በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ያጣመረውን እናንተ አትለያዩት

አምላክ ያጣመረውን እናንተ አትለያዩት

አምላክ ያጣመረውን እናንተ አትለያዩት

‘ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ሰው አይለየው።’—ማቴዎስ 19:6

1, 2. ባልና ሚስት አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው መጠበቁ ቅዱስ ጽሑፍዊም ሆነ ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

 በመኪና ረዥም መንገድ ለመጓዝ ተዘጋጅተሃል እንበል። በጉዞህ ላይ ችግሮች ያጋጥሙህ ይሆን? ምንም አያጋጥመኝም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይሆናል! ለምሳሌ፣ የአየሩ ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ በዝግታና በጥንቃቄ ለማሽከርከር ትገደድ ይሆናል። አንድ ቦታ ላይ ስትደርስ መኪናዋ ልትበላሽብህ ትችላለች፤ ችግሩ ከአቅምህ በላይ በመሆኑ መኪናዋን መንገዱ ዳር ላይ አቁመህ እርዳታ መጠየቅ ያስፈልግህ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ስላጋጠሙህ ‘ጉዞውን መጀመሬ ስህተት ነበር፤ መኪናዋንም ልተዋት ይገባል’ ብለህ መደምደም ይኖርብሃል? በፍጹም። ረዥም ጉዞ ስታደርግ ችግሮች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ ስለምትጠብቅ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚረዱህን መንገዶች በጥበብ ትፈልጋለህ።

2 ትዳርን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ችግሮች መፈጠራቸው የማይቀር በመሆኑ ሊጋቡ ያሰቡ አንድ ወንድና ሴት ፈጽሞ ከችግር ነጻ የሆነ ሕይወት እንደሚኖራቸው መጠበቃቸው ሞኝነት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 7:28 ላይ ባልና ሚስት “ብዙ ችግር” እንደሚያጋጥማቸው በግልጽ ይናገራል። እንዲህ የተባለው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር፣ ባሎችና ሚስቶች ፍጹማን ባለመሆናቸውና የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ በመሆኑ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ሮሜ 3:23) በዚህም የተነሳ እርስ በርስ የሚጣጣሙና መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ባልና ሚስትም እንኳ አልፎ አልፎ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

3. (ሀ) በዓለም ላይ ብዙዎች ስለ ጋብቻ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) ክርስቲያኖች ትዳራቸውን ጠብቀው ለማቆየት የሚጥሩት ለምንድን ነው?

3 በዘመናችን አንዳንድ ባለትዳሮች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው መጀመሪያ የሚታያቸው ትዳራቸውን ማፍረስ ነው። በብዙ አገሮች የፍቺ ቁጥር በጣም እያሻቀበ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ችግሮች ሲገጥሟቸው መፍትሔ ለማግኘት ይሞክራሉ እንጂ ከችግሩ አይሸሹም። ለምን? ጋብቻን ከይሖዋ እንደተገኘ ቅዱስ ስጦታ አድርገው ስለሚመለከቱት ነው። ኢየሱስ ባልና ሚስትን አስመልክቶ “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” ብሏል። (ማቴዎስ 19:6) እርግጥ ነው፣ በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት መመራት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የማይመሩ ዘመዶች፣ አንዳንድ የጋብቻ አማካሪዎች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ባይኖራቸውም እንዲለያዩ ወይም እንዲፋቱ ያበረታቷቸዋል። a ክርስቲያኖች ግን ትዳርን ለማፍረስ ከመቸኮል ይልቅ ችግሮችን በመፍታት ጋብቻን ዘላቂ ለማድረግ መጣር የተሻለ እንደሆነ ያውቃሉ። በእርግጥም ገና ከጅምሩ፣ ሰዎች በሚሰጡን ምክር ከመመራት ይልቅ በይሖዋ መንገድ ነገሮችን ለማከናወን ቁርጥ አቋም መያዛችን አስፈላጊ ነው።—ምሳሌ 14:12

ለችግሮች መፍትሔ ማግኘት

4, 5. (ሀ) በትዳር ውስጥ ምን ዓይነት ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ? (ለ) በአምላክ ቃል ላይ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች በጋብቻ ውስጥ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜም እንኳ ውጤታማ የሆኑት ለምንድን ነው?

4 በማንኛውም ትዳር ውስጥ አልፎ አልፎ ችግሮችን ለመፍታት ለየት ያለ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቅን አለመግባባቶችን መፍታቱ በቂ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ ግን ባልና ሚስቱ ያላቸውን ግንኙነት የሚያናጉ ከባድ ችግሮች ይኖሩ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ትዳር መሥርቶ ለረጅም ጊዜ የቆየ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲረዳችሁ መጠየቅ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ስላጋጠሟችሁ ጋብቻችሁ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በጋብቻችሁ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መልኩ ችግሮችን የመፍታትን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው።

5 ይሖዋ የሰው ልጅ ፈጣሪና የጋብቻ መሥራች እንደመሆኑ መጠን፣ የተሳካ ትዳር እንዲኖረን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ከማንም በተሻለ ያውቃል። ታዲያ በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ለማዳመጥና ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን? እንዲህ ካደረግን እንደምንጠቀም ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በጥንት ዘመን ለሕዝቡ “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” ብሏል። (ኢሳይያስ 48:18) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል የተሳካ ጋብቻ እንዲኖር ያደርጋል። እስቲ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች የሚሰጠውን ምክር እንመልከት።

“ሚስቶቻችሁን ውደዱ”

6. ለባሎች ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተሰጥቷቸዋል?

6 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለባሎች ግልጽ የሆነ መመሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ። ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው። ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ።”—ኤፌሶን 5:25, 28, 29, 33

7. (ሀ) የክርስቲያኖች ጋብቻ ዋነኛ መሠረት ምን ሊሆን ይገባል? (ለ) ባሎች ሚስቶቻቸውን መውደድ አለባቸው ሲባል ምን ማለት ነው?

7 ጳውሎስ በባልና ሚስት መካከል ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን በሙሉ አልዘረዘረም። ከዚህ ይልቅ የማንኛውም ክርስቲያን ትዳር መሠረት ሊሆን የሚገባውና በጋብቻ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳው ዋና ነገር ፍቅር እንደሆነ ጠቁሟል። ከላይ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ መውደድ የሚለው ሐሳብ ስድስት ጊዜ ተጠቅሷል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ባሎችን “ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ብሎ ሲመክራቸው የተጠቀመበት ቃል በበኩረ ጽሑፉ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት የሚያመለክት ነበር። ጳውሎስ፣ የትዳር ጓደኛሞች መጀመሪያ ላይ አንዳቸው ለሌላው የነበራቸው ፍቅር ሳይቀዘቅዝ እንዲቀጥል ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። በተለይ ብዙዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ለዕርቅ የማይሸነፉ” በሆኑበት “በመጨረሻው ዘመን” ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እንደነዚህ ያሉ ጎጂ ባሕርያት በዛሬው ጊዜ በርካታ ትዳሮችን እየሸረሸሩ ቢሆንም አፍቃሪ የሆነ ባል በዓለም ላይ የሚታየው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በአስተሳሰቡም ሆነ በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት አይፈቅድም።—ሮሜ 12:2

የሚስትህን ፍላጎት ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው?

8, 9. አንድ ክርስቲያን ባል የሚስቱን ፍላጎት በየትኞቹ መንገዶች ማሟላት አለበት?

8 ክርስቲያን ባል ከሆንክ የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ በማስወገድ ለሚስትህ እውነተኛ ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ቀደም ብለን ባየነው ደብዳቤ ላይ ለሚስትህ ልታደርግላት የሚገቡህን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል፤ እነዚህም የሚያስፈልጓትን ነገሮች ማሟላት እንዲሁም ለገዛ ሥጋህ እንደምታደርገው እርሷንም መንከባከብ ናቸው። ባለቤትህ የሚያስፈልጓትን ነገሮች እንዴት ማሟላት ትችላለህ? ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልጋትን በማቅረብ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎለታል:- “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 5:8

9 ይህ ሲባል ግን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ ብቻ በቂ ነው ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ባል ሚስቱ የሚያስፈልጓትን ቁሳዊ ነገሮች በሚገባ እያቀረበ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቿን ግን ላያሟላ ይችላል። ይሁን እንጂ በእነዚህ መንገዶችም ፍላጎቷን ማሟላት አስፈላጊ ነው። በርካታ ክርስቲያን ወንዶች ከጉባኤ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሥራ የሚበዛባቸው መሆኑ አይካድም። ሆኖም አንድ ባል ከበድ ያሉ የጉባኤ ኃላፊነቶች ስላሉት አምላክ የሰጠውን የቤተሰብ ራስ የመሆን ግዴታ ችላ ሊል ይገባል ማለት አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 3:5, 12) ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በዚህ መጽሔት ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሠፈሩት ብቃቶች መሠረት ‘እረኝነት የሚጀምረው ከቤት ነው’ ብሎ መናገር ይቻላል። አንድ ሽማግሌ ቤተሰቡን ችላ የሚል ከሆነ መብቱን ሊያጣ ይችላል።” b በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የሚስትህን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላትህ በጣም አስፈላጊ ነው።

ሚስትህን መንከባከብ ሲባል ምን ማለት ነው?

10. አንድ ባል ሚስቱን መንከባከብ የሚችለው እንዴት ነው?

10 ሚስትህን ትንከባከባታለህ ሲባል ስለምትወዳት ጥሩ አድርገህ ትይዛታለህ ማለት ነው። እንዲህ ማድረግ የምትችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ልታሳልፍ ይገባል። በዚህ ረገድ ሚስትህን ችላ የምትል ከሆነ ለአንተ ያላት ፍቅር እየቀዘቀዘ ሊሄድ ይችላል። ከዚህም በላይ አንተ ለሚስትህ በቂ ጊዜና ትኩረት እንደሰጠሃት ቢሰማህም የእርሷ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል ይኖርብሃል። የትዳር ጓደኛህን እንደምትንከባከባት መናገሩ ብቻ በቂ አይደለም። ሚስትህ ራሷ እንደምትንከባከባት ሊሰማት ይገባል። ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) እንደ አንድ አፍቃሪ ባል መጠን የሚስትህን ፍላጎት በትክክል መረዳትህን ማረጋገጥ ያስፈልግሃል።—ፊልጵስዩስ 2:4

11. አንድ ባል ሚስቱን የሚይዝበት መንገድ ከአምላክም ሆነ ከጉባኤው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚነካበት እንዴት ነው?

11 ሚስትህን እንደምትንከባከባት የምታሳይበት ሌላው መንገድ በንግግርህም ሆነ በድርጊትህ ርኅራኄ በማሳየት ነው። (ምሳሌ 12:18) ጳውሎስ ለቈላስይስ ክርስቲያኖች “ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” በማለት ጽፏል። (ቈላስይስ 3:19) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚያሳየው “መራራ አትሁኑባቸው” የሚለው የጳውሎስ ሐሳብ “እንደ ቤት ሠራተኛ አትመልከታት” ወይም “እንደ ባሪያ አትቁጠራት” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜም ሆነ በሰዎች ፊት የትዳር ጓደኛውን የሚጨቁን ባል፣ ሚስቱን እየተንከባከባት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አንድ ባል ሚስቱን ደግነት በጎደለው መንገድ የሚይዝ ከሆነ ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና ሊበላሽበት ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለባሎች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ [“እንዳይከለከል፣” የ1954 ትርጉም] በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው፣ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።” c1 ጴጥሮስ 3:7

12. አንድ ክርስቲያን ባል ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን ከያዘበት መንገድ ምን ሊማር ይችላል?

12 ‘ሚስቴ ምንጊዜም ቢሆን ትወደኛለች’ ብለህ በማሰብ የምታሳይህን ፍቅር አቅልለህ አትመልከተው። እንደምትወዳት ሁልጊዜ ግለጽላት። ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን የያዘበት መንገድ ለክርስቲያን ባሎች ምሳሌ የሚሆን ነው። ተከታዮቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተገቢ ያልሆኑ ባሕርያት ቢያሳዩም እርሱ ግን ደግና ይቅር ባይ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ሰዎችን “ወደ እኔ ኑ፤ . . . እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” በማለት ሊጋብዝ ችሏል። (ማቴዎስ 11:28, 29) አንድ ክርስቲያን ባል የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ኢየሱስ ጉባኤውን በያዘበት መንገድ ሚስቱን ሊንከባከባት ይገባል። ሚስቱን ከልቡ የሚንከባከብ ወንድ ይህንን በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ የሚያሳይ ሲሆን እንዲህ ማድረጉም ሚስቱ እውነተኛ እረፍት እንድታገኝ ያስችላታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ሚስቶች

13. መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቶችን የሚመለከቱ ምን ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቶችን የሚመለከቱ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። ኤፌሶን 5:22-24, 33 እንዲህ ይላል:- “ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። . . . ሚስትም ባሏን [“በጥልቅ፣” NW] ታክብር።”

14. ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው የሚገልጸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ሴቶችን ዝቅ አያደርግም የምንለው ለምንድን ነው?

14 ጳውሎስ መገዛትንና ማክበርን ጎላ አድርጎ እንደገለጸ ልብ እንበል። ሚስት ለባሏ እንድትገዛ ማሳሰቢያ ተሰጥቷታል። ይህ ደግሞ ከአምላክ ዝግጅት ጋር የሚስማማ ነው። በሰማይም ሆነ በምድር ላይ የሚኖር ፍጥረት ሁሉ ለአንድ አካል ይገዛል። ኢየሱስም እንኳ ለይሖዋ አምላክ ይገዛል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) እርግጥ ነው፣ አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን በአግባቡ የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስቱ ለእርሱ መገዛት ቀላል ይሆንላታል።

15. መጽሐፍ ቅዱስ ለሚስቶች ከሚሰጣቸው ምክሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

15 ጳውሎስ፣ ሚስት “ባሏን [“በጥልቅ፣” NW] ታክብር” በማለትም ተናግሯል። አንዲት ክርስቲያን ሚስት “ገርና ጭምት መንፈስ” ሊኖራት ይገባል እንጂ የባሏን ሥልጣን በትዕቢት የምትገዳደር ወይም በራስ የመመራት ዝንባሌ የምታሳይ መሆን የለባትም። (1 ጴጥሮስ 3:4) አምላካዊ አክብሮት ያላት ሚስት በቤቷ ውስጥ ተግታ በመሥራት ራሷ የሆነውን ባሏን ታስከብራለች። (ቲቶ 2:4, 5) ስለ ባሏ መልካም ነገር የምትናገር ከመሆኑም በላይ ሌሎች ለባሏ አክብሮት እንዲያጡ የሚያደርግ ምንም ነገር አታደርግም። ከዚህም በላይ እርሱ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ጠንክራ ትሠራለች።—ምሳሌ 14:1

16. ክርስቲያን ሚስቶች ከሣራና ከርብቃ ምሳሌ ምን ሊማሩ ይችላሉ?

16 አንዲት ክርስቲያን ሴት ገርና ጭምት መንፈስ ይኖራታል ሲባል የራሷ አመለካከት የላትም ወይም እርሷ የምትሰጠው ሐሳብ ዋጋ የለውም ማለት አይደለም። በጥንት ዘመን የነበሩ እንደ ሣራና ርብቃ ያሉ አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች ያሳሰቧቸውን ጉዳዮች ለባሎቻቸው ከመናገር ወደኋላ አላሉም፤ ይሖዋም የወሰዱትን እርምጃ እንደደገፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያሳያል። (ዘፍጥረት 21:8-12፤ 27:46 እስከ 28:4) ክርስቲያን ሚስቶችም የሚሰማቸውን መናገር ይችላሉ። ሆኖም ይህን የሚያደርጉት አሳቢነት በተሞላበት ሁኔታ እንጂ በሚያቃልል መንገድ መሆን የለበትም። ሐሳባቸውን እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚገልጹ ከሆነ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር የሚያደርጉት ውይይት ይበልጥ አስደሳች ይሆናል፤ የሚያቀርቡት ሐሳብም በባሎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል።

ቃል ኪዳንን ማክበር የሚጫወተው ሚና

17, 18. ባሎችና ሚስቶች፣ ሰይጣን የትዳርን ጥምረት ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት መከላከል የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

17 ጋብቻ የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን ነው። በመሆኑም ባልም ሆነ ሚስት ትዳራቸው የተሳካ እንዲሆን ልባዊ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። በግልጽ አለመነጋገር ችግሮች ተባብሰው የከፋ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሊያደርግ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ችግሮች ሲፈጠሩ ባልና ሚስት ይኮራረፋሉ፤ ይህም በመካከላቸው ቅሬታ እንዲፈጠር ያደርጋል። እንዲያውም አንዳንድ ባልና ሚስት ከትዳራቸው ውጭ የፍቅር ግንኙነት በመመሥረት ጋብቻቸውን ለማፍረስ ሰበብ ይፈልጋሉ። ኢየሱስ “ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 5:28

18 ሐዋርያው ጳውሎስ ያገቡትን ጨምሮ ሁሉንም ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።” (ኤፌሶን 4:26, 27) ዋነኛ ጠላታችን የሆነው ሰይጣን በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሊጠቀምባቸው ይሞክራል። እንዲሳካለት አትፍቀዱ! ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ እንድትችሉ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በመጠቀም በአምላክ ቃል ላይ ምርምር አድርጉ። በመካከላችሁ የተፈጠሩትን ልዩነቶች በእርጋታና በሐቀኝነት ተወያዩባቸው። ይሖዋ ስለ ትዳር ባወጣው መሥፈርት ረገድ የምታውቁትን ነገር በተግባር ለማዋል ጥረት አድርጉ። (ያዕቆብ 1:22-25) በትዳራችሁ ረገድ፣ ሁለታችሁም ሁልጊዜ ከአምላክ ጋር ለመሄድ እንዲሁም እርሱ ያጣመረውን ማንም ሰው ወይም ምንም ነገር እንዲለያየው ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ!—ሚክያስ 6:8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች በሚዘጋጀው ንቁ! መጽሔት የመጋቢት 2002 እትም ገጽ 10 ላይ የሚገኘውን “መፋታትና መለያየት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b መጠበቂያ ግንብ 10-110 ገጽ 12 ወይም መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 15, 1989 ገጽ 12 (እንግሊዝኛ) ተመልከት።

c አንድ ወንድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መብት ለማግኘት ብቁ እንዲሆን ‘የማይጣላ’ መሆን አለበት፤ ይህም ሲባል በሰዎች ላይ አካላዊ ጥቃት የማይሰነዝር ወይም በንግግሩ የማያስፈራራ ሊሆን ይገባል ማለት ነው። በመሆኑም መጠበቂያ ግንብ 17-111 (መስከረም 1, 1990 እንግሊዝኛ) በገጽ 25 ላይ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው በውጭ አምላካዊ ባሕርያትን እያሳየ በቤት ውስጥ ግን ጨቋኝ ቢሆን መብት ለማግኘት ብቁ አይሆንም።”—1 ጢሞቴዎስ 3:2-5, 12

ታስታውሳለህ?

• በክርስቲያኖች ትዳር ውስጥም እንኳ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉት ለምንድን ነው?

• አንድ ባል የሚስቱን ፍላጎቶች ማሟላትና እርሷን መንከባከብ የሚችለው እንዴት ነው?

• አንዲት ሚስት ለባሏ ጥልቅ አክብሮት እንዳላት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

• ባልና ሚስት ቃል ኪዳናቸውን ማጠናከር የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ባል በቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም የሚስቱን ፍላጎት ማሟላት አለበት

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚስቱን የሚንከባከብ ባል እረፍት እንድታገኝ ያደርጋታል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሚስቶች ስሜታቸውን አክብሮት በተሞላበት መንገድ ይገልጻሉ