በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎችን የማመስገንን አስፈላጊነት መገንዘብ

ሌሎችን የማመስገንን አስፈላጊነት መገንዘብ

ሌሎችን የማመስገንን አስፈላጊነት መገንዘብ

አንድ ሰው፣ አለቃው ብዙም እንደማያመሰግነው ሲናገር ሰምተህ ታውቃለህ? አንተ ራስህስ እንዲህ ዓይነት ቅሬታ አድሮብህ ያውቃል? ወጣት ልጅ ከሆንክ ደግሞ ወላጆህ ወይም አስተማሪዎችህ እንደማያመሰግኑህ ተሰምቶህ ያውቃል?

እነዚህን ቅሬታዎች ከሚያሰሙት ሰዎች አንዳንዶቹ በቂ ምክንያት ይኖራቸው ይሆናል። ሆኖም አንድ ጀርመናዊ ምሑር እንደተናገሩት እንዲህ ያለ ቅሬታ የሚያሰሙ ሠራተኞች ይበልጥ የሚያበሳጫቸው ነገር ምስጋና አለማግኘታቸው ሳይሆን አለቃቸው በግለሰብ ደረጃ የማያስብላቸው መሆኑ ነው። ያም ሆነ ይህ አንድ የጎደለ ነገር እንዳለ ግልጽ ነው። ከሰዎች ጋር አስደሳች ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ማመስገን እና በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው።

ከአምልኮ ጋር በተያያዘም ይህ አስፈላጊ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ የሚታወቀው አመስጋኝ በመሆን፣ ወዳጅነት በማሳየት እንዲሁም እርስ በርስ በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል። የጉባኤው አባላት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በመከተል በጉባኤ ውስጥ ሁልጊዜ ይህን የመሰለ ግሩም ሁኔታ እንዲኖር ጥረት ያደርጋሉ። ጉባኤያችን ምንም ያህል ፍቅር የሰፈነበት ቢሆንም እንኳ ሁልጊዜ ማሻሻያ ማድረግ ይቻላል። ይህን በአእምሯችን ይዘን አመስጋኝ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን ሦስት ግለሰቦችን እንመልከት:- እነርሱም ከክርስትና በፊት የነበረው ኤሊሁ የተባለ የአምላክ አገልጋይ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ናቸው።

ትሕትናና አክብሮት የተንጸባረቀበት ምክር

የአብርሃም የሩቅ ዘመድ እንደሆነ የሚገመተው ኤሊሁ፣ ኢዮብ ከአምላክ ጋር ስላለው ግንኙነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ኤሊሁ ትሑትና ሰው አክባሪ ነበር። ለመናገር አጋጣሚ እስኪያገኝ ድረስ በትዕግሥት ጠብቋል። ከዚህም በላይ የኢዮብ ወዳጅ ነን ያሉት ሰዎች የኢዮብን ድክመቶች ብቻ ሲናገሩ ኤሊሁ ግን ምክር ከመስጠት በተጨማሪ ቀና አካሄድ በመከተሉ ኢዮብን አመስግኖታል። ኤሊሁ ይህን ያደረገው ወዳጅነትና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ኢዮብን በማናገር እንዲሁም ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በስሙ በመጥራት ነው። “ኢዮብ ሆይ፣ ንግግሬን ስማ፤ የምለውንም ሁሉ አድምጥ [“እንድታደምጥ እለምንሃለሁ፣” የ1954 ትርጉም]” በማለት በትሕትና ጠይቆታል። ራሱን በኢዮብ ቦታ በማስቀመጥ “በእግዚአብሔር ፊት እኔም እንዳንተው ነኝ፤ የተፈጠርሁትም ደግሞ ከዐፈር ነው” ሲል በአክብሮት ተናግሮታል። አክሎም “የምትለው ካለህ፣ መልስ ስጠኝ፤ ትክክለኛነትህንም ማወቅ እፈልጋለሁና [“በጽድቅህ ደስ ተሰኝቻለሁና፣” NW] ተናገር” በማለት አመስግኖታል።—ኢዮብ 33:1, 6, 32

ሌሎችን በትሕትናና በአክብሮት መያዝ አመስጋኝ መሆናችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው። እንዲህ ስናደርግ፣ የምናነጋግረውን ሰው ‘ትኩረት ልሰጥህና ላከብርህ እንደሚገባ ይሰማኛል’ ብለን የነገርነው ያህል ነው። በዚህ መንገድ የወዳጅነት መንፈስ እንዳለንና በግለሰብ ደረጃ እንደምናስብለት እናሳያለን።

ትሑት መሆን ሲባል ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ ማለት ብቻ አይደለም። የሌሎችን ልብ ለመንካት፣ የምናሳየው ትሕትና እውነተኛና ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባል። እንዲሁም ከልብ እንደምናስብላቸውና እንደምንወዳቸው የሚያሳይ መሆን አለበት።

ሌሎችን ማመስገን ዘዴኛ መሆናችንን ያሳያል

ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎችን በማመስገን ዘዴኛ መሆናችንን ማሳየት እንደምንችል ጠቁሟል። ለአብነት ያህል፣ በሁለተኛው የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በአቴና እየሰበከ ሳለ ለአንዳንድ ግሪካውያን ፈላስፎች ስለ ክርስትና ማስረዳት ነበረበት። ይህንን ከባድ ተልእኮ እንዴት በዘዴ እንደተወጣው እንመልከት። “ከኤፊቆሮስና ከኢስጦኢክ የፍልስፍና ወገን የሆኑትም ወደ እርሱ መጥተው ይከራከሩት ነበር። አንዳንዶቹ፣ ‘ይህ ለፍላፊ ምን ለማለት ይፈልጋል?’ ይሉ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ . . . ‘ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል’ አሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:18) ሰዎቹ እንዲህ የመሰሉ አስተያየቶችን ቢሰነዝሩም ጳውሎስ በተረጋጋ መንፈስ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ” በማለት መለሰላቸው። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ጣዖት አምላኪ በመሆናቸው ከመንቀፍ ይልቅ ሃይማኖተኛ ስለሆኑ አመስግኗቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:22

ጳውሎስ ይህን ሲል ግብዝ መሆኑ ነበር? በፍጹም አይደለም። በአድማጮቹ ላይ መፍረድ የእሱ ኃላፊነት እንዳልሆነ እንዲሁም እሱ ራሱ በአንድ ወቅት እውነትን የማያውቅ ሰው እንደነበረ ተገንዝቦ ነበር። የእሱ ኃላፊነት የአምላክን መልእክት መስበክ እንጂ በሰዎች ላይ መፍረድ አልነበረም። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ያስተዋሉትን እውነታ እሱም ከራሱ ተሞክሮ መገንዘብ ችሎ ነበር:- በቅንነት የሐሰት ሃይማኖትን ደግፈው የሚከራከሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከጊዜ በኋላ እውነተኛውን ሃይማኖት አጥብቀው ሊይዙ ይችላሉ።

ጳውሎስ የተጠቀመበት ዘዴ ውጤታማ በመሆኑ መልካም ፍሬ አስገኝቶለታል። “አንዳንድ ሰዎች ግን ጳውሎስ ባለው በመስማማት ተከተሉት፤ አመኑም፤ ከእነዚህም ዲዮናስዮስ የተባለው የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት አባል፣ ደማሪስ የተባለች ሴትና ሌሎችም ሰዎች ነበሩ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:34) የአቴና ሰዎች የሐሰት አማልክትን ቢያመልኩም እንኳ ጳውሎስ እውነተኛ እውቀት ስለሌላቸው እነዚህን ሰዎች ከመንቀፍ ይልቅ ቅን ልቦና ያላቸው በመሆናቸው እነሱን ማመስገኑ የጥበብ እርምጃ ነበር! ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ በማግኘታቸው የተሳሳተ ጎዳና የሚከተሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ልብ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ጳውሎስ፣ በዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ፊት የመከላከያ መልስ እንዲያቀርብ በተጠየቀ ጊዜም በዘዴ ተጠቅሟል። ሄሮድስ ከእህቱ ከበርኒቄ ጋር የጾታ ብልግና ይፈጽም እንደነበር ይታወቃል፤ ይህ ደግሞ የአምላክ ቃል በግልጽ የሚያወግዘው ድርጊት ነበር። ያም ቢሆን ጳውሎስ ሄሮድስን አላወገዘውም። ከዚህ ይልቅ ሄሮድስ ሊመሰገንበት የሚገባውን ምክንያት በመፈለግ እንዲህ አለው:- “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤ ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 26:1-3

እኛም ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ እንዲህ ማድረጋችን የጥበብ ኣካሄድ ነው። ጎረቤቶቻችንን፣ አብረውን የሚማሩትን ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦቻችንን ማመስገን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ እነሱም መልካም ባሕርይ እንዲያሳዩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ምስጋና የሚገባቸውን ሰዎች በማመስገን ልባቸውን መንካት የምንችል ሲሆን እንዲህ በማድረግም አንዳንድ ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የተሳሳተ አመለካከታቸውንና ድርጊታቸውን ትተው ከትክክለኛው እውቀት ጋር የሚስማማ አካሄድ እንዲከተሉ ልናበረታታቸው እንችል ይሆናል።

ኢየሱስ አመስጋኝ በመሆን ረገድ የተወው ግሩም ምሳሌ

ኢየሱስ ሰዎችን ያመሰግን ነበር። ለአብነት ያህል፣ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የአምላክን መመሪያ በመከተል በትንሿ እስያ ለሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች በዮሐንስ አማካኝነት መልእክት ልኮ ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምስጋና የሚገባቸውን ሳያመሰግናቸው አላለፈም። በኤፌሶን፣ በጴርጋሞንና በትያጥሮን የነበሩትን ጉባኤዎች እንዲህ በማለት አመስግኗቸዋል:- “ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው . . . ዐውቃለሁ”፤ “ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል። . . . በእኔ ያለህን እምነት አልካድህም” እንዲሁም “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስ፣ ጠንከር ያለ ምክር ያስፈልገው በነበረው በሰርዴስ ጉባኤም እንኳ ሊመሰገኑ ለሚገባቸው አንዳንድ ግለሰቦች ትኩረት በመስጠት እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን ልብሳቸውን ያላሳደፉ ጥቂት ሰዎች በሰርዴስ ከአንተ ጋር አሉ፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።” (ራእይ 2:2, 13, 19፤ 3:4) ኢየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በጥቂቶች ስህተት የተነሳ አንድን ቡድን በአጠቃላይ መንቀፍ የለብንም፤ ወይም ደግሞ ሰዎች ሊመሰገኑበት የሚገባውን ነጥብ ሳናነሳ ምክር መስጠት አይኖርብንም። ይሁን እንጂ ሰዎችን የምናመሰግነው ምክር ልንሰጥ ስናስብ ብቻ ከሆነ ምስጋናችን ተሰሚነት ላያገኝ እንደሚችል ማስታወሳችን ጥሩ ነው። በተቻለ መጠን ሌሎችን ከማመስገን ወደኋላ አንበል! እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሌላ ጊዜ ምክር መስጠት ቢያስፈልገን የምንሰጠው ምክር በቀላሉ ተቀባይነት ያገኛል።

ተገቢውን ምስጋና የሚሰጡ ሽማግሌዎች

በአንድ የአውሮፓ አገር ውስጥ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የምታገለግለው ኮርኔሊያ የተባለች ክርስቲያን፣ በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች፣ በግል ጥናትና መጽሔቶችን በማንበብ ረገድ ምን ዓይነት ልማድ እንዳላት ጠይቋት እንደነበር ታስታውሳለች። ኮርኔሊያ “በዚህ ወቅት ኃፍረት ተሰማኝ” በማለት ተናግራለች፤ ያም ቢሆን መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ሁሉንም ርዕሶች እንደማታነብ ነገረችው። “ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ይህን ባለማድረጌ ምክር ከመስጠት ይልቅ የቻልኩትን ያህል በማንበቤ አመሰገነኝ። እንዲህ ማድረጉ በጣም ስላበረታታኝ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እያንዳንዱን ርዕስ ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ።”

በአውሮፓ በሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉት ሬይ፣ የአቅኚነት አገልግሎት የጀመሩበትን ቀን አይረሱትም። ሰብዓዊ ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ በርካታ መብቶች ያሉት የጉባኤው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች፣ በዚያን ቀን ማታ ልክ ወደ መንግሥት አዳራሹ እንደገባ በቀጥታ ወደ ሬይ በመሄድ “በአቅኚነት ያሳለፍከው የመጀመሪያ ቀን እንዴት ነበር?” በማለት ጠየቀው። ይህ ከሆነ ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ወንድም ሬይ የዚያን ሽማግሌ አሳቢነት እስካሁን ያስታውሱታል።

እነዚህ ሁለት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ሌሎች ላደረጉት ነገር ካንገት በላይ በሆነ ንግግር ወይም በሽንገላ ቃላት ሳይሆን ከልብ በመነጨና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አድናቆታችንን ከገለጽንላቸው ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንድናመሰግን የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉን። ለአብነት ያህል፣ ይሖዋን ለማገልገል ፍላጎት ስላላቸው፣ ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው ሐሳቦች ስለሚሰጡ፣ ፍርሃታቸውን አሸንፈው በስብስባዎች ላይ ንግግር ወይም ክፍል ለማቅረብ ጥረት ስለሚያደርጉ፣ በቅንዓት ስለሚሰብኩና ስለሚያስተምሩ ብሎም ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ እንቅስቃሴዎችና ለመንፈሳዊ ግቦች ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት ስለሚያደርጉ ሊመሰገኑ ይገባል። እኛም ሌሎችን ስናመሰግን እንባረካለን። እንዲሁም ደስተኞች እንድንሆንና አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ የጉባኤውን አባላት ለሚያከናውኑት መልካም ተግባር ሊያመሰግኗቸው ይገባል። ምክር መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይህን ሊያደርጉ ይገባል። በሌላ በኩል ግን ሁሉም ነገር ፍጹም ትክክል በሆነ መንገድ እንዲሠራ በመጠበቅ ትንንሽ ስህተቶችን እንደ ከባድ ድክመት የመመልከት ዝንባሌ እንዳይኖራቸው ይጠነቀቃሉ።

እንደ ኤሊሁ ሰው አክባሪና አፍቃሪ፣ እንደ ጳውሎስ ዘዴኛ የሆኑ እንዲሁም እንደ ኢየሱስ ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳዩ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለወንድሞቻቸው እውነተኛ የብርታት ምንጭ ይሆናሉ። ሰዎችን ማመስገናችን የበለጠ እንዲሠሩ የሚያበረታታቸው ከመሆኑም በላይ እኛ ራሳችን ከሌሎች ጋር አስደሳች ግንኙነት እንዲኖረንና ተስማምተን መኖር እንድንችል ያደርጋል። ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት በሰማይ የሚኖረው አባቱ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ ሲያመሰግነው ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል አስበው! (ማርቆስ 1:11) ወንድሞቻችንን ከልብ በመነጨ ስሜት በማመስገን የደስታ ምንጭ እንሁንላቸው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ዘዴኛ መሆኑ ጥሩ ውጤት አስገኝቶለታል፤ እኛም እንዲህ በማድረግ ተመሳሳይ ውጤት ልናገኝ እንችላለን

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልብ የመነጨ ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማመስገን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል