በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ እርዳታ አምባገነናዊ አገዛዞችን ተቋቁመን ማለፍ ችለናል

በይሖዋ እርዳታ አምባገነናዊ አገዛዞችን ተቋቁመን ማለፍ ችለናል

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ እርዳታ አምባገነናዊ አገዛዞችን ተቋቁመን ማለፍ ችለናል

ሄንሪክ ዶርኒክ እንደተናገረው

የተወለድኩት በ1926 ነው። ወላጆቼ አጥባቂ ካቶሊኮች የነበሩ ሲሆን በደቡባዊ ፖላንድ፣ ካቶቪትሳ አቅራቢያ በምትገኘው ሩዳ ሽሎስካ የተባለች የማዕድን ማውጫ ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ወላጆቻችን እኔን፣ ታላቅ ወንድሜን በርናርድን እንዲሁም ሩዝሃ እና ኤዲታ የተባሉትን ታናናሽ እህቶቼን እንድንጸልይ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድና ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ አስተምረውን ነበር።

ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሰማ

በጥር 1937 የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ቀን አባቴ በጣም ደስ ብሎት ወደ ቤት መጣ። የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡትን አንድ ትልቅና ብዙ ገጾች ያሉት መጽሐፍ ይዞ ነበር። “ልጆች፣ ምን ይዤ እንደመጣሁ ተመልከቱ፤ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ!” አለን። ከዚያን ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አይቼ አላውቅም ነበር።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሩዳ ሽሎስካ እና በአካባቢዋ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስታሳድር ቆይታለች። ቀሳውስቱ ከማዕድን ማውጫው ባለቤቶች ጋር በጣም ይቀራረቡ የነበረ ሲሆን ሠራተኞቹም ሆነ ቤተሰቦቻቸው አለምንም ማንገራገር እንዲታዘዟቸው ይፈልጉ ነበር። ከሠራተኞቹ አንዱ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ባይገኝ ወይም ኃጢአቱን ለመናዘዝ ፈቃደኛ ባይሆን እንደ እምነት የለሽ ተደርጎ የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ ከሥራ ሊባረር ይችል ነበር። አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት በመጀመሩ እንዲህ ዓይነት ማስፈራሪያ ደረሰበት። ሆኖም አንድ ቄስ ቤታችን ሲመጣ፣ ቄሱ የሃይማኖት ሰው ቢመስልም ግብዝ መሆኑን በመግለጽ አባቴ በሰው ሁሉ ፊት አጋለጠው። ኃፍረት የተከናነበው ቄስ ሌላ ችግር ውስጥ መግባት ስላልፈለገ አባቴ ከሥራው አልተባረረም።

አባቴ በዚህ መንገድ ቄሱን ሲያፋጥጠው መመልከቴ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ያደረግሁትን ውሳኔ አጠናከረልኝ። እያደር ይሖዋን እየወደድኩት ስሄድ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መሠረትኩ። አባቴ ከቄሱ ጋር ከተነጋገረ ከጥቂት ወራት በኋላ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኘን፤ እዚያም አባቴ “ይህ ኢዮናዳብ ነው” ተብሎ 30 ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ተዋወቀ። ብዙም ሳይቆይ “ኢዮናዳብ” የሚለው ስም ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች እንደሚያመለክትና ቁጥራቸውም እያደገ እንደሚሄድ ተገነዘብኩ። a2 ነገሥት 10:15-17

“አንተ ልጅ፣ ጥምቀት ምን ማለት እንደሆነ ገብቶሃል?”

አባቴ እውነትን ካወቀ በኋላ መጠጣት ያቆመ ሲሆን ጥሩ ባልና አባት ሆነ። ያም ሆኖ ግን እናታችን ሃይማኖታዊ አመለካከቱን አልተቀበለችውም፤ እንዲያውም እንደቀድሞው እየኖረ ካቶሊክ ቢሆን እንደምትመርጥ ትናገር ነበር። ሆኖም ፖላንድ ወራሪዎቹን ጀርመኖች እንድታሸንፍ ሲጸልዩ የነበሩት ቀሳውስት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላ ደግሞ ሂትለር ድል በመቀዳጀቱ የምስጋና ጸሎት ሲያቀርቡ ተመለከተች። በመሆኑም በ1941 እናቴ ከእኛ ጋር ይሖዋን ማገልገል ጀመረች።

ከዚያ ቀደም ብሎ ራሴን ለአምላክ መወሰኔን ለማሳየት መጠመቅ እንደምፈልግ ብገልጽም የጉባኤው ሽማግሌዎች ትንሽ እንደሆንኩ ስለተሰማቸው እንድቆይ ነገሩኝ። ውሎ አድሮ ግን በታኅሣሥ 10, 1940 ኮንራድ ግራቦቪ የተባለ ወንድም (ከጊዜ በኋላ ታማኝነቱን እንደጠበቀ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ሞቷል) ትኩረት በማይስብ መንገድ በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ የጥምቀት ጥያቄ ጠየቀኝ። ይህ ወንድም አምስት ጥያቄዎችን ከጠየቀኝ በኋላ የሰጠሁት መልስ ስላረካው አጠመቀኝ። ካቀረበልኝ ጥያቄዎች አንዱ “አንተ ልጅ፣ ጥምቀት ምን ማለት እንደሆነ ገብቶሃል?” የሚል ሲሆን ሌላው ጥያቄ ደግሞ እንዲህ የሚል ነበር:- “ጦርነት እየተካሄደ በመሆኑ፣ ታማኝ የምትሆነው ለሂትለር ነው ወይስ ለይሖዋ የሚለውን መወሰን እንዳለብህና የምታደርገው ውሳኔ ደግሞ ሕይወትህን ሊያሳጣህ እንደሚችል ታውቃለህ?” ያለምንም ማንገራገር “አዎን” ብዬ መለስኩ።

ስደት ጀመረ

ወንድም ኮንራድ ግራቦቪ እንዲህ ያለ ጥያቄ የጠየቀኝ ለምን ነበር? በ1939 የጀርመን ሠራዊት ፖላንድን ስለወረረ ከዚያ በኋላ እምነታችንና ታማኝነታችን ከባድ ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። በየቀኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መያዛቸውን፣ ከአገር መባረራቸውንና ወደ ወኅኒ ቤት ወይም ማጎሪያ ካምፕ መላካቸውን ስንሰማ ሁኔታዎቹ ይበልጥ አስጨናቂ ሆኑ። ብዙም ሳይቆይ እኛም ተመሳሳይ መከራ ገጠመን።

ናዚዎች፣ ወጣቱ ትውልድ የሂትለር መንግሥት ቀናተኛ ደጋፊ እንዲሆን ይፈልጉ ስለነበር እኔ ወንድሜና እህቶቼ በዚህ ረገድ ፈተና ገጠመን። አባቴና እናቴ ቮልክሊስት (የጀርመን ዜግነት ያላቸው ወይም እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ዝርዝር የያዘ ሰነድ) ላይ ለመፈረም በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት ተነፈጉ። አባቴ በኦሽቪትዝ ወደሚገኘው ማጎሪያ ካምፕ ተላከ። በየካቲት ወር 1944 እኔና ወንድሜ በግሮድኩቭ (ግሮትካው) ኒሳ አቅራቢያ ወደሚገኝ የጸባይ ማረሚያ ተቋም ተላክን፤ እህቶቻችን ደግሞ በኦፖል አቅራቢያ በቻርኖቮንሲ (ክሎስተብሩክ) ወደሚገኝ የካቶሊክ ገዳም ተወሰዱ። ባለ ሥልጣናቱ ወደዚያ የላኩን “የወላጆቻችን የተሳሳተ አመለካከት” እንደሆነ ያሰቡትን እምነታችንን ለማስተው ነበር። በዚህ ጊዜ እናታችን ብቻዋን ቤት ቀረች።

በጸባይ ማረሚያ ተቋሙ ግቢ ውስጥ የስዋስቲካ ምልክት ያለበት ባንዲራ ሲሰቀል ቀኝ እጃችንን አንስተን “ሃይል ሂትለር” በማለት ለባንዲራው ሰላምታ እንድንሰጥ እንታዘዝ ነበር። ይህ ከባድ የእምነት ፈተና ቢሆንም እኔም ሆንኩ በርናርድ አቋማችንን አላላላንም። በዚህም የተነሳ “አክብሮት የጎደለው ባሕርይ” አሳይታችኋል ተብለን በኃይል እንደበደብ ነበር። የኤስ ኤስ ወታደሮች ቅስማችንን ለመስበር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ውጤታማ ባለመሆኑ እንዲህ በማለት የመጨረሻ አማራጭ አቀረቡልን:- “ለጀርመን መንግሥት ታማኝ መሆናችሁን በሚያሳይ ሰነድ ላይ በመፈረም የቫርማክት [የጀርመን ሠራዊት] አባል መሆን ትችላላችሁ፤ አለዚያ ግን ወደ ማጎሪያ ካምፕ ትላካላችሁ።”

ነሐሴ 1944 ባለ ሥልጣናቱ ወደ ማጎሪያ ካምፕ እንድንላክ ሐሳብ ባቀረቡበት ወቅት እንዲህ ብለው ነበር:- “እነሱን ምንም ነገር እንዲያደርጉ ማሳመን የማይቻል ነው። ሰማዕት መሆናቸው ያስደስታቸዋል። ይህ የዓመጸኝነት አቋማቸው ለሌሎች ታራሚዎችም የሚያሰጋ ነው።” ሰማዕት የመሆን ፍላጎት ባይኖረኝም ለይሖዋ ታማኝ በመሆኔ የሚደርስብኝን ሥቃይ በድፍረትና በክብር መቀበሌ ያስደስተኝ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:41) የደረሰብኝን መከራ በምንም ዓይነት በራሴ ኃይል መቋቋም አልችልም ነበር። በሌላ በኩል ግን ወደ ይሖዋ ከልቤ መጸለዬ ወደ እርሱ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል፤ እርሱም አስተማማኝ ረዳት ሆኖልኛል።—ዕብራውያን 13:6

በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ

ብዙም ሳይቆይ በሳይሊዥያ ወደሚገኘው ግሮስ ሮዝን ማጎሪያ ካምፕ ተላክሁ። በዚያም የእስር ቤት ቁጥርና የይሖዋ ምሥክር መሆኔን የሚያሳይ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን ምልክት ተሰጠኝ። የኤስ ኤስ ወታደሮች፣ አንድ ነገር ለማድረግ ከተስማማሁ ከካምፑ መውጣት እንደምችል አልፎ ተርፎም በናዚ ሠራዊት ውስጥ ሥልጣን እንደሚሰጠኝ በመግለጽ ምርጫ አቀርቡልኝ። “የሂትለርን መንግሥት የሚቃወሙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አመለካከት መካድ አለብህ” አሉኝ። ከዚህ ጋር የሚወዳደር ምርጫ የቀረበለት ሌላ እስረኛ አልነበረም። ከካምፑ የመውጣት አጋጣሚ የተሰጣቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። ያም ቢሆን ግን በሺዎች እንደሚቆጠሩ ሌሎች ወንድሞች ሁሉ እኔም የተሰጠኝን “መብት” ፈጽሞ እንደማልቀበለው ገለጽኩላቸው። ጠባቂዎቹም “የሬሳ ማቃጠያውን ቤት ጭስ ማውጫ በደንብ ተመልከተው። የቀረበልህን ምርጫ በቁም ነገር ብታስብበት ይሻልሃል፤ አለዚያ ነፃ የምትወጣው በዚያ ጭስ ማውጫ በኩል ይሆናል” አሉኝ። ምርጫውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን በቆራጥነት በድጋሚ ነገርኳቸው፤ በዚህ ወቅት “ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም” ውስጤን ሞላው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

በካምፑ ውስጥ የእምነት ባልንጀሮቼን እንዳገኝ የጸለይኩ ሲሆን ይሖዋም ጸሎቴን ሰማኝ። ካገኘኋቸው የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ወንድም ጉስታፍ ባውመርት ሲሆን ይህ ወንድም በደግነትና በፍቅር ይንከባከበኝ ነበር። በእርግጥም ይሖዋ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ሆኖልኛል።—2 ቆሮንቶስ 1:3

ከጥቂት ወራት በኋላ የሩሲያ ወታደሮች እየተቃረቡ በመምጣታቸው ናዚዎች ካምፑን በፍጥነት ለቀው ለመውጣት ተገደዱ። ለመሄድ እየተዘጋጀን እያለ ወንድሞች፣ ሕይወታችንን አደጋ ላይ ጥለን ወደ ሴቶቹ እስር ቤት ለመሄድና ወደ 20 የሚጠጉ መንፈሳዊ እህቶቻችንን ሁኔታ ለማየት ወሰንን። ከእነዚህ እህቶች መካከል ኤልዛ አፕት እና ጌርትሩት ኦት ይገኙበታል። b እህቶች እኛን ሲያዩ በፍጥነት መጡ፤ ጥቂት የሚያበረታቱ ሐሳቦች ከተለዋወጥን በኋላ “ታማኝ የሆነ፣ ደፋር የሆነ፣ አይረታም በፍርሃት” የሚሉትን ቃላት የያዘውን መዝሙር ዘመሩ። c ሁላችንም ዓይናችን እንባ አቅርሮ ነበር!

ወደ ቀጣዩ ካምፕ ተዛወርን

ናዚዎች ከ100 እስከ 150 የምንሆን እስረኞችን በከሰል መጫኛ ባቡር ፉርጎዎች ውስጥ አጨቁን፤ ምግብና ውኃ ያልነበረን ከመሆኑም በላይ ዝናብ ስለሚጥል ከፍተኛ ቅዝቃዜና ውርጭ ነበር። በውኃ ጥም ከመቃጠላችንም በተጨማሪ በትኩሳት እንሠቃይ ነበር። የታመሙና የደከሙ እስረኞች ተዝለፍልፈው እየወደቁ ሲሞቱ በፉርጎዎቹ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ቁጥር እያነሰ ሄደ። እግሮቼና መገጣጠሚያዎቼ በጣም ስላበጡ መቆም አቃተኝ። ለአሥር ቀናት ከተጓዝን በኋላ በሕይወት የተረፍነው በጣት የምንቆጠር እስረኞች ሚትልባው ዶራ ወደተባለው የቅጣት ካምፕ ደረስን፤ ይህ ካምፕ የሚገኘው በዋይመር፣ ቱሪንጂ አቅራቢያ ባለው በኖርትሃውዘን ከተማ ውስጥ ነው። የሚገርመው በዚህ አሰቃቂ ጉዞ ላይ አንድ ወንድም አልሞተም።

ጉዞው ካስከተለብኝ መጎሳቆል እንዳገገምኩ በካምፑ ውስጥ የተቅማጥ ወረርሽኝ በመግባቱ እኔና አንዳንድ ወንድሞች ታመምን። በካምፑ ውስጥ የሚሰጠንን ሾርባ ትተን ደረቅ ዳቦ ብቻ እንድንበላ ተነገረን። እንዲህ በማድረጌ ብዙም ሳይቆይ ተሻለኝ። በመጋቢት ወር 1945 የዚያ ዓመት ጥቅስ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው በማቴዎስ 28:19 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንደሆነ ሰማን። ብዙም ሳይቆይ ከካምፑ ወጥተን ምሥራቹን መስበካችንን እንደምንቀጥል ተሰምቶን ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአርማጌዶን እንደሚደመደም እናስብ ስለነበር ይህ ጥቅስ በደስታ እንድንሞላና ተስፋ እንዲኖረን አድርጎናል። ይሖዋ በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት በሚያስደንቅ መንገድ አበረታቶናል!

ከካምፖቹ ነፃ መውጣት

ሚያዝያ 1, 1945 የሕብረ ብሔሩ ጦር፣ የኤስ ኤስ ወታደሮችን ሠፈርና በአቅራቢያው የሚገኘውን እኛ የነበርንበትን ካምፕ በቦምብ ደበደበው። በዚህ ወቅት ብዙዎች የሞቱ ሲሆን በርካታ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በቀጣዩ ቀንም በቦምብ የተደበደብን ሲሆን በዚህ ጥቃት ወቅት የደረሰው ኃይለኛ ፍንዳታ አሽቀንጥሮ ጣለኝ።

በዚህ ወቅት ፍሪትዝ ኡልሪክ የተባለ አንድ ወንድም ሊረዳኝ መጣ። በሕይወት እንዳለሁ ተስፋ በማድረግ የፍርስራሽ ክምሩን በመቆፈር ጎትቶ አወጣኝ። ራሴን ሳውቅ ፊቴና ሰውነቴ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰብኝና መስማት እንደማልችል ተረዳሁ። የፍንዳታው ድምፅ የጆሬዬን ታምቡር ጎድቶት ነበር። ጆሮዬ እስኪድን ድረስ ለረጅም ዓመታት ተሠቃይቻለሁ።

በሺህ ከሚቆጥሩት እስረኞች መካከል ከዚህ የቦምብ ድብደባ የተረፉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከወንድሞቻችን አንዳንዶቹ የሞቱ ሲሆን ከእነሱ መካከል የተወደደው ወንድማችን ጉስታፍ ባውመርት ይገኝበታል። በሰውነቴ ላይ ያለው ቁስል ማመርቀዝ ስለጀመረ ኃይለኛ ትኩሳት ያዘኝ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የሕብረ ብሔሩ ጦር አገኘንና ነፃ ወጣን። በዚህ መሃል የሞቱ ወይም የተገደሉ እስረኞች አስከሬን የታይፈስ ወረርሽኝ እንዲነሳ አደረገ። እኔም ይህ በሽታ ስለያዘኝ ከሌሎች ሕመምተኞች ጋር ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ። ሐኪሞቹ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የተረፍነው ሦስት ብቻ ነበርን። በእነዚህ የመከራ ወቅቶች ይሖዋ በታማኝነት እንድጸና ስላበረታኝ በጣም አመሰግነዋለሁ! ይሖዋ ‘ከሞት ጥላ’ ስላተረፈኝም እጅግ አመሰግነዋለሁ።—መዝሙር 23:4

በመጨረሻ ወደ ቤት ተመለስኩ!

ጀርመኖች ከተሸነፉ በኋላ ወዲያው ወደ ቤቴ የምመለስ መስሎኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ካሰብኩት በላይ አስቸጋሪ ሆነብኝ። ካቶሊክ አክሽን የተባለ ንቅናቄ አባላት የነበሩ የቀድሞ እስረኞች ስላወቁኝ “ግደሉት!” ብለው እየጮሁ መሬት ላይ ጥለው ረጋገጡኝ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ደርሶ ከእነዚህ ጨካኞች አስጣለኝ፤ ሆኖም ሰውነቴ በመቁሰሉና ታይፈሱ አቅም አሳጥቶኝ ስለነበር ለማገገም ረጅም ጊዜ ፈጀብኝ። በመጨረሻ ግን ወደ ቤት መመለስ ቻልኩ። ከቤተሰቤ ጋር በመገናኘቴ በጣም ተደስቼ ነበር! እንደሞትኩ አስበው ስለነበር ሁሉም ሲያዩኝ በጣም ተደሰቱ።

ብዙም ሳይቆይ የስብከቱን ሥራ የቀጠልን ሲሆን እውነትን የተጠሙ በርካታ ቅን ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። እኔም ለጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማድረስ ኃላፊነት ተሰጠኝ። እኔና ሌሎች ወንድሞች ከጀርመን ቅንርጫፍ ቢሮ ተወካዮች ጋር በዋይመር ተገናኝተን ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተሙትን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ወደ ፖላንድ የመውሰድ ልዩ መብት አግኝተን ነበር። እነዚህ ጽሑፎች ወዲያውኑ ከተተረጎሙ በኋላ ስቴንስል ተዘጋጅቶ መጠበቂያ ግንቦች ታተሙ። በሎድዝ የሚገኘው ቢሯችን በፖላንድ የሚከናወነውን ሥራ ሙሉ በሙሉ መከታተል ሲጀምር ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቋሚነት ማግኘት ጀመሩ። እኔም ሰፊ በሆነው የሳይሊዥያ ክልል ልዩ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ በዚያን ጊዜ አብዛኛው የሳይሊዥያ ክፍል የፖላንድ ግዛት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በፖላንድ አዲስ በተቋቋመው የኮሚኒስት አገዛዝ እንደገና ስደት ደረሰብን። በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ የተነሳ በ1948 የሁለት ዓመት እስራት ተበየነብኝ። በወኅኒ ቤት እያልሁ በርካታ እስረኞች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ መርዳት ችዬ ነበር። ከእነዚህ እስረኞች አንዱ ከእውነት ጎን የቆመ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠምቋል።

በ1952 ለዩናይትድ ስቴትስ ትሰልላለህ በሚል ክስ እንደገና ታሰርኩ! ፍርዴን እየተጠባበቅሁ እያለ በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ታስሬ ቀንና ሌሊት ምርመራ ይደረግብኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በዚህ ጊዜም ከአሳዳጆቼ እጅ ያዳነኝ ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት እንዲህ ዓይነት ምርመራ አልተደረገብኝም፤ እንዲሁም ከሌሎች እስረኞች ተነጥዬ ለብቻዬ አልታሰርኩም።

ለመጽናት የረዱኝ ነገሮች

እነዚያን በመከራና በችግር የተሞሉ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ያበረታቱኝን አንዳንድ ዋና ዋና ነጥቦች መጥቀስ እችላለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለመጽናት የረዳኝን ጥንካሬ ያገኘሁት ከይሖዋና ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ወደሆነው ወደ ይሖዋ ዘወትር ከልብ የመነጨ ልመና ማቅረብና ቃሉን በየዕለቱ ማጥናት፣ እኔንም ሆነ ሌሎችን በመንፈሳዊ ሕያው ሆነን እንድንቀጥል ረድቶናል። በእጅ የተገለበጡ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችም እምነታችንን የሚያጠናክር መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ አስችለውናል። በማጎሪያ ካምፖቹ ውስጥ፣ ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛና ዝግጁ የነበሩ አሳቢ የእምነት ባልንጀሮቼም ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።

ከይሖዋ ያገኘኋት ሌላዋ በረከት ደግሞ ባለቤቴ ማሪያ ነበረች። በጥቅምት ወር 1950 የተጋባን ሲሆን ሃሊና የተባለች ሴት ልጅ ወለድን፤ እሷም ይሖዋን የምትወድ የአምላክ አገልጋይ ናት። እኔና ማሪያ በትዳር ዓለም 35 ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ማሪያ ለረጅም ጊዜ ሲያሠቃያት በነበረ ሕመም የተነሳ ሞተች። የማሪያ ሞት ለከፍተኛ ሐዘንና ሥቃይ ዳርጎኛል። ለተወሰነ ጊዜ ‘እንደተጣልኩ’ ተሰምቶኝ የነበረ ቢሆንም ‘አልጠፋሁም።’ (2 ቆሮንቶስ 4:9) በታማኝነት ይሖዋን እያገለገሉ ያሉት ልጄ፣ ባለቤቷና የልጅ ልጆቼ በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ድጋፍ ሰጥተውኛል።

ከ1990 ጀምሮ በፖላንድ በሚገኘው ቅንርጫፍ ቢሮ ውስጥ እያገለገልኩ ነው። በየዕለቱ ግሩም ከሆነው የቤቴል ቤተሰብ ጋር መገናኘት ታላቅ በረከት ነው። ከጊዜ ወደጊዜ ጤናዬ እያሽቆለቆለ በመሄዱ አንዳንድ ጊዜ ክንፏን እንደተመታች ወፍ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ያም ቢሆን ግን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እጠባበቃለሁ፤ እስከዛሬም ድረስ ‘ቸርነቱ ስለበዛልኝ ለይሖዋ እዘምራለሁ።’ (መዝሙር 13:6) ረዳቴ የሆነው ይሖዋ፣ የሰይጣን የጭቆና አገዛዝ ያስከተለውን ማንኛውንም ጉዳት የሚያስተካክልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የጥር 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 አንቀጽ 6ን ተመልከት።

b በሚያዝያ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 12-15 ላይ የወጣውን የኤልዛ አፕትን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

c ይህ መዝሙር በ1928 በይሖዋ ምሥክሮች ተዘጋጅቶ በወጣው ይሖዋን የሚያወድሱ መዝሙሮች በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ መዝሙር ቁጥር 101 ሲሆን አሁን በእጃችን ባለው መዝሙር መጽሐፍ ላይ ደግሞ ቁጥር 56 ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማጎሪያ ካምፑ ውስጥ ይህ የእስረኛ ቁጥርና ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን ምልክት ተሰጠኝ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1980 ከባለቤቴ ከማሪያ ጋር