የሚያራምደው በብልሃትና በማስተዋል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ አቋሙን አላላላም። እንዲያውም 1 ነገሥት 18:3 “አብድዩም እግዚአብሔርን በጣም የሚፈራ ሰው ነበር” በማለት ይናገራል። አዎን፣ አብድዩ ያሳየው አምላካዊ ፍርሃት ፍጹም የተለየ ነበር! እንዲህ ዓይነቱ ጤናማ ፍርሃት ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት ማስገደል ስትጀምር የሚያስገርም ድፍረት እንዲያሳይ አስችሎታል።

19. አብድዩ ደፋር መሆኑን የሚያሳይ ምን ነገር አድርጓል?

19 ይህን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ እናነባለን:- “ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት እያስገደለች በነበረበት ጊዜ፣ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውሃ ይሰጣቸው ነበር።” (1 ነገሥት 18:4) ከሁኔታው መገመት እንደምትችለው መቶ ሰዎችን በድብቅ መመገብ እጅግ አደገኛ ሥራ ነው። አብድዩ አክዓብና ኤልዛቤል እንዳይዙት ብቻ ሳይሆን ወደ ቤተ መንግሥቱ በተደጋጋሚ የሚመጡት 850 የሐሰት ነቢያት እንዳያዩት ጭምር መጠንቀቅ ነበረበት። ከዚህም ባሻገር፣ ከገበሬው አንስቶ እስከ መሳፍንቱ ድረስ ያሉት በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ የሐሰት አምላኪዎች የንጉሡንና የንግሥቲቱን ውዳሴ ለማግኘት ሲሉ አብድዩን ከማጋለጥ ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ አብድዩ ከዚያ ሁሉ ጣዖት አምላኪ አፍንጫ ሥር ሆኖ ለይሖዋ ነቢያት የሚያስፈጓቸውን ነገሮች ያቀርብላቸው ነበር። በእርግጥም አምላካዊ ፍርሃት አንድን ሰው ደፋር የማድረግ ኃይል አለው!

20. አብድዩ ፈሪሃ አምላክ ያለው መሆኑ ፍርሃትን ለማስወገድ የረዳው እንዴት ነው? የእርሱ ምሳሌስ እንዴት ይረዳሃል?

20 አብድዩ በድፍረት እርምጃ የወሰደው አምላክን ከመፍራቱ የተነሳ ስለነበረ ይሖዋም ከጠላቶቹ ጠብቆት መሆን አለበት። ምሳሌ 29:25 “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል” ይላል። አብድዩ የተለየ ሰው አልነበረም፤ ሁላችንም ሊሰማን እንደሚችለው ሁሉ እርሱም ተይዞ እንዳይገደል ፈርቶ ነበር። (1 ነገሥት 18:7-9, 12) ሆኖም አምላካዊ ፍርሃት ማንኛውንም ሰው እንዳይፈራ ድፍረት ሰጥቶታል። አብድዩ ለሁላችንም፣ በተለይም ደግሞ ነጻነታቸውን አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ይሖዋን ለሚያመልኩ ሰዎች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። (ማቴዎስ 24:9) አዎን፣ ሁላችንም ይሖዋን “በአክብሮትና በፍርሀት” ለማምለክ ከልብ እንጣር።—ዕብራውያን 12:28

21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

21 ድፍረት እንድናገኝ የሚረዱን ባሕርያት እምነትና አምላካዊ ፍርሃት ብቻ አይደሉም፤ ፍቅርም ቢሆን ከሁሉ የላቀ ብርታት ይሰጠናል። ጳውሎስ “እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንም” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7) አስጨናቂ በሆነው በዚህ የመጨረሻ ቀን ውስጥ ስንኖር ፍቅር ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችል ድፍረት የሚሰጠን እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ሰው ነቢዩ አብድዩ አይደለም።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢያሱና ካሌብ ደፋሮች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው?

• እውነተኛ እምነት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

• ሄኖክ የአምላክን የፍርድ መልእክት ለማወጅ ያልፈራው ለምንድን ነበር?

• አምላካዊ ፍርሃት ድፍረት እንድናገኝ የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ኢያሱን “ደፋር ሁን፤ በርታ” ሲል አዝዞታል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብድዩ ለይሖዋ ነቢያት ጥበቃና እንክብካቤ አድርጎላቸዋል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄኖክ የአምላክን ቃል በድፍረት አውጇል