በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንቶቹ ጸሐፍትና የአምላክ ቃል

የጥንቶቹ ጸሐፍትና የአምላክ ቃል

የጥንቶቹ ጸሐፍትና የአምላክ ቃል

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው ያበቁት ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዓመታት አይሁዳውያን ሊቃውንት በተለይ ሶፌሪምና በኋላም ማሶሬቶች የዕብራይስጡን ጽሑፍ በጥንቃቄ በመገልበጥ ረገድ የታወቁ ነበሩ። ይሁንና እጅግ ጥንታዊ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት ሶፌሪም ከኖሩበት ዘመን ከአንድ ሺህ ዓመት ቀደም ብሎ ማለትም በሙሴና በኢያሱ ዘመን ነው። በዚያን ጊዜ የነበሩት መጻሕፍት የሚጻፉት በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ እንደ ፓፒረስና ብራና ባሉ ነገሮች ስለነበር ጥቅልሎቹ በተደጋጋሚ ተገልብጠው እንደሚሆን እሙን ነው። በጥንት ዘመን ስለነበረው የጸሐፍት ሙያ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? በጥንቷ እስራኤል በሙያቸው የተካኑ ጸሐፊዎች ነበሩ?

በዘመናችን ካሉት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል ረጅም ዘመን ያስቆጠሩት ከሙት ባሕር ከተገኙት ጥቅልሎች ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን ከእነዚህ አንዳንዶቹ የተገለበጡት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ነው። ከዚህ ዘመን በፊት የተገለበጡት “እጅግ ጥንታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ አይገኙም” ሲሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ቋንቋዎችና አርኪኦሎጂ ምሑር የሆኑት ፕሮፌሰር አለን ሚለርድ ተናግረዋል። አክለውም “የአካባቢው ባሕል የጥንት ጸሐፍት እንዴት ሥራቸውን እንዳከናወኑ ለማወቅ ያስችላል። ይህንን ማወቃችን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ታሪካቸውን ለመገምገም ይረዳናል።”

የጸሐፍት ሙያ በጥንት ዘመን

ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ትምህርታዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊና ሕግ ነክ የሆኑ ጽሑፎች ከዛሬ 4,000 ዓመታት በፊት መስጴጦምያ ውስጥ ይዘጋጁ ነበር። በዚህ ጊዜ ጸሐፊዎችን የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከሚያስተምሯቸው ደንቦች መካከል ከዋናው ጽሑፍ ላይ ሳይጨምሩ ወይም ሳይቀንሱ በታማኝነት የመገልበጥ አስፈላጊነት ይገኝበታል። በዘመናችን ያሉ ምሑራን ለ1,000 ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ዓመታት በተደጋጋሚ ሲገለበጡ በቆዩ የባቢሎናውያን ጽሑፎች ላይ ያገኙት ለውጥ በጣም ጥቂት ነው።

የጸሐፍት ሙያ በመስጴጦምያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ዚ ኦክስፎርድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አርኪኦሎጂ ኢን ዘ ኒር ኢስት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት አጋማሽ ላይ የሚኖር አንድ ባቢሎናዊ ጸሐፊ በመላው መስጴጦምያ፣ በሶርያ፣ በከነዓንና ሌላው ቀርቶ በግብፅ እንኳ ከተለመደው የአጻጻፍ ስልት ጋር የቅርብ ትውውቅ ነበረው።” a

በሙሴ ዘመን፣ በግብፅ የጸሐፊነት ሙያ እጅግ ከፍ ተደርጎ ይታይ የነበረ ሲሆን ጸሐፍትም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ያለማሰለስ ይገለብጡ ነበር። ከ4,000 ዓመት በላይ ዕድሜ ባላቸው የግብፃውያን መቃብሮች ላይ ጸሐፍት ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ሥዕሎች ይገኛሉ። ከላይ የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ በጊዜው ስለነበሩት ጸሐፍት እንዲህ ይላል:- “ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት [ጸሐፍት] የመስጴጦምያንና የግብፅን ታላቅ ሥልጣኔ አጉልተው የሚያሳዩ በርካታ ጽሑፎችን ገልብጠውና አሰባስበው እንዲሁም ለጸሐፊነት ሙያ የሥነ ምግባር ደንቦችን አውጥተው ነበር።”

ከእነዚህ “የሥነ ምግባር ደንቦች” መካከል አንዱ ከጽሑፉ መጨረሻ ላይ አንዳንድ መረጃዎችን ማስፈርን ይጠይቃል። እነዚህ መረጃዎች ጽሑፉን የገለበጠውን ሰውና የተገለበጠው ጽሑፍ ባለቤት ስም፣ ቀኑን፣ ምንጩን፣ የመሥመሮቹን ብዛት እና የመሳሰሉትን ይይዛሉ። ብዙውን ጊዜ ጽሑፉን የሚገለብጡት ሰዎች “ከዋናው ቅጂ የተገለበጠና በድጋሚ የተጣራ” የሚል ጽሑፍ ያሰፍሩ ነበር። እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች የጥንት ጸሐፍት አንድ ጽሑፍ በትክክል መገልበጡ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸው እንደነበር ያሳያሉ።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፕሮፌሰር ሚለርድ እንዲህ ብለዋል:- “ጽሑፎችን የመገልበጡ ሂደት ስህተቶችን ለማስወገድ የሚረዱ እንደ ማጣራትና ማረም የመሳሰሉ ዘዴዎችን ይጨምር እንደነበረ ማስተዋል ይቻላል። በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ የተነሱት ማሶሬቶችም ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዳንዶቹን፣ በተለይም መሥመሮችን ወይም ቃላቶችን የመቁጠርን ዘዴ ይጠቀሙ ነበር።” በመሆኑም ሙሴና ኢያሱ በነበሩበት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ጽሑፎች በጥንቃቄና በትክክል መገልበጥ አለባቸው የሚለው አስተሳሰብ እንደነበር ግልጽ ነው።

እስራኤላውያን ብቃት ያላቸው ጸሐፊዎች ነበሯቸው? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ጸሐፍት

ሙሴ ያደገው በፈርዖን ቤት ነበር። (ዘፀአት 2:10፤ የሐዋርያት ሥራ 7:21, 22) ስለ ግብፅ ጥንታዊ ታሪክ የሚያጠኑ ምሑራን እንደተናገሩት ሙሴ የቀሰመው ትምህርት፣ የግብፃውያንን የአጻጻፍና የአነባበብ ስልት ማወቅን እንዲሁም ቢያንስ በተወሰነ መጠን የጸሐፍትን ሙያ መማርን ሳይጨምር አይቀርም። ፕሮፌሰር ጄምስ ሆፍሚየር ኢዝራኤል ኢን ኢጂፕት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሙሴ አንዳንድ ክስተቶችን መዝግቦ የማቆየት፣ ሕዝቡ ያደረገውን ጉዞ የመዘገብና ሌሎች የጸሐፊነት ተግባሮችን የማከናወን ችሎታ እንደነበረው የሚያሳዩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የሚደግፍ ማስረጃ አለ።” b

መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቷ እስራኤል የጸሐፊነት ሙያ ያላቸው ሌሎች ሰዎችም እንደነበሩ ይገልጻል። ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንዳሰፈረው ሙሴ “የተላለፉ ውሳኔዎችን በጽሑፍ የሚያሰፍሩና የሥልጣን ተዋረዶችን የሚመዘግቡ . . . የተማሩ ሰዎችን ሾሟል።” ለዚህ ድምዳሜ መሠረት የሆነው በዘዳግም 1:15 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ዘገባ ነው:- “ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች . . . ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ አምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምንት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው።” እነዚህ ሹማምንት እነማን ናቸው?

“ሹም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሙሴና በኢያሱ ዘመን ከተከናወኑ ነገሮች ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። የተለያዩ ምሑራን ለዚህ ቃል “ጸሐፊ”፣ “‘የሚጽፍ’ ወይም ‘የሚዘግብ’ ሰው” እንዲሁም “ዳኛን በጽሕፈት ሥራ የሚረዳ ሹም” የሚል ፍቺ ሰጥተውታል። ይህ የዕብራይስጥ ቃል በተደጋጋሚ መጠቀሱ በእስራኤል የጸሐፊነት ሙያ ያላቸው በርካታ ሰዎች እንደነበሩና ብሔሩን በማስተዳደር ረገድ የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች እንደነበሯቸው ያሳያል።

ሦስተኛው ምሳሌያችን የእስራኤል ካህናት ናቸው። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ እንደገለጸው ካህናቱ “ሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ሥራዎች ያከናውኑ ስለነበር የተማሩ መሆን ነበረባቸው።” ለምሳሌ ያህል ሙሴ የሌዊን ልጆች “በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣ . . . ይህን ሕግ በእነርሱ [በእስራኤል] ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ” ሲል አዟቸዋል። የሕጉ ግልባጭ በካህናቱ እጅ ነበር። ሌሎች ግልባጮች ማዘጋጀት ሲያስፈልግ ካህናቱ ፈቃድ የመስጠትም ሆነ የሥራውን አፈጻጸም የመከታተል ኃላፊነት ነበራቸው።—ዘዳግም 17:18, 19፤ 31:10, 11

የሕጉ ቃል የመጀመሪያ ግልባጭ እንዴት እንደተዘጋጀ ተመልከት። ሙሴ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ለእስራኤላውያን እንዲህ አላቸው:- “አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራ ቅባቸው። . . . የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው።” (ዘዳግም 27:1-4) ኢያሪኮ እና ጋይ ከጠፉ በኋላ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር እምብርት ላይ በሚገኘው በጌባል ተራራ ተሰበሰቡ። በዚያም ኢያሱ “ሙሴ የጻፈውን የሕግ መጽሐፍ” በመሠዊያው ድንጋይ ላይ ቀረጸው። (ኢያሱ 8:30-32) እስራኤላውያን ማንበብና መጻፍ ባይችሉ ኖሮ እንዲህ ማድረግ ባላስፈለገ ነበር። ይህም የጥንት እስራኤላውያን ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያስችል የቋንቋ ችሎታና ክህሎት እንደነበራቸው ይጠቁማል።

ቅዱሳን መጻሕፍት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው

ከሙሴና ከኢያሱ ዘመን በኋላ የተለያዩ የዕብራይስጥ ጥቅልሎች የተጻፉ ሲሆን በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎችም ተዘጋጅተውላቸዋል። እነዚህ ግልባጮች ሲያረጁ ወይም በእርጥበትና በሻጋታ ሲበላሹ በሌላ ቅጂ መተካት ነበረባቸው። በመሆኑም ግልባጭ የማዘጋጀቱ ሂደት ለዘመናት ቀጥሏል።

የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት የሚገለብጡ ሰዎች የተቻላቸውን ያህል ቢጠነቀቁም አንዳንድ ስህተቶች አልጠፉም። ይሁንና ጸሐፍት የሠሩት ስህተት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለውጦታል? በጭራሽ። የዛሬዎቹን ቅጂዎች ከጥንቶቹ ጋር በማነጻጸር ማወቅ እንደተቻለው በጥቅሉ ሲታይ ስህተቶቹ ከቁብ የሚቆጠሩ አይደሉም፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ይዘት ላይ የሚያመጡት ለውጥ የለም።

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ቀደም ሲል ለተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የነበረውን አመለካከት ማወቃቸው የቅዱሳን መጻሕፍት አጠቃላይ ይዘት እንዳልተለወጠ ማረጋገጫ ይሆናቸዋል። ኢየሱስ “በሙሴ መጽሐፍ . . . አላነበባችሁምን?” እንዲሁም “ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን?” የሚሉትን አገላለጾች መጠቀሙ እርሱ በምድር በኖረበት ጊዜ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት በእጅ የተጻፉ ግልባጮች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ አድርጎ እንደተመለከታቸው ያሳያል። (ማርቆስ 12:26፤ ዮሐንስ 7:19) ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል” ሲል መናገሩ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አስተማማኝና ትክክለኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል።—ሉቃስ 24:44

በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት ከጥንት ጀምሮ ትክክለኛነታቸውን ጠብቀው እንደተላለፉልን እርግጠኛ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተናገረው “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 40:8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት አጋማሽ ላይ የኖረው ኢያሱ ቂርያትሤፍር ስለተባለች የከነዓናውያን ከተማ ጠቅሶ ነበር። የዚህች ከተማ ስም “የመጽሐፍ ከተማ” ወይም “የጸሐፊው ከተማ” የሚል ትርጉም አለው።—ኢያሱ 15:15, 16

b ሙሴ ሕግ ነክ ጉዳዮችን በጽሑፍ ማስፈሩን የሚያሳዩ ሐሳቦችን በዘፀአት 24:4, 7፤ 34:27, 28 እና በዘዳግም 31:24-26 ላይ ማግኘት ይቻላል። ዘዳግም 31:22 መዝሙር መጻፉን ይገልጻል፤ ዘኍልቍ 33:2 ደግሞ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ስላደረጉት ጉዞ መዘገቡን ይናገራል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ግብፃዊ ጸሐፊ በሥራ ላይ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እጅግ ጥንታዊ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ ዘመን ነው