በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጽንፈኞች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?

ጽንፈኞች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?

ጽንፈኞች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?

ሚዛናዊ በመሆን ረገድ ይሖዋን የሚተካከለው የለም። “ሥራውም ፍጹም ነው” እንዲሁም ፍርዱ ምሕረትን አጣምሮ የያዘ ስለሆነ ፈጽሞ ጭካኔ አይንጸባረቅበትም። (ዘዳግም 32:4) ፍቅሩ ሚዛኑን የሳተ አይደለም፤ ምክንያቱም ነገሮችን የሚያደርገው ፍጹም ከሆኑት ሕጎቹ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። (መዝሙር 89:14፤ 103:13, 14) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የተፈጠሩት በሁሉም ረገድ ሚዛናዊ እንዲሆኑ ተደርገው ነው። በመሆኑም ወደየትኛውም ጽንፍ ያዘነበሉ አልነበሩም። ይሁንና ኃጢአት በመሥራታቸው ፍጽምና የጎደላቸው ማለትም ‘ነውር’ ያለባቸው ሆኑ፤ ይህ ደግሞ ሚዛናቸውን እንዳይጠብቁ አድርጓቸዋል።—ዘዳግም 32:5

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ጎማው በአንድ በኩል ያበጠ መኪና ወይም ብስክሌት ነድተህ ታውቃለህ? ጉዞህ አስቸጋሪ ብሎም ለአደጋ የሚያጋልጥ እንደሚሆንብህ እሙን ነው። እንዲህ ያለው ጎማ የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ወይም ጨርሶ ከመተንፈሱ በፊት ጥገና ሊደረግለት ይገባል። በተመሳሳይም ፍጽምና የጎደለው ስብዕናችን አባጣ ጎርባጣ አለው። “እብጠቱ” እየጨመረ እንዲሄድ ከፈቀድን የሕይወት ጉዟችን አስቸጋሪ አልፎ ተርፎም አደገኛ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ፣ መልካም ባሕሪያችን ማለትም ጠንካራ ጎናችን ወደ አንድ ጽንፍ ሊመራን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያበጁ የሚያዝ ቢሆንም በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ፈሪሳውያን ግን ከልክ በላይ ‘የቀሚሳቸውን ዘርፍ በማስረዘም’ ከሌላው ሕዝብ የተለዩ ሆነው ለመታየት ይፈልጉ ነበር። ዓላማቸው ከወንድሞቻቸው ይልቅ ቅዱስ መስለው መታየት ነበር።—ማቴዎስ 23:5፤ ዘኍልቍ 15:38-40

በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በማንኛውም መንገድ ሌላው ቀርቶ አስደንጋጭ ነገሮችን በማድረግ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ይሞክራሉ። እንዲህ ማድረግ “እኔም እኮ እንደ እናንተው ሰው ነኝ! እባካችሁ እዩኝ!” የሚል የተስፋ መቁረጥ ጩኸት የማሰማት ያህል ሊሆን ይችላል። ይሁንና አንድ ክርስቲያን በአለባበስ፣ በአስተሳሰብና በሚያደርጋቸው ነገሮች ጽንፈኛ መሆኑ እውነተኛ ፍላጎቱን ሊያረካለት አይችልም።

ለሥራ ተገቢውን አመለካከት መያዝ

ምንም ዓይነት ሰዎች እንሁን ወይም በየትኛውም ሥፍራ እንኑር፣ ጥሩ ሥራ መሥራት ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ነው። የተፈጠርነው በመሥራት እርካታ እንድናገኝ ተደርገን ነው። (ዘፍጥረት 2:15) መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ስንፍናን ያወግዛል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ሲል በግልጽ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:10) በእርግጥም ልግመኛ መሆን ለድህነት ከመዳረግና እርካታን ከማሳጣትም በላይ የአምላክን ሞገስ ያሳጣል።

አንዳንዶች ደግሞ ወደ ሌላኛው ጽንፍ በመሄድ በሥራ ሱስ ከመጠመዳቸውም ባሻገር በፈቃደኝነት ለሥራቸው ባሪያዎች ይሆናሉ። ገና በማለዳ ከቤታቸው ይወጣሉ፤ አምሽተውም ይመለሳሉ። ይህንን የሚያደርጉት ቤተሰባቸውን ለመንከባከብ እንደሆነ በመናገር ሰበብ ያቀርባሉ። ይሁንና የእነዚህ ሰዎች በሥራ ሱስ መጠመድ ቤተሰባቸውን ጉዳት ላይ ጥሎት ሊሆን ይችላል። ባለቤቷ በሥራ ቦታ ላይ ተጨማሪ ሰዓታት የሚያሳልፍ አንዲት የቤት እመቤት እንዲህ ብላለች:- “በዚህ የቅንጦት ቤት ውስጥ ባሉት ነገሮች ምትክ ባለቤቴ ከእኔና ከልጆቻችን ጋር አብሮ የሚሆንበትን አጋጣሚ ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር።” ከልክ በላይ ለመሥራት የሚመርጡ ሰዎች ንጉሥ ሰሎሞን ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንደሚከተለው ሲል የሰጠውን ምክር በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል:- “እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር።”—መክብብ 2:11

አዎን፣ ሥራን በተመለከተ ሁለቱንም ጽንፎች ማስወገድ ይኖርብናል። ታታሪ ሠራተኞች መሆን አለብን። ሆኖም ለሥራ ባሪያ መሆን ደስታችንን እንደሚያሳጣንና ከዚያም ያለፈ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም።—መክብብ 4:5, 6

ደስታን በተመለከተ ጽንፈኛ አመለካከት አይኑርህ

መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ያሉ “ሰዎች . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 4) ተድላን ማሳደድ ሰይጣን ሰዎችን ከአምላክ ለማራቅ ከሚጠቀምባቸው ውጤታማ ዘዴዎች መካከል አንዱ ሆኗል። አለቅጥ መዝናናት እንዲሁም ከፍተኛ ደስታ ለማግኘት ሲባል አደገኛ በሆኑ የስፖርት ዓይነቶች መካፈል እየተለመደ መጥቷል። እንደነዚህ ያሉ የስፖርት ዓይነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል፤ በስፖርቶቹ የሚሳተፉት ሰዎች ቁጥርም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ነው። እነዚህን ስፖርቶች ተወዳጅ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እርካታ ስለሌላቸው ከፍተኛ ደስታ ሊያገኙ የሚችሉበትን አጋጣሚ የሚያስሱ መሆናቸው ነው። ይሁንና ይህን ዓይነቱን ደስታ ማግኘት ከፈለጉ በየጊዜው ይበልጥ አደገኛ የሆኑ ነገሮችን መሞከር ግድ ይሆንባቸዋል። ጠንቃቃ የሆኑ ክርስቲያኖች ለሕይወትም ሆነ ሕይወት ሰጪ ለሆነው አካል አክብሮት ስላላቸው አደጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉ የስፖርት ዓይነቶች ይርቃሉ።—መዝሙር 36:9

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ከፈጠራቸው በኋላ እንዲኖሩ ያስቀመጣቸው የት ነው? በኤደን የአትክልት ሥፍራ ነው። ኤደን የሚለው ቃል መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ‘ደስታ’ የሚል ፍቺ አለው። (ዘፍጥረት 2:8) ሰዎች ደስተኛ ሕይወት መምራታቸው ይሖዋ ለሰዎች ካለው ዓላማ መካከል አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ስለ ደስታ ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ያደረ ሰው ነበር። በመሆኑም የይሖዋን ሕግና መመሪያ ከመከተል ፈጽሞ ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም። በጣም ደክሞት በነበረበት ወቅት እንኳ ጊዜ ወስዶ ችግረኞችን ይረዳ ነበር። (ማቴዎስ 14:13, 14) አዎን፣ ኢየሱስ በግብዣ ላይ ይገኝ ነበር፤ በተጨማሪም እረፍት ያደርግና ይዝናና ነበር። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጠላቶቹ እነዚህን ነገሮች በማድረጉ እንደሚነቅፉት ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት “በላተኛና ጠጪ” ብለውታል። (ሉቃስ 7:34፤ 10:38፤ 11:37) ይሁንና ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ለአምላክ ያደረ እንዲሆን የግድ ደስታ አጥቶ መኖር አለበት የሚል እምነት አልነበረውም።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመዝናኛ ረገድ ጽንፈኛ ከመሆን መቆጠባችን ጥበብ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ለተድላና ለመዝናኛ ቅድሚያውን መስጠት ፈጽሞ እውነተኛ ደስታ አያስገኝልንም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ችላ እንድንል ያደርገናል። ያም ሆኖ ደስታን ከሚያስገኙ ነገሮች ፈጽሞ መራቅም ሆነ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ደስታ ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎችን መንቀፍ አይኖርብንም።—መክብብ 2:24፤ 3:1-4

ሚዛናዊ ሕይወት በመምራት ደስተኛ ሁን

ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 3:2) ጽንፈኝነትን ለማስወገድ ስንጥር ይህን አባባል እውነት ሆኖ እናገኘው ይሆናል። ታዲያ ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል? ጠንካራና ደካማ ጎናችንን ለይተን ማወቅ ይገባናል። እንዲህ ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ሳይታወቀን ወደ አንዱ ጽንፍ ልናዘነብል እንችላለን። በመሆኑም ከበሰሉ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብና የሚሰጡንን ሚዛናዊ ምክር ማዳመጥ ጥበብ ነው። (ገላትያ 6:1) አንድ ወዳጃችን አሊያም ተሞክሮ ያካበተ የጉባኤ ሽማግሌ ይህን የመሰለውን ምክር እንዲሰጠን ልንጠይቅ እንችላለን። ቅዱሳን መጻሕፍት ከሚሰጡን ጥቅም በተጨማሪ እንዲህ ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በይሖዋ ፊት ያለንን አቋም ለመመርመር የሚረዳ “መስተዋት” ሆኖ ያገለግለናል።—ያዕቆብ 1:22-25

ጽንፈኝነትን ልናስወግደው እንደምንችል ማወቃችን ሊያስደስተን ይገባል። ብርቱ ጥረት በማድረግና የይሖዋን ድጋፍ በማግኘት ሚዛናዊ መሆን ይቻላል፤ ይህም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። ደስተኞች መሆናችን ደግሞ ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እየተሻሻለ እንዲሄድና ለምንሰብክላቸው ሰዎችም ግሩም ምሳሌ እንድንሆን ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ሚዛናዊና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ይበልጥ እንመስለዋለን።—ኤፌሶን 5:1

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

©Greg Epperson/age fotostock