በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ብሉይ ኪዳን” በዘመናችንም ጠቃሚ ነው?

“ብሉይ ኪዳን” በዘመናችንም ጠቃሚ ነው?

“ብሉይ ኪዳን” በዘመናችንም ጠቃሚ ነው?

በ1786 አንድ ፈረንሳዊ ሐኪም ትሬቴ ዳናቶሚ ኤ ደ ፊዝዮሎዢ (የሰውነት አሠራርና የሰው አካል ጥናት) የተባለ መጽሐፍ አሳተመ። ይህ መጽሐፍ በጊዜው ከነበሩት ስለ ነርቭ ሥርዓት ከሚያወሱ መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ ትክክለኛ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ የማይገኝ በመሆኑ በቅርቡ አንዱ ቅጂ ብቻ ከ27 ሺህ ዶላር በሚበልጥ ገንዘብ ተሽጧል! ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ ታካሚዎች ከረጅም ጊዜ በፊት በተጻፈው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው ጥናት ላይ ተመሥርቶ ሕክምና በሚሰጥ ዶክተር አይተማመኑም። ይህ መጽሐፍ ከታሪክና ከሥነ ጽሑፍ አንጻር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑ በዛሬው ጊዜ ለሚገኝ ታካሚ ጠቃሚ እንዲሆን አያደርገውም።

በርካታ ሰዎች ብሉይ ኪዳን ተብለው ስለሚጠሩት መጻሕፍት እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው። ስለ እስራኤላውያን ታሪክ የሚያወሳውን ዘገባም ሆነ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን ማራኪ ግጥሞች ያደንቋቸዋል። ያም ሆኖ ከ2,400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ይህ መጽሐፍ የያዘውን መመሪያ መከተል ምክንያታዊ ሆኖ አይታያቸውም። በዛሬው ጊዜ ያለው ሳይንሳዊ እውቀት፣ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም የቤተሰብ ሕይወት እንኳ ሳይቀር መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዘመን በጣም የተለየ ነው። ክርስቺያኒቲ ቱዴይ የተባለው ጽሑፍ የቀድሞ አዘጋጅ የነበሩት ፊሊፕ ያንሲ፣ ዘ ባይብል ጂሰስ ሬድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ብሉይ ኪዳንን መረዳት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም፤ ለመረዳት ቀላል የሆነው ክፍልም እንኳ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሰዎችን የሚያስከፋ ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሰዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሦስት አራተኛ ክፍል የሚሸፍነውን ብሉይ ኪዳንን ብዙ ጊዜ አያነቡትም።” እንዲህ ያለው አመለካከት ግን አዲስ አይደለም።

ሐዋርያው ዮሐንስ በ100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ከሞተ 50 ዓመት እንኳ ሳይሆነው ማርሲየን የተባለ አንድ ሀብታም ወጣት፣ ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንን ሊቀበሉት እንደማይገባ በሕዝብ ፊት ያስተምር ነበር። ራቢን ሌን ፎክስ የተባሉት እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት ማርሲየን እንደሚከተለው በማለት ይከራከር ነበር:- “በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጸው ‘አምላክ’ ሽፍቶችንና የእስራኤል ንጉሥ እንደነበረው እንደ ዳዊት ያሉ አሸባሪዎችን የሚደግፍ ‘የለየለት አረመኔ’ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ክርስቶስ የገለጸው አምላክ [በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው] እጅግ የላቀ፣ ሙሉ በሙሉ የተለየና አዲስ ነበር።” ፎክስ እንደጻፉት ይህ እምነት “‘ማርሲዮኒዝም’ ተብሎ መጠራት የጀመረ ሲሆን እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ድረስ በተለይም የሶርያ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ በስተ ምሥራቅ በሚገኙ ሰዎች ዘንድ ተከታዮችን ማግኘቱን ቀጠለ።” ዛሬም ቢሆን አንዳንዶች እንደዚህ ዓይነት አስተሳስብ አላቸው። በዚህም የተነሳ ከ1,600 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉም በኋላ ፊሊፕ ያንሲ “ክርስቲያኖች ስለ ብሉይ ኪዳን ያላቸው እውቀት በፍጥነት እየጠፋ ሲሆን ዘመናዊው ኅብረተሰብ ደግሞ ብሉይ ኪዳንን ጨርሶ አያውቀውም ማለት ይቻላል” ሲሉ ጽፈዋል።

ታዲያ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ተተክቷል? በብሉይ ኪዳን ውስጥ አምላክ ‘የሰራዊት ጌታ’ እንደሆነ የሚናገረውን ሐሳብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኘው ‘የፍቅርና የሰላም አምላክ’ ከሚለው ጥቅስ ጋር ማስማማት የምንችለው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 13:13፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11) ብሉይ ኪዳን በአሁኑ ጊዜ ሊጠቅምህ ይችላል?