በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥንታዊ የሸክላ ስብርባሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባን ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ

ጥንታዊ የሸክላ ስብርባሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባን ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ

ጥንታዊ የሸክላ ስብርባሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባን ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በጥንት ዘመን ስለነበሩ ሰዎችና ቦታዎች እንዲሁም ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የሚናገራቸው ነገሮች በሙሉ ትክክል ናቸው። የቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛነት የተመካው በአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ላይ ባይሆንም፣ እነዚህ ግኝቶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያለን ግንዛቤ ትክክለኛ መሆኑን እንድናረጋግጥ ወይም ስለተከሰቱት ሁኔታዎች ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዱናል።

አርኪኦሎጂስቶች የመሬት ቁፋሮ በሚያደርጉበት ወቅት በአብዛኛው የሚያገኙት የሸክላ ስብርባሪዎችን ነው። የሸክላ ስብርባሪዎች ግብጽንና መስጴጦምያን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ጥንታዊ አካባቢዎች ውስጥ በርካሽ የሚገኙ የጽሑፍ መሣሪያዎች ሆነው ያገለግሉ ነበር። የሸክላ ስብርባሪዎች በዘመናችን እንዳሉት ማስታወሻ ደብተሮች ወይም ወረቀቶች ሁሉ ውሎችን፣ ሒሳቦችን፣ ሽያጮችንና የመሳሰሉትን ነገሮች ለመመዝገብ ያገለግሉ ነበር። በአብዛኛው በቀለም የሚከተብባቸው እነዚህ ስብርባሪዎች ከአንድ ቃል አንስቶ እስከ በርካታ መሥመሮች አሊያም አምዶች ሊኖሯቸው ይችላል።

በእስራኤል በተደረጉ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ በርካታ የሸክላ ስብርባሪዎች ተገኝተዋል። በተለይም ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛውና በስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የሸክላ ስብርባሪዎችን የያዙ ሦስት ስብስቦች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘገቡት ታሪኮች ትክክል መሆናቸውን ስለሚያረጋግጡ ትኩረት የሚስቡ ናቸው። እነዚህ ስብስቦች የሰማርያ፣ የዓራድና የለኪሶ የሸክላ ስብርባሪ ስብስቦች በመባል ይታወቃሉ። እስቲ እነዚህን ስብስቦች ጠለቅ ብለን እንመርምር።

የሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች

ሰማርያ፣ በአሦራውያን እስከጠፋችበት ጊዜ ማለትም እስከ 740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ አሥሩን ነገዶች ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች። አንደኛ ነገሥት 16:23, 24 ከተማዋ የተቆረቆረችው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት [947 ከክርስቶስ ልደት በፊት]፣ ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ . . . እርሱም የሰማርያን ኰረብታ በሁለት መክሊት ጥሬ ብር ከሳምር ላይ ገዝቶ ከተማ ሠራባት፤ ስሟንም . . . ሰማርያ ብሎ ጠራት።” ይህቺ ከተማ ሰባስቴ ተብላ መጠራት እስከጀመረችበት እስከ ሮማውያን ዘመን ድረስ ሰዎች ይኖሩባት ነበር። በመጨረሻም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባድማ ሆነች።

በ1910 የጥንቷ ሰማርያ በነበረችበት ቦታ ላይ ቁፋሮ ሲደረግ አርኪኦሎጂስቶች በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈባቸው የሸክላ ስብርባሪ ስብስቦችን አገኙ። በእነዚህ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ ከሰማርያ አቅራቢያ ከነበሩት አካባቢዎች ወደ ከተማዋ በመርከብ ይላኩ የነበሩ የዘይትና የወይን ጭነቶች ዝርዝር ተጽፏል። ኤንሸንት ኢንስክሪፕሽንስ—ቮይስዝ ፍሮም ዘ ቢብሊካል ዎርልድ የተባለው መጽሐፍ ስለ እነዚህ ግኝቶች አስተያየት ሲሰጥ እንደሚከተለው ብሏል:- “በ1910 የተገኙት 63 የሸክላ ስብርባሪዎች . . . ከጥንቱ እስራኤል ከተረፉ እጅግ ጠቃሚ የጽሑፍ ስብስቦች መካከል መመደባቸው የተገባ ነው። የሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎችን ጠቃሚ ናቸው ያሰኛቸው ይዘታቸው ሳይሆን . . . የእስራኤላውያንን የተጸውዖና የጎሳ ስም እንዲሁም የቦታዎችን ስም ዝርዝር መያዛቸው ነው።” እነዚህ ስሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ይዘው፣ ምድሪቱን በተከፋፈሉበት ጊዜ ለምናሴ ነገድ ከተሰጡት አገሮች መካከል አንዷ ሰማርያ ነበረች። ኢያሱ 17:1-6 እንደሚገልጸው በምናሴ የልጅ ልጅ በገለዓድ በኩል የመጡት አሥሩ የምናሴ ነገዶች በዚህ አካባቢ መሬት ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ነገዶች አቢዔዝር፣ ኬሌግ፣ እሥራኤል፣ ሴኬምና ሸሚዳ ነበሩ። ስድስተኛ ልጅ የሆነው ኦፌር ሴቶች እንጂ ወንዶች የልጅ ልጆች አልነበሩትም። የኦፌር አምስት የልጅ ልጆች ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ቲርጻ የሚባሉ ሲሆን ለእያንዳንዳቸው ርስት ተሰጥቷቸዋል።—ዘኍልቍ 27:1-7

የሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች ከእነዚህ ነገዶች መካከል የሰባቱን ስም ይዘዋል። እነዚህም የገለዓድ አምስት ወንዶች ልጆችና ሁለቱ የኦፌር የልጅ ልጆች ማለትም ዔግላና ኑዓ ናቸው። ኤን አይ ቪ አርኪኦሎጂካል ስተዲ ባይብል እንዲህ ብሏል:- “በሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የነገድ ስሞች በምናሴ ዘሮችና መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሕዝቦች ሰፍረውባቸዋል ብሎ በሚናገራቸው ቦታዎች መካከል ተያያዥነት እንዳለ የሚያሳዩ ከቅዱሳን መጽሐፍት ውጪ ያሉ ተጨማሪ ማስረጃዎች ሆነዋል።” በመሆኑም እነዚህ የሸክላ ስብርባሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቱ የእስራኤላውያን ነገድ መዝግቦ ያቆየው ታሪክ ትክክለኛ እንደሆነ ያረጋግጣሉ።

የሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች በወቅቱ የነበረው የእስራኤላውያን ሃይማኖታዊ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጸው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ይመስላል። በሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ የሰፈሩት ጽሑፎች በተጻፉበት ወቅት እስራኤላውያን የይሖዋን አምልኮ የከነዓናውያን አምላክ ከነበረው ከበኣል አምልኮ ጋር ቀላቅለው ያራምዱ ነበር። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈው የሆሴዕ መጽሐፍ እስራኤል ይሖዋን “ጌታዬ” ወይም ‘በኣሌ’ ከማለት ይልቅ ንስሐ በመግባት “ባሌ” ብላ የምትጠራበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮአል። (ሆሴዕ 2:16, 17፣ የግርጌ ማስታወሻ) በሰማርያ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ የተጻፉት አንዳንድ ስሞች “በኣል አባቴ ነው፣” “በኣል ይዘምራል፣” “በኣል ኃያል ነው፣” እና “በኣል ያስታውሳል” እንደሚሉት ያሉ ትርጉሞች አሏቸው። የበኣል አምልኮ እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ በሸክላዎቹ ላይ ከሰፈሩት የእስራኤላውያን ስሞች መካከል በውስጣቸው “በኣል” የሚለውን ቃል የያዙ ብዙ ስሞች ይገኛሉ።

የዓራድ የሸክላ ስብርባሪዎች

ዓራድ በኢየሩሳሌም ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ኔጌብ በሚባል ከፊል በረሃማ አካባቢ የምትገኝ ጥንታዊ ከተማ ነች። በዓራድ በተደረጉት ቁፋሮዎች ከንጉሥ ሰሎሞን የንግሥና ዘመን (1037-998 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አንስቶ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እስከጠፋችበት እስከ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ የተሠሩ ስድስት የእስራኤላውያን ምሽጎች ተገኝተዋል። አርኪኦሎጂስቶች፣ በዓራድ በብዛታቸው ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የሸክላ ስብርባሪዎችን አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በሌሎች ቋንቋዎች የተጻፉ ከ200 በላይ የሸክላ ስብርባሪዎች ይገኙበታል።

ከዓራድ የሸክላ ስብርባሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ስለ ካህናት ቤተሰብ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የሸክላ ስባሪ በዘፀአት 6:24 እና በዘኍልቍ 26:11 ላይ እንደተገለጸው “የቆሬ ወንዶች ልጆች” የሚል ሐረግ ይዟል። በመዝሙር 42፣ 44 እስከ 49፣ 84፣ 85፣ 87 እና 88 አናት ላይ የሰፈሩት መግለጫዎች መዝሙራቱን የጻፉት “የቆሬ ልጆች” እንደሆኑ በግልጽ ይናገራሉ። በዓራድ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ የተጠቀሱት ሌሎች የካህናት ቤተሰቦች ደግሞ ጳስኮር እና ሜሪሞት ናቸው።—1 ዜና መዋዕል 9:12፤ ዕዝራ 8:33

ሌላም ምሳሌ ተመልከት። አርኪኦሎጂስቶች፣ ባቢሎናውያን እስራኤልን ከማጥፋታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ በተገነባ ምሽግ ፍርስራሽ ውስጥ ለምሽጉ አዛዥ የተጻፈ መልእክት የሰፈረበት የሸክላ ስባሪ አግኝተዋል። ዘ ኮንቴክስት ኦቭ ስክሪፕቸር የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው መልእክቱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ለጌታዬ ለኤልያሺብ። ያህዌህ [ይሖዋ] ደህንነትህን ይጠብቅልህ ዘንድ እመኛለሁ። . . . ያዘዝከኝ ነገር በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በያህዌህ ቤተ መቅደስ ውስጥ እየኖረ ነው።” በርካታ ምሑራን እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቤተ መቅደስ በሰሎሞን የተገነባው በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እንደሆነ ያምናሉ።

የለኪሶ የሸክላ ስብርባሪዎች

በቅጥር የተከበበችው የጥንቷ የለኪሶ ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ 43 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። በ1930 በዚህ ስፍራ ላይ በተደረጉት የመሬት ቁፋሮዎች የሸክላ ስብርባሪዎች ክምችት ተገኘ። ከእነዚህ ስብርባሪዎች መካከል ቢያንስ 12ቱ ደብዳቤዎች ሲሆኑ “ይሁዳ አይቀሬውን [የባቢሎን ንጉሥ] የናቡከደነፆርን ጥቃት ለመመከት ስትዘጋጅ የነበረችባቸውን የጭንቀት ጊዜያት የሚያወሱና በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚገልጹ በመሆናቸው . . . እጅግ ጠቃሚ” እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ የሆኑት በያኦሽ (በለኪሶ የነበረ የጦር መኮንን ሳይሆን አይቀርም) እና በበታቹ ባለ የጦር አዛዥ መካከል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦችን የያዙት ሸክላዎች ናቸው። ደብዳቤዎቹ የተጻፉበት መንገድ በዘመኑ ይኖር ከነበረው ከነቢዩ ኤርምያስ ያጻጻፍ ስልት ጋር ተመሳሳይነት አለው። ከእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ ሁለቱ መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ስለነበሩት ሁኔታዎች የሚናገረውን ሐሳብ የሚደግፉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በኤርምያስ 34:7 ላይ ነቢዩ በወቅቱ ስለነበሩት ሁኔታዎች ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- “በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩ።” በለኪሶ የተገኙትን ደብዳቤዎች ከጻፉት ሰዎች አንዱ እየገለጸ የነበረው ይህንኑ ክንውን ይመስላል። እንዲህ ብሏል:- “የለኪሶን [የእሳት] ምልክቶች አይተናል . . . ዓዜቃን ግን ልናያት አልቻልንም።” በርካታ ምሑራን ይህ አነጋገር አዜቃ በባቢሎን እጅ እንደወደቀችና ቀጣይዋ ደግሞ ለኪሶ መሆኗን እንደሚያመለክት ያምናሉ። በዚህ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው ‘የእሳት ምልክት’ ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። በኤርምያስ 6:1 [የ1980 ትርጉም] ላይም እንዲህ ስላለው የመልእክት መለዋወጫ መንገድ ተጠቅሷል።

በለኪሶ የተገኘው ሌላው ደብዳቤ ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስና ነቢዩ ሕዝቅኤል የይሁዳው ንጉሥ ባቢሎን ላይ ባስነሳው ዓመጽ የግብጽን ድጋፍ ለማግኘት ስላደረገው ጥረት የጻፉትን ሐሳብ የሚደግፍ ይመስላል። (ኤርምያስ 37:5-8፤ 46:25, 26፤ ሕዝቅኤል 17:15-17) በለኪሶ የተገኘው ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “ባሪያህ የሚከተለው መረጃ ደርሶታል:- የኤልናታን ልጅ የሆነው ጄነራል ኮንያሁ ወደ ግብጽ ለመግባት ወደ ደቡብ ሄዷል።” በጥቅሉ ሲታይ ምሑራን ይህን እንቅስቃሴ ከግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ ጥረት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ከዚህም በተጨማሪ በለኪሶ የተገኙት የሸክላ ስብርባሪዎች በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ ስሞችን ይዘዋል። እነዚህም ኔርያ፣ ያእዛንያ፣ ገማርያ፣ ኤልናታን እና ሆሻያን ናቸው። (ኤርምያስ 32:12፤ 35:3፤ 36:10, 12፤ 42:1) እነዚህ ስሞች የሚያመለክቱት ተመሳሳይ ግለሰቦችን ይሁን አይሁን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ይሁንና ኤርምያስ የኖረው በዚሁ ዘመን ስለነበር የስሞቹ መመሳሰል ትኩረት የሚስብ ነው።

ተመሳሳይ ገጽታ

የሰማርያ፣ የዓራድና የለኪሶ የሸክላ ስብርባሪ ስብስቦች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ከእነዚህ መካከል የቤተሰብና የቦታ ስሞች እንዲሁም በዘመኑ ስለነበሩት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የሚናገሩት ነጥቦች መመሳሰል ይገኙበታል። ይሁንና በሦስቱም ስብስቦች ላይ የሚንጸባረቅ አንድ እጅግ ጠቃሚ ገጽታ አለ።

በዓራድና በለኪሶ የተገኙት ደብዳቤዎች “ይሖዋ ሰላም ይስጣችሁ” እንደሚለው ያሉ ሐረጎችን ይዘዋል። በለኪሶ በተገኙት ሰባት ደብዳቤዎች ላይ የአምላክ ስም 11 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህም በላይ በሦስቱም ስብስቦች ላይ ያሉት በርካታ የዕብራይስጥ ስሞች ይሖዋ የሚለውን ስም ምሕጻረ ቃል ይዘዋል። በመሆኑም እነዚህ የሸክላ ስብርባሪዎች፣ በዘመኑ የነበሩት እስራኤላውያን መለኮታዊውን ስም በስፋት የመጠቀም ልማድ እንደነበራቸው ያረጋግጣሉ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓራድ ባሉት ፍርስራሾች ውስጥ የተገኘ ኤልያሺብ ለተባለ ሰው ደብዳቤ የተጻፈበት የሸክላ ስባሪ

[ምንጭ]

ፎቶ © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በለኪሶ የተገኘ የአምላክን ስም የያዘ ደብዳቤ

[ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum