በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች የምታደርጉት ነገር የወላጆቻችሁን ልብ ይነካል

ወጣቶች የምታደርጉት ነገር የወላጆቻችሁን ልብ ይነካል

ወጣቶች የምታደርጉት ነገር የወላጆቻችሁን ልብ ይነካል

አረጋዊ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል። (3 ዮሐንስ 4) ምንም እንኳ እዚህ ጥቅስ ላይ ልጆች የተባሉት ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ቢሆኑም ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ወላጅ ዮሐንስ የገለጻቸውን የእነዚህን ቃላት ስሜት በደንብ ይረዳል። ወላጆች በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ ሁሉ ልጆችም በወላጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ።

የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ልጆች የሚያደርጉት ነገር ወላጆቻቸውን በእጅጉ እንደሚነካ አስተውሎ ስለነበር “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ተላላ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 10:1) በመሆኑም ከፍ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም ልጆች የሚያደርጓቸው ነገሮች በወላጆቻቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ልብ ማለት ይኖርባቸዋል። ይህ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቻችሁ እናንተን ለማሳደግ ምን ያህል እንደለፉ እስቲ አስቡ! ስለ እናንተ መጨነቅና መጸለይ የጀመሩት ገና ከመወለዳችሁ በፊት ነው። ከተወለዳችሁ በኋላም ቢሆን ወላጆቻችሁ እናንተን በማግኘታቸው በጣም የተደሰቱ ከመሆኑም በላይ ወላጅ በመሆን ስላገኙት አስደሳች ሆኖም ትልቅ መብትና ከባድ ኃላፊነት አምላክን አመስግነውት መሆን አለበት። እናንተን የማሳደግ ኃላፊነት በእነርሱ ትከሻ ላይ የወደቀ ሲሆን እነርሱም የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናቸው መጠን ይህን ሁኔታ በቁም ነገር ተመልክተውታል።

ወላጆቻችሁ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች አስተማማኝ መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል፤ እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ ተሞክሮ ያካበቱ ወላጆችን ምክር ጠይቀዋል። በተጨማሪም ጭንቀቶቻቸውን ለአምላክ በጸሎት መንገራቸውን አላቋረጡም። (መሳፍንት 13:8) እያደጋችሁ ስትሄዱ ወላጆቻችሁ መልካም ባሕርያቶቻችሁን ጠንቅቀው የሚያውቁ ቢሆንም ድክመቶቻችሁንም ማስተዋላቸው አይቀርም። (ኢዮብ 1:5) በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስትሆኑ ተፈታታኝ ነገሮች ብቅ ማለት ይጀምራሉ። አንዳንዴ ዓመጸኛ የምትሆኑበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ወላጆቻችሁ በሰማይ የሚኖረውን አባታችሁን ይሖዋን ማምለካችሁን እንድትቀጥሉ መርዳት የሚችሉበትን ዘዴ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ይጸልያሉ፣ ብዙ ያነባሉ እንዲሁም ስለ እናንተ በጣም ያስባሉ።

ወላጆቻችሁ መቼም ቢሆን የእናትነትና የአባትነት ስሜታቸው አይጠፋም። ካደጋችሁ በኋላም ቢሆን ለአካላዊ፣ ለአእምሯዊ፣ ለስሜታዊና ለመንፈሳዊ ደኅንነታችሁ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ ሲያሳድጓችሁ የራሳችሁን ምርጫ የማድረግ ነጻነት እንዳላችሁ ያውቃሉ፤ እንዲሁም የምታደርጓቸው ምርጫዎች ሕይወታችሁን ወዴት አቅጣጫ እንደሚመሩት በእርግጠኝነት መናገር አይችሉም። የምትከተሉትን የሕይወት አቅጣጫ በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ያለባችሁ እናንተ ራሳችሁ ናችሁ።

ወላጆች፣ ልጆቻቸው “በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ” ከሌላቸው ልጆቻቸው ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አካሄድ መከተላቸው ደግሞ ከፍተኛ ሐዘን ያስከትልባቸዋል ቢባል ምክንያታዊ አይሆንም? በእርግጥም የሞኝነት አካሄድ የሚከተሉ ልጆች ወላጆቻቸውን ያሳዝናሉ። ሰሎሞን “ተላላ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤ ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል” በማለት ገልጿል። (ምሳሌ 17:25) አንድ ልጅ እውነተኛውን አምላክ ማምለክ ሲያቆም ወላጆች ምንኛ ያዝናሉ!

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የምታደርጓቸው ነገሮች በቤተሰባችሁ ብሎም በሌሎች ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የምታሳዩት ባሕርይ የወላጆቻችሁን ልብ በእጅጉ ይነካል። በአምላክና በሕጎቹ ላይ ፊታችሁን ካዞራችሁ ወላጆቻችሁ በጣም ያዝናሉ። በአንጻሩ ደግሞ ለአምላክ ታማኝና ታዛዥ ከሆናችሁ እጅግ ይደሰታሉ። በመሆኑም የወላጆቻችሁን ልብ ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ! ለሚያሳድጓችሁ፣ ለሚንከባከቧችሁና ለሚወዷችሁ ወላጆቻችሁ ከዚህ የተሻለ ምን ውድ ስጦታ ልትሰጧቸው ትችላላችሁ?