በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ትችላለህ!

የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ትችላለህ!

የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ትችላለህ!

በሕይወቱ ውስጥ አንድ ዓይነት የፍትሕ መጓደል ያልደረሰበት ማን አለ? አንዳንዶቹ የፍትሕ መጓደሎች እንደተፈጸሙብን አድርገን የምናስባቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ግን በእርግጥ በሕይወታችን ላይ የደረሱ ናቸው።

ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምብን የተወሰነ ስሜታዊ ሥቃይ ብሎም መንፈሳዊ ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። ሁኔታውን ለማስተካከል ከፍተኛ ፍላጎት ይኖረን ይሆናል። እንዲህ የሚሰማን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ‘ፍትሕ የማያጓድለው’ ፈጣሪያችን ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ጠንካራ የፍትሕ ስሜት እንዲኖራቸው አድርጎ መሆኑ ነው። (ዘዳግም 32:4 NW፤ ዘፍጥረት 1:26) ይሁንና ፍትሕ እንደተጓደለ ሆኖ እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። በአንድ ወቅት አንድ ጠቢብ ሰው የተሰማውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።” (መክብብ 4:1) ታዲያ የፍትሕ መጓደልን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

የፍትሕ መጓደል ሲባል ምን ማለት ነው?

የፍትሕን መሥፈርት የሚጥስ ድርጊት ወይም ሁኔታ ኢፍትሐዊ ይባላል። ለሰው ልጆች የፍትሕ መሥፈርት የሚሆነው ምንድን ነው? ጻድቅና የማይለወጠው ፈጣሪያችን ፍትሐዊ የሆነውንና ያልሆነውን የመወሰን ወይም የፍትሕን መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን እንዳለው ግልጽ ነው። በአምላክ አመለካከት ‘በሕይወት መንገድ’ መመላለስ ማለት ‘ኢፍትሐዊ ድርጊት አለመፈጸምን’ ይጨምራል። (ሕዝቅኤል 33:15 NW) በመሆኑም ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰው ሲፈጥር ሕሊና ማለትም ትክክልና ስሕተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳውን ውስጣዊ ድምፅ ሰጥቶታል። (ሮሜ 2:14, 15) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትክክል የሆነው የቱ እንደሆነና እንዳልሆነ ገልጿል።

ፍትሕ እንደተጓደለብን ሆኖ ሲሰማን ምን ማድረግ እንችላለን? ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ተፈጽሞብን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ጉዳዩን በሚዛናዊነት መመርመር ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል ዮናስ የተባለው ዕብራዊ ነቢይ የነበረበትን ሁኔታ እንመልከት። ይሖዋ ዮናስን ወደ ነነዌ በመሄድ የከተማይቱን ነዋሪዎች ስለሚመጣው የጥፋት ፍርድ እንዲነግራቸው ላከው። መጀመሪያ ላይ ዮናስ የተሰጠውን ትእዛዝ ከመፈጸም ይልቅ ወደ ሌላ ቦታ ሸሽቶ ሄደ። በኋላ ግን ወደ ነነዌ በመሄድ ስለሚመጣው የጥፋት ፍርድ በመናገር ነዋሪዎቹን አስጠነቀቃቸው። ይሖዋም የሰጡትን ጥሩ ምላሽ በመመልከት ከተማዋንም ሆነ ነዋሪዎቿን ላለማጥፋት ወሰነ። በዚህ ወቅት ዮናስ ምን ተሰማው? ዮናስ “ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ።” (ዮናስ 4:1) ዮናስ፣ ይሖዋ ከፍተኛ የፍትሕ መጓደል እንደፈጸመ ሆኖ ተሰምቶት ነበር።

ልብን ማንበብ የሚችለው እንዲሁም ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወደው’ ይሖዋ እንዳልተሳሳተ ግልጽ ነው። (መዝሙር 33:5) ዮናስ፣ ይሖዋ ይህን የወሰነው ፍጹም ከሆነው ፍትሑ ጋር በሚስማማ መንገድ መሆኑን መረዳት ነበረበት። ፍትሕ እንደተጓደለብን ሆኖ ሲሰማን ‘ይሖዋ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩን ከዚህ በተለየ መንገድ ይመለከተው ነበር?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

የፍትሕ መጓደልን መቋቋም

መጽሐፍ ቅዱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ስለተፈጸመባቸው ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። እነዚህ ሰዎች የገጠሟቸውን ከባድ ችግሮች የተወጡት እንዴት እንደሆነ በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ቅናት ያደረባቸው ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ለባርነት የሸጡትን ዮሴፍን ተመልከት። በግብጽ እያለ የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ ለማባበል ትጥር የነበረ ቢሆንም ዮሴፍ ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህም ምክንያት አስገድዶ ሊደፍረኝ ሞክሯል በማለት በሐሰት ከሰሰችው። በመሆኑም ዮሴፍ እስር ቤት ገባ። ያም ሆኖ የዮሴፍ እምነት ከታሰረበት የእግር ብረት ይበልጥ የጠነከረ ነበር። የደረሰበት ኢፍትሐዊ ድርጊት መንፈሳዊነቱንም ሆነ በይሖዋ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያዳክምበት አልፈቀደም።—ዘፍጥረት 37:18-28፤ 39:4-20፤ መዝሙር 105:17-19

የፍትሕ መጓደል የደረሰበት ሌላው ሰው ደግሞ ናቡቴ ነው። ይህ ሰው አክዓብ የተባለው የእስራኤል ንጉሥ ሚስት የነበረችው የኤልዛቤል የጭካኔ ድርጊት ሰለባ ሆኗል። ንጉሥ አክዓብ በቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ የሚገኘውን የናቡቴን የእርሻ ቦታ የራሱ ለማድረግ ተመኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ እስራኤላዊ መሬቱን ለዘለቄታው እንዳይሸጥ የሚከለክል ሕግ ስለነበር ናቡቴ ንጉሡ ያቀረበለትን የግዢ ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። (ዘሌዋውያን 25:23) በዚህ ጊዜ ክፉዋ የአክዓብ ሚስት፣ ናቡቴን ‘አምላክንና ንጉሡን ሰድቧል’ ብለው በሐሰት የሚከሱት ምሥክሮች አዘጋጀች። ስለሆነም ናቡቴና ወንዶች ልጆቹ ተገደሉ። ናቡቴ ሕዝቡ እሱን ለመግደል ድንጋይ ሲያነሳ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ገምት!—1 ነገሥት 21:1-14፤ 2 ነገሥት 9:26

ይሁንና ከላይ የተጠቀሱት ታሪኮች በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ከተፈጸሙት ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ጋር ሲነጻጸሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። ኢየሱስ የሞት ፍርድ የተበየነበት በሐሰት ተወንጅሎ ሲሆን ብይኑን ያስተላለፈውም ፍርድ ቤት የተሰየመው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ነበር። የክሱን ጉዳይ እንዲያይ የተሰየመው ሮማዊ ገዥ ከእውነት ጎን ለመቆም የሚያስችል ድፍረት አልነበረውም። (ዮሐንስ 18:38-40) አዎን፣ ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ያደረሰው የፍትሕ መጓደል እስካሁን ድረስ በማንኛውም ሰው ላይ ከፈጸመው እጅግ የከፋ ነው!

እነዚህ ታሪኮች ይሖዋ ለፍትሕ መጓደል ግድ እንደማይሰጠው የሚያሳዩ ናቸው? በጭራሽ! ይሖዋ እነዚህን ሁኔታዎች የተመለከታቸው ከሰው አመለካከት አንጻር አይደለም። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ዮሴፍ ለባርነት በመሸጡ የቤተሰቡን ሕይወት ከሞት ታድጓል። የቤተሰቡን ሕይወት ችግር ላይ የጣለው ከፍተኛ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት በግብጽ የእህል ግምጃ ቤት ኃላፊ መሆን ችሏል። ይሖዋ የፍትሕ መጓደል እንዲደርስበት ባይፈቅድ ኖሮ ዮሴፍ እስር ቤት ባልገባ ነበር። ይህም አብረውት የታሰሩትን ሁለት ሰዎች ሕልም እንዲፈታላቸውና በኋላም አንደኛው ስለ ዮሴፍ ሁኔታ ለፈርዖን ተናግሮ የእህል ግምጃ ቤት ኃላፊ ለመሆን የሚያስችለው አጋጣሚ ባልተፈጠረለት ነበር።—ዘፍጥረት 40:1፤ 41:9-14፤ 45:4-8

ስለ ናቡቴስ ምን ማለት ይቻላል? አሁንም ሁኔታውን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት ሞክር። ናቡቴ በመቃብር ውስጥ ቢሆንም እንኳ ሙታንን ማስነሳት በሚችለው በይሖዋ ፊት ሕያው ነው። (1 ነገሥት 21:19፤ ሉቃስ 20:37, 38) ናቡቴ ይሖዋ ከሞት እስኪያስነሳው ድረስ መጠበቅ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ሙታን አንዳች የማያውቁ በመሆናቸው ናቡቴ በሞት አንቀላፍቶ የሚቆየው ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው። (መክብብ 9:5) ከዚህም ባሻገር ይሖዋ በአክዓብና በቤተሰቡ ላይ የጥፋት ፍርድ በማምጣት ለናቡቴ ተበቅሎለታል።—2 ነገሥት 9:21, 24, 26, 35, 36፤ 10:1-11፤ ዮሐንስ 5:28, 29

ኢየሱስም ቢሆን በደረሰበት ኢፍትሐዊ ድርጊት ሕይወቱን አጥቷል። ያም ሆኖ አምላክ ከሞት አስነስቶ ‘ግዛትና ሥልጣን፣ ኀይልና ጌትነት እንዲሁም ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ’ ስም በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል። (ኤፌሶን 1:20, 21) ሰይጣን በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ያደረሰው የፍትሕ መጓደል ይሖዋ ለልጁ ወሮታ ከመክፈል አላገደውም። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ፈቃዱ ቢሆን ኖሮ አላግባብ በመታሰር የደረሰበትን የፍትሕ መጓደል ወዲያውኑ ሊያስወግደው እንደሚችል እርግጠኛ ነበር። ይሁንና ክርስቶስ፣ ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተመዘገቡትን ትንቢቶች የሚያስፈጽምበትና የፍትሕን መጓደል የሚያስወግድበት ጊዜ እንዳለው ያውቃል።

ሰይጣንና ወኪሎቹ ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ላይ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን እንደሚፈጽሙ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ይሖዋ ሁኔታውን ደረጃ በደረጃ በማስተካከል ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግዳል። በመሆኑም ኢፍትሐዊነት ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ለማየት አምላክን መጠበቅ ይኖርብናል።—ዘዳግም 25:16 NW፤ ሮሜ 12:17-19

ይሖዋ የፍትሕ መጓደል እንዲደርስብን የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

ይሖዋ አንዳንድ ሁኔታዎችን የማያስተካክልበት የራሱ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል። በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ሥልጠና እንድናገኝ ሲል የፍትሕ መጓደል እንዲደርስብን ሊፈቅድ ይችላል። እርግጥ ነው ‘አምላክ ማንንም በክፉ አይፈትንም።’ (ያዕቆብ 1:13) ያም ሆኖ አንድ ችግር ሲደርስብን ሁኔታውን ለማስተካከል ጣልቃ ላይገባ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ለእንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ጥሩ ምላሽ ለሚሰጡት ሰዎች ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን [“ሥልጠናችሁን እንድትፈጽሙ፣” NW] ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።”—1 ጴጥሮስ 5:10 የ1954 ትርጉም

ከዚህም በላይ ይሖዋ አንድ ዓይነት የፍትሕ መጓደል እንዲኖር መፍቀዱ ኢፍትሐዊ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ከመንገዳቸው ተመልሰው ንስሐ የሚገቡበት ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የጴጥሮስን ማሳሰቢያ የሰሙ አንዳንድ አይሁዳውያን ‘ልባቸው እጅግ የተነካው’ ኢየሱስ ከተገደለ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነበር። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቃል ከልባቸው ተቀብለው ተጠምቀዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:36-42

ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሁሉ ንስሐ ይገባሉ ማለት እንደማይቻል የታወቀ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከበፊቱ የከፋ ኢፍትሐዊ ድርጊት መፈጸማቸውን ይቀጥሉ ይሆናል። ይሁንና ምሳሌ 29:1 “ከብዙ ተግሣጽ በኋላ ዐንገቱን የሚያደነድን ሰው፣ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም” ይላል። በእርግጥም ይሖዋ መጥፎ ድርጊት መሥራታቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችን ውሎ አድሮ ሙሉ በሙሉ ያጠፋቸዋል።—መክብብ 8:11-13

የፍትሕ መጓደል ካደረሰብን ጉዳት ለማገገም የቱንም ያህል ጊዜ ይውሰድብን ይሖዋ ከዚህ ችግር እንድንላቀቅ እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል እንደሚያስወግድልን እርግጠኞች ነን። ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘ጽድቅ በሚኖርበት’ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል።—2 ጴጥሮስ 3:13

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናቡቴ ከባድ ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምበት ምን ያህል ተሰምቶት ይሆን?