በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዘፍጥረት 27:18, 19 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ያዕቆብ፣ ዔሳውን መስሎ መቅረቡ ስህተት ነበር?

ይህን ዘገባ ሳታውቀው አትቀርም። ይስሐቅ ባረጀ ጊዜ ዔሳውን “ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ . . . ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ” በማለት እንስሳ አድኖ እንዲያበላው ጠየቀው። ርብቃ፣ ባለቤቷ ያለውን ስለሰማች የሚጣፍጥ ምግብ ካዘጋጀች በኋላ ያዕቆብን “[አባትህ] ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ፣ [ምግቡን] ይዘህለት ግባና ይብላ” አለችው። ከዚያም ያዕቆብ የዔሳውን ልብስ ለብሶ እንዲሁም አንገቱና እጆቹ ላይ የጠቦቶች ቆዳ አድርጎ እናቱ አጣፍጣ ያዘጋጀችውን ምግብ በመያዝ ወደ አባቱ ሄደ። ያዕቆብ ወደ አባቱ ሲገባ፣ ይስሐቅ “አንተ ማን ነህ?” አለው። ያዕቆብም “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” በማለት መለሰለት። ይስሐቅም ያዕቆብን ስላመነው መረቀው።—ዘፍጥረት 27:1-29

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ የተከሰተው በድንገት እንደሆነ ቢገልጽም ርብቃና ያዕቆብ እንዲህ ያደረጉበትን ምክንያት በዝርዝር አይነግረንም። የአምላክ ቃል ርብቃና ያዕቆብ ያደረጉትን ነገር የሚደግፍም ሆነ የሚያወግዝ ሐሳብ አልያዘም፤ በመሆኑም ይህ ዘገባ ለውሸትና ለማጭበርበር ሰበብ አይሆንም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁኔታው የበለጠ ለማወቅ የሚያስችለን ሐሳብ ይዟል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዘገባው የአባቱን ምርቃት የማግኘት መብት የነበረው ያዕቆብ እንጂ ዔሳው እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ያዕቆብ፣ ለመብቱ አድናቆት ካልነበረው መንትያ ወንድሙ ብኩርናውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ገዝቶት ነበር፤ ዔሳው ረሃቡን ለማስታገስ ሲል ብኩርናውን በምግብ በመሸጡ ‘ብኩርናውን አቃሎታል።’ (ዘፍጥረት 25:29-34) በመሆኑም ያዕቆብ የአባቱን ምርቃት ለመቀበል ባለመብት ነበር።

በሁለተኛ ደረጃ ይስሐቅ፣ የመረቀው ያዕቆብን እንደሆነ ሲያውቅ ሁኔታውን ለማስተካከል አልሞከረም። ምናልባትም ይስሐቅ መንትያዎቹ ከመወለዳቸው በፊት ይሖዋ ለርብቃ “ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” እንዳላት አስታውሶ ይሆናል። (ዘፍጥረት 25:23) ይስሐቅ፣ ቀደም ሲል ያዕቆብን የመረቀው ቢሆንም ልጁ ወደ ካራን ሊሄድ ሲል ተጨማሪ ምርቃት የመረቀው መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።—ዘፍጥረት 28:1-4

በመጨረሻም፣ ይሖዋ ሁኔታውን ይመለከትና በትኩረት ይከታተል እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። የይስሐቅ ምርቃት አምላክ ለአብርሃም ከገባው ቃል ጋር የተያያዘ ነበር። (ዘፍጥረት 12:2, 3) አምላክ፣ ያዕቆብ እንዲመረቅ ባይፈልግ ኖሮ በሆነ መንገድ ጣልቃ መግባት ይችል ነበር። እንዲያውም ይሖዋ ለያዕቆብ “የምድርም ሕዝቦች ሁሉ . . . በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ” በማለት ጉዳዩን ይበልጥ አጠናክሮለታል።—ዘፍጥረት 28:10-15