በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢዩኤል እና የአሞጽ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የኢዩኤል እና የአሞጽ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የኢዩኤል እና የአሞጽ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

ኢዩኤል ‘የባቱኤል ልጅ’ መሆኑን ከመግለጹ በቀር ስለራሱ የተናገረው ነገር የለም። (ኢዩኤል 1:1) ኢዩኤል በስሙ በሚጠራው መጽሐፍ ውስጥ ከመልእክቱ ጋር ከተያያዙ ጉዳዮች ውጪ ስለ ሌሎች ነገሮች የጻፈው በጣም ጥቂት በመሆኑ ትንቢቱን የተናገረበትን ጊዜ እንኳ በግምት ካልሆነ በቀር በትክክል ማወቅ አይቻልም። ኢዩኤል ትንቢቱን የተናገረው ዖዝያን በይሁዳ ላይ ከነገሠ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማለትም በ820 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል። ኢዩኤል ስለ ራሱ ብዙም ያልተናገረው ለምንድን ነው? በመልእክቱ እንጂ በመልእክተኛው ላይ ትኩረት ማድረግ ስላልፈለገ ሊሆን ይችላል።

በዖዝያን ዘመን የነበረው ሌላው ነቢይ ደግሞ “እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ” የሆነው አሞጽ የተባለ ከይሁዳ የመጣ የአምላክ አገልጋይ ነው። (አሞጽ 7:14) በይሁዳ ትንቢት ከሚናገረው ከኢዩኤል በተለየ መልኩ አሞጽ በሰሜናዊው የአሥሩ የእስራኤል ነገድ መንግሥት ላይ ትንቢት እንዲናገር ተላከ። ይህ መጽሐፍ የተጠናቀቀው አሞጽ ወደ ይሁዳ ከተመለሰ በኋላ በ804 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የተጻፈውም ቀለል ባለ ሆኖም ገላጭ በሆነ መንገድ ነው።

“ወዮ ለዚያ ቀን” የተባለው ለምንድን ነው?

(ኢዩኤል 1:1 እስከ 3:21)

ኢዩኤል ምድሪቷን የተምች፣ የአንበጣና የኵብኵባ መንጋ ሲወራት በራእይ ተመለከተ። ወራሪዎቹ “ኀያልና ብዙ ሰራዊት” እንዲሁም “ተዋጊዎች” ተብለው ተጠርተዋል። (ኢዩኤል 1:4፤ 2:2-7) ኢዩኤል “ወዮ ለዚያ ቀን፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል” በማለት በሐዘን ተናገረ። (ኢዩኤል 1:15) ይሖዋ የጽዮንን ነዋሪዎች “በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት መክሯቸዋል። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ‘ለሕዝቡ ይራራል’ እንዲሁም “የሰሜንን ሰራዊት” ማለትም ነፍሳቱን ከእነሱ ያርቃል። ይሁን እንጂ ታላቁ የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት አምላክ ‘መንፈሱን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ያፈሳል፤’ እንዲሁም ‘ድንቆችን በሰማያትና በምድር ላይ ያሳያል።’—ኢዩኤል 2:12, 18-20, 28-31

ብሔራት “ማረሻችሁ ሰይፍ፣ ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት” ተብለው ለጦርነት እንዲዘጋጁ ተጠርተዋል። እነዚህ ብሔራት ወደሚፈረድባቸውና ወደሚጠፉበት ‘ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም እንዲወርዱ’ ታዘዋል። ሆኖም “ይሁዳ ለዘላለም . . . መኖሪያ ትሆናለች።”—ኢዩኤል 3:10, 12, 20

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

1:15፤ 2:1, 11, 31፤ 3:14—“የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን” ምንድን ነው? የይሖዋ ቀን፣ ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ ነው፤ ይህ ቀን በጠላቶቹ ላይ ጥፋት የሚያስከትል ሲሆን ለእውነተኛ አምላኪዎቹ ግን መዳን ያስገኛል። ለአብነት ያህል፣ በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት የጥንቷ ባቢሎን፣ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ስትደረግ የይሖዋ ቀን መጥቶባታል። (ኢሳይያስ 13:1, 6) በቅርቡ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ መለኮታዊ ፍርድ የሚፈጸምበት “የይሖዋ ቀን” ይመጣል።—ራእይ 18:1-4, 21

2:1-10, 28—ምድሪቱ በነፍሳት ሠራዊት ስለ መወረሯ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? የከነዓን ምድር፣ በኢዩኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን ያህል ስፋት ባለው መንገድ በነፍሳት ሠራዊት እንደተወረረች የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የለም። በመሆኑም ኢዩኤል የገለጸው ወረራ፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተከናወነውን ሁኔታ የሚያመለክት ትንቢት ሊሆን ይችላል፤ በዚያ ወቅት ይሖዋ በመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች ላይ መንፈሱን ሲያፈስስ እነዚህ ደቀ መዛሙርት የሐሰት ሃይማኖት መሪዎችን የሚያሠቃይ መልእክት መስበክ ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 2:1, 14-21፤ 5:27-33) እኛም በዛሬው ጊዜ በዚህ ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል።

2:32—‘የይሖዋን ስም መጥራት’ ሲባል ምን ማለት ነው? የአምላክን ስም መጥራት ሲባል ስሙን ማወቅና በጥልቅ ማክበር እንዲሁም የዚህ ስም ባለቤት በሆነው አምላክ መታመንና መመካት ማለት ነው።—ሮሜ 10:13, 14

3:14—‘ፍርድ የሚሰጥበት ሸለቆ’ ምንድን ነው? የአምላክ ፍርድ የሚፈጸምበት ምሳሌያዊ ቦታ ነው። ኢዮሣፍጥ (“ይሖዋ ፈራጅ ነው” ማለት ነው) በተባለው የይሁዳ ንጉሥ ዘመን፣ ይሁዳ በዙሪያዋ ካሉት ብሔራት ጋር ጦርነት ገጥማ የነበረ ሲሆን በዚያ ወቅት አምላክ የብሔራቱን ሠራዊት ግራ በማጋባት ሕዝቡን አድኗቸዋል። በዚህም ምክንያት ይህ ቦታ ‘የኢዮሣፍጥ ሸለቆ’ በመባልም ይጠራል። (ኢዩኤል 3:2, 12) በዘመናችን ይህ መጠሪያ፣ ብሔራት በመጭመቂያ ውስጥ እንዳለ ወይን የሚረገጡበትን ምሳሌያዊ ቦታ ያመለክታል።—ራእይ 19:15

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:13, 14 ለመዳን ከልብ ንስሐ መግባትና ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን መቀበል አስፈላጊ ነው።

2:12, 13 እውነተኛ ንስሐ ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። እንዲህ ያለው ንስሐ የሚገለጸው ‘ልብስን እንደ መቅደድ’ ባለ የሚታይ ተግባር ሳይሆን ‘ልብን በመቅደድ’ ማለትም ከልብ የመነጨ ንስሐ በማሳየት ነው።

2:28-32 ‘ከታላቁና ከሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ የሚድነው ‘የይሖዋን ስም የሚጠራ’ ብቻ ነው። ይሖዋ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሱን በማፍሰሱና ወጣቶችና አረጋውያን እንዲሁም ወንዶችና ሴቶች ትንቢት እንዲናገሩ ማለትም “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” እንዲያውጁ በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (የሐዋርያት ሥራ 2:11) የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲሄድ ‘በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልንኖር’ ይገባናል።—2 ጴጥሮስ 3:10-12

3:4-8, 19 በይሁዳ ዙሪያ ያሉት ብሔራት አምላክ የመረጣቸውን ሕዝቦች በማንገላታታቸው እንደሚቀጡ ኢዩኤል ትንቢት ተናግሮ ነበር። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የጢሮስን ከተማ ባወደመበት ወቅት ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ታላቁ እስክንድር በደሴት ላይ የምትገኘውን የጢሮስ ከተማ ድል ባደረጋት ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችና ታላላቅ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 30,000 የሚሆኑ የደሴቲቱ ነዋሪዎችም በባርነት ተሽጠዋል። እስክንድርና ተተኪዎቹ በፍልስጥኤማውያን ላይም ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰዋል። ኤዶም ደግሞ በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ባድማ ሆናለች። (ሚልክያስ 1:3) ፍጻሜያቸውን ያገኙት እነዚህ ትንቢቶች ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። ከዚህም በላይ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አምላኪዎቹን በሚያሳድዱት ብሔራት ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ያሳያሉ።

3:16-21 ‘ሰማይና ምድር የሚናወጡ’ ሲሆን ብሔራትም የይሖዋን የቅጣት ፍርድ ይቀበላሉ። ይሖዋ ግን ‘ለሕዝቡ መሸሸጊያ በመሆን’ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ በክፉው ዓለም ላይ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ እየቀረበ ሲሄድ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና አጠናክረን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አይገባንም?

“አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ”

(አሞጽ 1:1 እስከ 9:15)

አሞጽ፣ የእስራኤላውያን ጠላቶች ለሆኑት በዙሪያቸው ላሉት ብሔራት እንዲሁም ለይሁዳና ለእስራኤል የሚናገረው መልእክት አለው። ሶርያ፣ ፍልስጥኤም፣ ጢሮስ፣ ኤዶም እና ሞዓብ የአምላክን ሕዝቦች በጭካኔ ስላሠቃዩአቸው ጥፋት ይጠብቃቸዋል። የይሁዳ ነዋሪዎች ደግሞ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ በመናቃቸው’ ይጠፋሉ። (አሞጽ 2:4) የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥትስ ምን ይደርስበታል? ሕዝቡ ከፈጸሟቸው ኃጢአቶች መካከል ድሆችን በስግብግብነት መጨቆን፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም የአምላክን ነቢያት ማቃለል ይገኙበታል። ይሖዋ ‘የቤቴልን መሠዊያዎች እንደሚያፈርስና የክረምቱን ቤት፣ ከበጋው ቤት ጋር እንደሚመታው’ አሞጽ አስጠንቅቋል።—አሞጽ 3:14, 15

ጣዖት አምላኪዎቹ እስራኤላውያን በተለያየ መንገድ ቅጣት ቢደርስባቸውም ልባቸውን አደነደኑ። አሞጽ የእስራኤልን ሕዝብ “አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ” ብሏቸዋል። (አሞጽ 4:12) እስራኤላውያን የይሖዋ ቀን ሲመጣባቸው ‘ከደማስቆ ወዲያ [ወደ አሦር] ይሰደዳሉ።’ (አሞጽ 5:27) አሞጽ የቤቴል ካህን ከነበረው ከአሜስያስ ተቃውሞ ቢደርስበትም ይህ እንዲፈራ አላደረገውም። ይሖዋ፣ ለአሞጽ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ከእንግዲህም አልምራቸውም” አለው። (አሞጽ 8:2) ወደ መቃብር ቢወርዱም ሆነ ወደ ተራራ ቢወጡ ከአምላክ ፍርድ አያመልጡም። (አሞጽ 9:2, 3) ያም ቢሆን ግን ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት እንደገና እንደሚቋቋሙ ቃል ገብቶላቸዋል:- “የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ፤ እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።”—አሞጽ 9:14

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

4:1—“የባሳን ላሞች” እነማንን ያመለክታሉ? ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ ከፍ ብሎ በሚገኘው የባሳን አምባ፣ ላሞችን ጨምሮ ምርጥ በሆኑ የእንስሳት ዝርያዎች የታወቀ ነበር። በአካባቢው ለምለም የግጦሽ መሬት መኖሩ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል። አሞጽ በሰማርያ የሚገኙትን ቅንጦት የሚወዱ ሴቶች ከባሳን ላሞች ጋር አመሳስሏቸዋል። እነዚህ ሴቶች ምቾታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ‘ባሎቻቸው’ ድሆችን እንዲጨቁኑ ይገፋፏቸው እንደነበር ጥርጥር የለውም።

4:6 የ1954 ትርጉም—“ጥርስን ማጥራት” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? “እንጀራን ማጣት” ከሚለው ሐሳብ ጋር የተገለጸው ይህ አባባል ምግብ በማጣት ምክንያት ጥርስ ንጹሕ የሚሆንበትን የረሃብ ጊዜ ሊያመለክት ይችላል።

5:5—እስራኤላውያን “ቤቴልን አትፈልጉ” መባላቸው ምን ትርጉም አለው? ኢዮርብዓም በቤቴል የጥጃ አምልኮ አቋቁሞ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ የሐሰት አምልኮ ማዕከል ነበረች። ጌልገላ እና ቤርሳቤህም የክህደት አምልኮ የሚከናወንባቸው ቦታዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እስራኤላውያን ከተነገረው ጥፋት ለመዳን ወደነዚህ ቦታዎች ለአምልኮ መሄዳቸውን አቁመው ይሖዋን መፈለግ ነበረባቸው።

7:1 የ1954 ትርጉም—‘የንጉሡ አጨዳ’ ምን ያመለክታል? ንጉሡ፣ ለፈረሰኞቹና ለእንስሳቱ እንዲሆን በሕዝቡ ላይ የጣለውን ግብር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይህ ግብር መከፈል ያለበት “የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ” ነበር። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሰብላቸውን መሰብሰብ ይችላሉ። ሆኖም ይህን ከማድረጋቸው በፊት የአንበጣ መንጋ መጥቶ ሰብላቸውንም ሆነ በምድሪቱ ላይ ያለውን ሣር ቅጠል በሙሉ አወደመው።

8:1, 2—“የጎመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት” ምን ትርጉም አለው? የይሖዋ ቀን መቅረቡን ያመለክታል። የጎመራ ፍሬ የሚሰበሰበው በመከር ወራት ማብቂያ ማለትም በእርሻው ዓመት መገባደጃ አካባቢ ነው። ይሖዋ፣ ለአሞጽ “የጎመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት” ሲያሳየው እስራኤል የምትጠፋበት ጊዜ መቅረቡን ማመልከቱ ነበር። በመሆኑም አምላክ ለአሞጽ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ከእንግዲህም አልምራቸውም” ብሎታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:3, 6, 9, 11, 13፤ 2:1, 4, 6 ይሖዋ እስራኤልን፣ ይሁዳንና በዙሪያቸው ያሉትን ስድስት ብሔራት በተመለከተ ቁጣውን ‘እንደማይመልስ’ ተናግሯል። ከይሖዋ ፍርድ ማምለጥ አይቻልም።—አሞጽ 9:2-5

2:12 በትጋት የሚያገለግሉትን አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስዮናውያን ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ትተው እንደሌላው ሰው እንዲኖሩ በመገፋፋት ተስፋ ልናስቆርጣቸው አይገባም። ከዚህ ይልቅ በያዙት መልካም ሥራ እንዲገፉበት ልናበረታታቸው ይገባል።

3:8 አንድ ሰው፣ አንበሳ ሲያገሣ ሲሰማ እንደሚፈራ ሁሉ አሞጽም ይሖዋ “ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” ባለው ጊዜ ለመስበክ ተነሳስቷል። (አሞጽ 7:15) በተመሳሳይም አምላካዊ ፍርሃት የመንግሥቱ መልእክት ቀናተኛ ሰባኪዎች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል።

3:13-15፤ 5:11 አሞጽ ዝቅተኛ ኑሮ የነበረው እረኛ ቢሆንም ባለጠጋ በመሆናቸው ግዴለሽ ለሆኑት ሰዎች በይሖዋ እርዳታ ‘ለመመስከር’ ችሏል። በተመሳሳይም የምናገለግልበት ክልል ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን የመንግሥቱን መልእክት እንድናውጅ ይሖዋ ያስታጥቀናል።

4:6-11፤ 5:4, 6, 14 እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ ‘እንዲመለሱ’ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ ለመቀበል አሻፈረኝ ቢሉም “እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ” ተብለዋል። ይሖዋ ይህ ክፉ ሥርዓት እንዲቀጥል በትዕግሥት እስከፈቀደ ድረስ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲመለሱ ልናሳስባቸው ይገባል።

5:18, 19 ዝግጁ ሳይሆኑ ‘የይሖዋን ቀን መሻት’ ሞኝነት ነው። እንዲህ ማድረግ ከአንበሳ ሸሽቶ ድብ ካጋጠመው፣ ከድቡ ሲሸሽ ደግሞ እባብ ከነደፈው ሰው ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በመንፈሳዊ ‘መትጋታችንና’ ዝግጁ መሆናችን የጥበብ አካሄድ ነው።—ሉቃስ 21:36

7:12-17 የአምላክን መልእክት በድፍረትና በልበ ሙሉነት ማወጅ አለብን።

9:7-10 ታማኝነታቸውን ያጎደሉት እስራኤላውያን ታማኝ የነበሩት የቀድሞ የእምነት አባቶችና አምላክ ከግብጽ ያወጣቸው የተመረጡ ሕዝቦቹ ዝርያ ነበሩ፤ ይህ መሆኑ ግን በአምላክ ዘንድ ጥሩ አቋም እንዳልነበራቸው እንደ ኩሻውያን እንዳይታዩ አላደረጋቸውም። በማያዳላው አምላክ ፊት ተቀባይነት ማግኘታችን ‘እሱን በመፍራታችንና ጽድቅን በማድረጋችን’ እንጂ በዘር ሐረጋችን ላይ የተመካ አይደለም።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ምን ማድረግ አለብን?

ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ላይ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ቀን ቀርቧል። ይሖዋ በአምላኪዎቹ ላይ መንፈሱን በማፍሰስ ስለመጪው የአምላክ ቀን የሰው ዘሮችን እንዲያስጠነቅቁ አስታጥቋቸዋል። ታዲያ እኛስ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና ‘ስሙን እንዲጠሩ’ በመርዳቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ መካፈል አይኖርብንም?—ኢዩኤል 2:31, 32

አሞጽ “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (አሞጽ 5:15) የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲሄድ ወደ አምላክ መጠጋታችን እንዲሁም ከዚህ ክፉ ዓለምና ጎጂ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጓደኞች መራቃችን ጥበብ የተንጸባረቀበት አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት የኢዩኤልና የአሞጽ መጻሕፍት ለጊዜያችን የሚጠቅም ትምህርት ይዘውልናል።—ዕብራውያን 4:12

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዩኤል “የይሖዋ ቀን ቀርቦአል” በማለት ተንብዮአል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ አሞጽ ሁሉ እኛም የአምላክን መልእክት በድፍረትና በልበ ሙሉነት ማወጅ ይኖርብናል