በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በድንጋይ ቤት’ የተካሄደ መንፈሳዊ ግንባታ

‘በድንጋይ ቤት’ የተካሄደ መንፈሳዊ ግንባታ

‘በድንጋይ ቤት’ የተካሄደ መንፈሳዊ ግንባታ

በአፍሪካ የምትገኘው ይህች አገር ስሟ “የድንጋይ ቤት” የሚል ፍቺ አለው። አገሪቱ በቪክቶሪያ ፏፏቴና በተለያዩ የዱር አራዊቶቿ ትታወቃለች። ከዚህም ባሻገር በደቡብ ሰሃራ ካሉት ጥንታዊ ሰው ሠራሽ ሕንጻዎች መካከል ትላልቅ የሆኑት ይገኙባታል። እንዲሁም መሃል ለመሃል አቋርጧት የሚያልፍ ጥቁር ድንጋይ የሚበዛበት ተራራማ ቦታ አላት። የዚህ ከፍተኛ ቦታ የአየር ንብረት ወይና ደጋ መሆኑ መሬቱ ለም እንዲሆን አስችሎታል። ይህች አገር 12 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ዚምባብዌ ናት።

ህች አገር የድንጋይ ቤት የሚል ስያሜ የተሰጣት ለምንድን ነው? በ1867፣ አዳም ሬንደርስ የተባለው አዳኝና አሳሽ ከ720 ሄክታር በሚበልጥ ቦታ ላይ የተሠሩ ትላልቅ የድንጋይ ቤቶች አገኘ። ቀደም ሲል ሲጓዝበት በነበረው የደቡባዊ አፍሪካ ክፍል የሚገኙት አብዛኞቹ ቤቶች የሣር ክዳን ያላቸው የጭቃ ቤቶች ነበሩ። ከዚያም አሁን ታላቋ ዚምባብዌ ተብላ በምትጠራው ቦታ ሲደርስ የአንድ ትልቅ ከተማ የድንጋይ ፍርስራሽ አገኘ።

ይህ ፍርስራሽ የሚገኘው ከአሁኗ ማስቪንጎ ከተማ በስተ ደቡብ ነው አንዳንዶቹ ግንቦች ከ9 ሜትር የሚበልጥ ከፍታ ያላቸው ሲሆን የተገነቡባቸው ጥቁር ድንጋዮች የተካቡት ያለ ምንም ማያያዣ ነው። ከፍርስራሹ መሃል አንድ ለየት ያለ ሾጣጣ ቅርጽ ያለው ማማ ይገኛል። የዚህ ማማ ቁመት 11 ሜትር ሲሆን ያረፈበት ቦታ ደግሞ መሃል ለመሃል ሲለካ 6 ሜትር ይሆናል። ይህ ማማ የተገነባበት ዓላማ በትክክል አይታወቅም። ቤቶቹ የተሠሩት ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ8ኛው መቶ ዘመን እንደሆነ የሚገመት ቢሆንም ሰዎች በአካባቢው መኖር የጀመሩት ቤቶቹ ከመሠራታቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንደሆነ ማስረጃዎች ያሳያሉ።

ቀደም ሲል ሮዴዢያ ትባል የነበረችው ይህች አገር በ1980 ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ስትወጣ ዚምባብዌ የሚል ስያሜ ተሰጣት። አብዛኞቹ ሕዝቦቿ የመጡት ከሁለት ዋና ዋና ጎሳዎች ማለትም ከሾና እና ከእንድቤሌ ሲሆን ብዙሃኑ የሾና ጎሳ አባላት ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲያገለግሉ እንዳስተዋሉት ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ ነው። አንዳንድ ጊዜ በሩን ያንኳኳው እንግዳ ገና ማንነቱ ሳይታወቅ “ግቡ” እንዲሁም “እባክዎ አረፍ ይበሉ” የሚል ግብዣ ይቀርብለታል። አብዛኞቹ የዚምባብዌ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ያላቸው ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ ልጆቻቸው ቁጭ ብለው እንዲያዳምጡ ያደርጋሉ።

የሚያጽናናና የሚያንጽ መልእክት ማድረስ

መገናኛ ብዙሃን ስለ ዚምባብዌ ሲያወሱ “ኤድስ” እና “ድርቅ” የሚሉትን ቃላት መስማት የተለመደ ነው። የኤድስ ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚና በሕዝቦቻቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል። በዚምባብዌ ወደ ሆስፒታል ከሚገቡት ሕሙማን ብዙዎቹ ከኤች አይ ቪ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ችግሮች የተነሳ የሚመጡ ናቸው። በዚህ በሽታ ምክንያት ብዙ ቤተሰቦች ፈርሰዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በዚምባብዌ የሚገኙ ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረውን የአምላክ መመሪያ መከተል የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝ በመስበክ ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስጦታ የሆነው የጾታ ግንኙነት በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ መሆን እንዳለበት፣ ግብረ ሰዶም በአምላክ ዘንድ የተጠላ እንደሆነና የይሖዋ ሕግ ደምን ለሕክምና መጠቀምንም ይሁን ለመዝናናት ተብሎ አደገኛ ዕጾችን መውሰድን እንደሚከለክል ያስተምራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ሮሜ 1:24-27፤ 1 ቆሮንቶስ 7:2-5፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) ከዚህም ባሻገር የይሖዋ ምሥክሮች፣ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በሽታን ሁሉ እንደሚያስወግድ የሚገልጽ አስተማማኝ ተስፋ ያዘለ መልእክት ያሰራጫሉ።—ኢሳይያስ 33:24

ቁሳዊ እርዳታ መስጠት

ባለፉት አሥር ዓመታት ድርቅ ዚምባብዌን ክፉኛ አጥቅቷታል። የዱር እንስሳት በረሃብና በጥም ሞተዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች አልቀዋል። ሰደድ እሳት ብዙ ሄክታር ደን አውድሟል። በርካታ ልጆችና አረጋውያን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሕይወታቸው ተቀጥፏል። ሌላው ቀርቶ ታላቁ የዛምቢዚ ወንዝ በጣም ከመቀነሱ የተነሳ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል።

ይህን የመሰለው አስከፊ ሁኔታ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስምንት የእርዳታ ኮሚቴዎች እንዲያቋቁሙ አነሳስቷቸዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ወንድሞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመሩ። ያገኙትን መረጃም ለሚመለከተው የእርዳታ ኮሚቴ አስተላለፉ። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “ባለፉት አምስት ዓመታት ከ10,000 ኩንታል በላይ በቆሎ፣ 100 ኩንታል የደረቁ ዓሦችና ተመሳሳይ መጠን ያለው ቦሎቄ አከፋፍለናል። መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ሃያ ኩንታል ሙፉሽዋ [የደረቀ አትክልት] አዘጋጅተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አልባሳት ሰጥተናል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል።” ሌላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “የእርዳታ ቁሳቁሶቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል ፈቃድ ከዚምባብዌና ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ ማለፍ ጠይቆብን የነበረ ሲሆን በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህን ቁሳቁስ ለማጓጓዝ የሚያስችል በቂ ነዳጅ አልነበረንም፤ የሆነ ሆኖ በመጨረሻ ተሳክቶልናል። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ፣ የሰማዩ አባታችን የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያውቅ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን አረጋግጦልኛል።”—ማቴዎስ 6:32

ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች ሲያገለግሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው? አንዳንዶች ለራሳቸውም ሆነ ለሚያርፉበት ቤተሰብ የሚሆን ምግብ ይይዛሉ። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ተናግሯል:- አንዳንድ እህቶች ‘አገልግሎታችንን አቋርጠን የመንግሥት እርዳታ ከሚጠባበቁት ሰዎች ጋር መሰለፍ ይሻለን ይሆን’ ብለው አስበው ነበር። ይሁንና እነዚህ እህቶች በይሖዋ በመታመን በስብከት እንቅስቃሴያቸው ላይ ለማተኮርና የሚሆነውን ለማየት ወሰኑ። በዚያን ዕለት የመንግሥት እርዳታ ሳይመጣ ቀረ።

በሚቀጥለው ቀን የጉባኤ ስብሰባ ይካሄድ ስለነበር እነዚህ እህቶች አሁንም ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ገጠማቸው። በስብሰባው ላይ ይገኙ ይሆን? ወይስ ይመጣል የተባለውን እርዳታ ለማግኘት ይሄዳሉ? ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች በማስቀደም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኙ። (ማቴዎስ 6:33) ወንድሞች የመደምደሚያውን መዝሙር እየዘመሩ ሳለ የከባድ መኪና ድምፅ ሰሙ። በእርዳታ ኮሚቴ ውስጥ በሚሠሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው አማካኝነት ያሉበት ድረስ እርዳታ መጣላቸው! በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩት ታማኝ ምሥክሮች የተሰማቸው ደስታና የአመስጋኝነት መንፈስ ይህ ነው የሚባል አልነበረም።

ፍቅር ያንጻል

የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ላልሆኑ ሰዎች ደግነት ማሳየት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ከፍቷል። በማስቪንጎ አካባቢ የሚያገለግል አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ጋር ሆኖ በመስበክ ላይ እያለ አንዲት ልጅ መንገድ ዳር ተኝታ ተመለከተ። ወንድሞች ልጅቷ በደንብ መናገር እንዳቃታትና ድምጿ እንደሚንቀጠቀጥ ሲመለከቱ በጣም መታመሟን ተገነዘቡ። የልጅቷ ስም ሃመንያሪ ሲሆን ትርጉሙም በሾና ቋንቋ “አታፍሩም?” ማለት ነው። ወንድሞች፣ ይህች ልጅ ከቤተ ክርስቲያኗ አባላት ጋር ሆና የአምልኮ ሥርዓት ለማካሄድ ወደ ተራራ ስትጓዝ እንደነበረና ስትታመም አብረዋት የነበሩት ሰዎች ጥለዋት መሄዳቸውን ተረዱ። ከዚያም ወንድሞች በደግነት በአቅራቢያ ወደሚገኘው መንደር ወሰዷት።

በመንደሩ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ሃመንያሪ ማን እንደሆነች ያውቁ ስለነበር ዘመዶቿን ጠሯቸው። መንደርተኞቹ የይሖዋ ምሥክሮችን አስመልክተው “ይህ እውነተኛ ሃይማኖት ነው። ክርስቲያኖች ሊያሳዩት የሚገባው ፍቅር ይህ ነው” ብለዋል። (ዮሐንስ 13:35) ወንድሞች ከመንደሩ ከመውጣታቸው በፊት ለሃመንያሪ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚለውን ትራክት ሰጧት። a

በሚቀጥለው ሳምንት ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ሃመንያሪ በምትኖርበት አካባቢ የሚገኘውን ጉባኤ ይጎበኝ ስለነበር ሃመንያሪ በሰላም ቤቷ መግባቷን ለማረጋገጥ ፈለገ። መላው ቤተሰቧ እርሱንም ሆነ በአካባቢው የሚኖሩትን ወንድሞች በደስታ ተቀበሏቸው። ወላጆቿ “እናንተ የምትከተሉት ሃይማኖት ትክክል ነው። መንገድ ላይ የተጣለችውን ልጃችንን ከሞት አትርፋችሁልናል” በማለት ተናገሩ። የልጃቸውን የእምነት ባልደረቦች “እንደ ሃመንያሪ ስም ትርጉም፣ እንድትሞት ጥላችኋት መሄዳችሁ ምንም አላሳፈራችሁም?” ብለዋቸው ነበር። ወንድሞች ከሃመንያሪ ቤተሰብ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከተወያዩ በኋላ ጽሑፎችን አበረከቱላቸው። በተጨማሪም ቤተሰቡ ወንድሞች ተመልሰው እንዲመጡና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኗቸው ተስማሙ። የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት አመለካከታቸውን ለውጠዋል። ከእነዚህ መካከል የመንደሩ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረው የሃመንያሪ ታላቅ እህት ባል ይገኝበታል። ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ሆኗል።

የአምልኮ ቤቶችን መገንባት

በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ገጣሚ በመንፈስ አነሳሽነት “እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 63:1) በዚምባብዌ ለሚኖሩ ብዙ ሰዎች ይህ ምንኛ እውነት ነው! ቃል በቃል ድርቅን ተቋቁመው እየኖሩ ቢሆንም በመንፈሳዊ ግን አምላክንም ሆነ የእርሱን ጥሩነት ተጠምተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ አገልግሎት ካስገኘው ውጤት ይህን ለማየት ይቻላል። ዚምባብዌ በ1980 ነጻነቷን ስታገኝ በ476 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 10,000 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አሁን፣ ከ27 ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በሦስት እጥፍ አድጓል፤ የጉባኤዎች ቁጥር ደግሞ በእጥፍ ጨምሯል።

ከእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ የራሳቸው የሆነ የአምልኮ ቦታ ያላቸው ጥቂቶቹ ነበሩ። በጥር 2001፣ በዚምባብዌ ከሚገኙት ከ800 የሚበልጡ ጉባኤዎች መካከል የራሳቸው የአምልኮ ቦታ ማለትም የመንግሥት አዳራሽ የነበራቸው 98ቱ ብቻ ነበሩ። ብዙዎቹ ጉባኤዎች ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት ዛፍ ሥር ወይም ጎጆ ቤቶች ውስጥ ነበር።

ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር በልግስና ባደረገው መዋጮ እንዲሁም በፈቃደኝነት በሚሠሩ ትጉ ሠራተኞች እገዛ አማካኝነት በዚምባብዌ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቀለል ያሉ ሆኖም ክብር የተላበሱ አዳራሾችን ለማግኘት የሚያስችላቸውን የግንባታ ፕሮግራም ማካሄድ ጀመሩ። ባሕር ማዶ የሚኖሩ የግንባታ ሙያ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ወደ ዚምባብዌ ሄደው ከአገሬው ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር ለመሥራት ሁኔታቸውን አመቻችተዋል። የአገሬው ተወላጅ የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሚያማምሩ የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባቱ ሥራ ለመርዳት ከተለያዩ አገሮች ወደዚህ የመጡትን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ከልብ እናመሰግናለን። በተጨማሪም ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መዋጮ በማድረግ ሥራው ከግብ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን ሁሉ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን።”

በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል፣ ወንድሞች ለ50 ዓመታት ያህል በአንድ ትልቅ የቤዮባብ ዛፍ ሥር ይሰበሰቡ ነበር። የጉባኤው ሽማግሌዎች የአምልኮ ቦታ እንደሚሠራ ሲነገራቸው አንደኛው ሽማግሌ እንባውን መቆጣጠር አልቻለም። በዚያው አካባቢ በሚገኝ ሌላ ጉባኤ የሚያገለግሉ የ91 ዓመት ሽማግሌ “ይህን ቀን ለማየት ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ስማጸን ነበር!” ብለዋል።

እነዚህ የሚያማምሩ አዳራሾች የሚገነቡበትን ፍጥነት በተመለከተ ብዙዎች ሐሳብ ሰጥተዋል። አንድ ተመልካች “እናንተ ቀን ቀን ስትገነቡ አምላክ ደግሞ ሌሊት ሌሊት እየገነባላችሁ መሆን አለበት!” በማለት አስተያየት ሰጥቷል። በሠራተኞቹ መካከል ያለው አንድነትና የደስተኝነት መንፈስ ሳይስተዋል አልቀረም። በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከ350 በላይ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተዋል። ይህም 534 ጉባኤዎች በጡብ በተሠሩ ጠንካራ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ እንዲሰበሰቡ አስችሏቸዋል።

በዚምባብዌ በጣም አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ግንባታ መካሄዱን ቀጥሏል። የተገኘውን ውጤት ስንመለከት የዚህ ሁሉ በረከት ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ለማመስገን እንገፋፋለን። አዎን፣ ይሖዋ “ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ።”—መዝሙር 127:1

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዚምባብዌ

ሐራሬ

ማስቪንጎ

ታላቋ ዚምባብዌ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሾጣጣ ቅርጽ ያለው ማማ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኮንሴሽን ጉባኤ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሊንዳላ ጉባኤ ወንድሞችና እህቶች በአዲሱ የመንግሥት አዳራሻቸው

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፈራረሱ ደረጃዎች:- ©Chris van der Merwe/AAI Fotostock/age fotostock; ማማ:- ©Ingrid van den Berg/AAI Fotostock/age fotostock