በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር ድፍረት ይጨምራል

ፍቅር ድፍረት ይጨምራል

ፍቅር ድፍረት ይጨምራል

“እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንም።”—2 ጢሞቴዎስ 1:7

1, 2. (ሀ) ፍቅር አንድን ሰው ምን እንዲያደርግ ይገፋፋዋል? (ለ) የኢየሱስ ድፍረት ከሁሉ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?

 በቅርብ የተጋቡ አንድ ባልና ሚስት በምሥራቅ አውስትራሊያ ጠረፍ በምትገኝ ከተማ አቅራቢያ ጠልቀው ሲዋኙ ከቆዩ በኋላ ከውኃው ለመውጣት ሲቃረቡ አንድ ነጭ ሻርክ በፍጥነት እየተምዘገዘገ ወደ ሚስትየው መጣ። በዚህ ጊዜ ባልየው በድፍረት ሚስቱን ወደ ጎን በመግፋት ሻርኩ እሱን እንዲበላው አደረገ። ባሏን በሞት ያጣችው ይህቺ ሴት በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ “ሕይወቱን ለእኔ ሲል አሳልፎ ሰጥቷል” ስትል ተናግራለች።

2 አዎን፣ ፍቅር ሰዎች የሚያስገርም ድፍረት እንዲያሳዩ ይገፋፋቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም” ብሏል። (ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ ይህን በተናገረ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለአንድ ግለሰብ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ሕይወቱን የሠዋው ድንገት በተፈጠረ ሁኔታ በጀብደኝነት ተነሳስቶ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንደሚፌዝበትና እንደሚንገላታ ብሎም ያላግባብ እንደሚፈረድበት እንዲሁም በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እንደሚሞት ቀደም ብሎ ያውቅ ነበር። እንዲያውም ደቀ መዛሙርቱ ለሚገጥሟቸው ነገሮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በማሰብ እንደሚከተለው ብሏቸዋል:- “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል።”—ማርቆስ 10:33, 34

3. ኢየሱስ በጣም ደፋር እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

3 ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን የላቀ ድፍረት እንዲያሳይ አስተዋጽኦ ያደረጉት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? በዚህ ረገድ እምነትና አምላካዊ ፍርሃት ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል። (ዕብራውያን 5:7፤ 12:2) ከሁሉም በላይ ግን ኢየሱስን ደፋር እንዲሆን የረዳው ለአምላክና ለሰዎች ያለው ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 3:16) እኛም ከእምነትና ከአምላካዊ ፍርሃት በተጨማሪ ፍቅርን የምናዳብር ከሆነ የክርስቶስ ዓይነት ድፍረት ማሳየት እንችላለን። (ኤፌሶን 5:2) ይህን ዓይነቱን ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ምንጩን ማወቅ ይኖርብናል።

‘ፍቅር ከእግዚአብሔር ነው’

4. ይሖዋ የፍቅር ምንጭ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌትና ምንጭ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” (1 ዮሐንስ 4:7, 8) በመሆኑም አንድ ሰው አምላካዊ ፍቅርን መኮትኮት የሚችለው ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እንዲሁም ያወቀውን ነገር ከልብ በመታዘዝ ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ ሲችል ነው።—ፊልጵስዩስ 1:9፤ ያዕቆብ 4:8፤ 1 ዮሐንስ 5:3

5, 6. በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች የእርሱን ዓይነት ፍቅር እንዲያዳብሩ የረዳቸው ምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ከአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያት ጋር ሆኖ ባቀረበው የመጨረሻ ጸሎት ላይ አምላክን በማወቅና ፍቅርን በማዳበር መካከል ያለውን ግንኙነት ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።” (ዮሐንስ 17:26) ኢየሱስ የአምላክ ስም የሚወክላቸውን ግሩም ባሕርያት በቃልም ሆነ በተግባር በማንጸባረቅ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱና በአባቱ መካከል የሚታየውን ዓይነት ፍቅር እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ለማለት ችሏል።—ዮሐንስ 14:9, 10፤ 17:8

6 የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:22) የጥንት ክርስቲያኖች በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ ሲቀበሉ ኢየሱስ ያስተማራቸውን በርካታ ትምህርቶች ማስታወስ ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን ጽሑፎችን ይበልጥ መረዳት ችለው ነበር። ያገኙት ጥልቅ ማስተዋል ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዳጠናከረላቸው ግልጽ ነው። (ዮሐንስ 14:26፤ 15:26) ውጤቱስ ምን ነበር? ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቢሆንም እንኳ ምሥራቹን በድፍረትና በቅንዓት አውጀዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29

ድፍረትና ፍቅር በተግባር ሲገለጽ

7. ጳውሎስና በርናባስ በሚስዮናዊ ጉዟቸው ወቅት ምን ነገሮችን በጽናት ተቋቁመዋል?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንም” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7) ጳውሎስ ይህን የተናገረው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ነው። ከበርናባስ ጋር ባደረጉት ሚስዮናዊ ጉዞ ላይ የገጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። ጳውሎስና በርናባስ አንጾኪያን፣ ኢቆንዮንንና ልስጥራንን ጨምሮ በሌሎች ብዙ ከተሞች ውስጥ ሰብከው ነበር። በእነዚህ ከተሞች ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አንዳንድ ሰዎች ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ በጥላቻ ተሞልተው ይቃወሟቸው ጀመር። (የሐዋርያት ሥራ 13:2, 14, 45, 50፤ 14:1, 5) እንዲያውም በአንድ ወቅት በልስጥራን፣ በቁጣ የተሞሉ ሰዎች ጳውሎስን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጥለውት ሄደዋል! ሆኖም ጳውሎስ “ደቀ መዛሙርት ከበውት እንዳሉ ተነሣ፤ ወደ ከተማም ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄዱ።”—የሐዋርያት ሥራ 14:6, 19, 20

8. ጳውሎስና በርናባስ ያሳዩት ድፍረት ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንደነበራቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 በጳውሎስ ላይ የተቃጣው የመግደል ሙከራ እርሱንም ሆነ በርናባስን ፈርተው ወደኋላ እንዲሉ አድርጓቸዋል? በፍጹም! እንዲያውም በደርቤን “ብዙ ደቀ መዛሙርትም ካፈሩ በኋላ፣ ወደ ልስጥራን፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ።” ለምን? አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማበረታታትና በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ ለመርዳት ሲሉ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” ብለዋል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ለጳውሎስና ለበርናባስ ድፍረት የሰጣቸው ለክርስቶስ ‘በጎች’ ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ነው። (የሐዋርያት ሥራ 14:21-23፤ ዮሐንስ 21:15-17) ጳውሎስና በርናባስ አዲስ ለተቋቋሙት ጉባኤዎች ሽማግሌዎችን ከሾሙ በኋላ በጸሎት አማካኝነት “ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጧቸው።”

9. የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስ ላሳያቸው ፍቅር ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?

9 ጳውሎስ አሳቢና ደፋር ሰው መሆኑ በብዙዎቹ የጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል። ጳውሎስ ሦስት ዓመት ካገለገለባትና ብዙ መከራዎች ካየባት ከኤፌሶን ከተማ ከመጡ ሽማግሌዎች ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ ምን እንደተከሰተ እንመልከት። (የሐዋርያት ሥራ 20:17-31) በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክ መንጋ እንዲጠብቁ ካበረታታቸው በኋላ አብሯቸው ተንበርክኮ ጸለየ። ከዚያም “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን ዐቅፈው ሳሙት፤ ከሁሉም በላይ ልባቸውን የነካው፣ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቱን እንደማያዩ የተናገራቸው ቃል ነበር።” እነዚህ ወንድሞች ጳውሎስን ምንኛ ይወዱት ነበር! በእርግጥም ጳውሎስና በርናባስ መሄጃቸው ሲቃረብ ሽማግሌዎቹ ሊለቋቸው ስላልፈለጉ በግድ ‘ከእነርሱ መለየት’ አስፈልጓቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:36 እስከ 21:1

10. በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አንዳቸው ለሌላው ድፍረት የተሞላበት ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና ሌሎችም ለይሖዋ በጎች ሲሉ የሚያሳዩት ድፍረት የተሞላበት እንቅስቃሴ በጥልቅ እንዲወደዱ አድርጓቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በእርስ በርስ ጦርነት በሚታመሱ ወይም የስብከቱ ሥራ በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ሕይወታቸውንና ነጻነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ጉባኤዎችን ይጎበኛሉ። በተመሳሳይም በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የእምነት ወንድሞቻቸውን አሳልፈው ለመስጠትም ሆነ መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙት ከየት እንደሆነ ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ጨካኝ በሆኑ ገዥዎችና በደጋፊዎቻቸው ሥቃይ ደርሶባቸዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ምሥራቹን መስበካችንን አናቆምም ወይም ደግሞ ከወንድሞቻችን ጋር መሰብሰባችንን አንተውም በማለታቸው ለስደትና ለከፍተኛ ሥቃይ አልፎ ተርፎም ለሞት ተዳርገዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እኛም እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩት ዓይነት እምነትና ፍቅር ይኑረን!—1 ተሰሎንቄ 1:6

ፍቅራችሁ እንዲቀዘቅዝ አትፍቀዱ

11. ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ መንፈሳዊ ጥቃት የሚሰነዝረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? እነርሱስ በበኩላቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

11 ሰይጣን ወደ ምድር ሲጣል ንዴቱን ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁትና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው በያዙት’ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ለመወጣት ቆርጦ ነበር። (ራእይ 12:9, 17) ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ስደት ነው። ይሁንና ይህ ዘዴው ብዙውን ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ከመቼውም ይበልጥ እንዲፋቀሩና ብዙዎች ቅንዓታቸውን እንዲያቀጣጥሉ በማድረግ የተገላቢጦሽ ውጤት አምጥቷል። ሌላው የሰይጣን ስልት ደግሞ ለኃጢአት ዝንባሌ እንድንሸነፍ ማድረግ ነው። ውጊያው የሚደረገው በውስጣችን ማለትም ‘ተንኮለኛ’ የሆነው ልባችን ከሚያሳድርብን ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት ጋር በመሆኑ ይህን ዘዴ መቋቋም የተለየ ድፍረት ይጠይቃል።—ኤርምያስ 17:9፤ ያዕቆብ 1:14, 15

12. ሰይጣን ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማዳከም ‘የዓለምን መንፈስ’ የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

12 ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ሌላም አደገኛ የሆነ መሣሪያ አለ። ይኸውም ከአምላክ መንፈስ ጋር የሚቃረነውና አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ‘የዓለም መንፈስ’ ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:12) የዓለም መንፈስ ስግብግብነትንና ፍቅረ ንዋይን ማለትም ‘የዐይን አምሮትን’ ያበረታታል። (1 ዮሐንስ 2:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ቁሳዊ ነገሮችና ገንዘብ በራሳቸው መጥፎ ባይሆኑም ለእነዚህ ነገሮች ያለን ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር አይሎ ሲገኝ ያኔ ሰይጣን ድል ይቀዳጃል። የዓለም መንፈስ፣ ኃይል ወይም ‘የመግዛት’ ሥልጣን እንዲኖረው ያደረገው ኃጢአተኛ ሥጋችንን የሚማርክ፣ መሠሪ፣ ምሕረት የለሽና ልክ እንደ አየር በማንኛውም ቦታ የሚገኝ መሆኑ ነው። የዓለም መንፈስ ልብህን እንዲመርዘው አትፍቀድ!—ኤፌሶን 2:2, 3፤ ምሳሌ 4:23

13. የሞራል ጥንካሬያችን እንዴት ሊፈተን ይችላል?

13 ይሁንና የዓለምን ክፉ መንፈስ ለመቋቋምና ከዚህ መንፈስ ለመራቅ የሞራል ጥንካሬ ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ ያህል ትያትር ቤት እያለን ወይም ኮምፒውተር ስንጠቀም አሊያም ቴሌቪዥን ስንመለከት አስነዋሪ ድርጊቶች በሚመጡበት ጊዜ ትያትር ቤቱን ለቆ መውጣትም ይሁን ኮምፒውተሩንና ቴሌቪዥኑን ማጥፋት ድፍረት ይጠይቃል። እኩዮች የሚያሳድሩትን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቃወምም ሆነ ከመጥፎ ጓደኝነት ለመራቅ ድፍረት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞች፣ ከሥራ ባልደረቦች፣ ከጎረቤቶች አሊያም ከዘመዶች የሚመጣብንን ፌዝ ተቋቁሞ የአምላክን ሕግና መመሪያ ጠብቆ መኖርም ድፍረት ይጠይቃል።—1 ቆሮንቶስ 15:33፤ 1 ዮሐንስ 5:19

14. የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዳሳደረብን ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 በመሆኑም ለአምላክም ሆነ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማጠንከራችን እጅግ አስፈላጊ ነው! የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረብን መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ጊዜ ወስደን ግቦቻችንንና አኗኗራችንን መመርመር ይገባናል። የዓለም መንፈስ በጥቂቱም ቢሆን ተጽዕኖ እንዳሳደረብን ከተሰማን ይሖዋ ይህን ችግር ከሥሩ ነቅለን ለማስወገድ አልፎ ተርፎም በድጋሚ እንዳይበክለን ለመከላከል የሚያስችለንን ድፍረት እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ልባዊ ልመና አይንቅም። (መዝሙር 51:17) ከዚህም በተጨማሪ የእርሱ መንፈስ ከዓለም መንፈስ እጅግ የላቀ ኃይል አለው።—1 ዮሐንስ 4:4

የግል ችግሮቻችንን በድፍረት መጋፈጥ

15, 16. የክርስቶስን ዓይነት ፍቅር ማሳየታችን የግል ችግሮቻችንን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

15 የይሖዋ አገልጋዮች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል የኃጢአትና የዕድሜ መግፋት ውጤት የሆኑት በሽታ፣ የአካል ጉዳተኝነት፣ ጭንቀትና ሌሎች የተለያዩ ችግሮች ይገኙበታል። (ሮሜ 8:22) የክርስቶስን ዓይነት ፍቅር ማሳየታችን እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል በዛምቢያ በሚኖር አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገችውን የናማንጎልዋን ሁኔታ ተመልከት። የሁለት ዓመት ልጅ ሳለች የአካል ጉዳት የገጠማት ይህች እህት እንዲህ ትላለች:- “ሰዎች አካላዊ ሁኔታዬ ያስደነግጣቸዋል ብዬ ስለማስብ እሳቀቅ ነበር። ሆኖም መንፈሳዊ ወንድሞቼ ሁኔታውን በተለየ መልኩ እንድመለከተው ረድተውኛል። በመሆኑም ይህን ስሜት አሸንፌ ከጊዜ በኋላ ለመጠመቅ ቻልኩ።”

16 ናማንጎልዋ ተሽከርካሪ ወንበር ያላት ቢሆንም አቧራ በበዛበት አሸዋማ መንገድ ላይ እየዳኸች መሄድ ግድ የሚሆንባት ጊዜ አለ። ያም ሆኖ በዓመት ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ ለሁለት ወር ያህል ረዳት አቅኚ ሆና ታገለግላለች። አንዲት ሴት ናማንጎልዋ ቤቷ ሄዳ ስትመሠክርላት አለቀሰች። ለምን? ምክንያቱም የዚህች እህታችን እምነትና ድፍረት ልቧን በጥልቅ ስለነካው ነው። የናማንጎልዋ አምስት ጥናቶች መጠመቃቸውና ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ ይሖዋ እየባረካት እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ናማንጎልዋ “ብዙውን ጊዜ እግሬን በጣም የሚያመኝ ቢሆንም ይህ ወደኋላ እንድል እንዲያደርገኝ አልፈቅድም” ብላለች። ይህች እህት ሰውነታቸው ደካማ ቢሆንም እንኳ ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር መንፈሰ ጠንካራ እንዲሆኑ ከረዳቸው በምድር ዙሪያ ከሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ውስጥ አንዷ ነች። እነዚህ ምሥክሮች በይሖዋ ዓይን ውድ ናቸው!—ሐጌ 2:7

17, 18. ብዙዎች ያለባቸውን ሕመምም ሆነ ሌሎች ችግሮች ተቋቋመው እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው? አንተ የምታውቃቸውን ወንድሞች ምሳሌ ጥቀስ።

17 ከባድ ሕመምም ቢሆን ተስፋ የሚያስቆርጥ ብሎም የሚያስጨንቅ ሊሆን ይችላል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “እኔ ባለሁበት የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ውስጥ አንዲት እህት በስኳር በሽታና በኩላሊት ሕመም ትሠቃያለች። አንዲት ሌላ እህት በካንሰር፣ ሌሎች ሁለት እህቶች በከባድ አርትራይተስ፣ አንዲት እህት ደግሞ ሉፕስ እና ፋይብሮማያልጂያ በሚባሉ በሽታዎች ይሠቃያሉ። እነዚህ እህቶች አንዳንዴ ተስፋ ይቆርጣሉ። ይሁንና በጠና ካልታመሙ ወይም ሆስፒታል ካልገቡ በስተቀር ፈጽሞ ከጉባኤ አይቀሩም። ሁሉም ዘወትር በመስክ አገልግሎት ይካፈላሉ። እነዚህ እህቶች ‘ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ’ ያለውን ጳውሎስን ያስታውሱኛል። ፍቅራቸውንና ድፍረታቸውን አደንቃለሁ። ያሉበት ሁኔታ ለሕይወትና እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ሳይረዳቸው አልቀረም።”—2 ቆሮንቶስ 12:10

18 አንተም ከአካል ጉዳት፣ ከሕመም ወይም ከአንድ ዓይነት ችግር ጋር እየታገልክ ከሆነ በተስፋ መቁረጥ ወጥመድ ውስጥ እንዳትወድቅ የሚያስችልህን እርዳታ ለማግኘት ‘ሳታቋርጥ ጸልይ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:14, 17) እውነት ነው፣ ስሜትህ ይለዋወጥ ይሆናል፤ ሆኖም አበረታች በሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮችና በተለይ ደግሞ ውድ በሆነው የመንግሥቱ ተስፋ ላይ ለማተኮር ጣር። አንዲት እህት “የመስክ አገልግሎት ፍቱን መድኃኒት ሆኖልኛል” ብላለች። ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈሏ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዝ ረድቷታል።

ፍቅር ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ይረዳቸዋል

19, 20. (ሀ) በኃጢአት ውስጥ የወደቁ ሰዎች ወደ ይሖዋ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ድፍረት እንዲያገኙ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ ምን ጉዳይ እንመረምራለን?

19 በመንፈሳዊ የደከሙ ወይም ኃጢአት የሠሩ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ መመለስ ይከብዳቸዋል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች እውነተኛ ንስሐ ከገቡና ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ማደስ ከቻሉ ወደ ይሖዋ ለመመለስ የሚያስችል ድፍረት ያገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረውን የማሪዮን a ሁኔታ ተመልከት። ማሪዮ ከክርስቲያን ጉባኤ ርቆ የአልኮል መጠጥና የዕፅ ሱሰኛ ከሆነ ከ20 ዓመት በኋላ ለእስር ተዳረገ። ማሪዮ እንዲህ ይላል:- “ስለ ወደፊቱ ሕይወቴ በአንክሮ ማሰብና መጽሐፍ ቅዱስን በድጋሚ ማንበብ ጀመርኩ። ቀስ በቀስም የይሖዋን ባሕርያት በተለይም ደግሞ ብዙ ጊዜ የምጸልይለትን ምሕረቱን ማድነቅ ቻልኩ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ከድሮ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጬ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመርኩ ሲሆን በኋላም ውገዳው ተነሳልኝ። በሥጋ የዘራሁትን ማጨዴ አልቀረም። ይሁንና አሁን ቢያንስ ቢያንስ ግሩም የሆነ የወደፊት ተስፋ አለኝ። ይሖዋ ላሳየኝ ርኅራኄና ምሕረት ያለኝ የአመስጋኝነት ስሜት ወደር የለውም።”—መዝሙር 103:9-13፤ 130:3, 4፤ ገላትያ 6:7, 8

20 እርግጥ ነው፣ ማሪዮ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ለመመለስ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በመጸለይና በማሰላሰል ዳግም ያቀጣጠሉት ፍቅር አስፈላጊውን ድፍረትና ጥንካሬ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለማሪዮ የብርታት ምንጭ የሆነለት የመንግሥቱ ተስፋ ነው። አዎን፣ ከፍቅር፣ ከእምነትና ከአምላካዊ ፍርሃት በተጨማሪ ተስፋም ሕይወታችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። በቀጣዩ ርዕስ ይህን ውድ መንፈሳዊ ስጦታ በጥልቀት እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተቀይሯል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ላቅ ያለ ድፍረት እንዲያሳይ ፍቅር አስተዋጽኦ ያደረገው እንዴት ነው?

• ጳውሎስና በርናባስ ለወንድሞች ያላቸው ፍቅር የላቀ ድፍረት እንዲያሳዩ የረዳቸው እንዴት ነው?

• ሰይጣን ክርስቲያናዊ ፍቅርን ለመሸርሸር በየትኞቹ ዘዴዎች ይጠቀማል?

• ለይሖዋ ያለን ፍቅር የትኞቹን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ይሰጠናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ለሰዎች ያለው ፍቅር ለመጽናት የሚያስችል ድፍረት ሰጥቶታል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ድፍረት ይጠይቃል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናማንጎልዋ ሱቱቱ