በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለትምህርታችን ተጽፎአል”

“ለትምህርታችን ተጽፎአል”

“ለትምህርታችን ተጽፎአል”

“ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም።” (መክብብ 12:12) በዛሬው ጊዜ ያሉትን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጽሑፎች ስንመለከት ይህን ጥቅስ ከተጻፈበት ዘመን ባልተናነሰ ዛሬም እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። ታዲያ አስተዋይ የሆነ አንባቢ ለየትኞቹ መጻሕፍት ትኩረት መስጠት እንደሚገባው መወሰን የሚችለው እንዴት ነው?

በርካታ አንባቢያን አንድን መጽሐፍ ለማንበብ ሲያስቡ ስለ ደራሲው የተወሰነ ነገር ማወቅ ይፈልጋሉ። የመጽሐፍ አሳታሚዎች የደራሲውን የትውልድ ቦታ፣ የትምህርት ደረጃ እንዲሁም የጻፋቸውን ሌሎች መጻሕፍት የሚገልጽ አጠር ያለ አንቀጽ በመጽሐፉ ውስጥ ያሰፍራሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት ሴት ደራሲዎች፣ አንባቢያን ጸሐፊዋ ሴት በመሆኗ ለመጽሐፉ ዝቅተኛ ግምት እንዳያድርባቸው ሲሉ በወንድ የብዕር ስም ይጠቀሙ የነበረ መሆኑ የአንድ መጽሐፍ ደራሲ ማንነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ይጠቁማል።

የሚያሳዝነው ግን ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንዳንዶች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸው አምላክ ጠላቶቹን ያለ ምንም ምሕረት ያጠፋ ጨካኝ እንደሆነ ስለሚያምኑ ብሉይ ኪዳንን አያነቡትም። a እስቲ የዕብራይስጥና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ስላስጻፈው አምላክ ምን እንደሚሉ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አምላክ ለእስራኤል ብሔር “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏቸው ነበር። (ሚልክያስ 3:6) ከ500 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ስለ አምላክ ሲናገር “በእርሱ ዘንድ መለዋወጥ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:17) ይህ ከሆነ ታዲያ አንዳንዶች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸው አምላክ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተጠቀሰው አምላክ የተለየ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የአምላክ ባሕርያት በተለያየ መንገድ ስለተገለጹ ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ብቻ እንኳ አምላክ ‘ልቡ እጅግ እንዳዘነ’ እንዲሁም ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪና’ “የምድር ሁሉ ዳኛ” እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 6:6፤ 14:22፤ 18:25) ታዲያ እነዚህ የተለያዩ መግለጫዎች የተሰጡት ስለ አንድ አምላክ ነው? አዎን።

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድን ዳኛ ፊቱ ለፍርድ ቀርበው የነበሩ ሰዎች ሕግን በጥብቅ እንደሚያስፈጽም ሰው አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ልጆቹ አፍቃሪና ደግ አባት እንደሆነ አድርገው ያዩታል። ጓደኞቹ ደግሞ የሚቀረብና ተጫዋች ሰው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዳኛ፣ አባትና ጓደኛ የሆነው ይኸው ሰው ሲሆን የተለያዩ ባሕርያቱ በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ይታያሉ።

በተመሳሳይም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” እንደሆነ ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ግን ‘በደለኛውን ሳይቀጣ ዝም ብሎ እንደማይተው’ እናውቃለን። (ዘፀአት 34:6, 7) እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ዓይነት ባሕርያት የአምላክን ስም ትርጉም ያንጸባርቃሉ። “ይሖዋ” የሚለው ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” ማለት ነው። ይህም አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ያሳያል። (ዘፀአት 3:13-15 NW) ሆኖም እንዲህ የሚያደርገው ይኸው አምላክ ነው። ኢየሱስ “ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው” በማለት ተናግሯል።—ማርቆስ 12:29 NW

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተተክተዋል?

አዳዲስ የምርምር ውጤቶች ሲገኙ ወይም የብዙኃኑ አመለካከት ሲለወጥ ቀደም ብለው የነበሩ የመማሪያ መጻሕፍት በሌሎች መተካታቸው የተለመደ ነው። ታዲያ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተክተዋቸዋል? በፍጹም አልተኳቸውም።

ኢየሱስ፣ ስለ ምድራዊ አገልግሎቱ የሰፈረው ዘገባ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ የጻፏቸው መጻሕፍት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲተኳቸው አስቦ ቢሆን ኖሮ ይህን ግልጽ ያደርገው ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደረገ የሉቃስ ዘገባ ሲገልጽ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት [በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት] ስለ እርሱ የተጻፈውን [ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ] አስረዳቸው” ይላል። ቆየት ብሎም ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱና ለሌሎች ሰዎች ከተገለጠ በኋላ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው። (ሉቃስ 24:27, 44) ታዲያ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጊዜ ያለፈባቸው ከሆኑ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ማብቂያ ላይ ከእነዚህ መጻሕፍት ጠቅሶ መናገር ለምን አስፈለገው?

የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም የኢየሱስ ተከታዮች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር፤ እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ወደፊት የሚፈጸሙ ትንቢቶችንና በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማብራራት እንዲሁም ክርስቲያኖች በታማኝነት እንዲጸኑ የሚያበረታቱ የጥንት የአምላክ አገልጋዮችን ግሩም ምሳሌዎች ለማጉላት በእነዚህ መጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:16-21፤ 1 ቆሮንቶስ 9:9, 10፤ ዕብራውያን 11:1 እስከ 12:1) ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ [እንዲሁም] . . . ይጠቅማሉ” ብሏል። b (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በዛሬው ጊዜ የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

ለዕለታዊ ሕይወት የሚጠቅም ምክር

በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የዘር ጥላቻን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በምሥራቅ አውሮፓ በምትገኝ አንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ብሏል:- “የትም ቦታ ስንሄድ በቡድን መሆን አለብን። በቡድን ስንሆን እኛን ለማጥቃት አይደፍሩ ይሆናል።” ይህ የ21 ዓመት ወጣት አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ወደ ውጭ መውጣት አንችልም፤ በተለይም በምድር ውስጥ በሚጓዙ ባቡሮች አንሳፈርም። ሰዎች እኛን ሲያዩ ትኩረት የሚያደርጉት በቆዳችን ቀለም ላይ ነው።” የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይህን አሳሳቢ ሁኔታ በተመለከተ የሚናገሩት ነገር ይኖር ይሆን?

የጥንት እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ነበር:- “መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሮአችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤ አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና።” (ዘሌዋውያን 19:33, 34) በጥንቷ እስራኤል የነበረው ሕግ ስደተኞችን ወይም ‘መጻተኞችን’ በአክብሮት እንዲይዟቸው ሕዝቡን የሚያዝ ሲሆን ይህ ሕግ አሁንም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። በሕጉ ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች በዛሬው ጊዜ ያለውን የዘር ጥላቻ ለማስወገድ ይረዳሉ ቢባል አትስማማም?

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ዝርዝር ሐሳቦችን ባያካትቱም ገንዘብን በአግባቡ ስለ መጠቀም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችን ይዘዋል። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 22:7 “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” ይላል። ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክር የሚለግሱ በርካታ ባለሞያዎች በዱቤ ዕቃዎችን መግዛት ለኢኮኖሚ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ይናገራሉ።

በታሪክ ዘመናት ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ሀብታም የሆነው ንጉሥ ሰሎሞን፣ በዚህ ፍቅረ ንዋይ በተጠናወተው ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከፍሎ ሀብት የማሳደድ አባዜ እንዲህ በማለት በትክክል ገልጾታል:- “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው።” (መክብብ 5:10) ይህ እንዴት ያለ ጥበብ ያዘለ ማሳሰቢያ ነው!

የወደፊት ተስፋ

ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ጭብጡ አንድ ነው:- የአምላክ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠውና ስሙ የሚቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ነው።—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በአምላክ መንግሥት ሥር ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚገልጹ ሲሆን ይህ ደግሞ የሚያጽናናን ከመሆኑም በላይ የመጽናናት ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ የበለጠ እንድንቀርብ ይረዳናል። ለአብነት ያህል፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በሰውና በእንስሳት መካከል ስለሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነት እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል:- “ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።” (ኢሳይያስ 11:6-8) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው!

የዘር ጥላቻ የሚደርስባቸው፣ በከባድ ሕመም የሚሠቃዩ ወይም ከአቅማቸው በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር የገጠማቸው ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክርስቶስ ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ የሚል ትንቢት ይዘዋል:- “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል።” (መዝሙር 72:12, 13) እንዲህ ያሉት ተስፋዎች ለሚያምኑባቸው ሰዎች ጠቃሚ ናቸው፤ ምክንያቱም የወደፊቱን ጊዜ በተስፋና በልበ ሙሉነት እንዲጠባበቁ ይረዷቸዋል።—ዕብራውያን 11:6

ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ብሎ መጻፉ ምንም አያስደንቅም:- “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) አዎን፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አሁንም ቢሆን አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው የቃሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓቢይ ክፍል ሲሆኑ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ጠቃሚ ናቸው። ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ ጥረት በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ወደሆነው አምላክ ይበልጥ እንድትቀርብ ምኞታችን ነው።—መዝሙር 119:111, 112

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለን እንጠራቸዋለን። (“ብሉይ ኪዳን ወይስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት” የሚለውን በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ኪዳንን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለው ይጠሩታል።

b የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በዛሬው ጊዜ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዘዋል። ሆኖም ክርስቲያኖች፣ አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ ሥር እንዳልሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ብሉይ ኪዳን ወይስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት?

“ብሉይ ኪዳን” የሚለው አገላለጽ የሚገኘው በ2 ቆሮንቶስ 3:14 ላይ ሲሆን “ኪዳን” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪክኛ ዲያቴክ ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “ብሉይ ኪዳን” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው?

የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ኤድዋርድ ሮቢንሰን እንዲህ ብለዋል:- “የጥንቱ ቃል ኪዳን የሚገኘው በሙሴ መጻሕፍት ውስጥ ስለሆነ [ዲያቴክ] የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ፣ የሙሴን ጽሑፎች ማለትም ሕጉን ያመለክታል።” ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 3:14 ላይ ብሉይ ኪዳን ሲል ከክርስትና በፊት የነበሩት መጻሕፍት ክፍል የሆነውን የሙሴን ሕግ ማመልከቱ ነበር።

ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙት ለመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው መጠሪያ ምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስና ተከታዮቹ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጊዜ ያለፈባቸው ወይም አሮጌ እንደሆኑ ከማመልከት ይልቅ “ቅዱሳት መጻሕፍት” በማለት ጠርተዋቸዋል። (ማቴዎስ 21:42፤ ሮሜ 1:2) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከዚህ አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ ብሉይ ኪዳን የሚባሉትን መጻሕፍት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለው ይጠሯቸዋል፤ ምክንያቱም ከእነዚህ መጻሕፍት አብዛኞቹ መጀመሪያ የተጻፉት በዕብራይስጥ ነበር። በተመሳሳይም አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት የይሖዋ ምሥክሮች የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለው ይጠሯቸዋል፤ ይህንንም የሚሉት እነዚህን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የጻፏቸው ሰዎች የግሪክኛ ቋንቋን ስለተጠቀሙ ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው ጥብቅ ዳኛ፣ አፍቃሪ አባትና ጥሩ ጓደኛ ሊሆን ይችላል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ በሙሉ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሟል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርግ ሊረዱት የሚችሉት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?