በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው

“የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።”—1 ቆሮንቶስ 16:14

1. ወላጆች ልጅ ሲወልዱ ምን ይሰማቸዋል?

 ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ከሚደሰቱባቸው ወቅቶች አንዱ ልጅ ወልደው ያቀፉበት ጊዜ ነው ቢባል አብዛኞቹ ወላጆች ይስማማሉ። አሊያ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “እንደወለድኩ ልጄን ሳያት በጣም ተደስቼ ነበር፤ እስከ ዛሬ ድረስ ካየኋቸው ሕፃናት ሁሉ በጣም ቆንጆ እንደሆነች አሰብኩ።” ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አስደሳች ወቅት ለወላጆች ጭንቀትም ሊፈጥር ይችላል። የአሊያ ባለቤት “ልጄ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እንድትወጣ ላዘጋጃት መቻሌ አሳስቦኝ ነበር” ብሏል። በርካታ ወላጆች እንዲህ የሚሰማቸው ሲሆን ልጆቻቸውን በፍቅር ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነም ይገነዘባሉ። ይሁንና ልጆቻቸውን በፍቅር ለማሠልጠን የሚፈልጉ ወላጆች ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ከእነዚህ ችግሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

2. ወላጆች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

2 የምንኖረው የዚህ ሥርዓት ማብቂያ በጣም በተቃረበበት ጊዜ ውስጥ ነው። አስቀድሞ እንደተነገረው ባለንበት ኅብረተሰብ ውስጥ ፍቅር ጠፍቷል። ሰዎች ለቤተሰባቸው አባላት እንኳ “ፍቅር የሌላቸው” እንዲሁም “የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው [“ታማኝነት የጎደላቸው፣” NW]፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ አባላት እንዲህ ዓይነት ባሕርያት ከሚያንጸባርቁ ሰዎች ጋር በየዕለቱ መገናኘታቸው እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ፍጹማን ባለመሆናቸው ራሳቸውን ለመቆጣጠር፣ ሳያስቡት ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ላለመናገር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ማስተዋል የጎደለው እርምጃ ላለመውሰድ ከራሳቸው ጋር ይታገላሉ።—ሮሜ 3:23፤ ያዕቆብ 3:2, 8, 9

3. ወላጆች ልጆቻቸው ደስተኞች ሆነው እንዲያድጉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ወላጆች እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ልጆቻቸው ደስተኞችና በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ መርዳት ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? “የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል ነው። (1 ቆሮንቶስ 16:14) በእርግጥም ፍቅር ‘በፍጹም አንድነት ያስተሳስራል።’ (ቈላስይስ 3:14) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ፍቅር የሚገለጽባቸውን ሦስት መንገዶች አብራርቷል፤ እነዚህን ሦስት መንገዶች እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሠለጥኑ ፍቅርን ማሳየት የሚችሉባቸውን አንዳንድ መስኮች እንመልከት።—1 ቆሮንቶስ 13:4-8

ወላጆች ታጋሽ መሆን ያስፈልጋቸዋል

4. ወላጆች ታጋሽ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር ታጋሽ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) “ታጋሽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መቻልንና ቶሎ አለመቆጣትን ያመለክታል። ወላጆች ታጋሽ መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ ወላጆች ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት። አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የፈለጉትን ለማግኘት አንድ ጊዜ ብቻ በመጠየቅ አያቆሙም። አንድ ወላጅ፣ ልጁ የፈለገው ነገር እንደማይፈቀድለት ጠንከር አድርጎ ቢነግረውም ልጁ እንደሚፈቀድለት ተስፋ በማድረግ ደግሞ ደጋግሞ ይጠይቃል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች የተከለከሉት ነገር እንዲፈቀድላቸው ከወላጆቻቸው ጋር ሙግት ይገጥሙ ይሆናል፤ ወላጆች ደግሞ ልጆቹ ሊያደርጉት የፈለጉት ነገር የሞኝነት አካሄድ እንደሆነ ስለሚያውቁ አይፈቅዱላቸውም። (ምሳሌ 22:15) ከዚህም በላይ ልጆችም እንደ እኛ በተደጋጋሚ ይሳሳታሉ።—መዝሙር 130:3

5. ወላጆች ታጋሽ እንዲሆኑ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

5 ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ታጋሽና ቻይ ለመሆን ምን ሊረዳቸው ይችላል? ንጉሥ ሰሎሞን “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች” ብሏል። (ምሳሌ 19:11) ወላጆች፣ እነሱ ራሳቸው በአንድ ወቅት ‘እንደ ልጅ ይናገሩ፣ እንደ ልጅ ያስቡ እንዲሁም እንደ ልጅ ያሰሉ’ እንደነበር ማስታወሳቸው የልጆቻቸውን ባሕርይ ለመረዳት ያስችላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ወላጆች፣ እናንተም ልጆች በነበራችሁበት ጊዜ አንድ የማይሆን ነገር ለማድረግ ፈልጋችሁ እናታችሁ ወይም አባታችሁ እንዲፈቅዱላችሁ በመወትወት ያስቸገራችሁበትን ወቅት ታስታውሳላችሁ? በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበራችሁበት ጊዜ ወላጆቻችሁ ስሜታችሁን ወይም ችግራችሁን እንደማይረዱላችሁ ይሰማችሁ ነበር? ይህ ከሆነ ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ የሚያሳዩት ለምን እንደሆነ እንዲሁም ያደረጋችሁትን ውሳኔ እንዲያስታውሱ በትዕግሥት ዘወትር መርዳት የሚያስፈልግበትን ምክንያት መገንዘብ ትችላላችሁ። (ቈላስይስ 4:6) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወላጆች ለልጆቻቸው የእሱን ሕግጋት ‘እንዲያስጠኗቸው’ መናገሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ዘዳግም 6:6, 7) ‘ማስጠናት’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መደጋገም፣” “ደግሞ ደጋግሞ መናገር” እንዲሁም “መቅረጽ” የሚል ትርጉም አለው። ይህም ወላጆች ልጃቸው የአምላክን ሕግጋት እንዲታዘዝ ለማስተማር ደግመው ደጋግመው መናገር እንዳለባቸው ያሳያል። በተመሳሳይም በሕይወት ውስጥ የሚያስፈልጓቸውን ሌሎች ትምህርቶች ለማስተማር አብዛኛውን ጊዜ ደጋግሞ መናገር አስፈላጊ ነው።

6. አንድ ወላጅ ታጋሽ ይሆናል ሲባል ልጁን መረን ይለቀዋል ማለት ያልሆነው ለምንድን ነው?

6 አንድ ወላጅ ታጋሽ ይሆናል ሲባል ግን ልጁ፣ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች ሲያደርግ በቸልታ ይመለከተዋል ማለት አይደለም። የአምላክ ቃል “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል” ይላል። ይኸው ጥቅስ ልጆች እንዲህ እንዳይሆኑ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ሲገልጽ “የተግሣጽ በትር ጥበብን ታጐናጽፋለች” ብሏል። (ምሳሌ 29:15) አንዳንድ ጊዜ ልጆች፣ ወላጆቻቸው እነሱን የመቅጣት ሥልጣን እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም የክርስቲያኖች ቤተሰብ የሚመራው በዲሞክራሲያዊ መንገድ መሆን የለበትም፤ ወላጆች ልጆቹ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ የሚያወጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረው ልጆቹ ስለተስማሙበት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ የሁሉም ራስ የሆነው ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በፍቅር እንዲያሠለጥኗቸውና እንዲገሥጿቸው ሥልጣን ስለሰጣቸው ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 3:15፤ 6:1-4) እንዲያውም ተግሣጽ ጳውሎስ ቀጥሎ ከጠቀሰው የፍቅር መግለጫ ጋር የተያያዘ ነው።

በፍቅር ተግሣጽ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?

7. ልጆቻቸውን የሚወዱ ወላጆች በደግነት የሚገሥጿቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱ ተግሣጽ ምን ነገሮችን ያካትታል?

7 ጳውሎስ “ፍቅር ደግ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4 የ1980 ትርጉም) ልጆቻቸውን ከልባቸው የሚወዱ ወላጆች፣ ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ለልጆቻቸው ተግሣጽ ይሰጧቸዋል። ይህን በማድረግም ይሖዋን ይመስላሉ። ጳውሎስ፣ ይሖዋ “የሚወደውን ይገሥጻል” በማለት ጽፏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ተግሣጽ፣ ቅጣትን ብቻ እንደማያመለክት ልብ ማለት ያስፈልጋል። ማሠልጠንንና ትምህርት መስጠትንም ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ ተግሣጽ ዓላማው ምንድን ነው? ጳውሎስ ተግሣጽ “ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 12:6, 11) ወላጆች ልጆቻቸውን በአምላክ ፈቃድ መሠረት በደግነት የሚያሠለጥኗቸው ከሆነ ልጆቹ ሲያድጉ ሰላማዊና ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ አዋቂዎች እንዲሆኑ እየረዷቸው ነው ማለት ይቻላል። ልጆች “የእግዚአብሔርን ተግሣጽ” ከተቀበሉ ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል የሚያገኙ ሲሆን እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከብር ወይም ከወርቅ እጅግ የሚበልጥ ዋጋ አላቸው።—ምሳሌ 3:11-18

8. ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሣጽ አለመስጠታቸው በአብዛኛው ምን ያስከትላል?

8 በሌላ በኩል ግን ልጆችን አለመገሠጽ ደግነት አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል።” (ምሳሌ 13:24) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ተግሣጽ ሳይሰጣቸው ያደጉ ልጆች ራስ ወዳድና ደስታ የራቃቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ወላጆቻቸው ደግ ቢሆኑም ጥብቅ ገደቦችን የሚያወጡላቸው ልጆች በትምህርት ቤት ጎበዝ ተማሪዎች ይሆናሉ፤ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት የሚኖራቸው ከመሆኑም በላይ በአብዛኛው ደስተኞች ናቸው። እንግዲያው ልጆቻቸውን በደግነት የሚገሥጹ ወላጆች ከልባቸው እንደሚወዷቸው ያሳያሉ።

9. ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ምን ያስተምሯቸዋል? እነዚህን መመሪያዎችስ እንዴት ሊመለከቷቸው ይገባል?

9 ልጆችን በደግነትና በፍቅር መገሠጽ ምን ነገሮችን ይጨምራል? ወላጆች፣ ልጆቹ ምን እንደሚጠበቅባቸው በግልጽ ሊነግሯቸው ይገባል። ለአብነት ያህል፣ ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዲሁም ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች የመካፈልን አስፈላጊነት ተምረዋል። (ዘፀአት 20:12-17፤ ማቴዎስ 22:37-40፤ 28:19፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ልጆች እነዚህ ነገሮች ለድርድር የማይቀርቡ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

10, 11. ወላጆች ለቤተሰባቸው መመሪያዎች ሲያወጡ የልጆቻቸውን ፍላጎት ግምት ውስጥ የሚያስገቡት ለምን ሊሆን ይችላል?

10 አንዳንድ ጊዜ ግን ወላጆች ለቤተሰቡ መመሪያዎችን ሲያወጡ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ይፈልጉ ይሆናል። ወጣቶች የቤተሰቡን መመሪያዎች በተመለከተ በሚደረገው ውይይት ከተሳተፉ እነዚህን ደንቦች ለመታዘዝ ይነሳሱ ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸው በስንት ሰዓት ቤት መግባት እንዳለባቸው መወሰን ከፈለጉ ሰዓቱን መርጠው ለልጆቹ ያሳውቋቸው ይሆናል። አሊያም ደግሞ ልጆቹ በስንት ሰዓት ቤት ሊገቡ እንደሚፈልጉ ሐሳብ እንዲያቀርቡና ይህን ሰዓት የመረጡበትን ምክንያት እንዲናገሩ ሊፈቅዱላቸው ይችላሉ። ከዚያም ወላጆች፣ ልጆቻቸው ቤት እንዲገቡ የሚፈልጉበትን ሰዓትና ይህ ሰዓት ተገቢ ነው ያሉበትን ምክንያት ይነግሯቸዋል። በወላጆችና በልጆች መካከል የአመለካከት ልዩነት ቢኖር (ብዙውን ጊዜ መኖሩ አይቀርም) ወላጆች ምን ማድረግ አለባቸው? አንዳንድ ጊዜ ወላጆች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይወስኑ ይሆናል። ታዲያ ወላጆች እንዲህ ስላደረጉ ሥልጣናቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል ማለት ነው?

11 ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይሖዋ ከሎጥና ከቤተሰቡ ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ ሥልጣኑን ፍቅር በተንጸባረቀበት መንገድ እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት። መላእክቱ፣ ሎጥንና ሚስቱን እንዲሁም ልጆቹን ከሰዶም ካስወጧቸው በኋላ “ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለበለዚያ ትጠፋላችሁ” አሏቸው። ሆኖም ሎጥ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን” በማለት መለሰላቸው። ከዚያም “እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ” በማለት አማራጭ ሐሳብ አቀረበ። ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠው? “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 19:17-22) በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሥልጣኑን አሳልፎ መስጠቱ ነበር? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የሎጥን ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ደግነት ለማሳየት መርጧል። ወላጅ ከሆንክ ቤተሰቡ የሚመራባቸውን ደንቦች ስታወጣ የልጆቹን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት የምትችልበት ጊዜ አለ?

12. አንድ ልጅ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ምን ሊረዳው ይችላል?

12 እርግጥ ነው፣ ልጆች መመሪያዎቹን ብቻ ሳይሆን እነዚህን መመሪያዎች መጣስ የሚያስከትልባቸውን ቅጣትም ማወቅ ይኖርባቸዋል። ልጆቹ መመሪያዎቹን መጣስ ስለሚያስከትልባቸው ቅጣት ከወላጆቻቸው ጋር ከተነጋገሩና ሁኔታው ግልጽ ከሆነላቸው በኋላ ካጠፉ ሊቀጡ ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚቀጧቸው ሁልጊዜ እያስጠነቀቋቸው የማይቀጧቸው ከሆነ ፍቅር እያሳዩ ነው ሊባል አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል” ይላል። (መክብብ 8:11) እርግጥ ነው፣ አንድ ወላጅ ልጁን ላለማሳፈር ሲል ሌሎች ሰዎች ባሉበት ወይም በእኩዮቹ ፊት አይቀጣው ይሆናል። ሆኖም ልጆች፣ ወላጆቻቸው “አዎን” ካሉ አዎን፣ “አይደለም” ካሉ ደግሞ አይደለም ማለታቸው እንደሆነ ሲያውቁ፣ ይህ ቅጣት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳ ለወላጆቻቸው ያላቸው አክብሮትና ፍቅር ይጨምራል፤ እንዲሁም የመተማመን ስሜት ያድርባቸዋል።—ማቴዎስ 5:37

13, 14. ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በማሠልጠን ረገድ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ለልጆች የሚሰጣቸው ቅጣት ደግነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ቅጣቱም ሆነ ቅጣት የሚሰጥበት መንገድ የልጆቹን ሁኔታ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት። ፓም እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በተግሣጽ ረገድ የሁለቱ ልጆቻችን ሁኔታ የተለያየ ነው። ለአንዷ የሚሠራው ተግሣጽ ለሌላዋ አይሆንም።” ባለቤቷ ላሪ እንዲህ ብሏል:- “ትልቋ ልጃችን እልኸኛ ስለነበረች ጠንከር ያለ ተግሣጽ ካልተሰጣት በቀር አትሰማም ነበር። ትንሿ ግን ጠንከር ያለ ንግግር ሌላው ቀርቶ ፊታችንን ማኮሳተር ብቻ ይበቃት ነበር።” በእርግጥም አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ለእያንዳንዱ ልጅ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው ምን ዓይነት ተግሣጽ እንደሆነ ለማስተዋል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

14 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የአገልጋዮቹን ጠንካራና ደካማ ጎን ስለሚያውቅ ለወላጆች ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል። (ዕብራውያን 4:13) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በሚቀጣበት ጊዜ ከመጠን በላይ ጥብቅ ወይም ልል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ቢሆን ሕዝቡን የሚቀጣው “በመጠኑ” ነው። (ኤርምያስ 30:11) ወላጆች፣ የልጆቻችሁን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ታውቃላችሁ? ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ልጆቻችሁን ውጤታማ በሆነና ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማሠልጠን ትችላላችሁ? እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁን እንደምትወዷቸው እያሳያችሁ ነው።

ልጆቻችሁ የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሯችሁ አበረታቷቸው

15, 16. ወላጆች፣ ልጆቻቸው የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ሊያበረታቷቸው የሚችሉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ክርስቲያን ወላጆች ውጤታማ ሆኖ ያገኙት ዘዴ ምንድን ነው?

15 ሌላው የፍቅር ገጽታ ደግሞ ‘ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ የማይሰኝ’ መሆኑ ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:6) ወላጆች፣ ልጆቻቸው ትክክለኛና እውነት የሆነውን እንዲወዱ ሊያሠለጥኗቸው የሚችሉት እንዴት ነው? ወላጆች፣ ልጆቹ የሚናገሩትን ነገር ለመቀበል ቢከብዳቸውም እንኳ ልጆቹ ስሜታቸውን አውጥተው በሐቀኝነት እንዲናገሩ ማበረታታት በጣም አስፈላጊ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና ስሜት እንዳላቸው ሲናገሩ መስማት እንደሚያስደስታቸው እሙን ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አንድ ልጅ እውነተኛ ስሜቱን ሲገልጽ የክፋት ዝንባሌ እንዳለው በግልጽ ማየት ይቻል ይሆናል። (ዘፍጥረት 8:21) በዚህ ጊዜ ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? መጀመሪያ የሚታያቸው ነገር ልጆቻቸው እንዲህ ያለ ነገር ስለተናገሩ መቆጣት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወላጆች እንዲህ ካደረጉ ልጆቹ፣ ወላጆቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ መናገርን ይለምዳሉ። እርግጥ ነው፣ አክብሮት የጎደለው ንግግር ወዲያውኑ ሊታረም ይገባል፤ ይሁን እንጂ ልጆች ሥርዓታማ በሆነ መንገድ እንዴት ሐሳባቸውን መግለጽ እንደሚችሉ ማስተማርና ምን መናገር እንዳለባቸው መወሰን የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

16 ወላጆች፣ ልጆቻቸው የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አሊያ እንዲህ ብላለች:- “ልጆቻችን የሚነግሩን አንዳንድ ነገሮች የሚረብሹን ቢሆኑም በነገሩ መቆጣታችንን ላለማሳየት በመጣር ሐሳባቸውን በግልጽ እንዲያካፍሉን እናደርጋለን።” ቶም የተባለ አባት እንዲህ ብሏል:- “ልጃችን በእኛ አመለካከት በማትስማማበትም ጊዜ እንኳ ስሜቷን አውጥታ እንድትነግረን እናበረታታታለን። ሐሳቧን ስትገልጽ ሁልጊዜ የምናቋርጣትና እኛ የፈለግነውን እንድታደርግ የምናስገድዳት ከሆነ በዚህ ልትበሳጭና በልቧ ውስጥ ያለውን ከመናገር ወደኋላ ልትል እንደምትችል ይሰማናል። በሌላ በኩል ግን ሐሳቧን ስትገልጽ ማዳመጣችን እሷም እኛን እንድታዳምጠን ያነሳሳታል።” ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ እንዳለባቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 6:20) ሆኖም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በግልጽ በመወያየት ልጆቹ የማመዛዘን ችሎታ እንዲያዳብሩ መርዳት ይችላሉ። የአራት ልጆች አባት የሆነው ቪንሰንት እንዲህ ብሏል:- “ልጆቻችን የተሻለው አካሄድ የትኛው እንደሆነ ራሳቸው መመልከት እንዲችሉ ብዙውን ጊዜ የአንድን ነገር ጥቅምና ጉዳት እንወያያለን። እንዲህ ማድረጋችንም ልጆቹ የማመዛዘን ችሎታ እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል።”—ምሳሌ 1:1-4

17. ወላጆች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚሰጠውን ምክር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ወላጅ እንደሌለ አይካድም። ያም ቢሆን ግን ልጆቻችሁ እነሱን በትዕግሥት፣ በደግነትና በፍቅር ለማሠልጠን የምታደርጉትን ጥረት ከልብ እንደሚያደንቁት እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። ይሖዋም ጥረታችሁን እንደሚባርክላችሁ ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 3:33) ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች እንዲህ ያለ ጥረት የሚያደርጉት ልጆቻቸው ልክ እንደነሱ ይሖዋን እንዲወዱት ለማስተማር ስለሚፈልጉ ነው። ታዲያ ወላጆች እዚህ ታላቅ ግብ ላይ መድረስ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እንዲህ ማድረግ የሚቻልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ያብራራል።

ታስታውሳለህ?

• አንድ ወላጅ አስተዋይ መሆኑ ታጋሽ እንዲሆን የሚረዳው እንዴት ነው?

• ተግሣጽ ከደግነት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

• ወላጆችና ልጆች በግልጽ መወያየታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ ልጆች የነበራችሁበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ የልባቸውን አውጥተው በግልጽ እንዲነግሯችሁ ታበረታቷቸዋላችሁ?