በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን ኮርጅ

ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን ኮርጅ

ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን ኮርጅ

“እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ።”—ሉቃስ 8:18

1, 2. ኢየሱስ ምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት ሰዎችን የያዘበትን መንገድ መመርመር የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ” ባላቸው ጊዜ በማስተማሩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ነበር። (ሉቃስ 8:16-18) ክርስቲያን እንደ መሆንህ መጠን በምታገለግልበት ወቅት ይህ መመሪያ በአንተም ላይ ይሠራል። ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ትኩረት ሰጥተህ የምትሰማ ከሆነ በተግባር ላይ ታውላቸዋለህ፤ እንዲሁም ውጤታማ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ትሆናለህ። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ድምፅ ቃል በቃል መስማት አትችልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ትችላለህ። ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ በምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት ሰዎችን ስለያዘበት መንገድ ምን ይነግሩናል?

2 ኢየሱስ የተዋጣለት የምሥራቹ ሰባኪ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ረገድ ተወዳዳሪ አልነበረውም። (ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 8:28) ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ መስበክን ብቻ ሳይሆን ማስተማርንም ይጨምራል። ይሁንና አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥሩ ሰባኪዎች ቢሆኑም ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ይከብዳቸዋል። መስበክ ሲባል አንድን መልእክት ማወጅ ማለት ሲሆን ሰዎችን ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ማስተማር ግን አብዛኛውን ጊዜ ከምናስተምረው ሰው ጋር ወዳጅነት መመሥረትን ይጠይቃል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህን ለማድረግ የምንችለው ታላቅ አስተማሪ የሆነውንና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመኮረጅ ነው።—ዮሐንስ 13:13

3. ኢየሱስን መኮረጅህ ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

3 የኢየሱስን የማስተማር ዘዴ የምትኮርጅ ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ በተግባር ላይ ታውላለህ:- “በውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ ተመላለሱ፤ በተገኘውም ዕድል ሁሉ ተጠቀሙ። ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።” (ቈላስይስ 4:5, 6) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ኢየሱስን መኮረጅ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም እንዲህ ማድረግህ ‘ለእያንዳንዱ ሰው እንደየሁኔታው መልስ ለመስጠት’ ስለሚያስችልህ ውጤታማ አስተማሪ እንድትሆን ይረዳሃል።

ኢየሱስ ሌሎች እንዲናገሩ ያበረታታ ነበር

4. ኢየሱስ ጥሩ አድማጭ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ከልጅነቱ ጀምሮ ሰዎችን የማዳመጥና ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የማበረታታት ልማድ ነበረው። ለምሳሌ ያህል የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ “ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው” አግኝተውታል። (ሉቃስ 2:46) ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ የሄደው መምህራኑን በእውቀቱ ለማስደመም አልነበረም። መምህራኑን ጥያቄ ይጠይቃቸው የነበረ ቢሆንም ወደዚያ የሄደው ለማዳመጥ ነበር። ኢየሱስ፣ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ያስገኘለት አንዱ ባሕርይ ጥሩ አድማጭ የነበረ መሆኑ ሳይሆን አይቀርም።—ሉቃስ 2:52

5, 6. ኢየሱስ፣ ያስተምራቸው የነበሩ ሰዎች የሚሰጡትን ሐሳብ ያዳምጥ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

5 ኢየሱስ ከተጠመቀና መሲሕ ሆኖ ከተቀባም በኋላ ሰዎችን የማዳመጥ ፍላጎቱ አልቀነሰም። ንግግሩን ሊያዳምጡ የመጡትን ሰዎች እስኪረሳ ድረስ በሚያስተምረው ትምህርት አልተዋጠም። አብዛኛውን ጊዜ ንግግሩን ቆም አድርጎ ምን እንደሚያስቡ ይጠይቃቸውና የሚሰጡትን ምላሽ ያዳምጥ ነበር። (ማቴዎስ 16:13-15) ለምሳሌ ያህል፣ ወንድሟ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ማርታን “በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም” አላት። ቀጠል አድርጎም “ይህን ታምኛለሽን?” ሲል ጠየቃት። ማርታ፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” ስትለው ኢየሱስ እንዳዳመጣት ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 11:26, 27) ማርታ በዚህ መንገድ እምነቷን ስትገልጽ መስማቱ ምን ያህል አስደስቶት ይሆን!

6 ኢየሱስ በርካታ ደቀ መዛሙርት ጥለውት በሄዱ ጊዜ የሐዋርያቱን አመለካከት ለማወቅ ፈልጎ ስለነበር “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።” (ዮሐንስ 6:66-69) እነዚህ ቃላት ኢየሱስን ምንኛ አስደስተውት ይሆን! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እምነቱን በዚህ መንገድ ሲገልጽ መስማት እንደሚያስደስትህ ምንም ጥርጥር የለውም።

ኢየሱስ ሌሎችን በአክብሮት ያዳምጥ ነበር

7. በርካታ ሳምራውያን በኢየሱስ ያመኑት ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለው ሌላው ምክንያት ለሰዎች ያስብና ሲናገሩም በአክብሮት ያዳምጣቸው የነበረ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ በሲካር በሚገኝ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት አንዲት ሳምራዊት ሴት ሰበከላት። በዚህ ወቅት ተናጋሪው ኢየሱስ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እሷም ስትናገር አዳምጧታል። ኢየሱስ ከንግግሯ የአምልኮ ፍላጎት እንዳላት ስላስተዋለ አምላክ በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩትን እንደሚፈልግ ነገራት። ኢየሱስ ለዚህች ሴት አክብሮትና አሳቢነት አሳይቷታል። ሴትየዋም ወዲያውኑ ስለ እሱ ለሌሎች መሠከረች፤ በዚህም ምክንያት “ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእርሱ አመኑ።”—ዮሐንስ 4:5-29, 39-42

8. ሰዎች ሐሳባቸውን መግለጽ የሚያስደስታቸው መሆኑ በአገልግሎት ላይ ውይይት ለመጀመር የሚረዳህ እንዴት ነው?

8 አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አመለካከታቸውን መግለጽ ያስደስታቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ አቴና ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሐሳባቸውን ለሌሎች መግለጽና አዲስ ነገር መስማት ያስደስታቸው ነበር። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በከተማዋ በሚገኝ አርዮስፋጎስ በተባለ ቦታ ጥሩ ውጤት ያስገኘ ንግግር እንዲሰጥ አስችሎታል። (የሐዋርያት ሥራ 17:18-34) በዛሬው ጊዜም በአገልግሎት ላይ ለምታገኘው ሰው “[አንድ ርዕሰ ጉዳይ በመጥቀስ] በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አመለካከት እንዳለዎት ባውቅ ደስ ይለኛል” በማለት ውይይት መጀመር ትችላለህ። ሰውየው አመለካከቱን ሲገልጽ አዳምጥና ሐሳብ ስጥ ወይም ጥያቄ ጠይቀው። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል አሳየው።

ኢየሱስ ምን መናገር እንዳለበት ያውቅ ነበር

9. ኢየሱስ ለቀለዮጳና ለጉዞ ጓደኛው ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት ገልጦ ከማስረዳቱ’ በፊት ምን አድርጓል?

9 ኢየሱስ የሚናገረው ነገር ጠፍቶት አያውቅም። ጥሩ አድማጭ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች የሚያስቡትን ይረዳ ስለነበር ምን ማለት እንዳለበት ያውቃል። (ማቴዎስ 9:4፤ 12:22-30፤ ሉቃስ 9:46, 47) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ሳለ የተከሰተውን ሁኔታ እንመልከት። የወንጌል ዘገባ እንዲህ ይላል:- “[ደቀ መዛሙርቱ] እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፣ ‘እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?’ አላቸው። እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ ‘በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?’ ሲል መለሰለት። እርሱም፣ ‘የሆነው ነገር ምንድን ነው?’ አላቸው።” ታላቁ አስተማሪ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሰዎችን እንዳስተማረ፣ ተአምራት እንደፈጸመና በኋላም እንደተገደለ ሲተርኩለት አዳመጠ። አሁን ደግሞ አንዳንዶች ከሞት ተነስቷል እንደሚሉ ነገሩት። ኢየሱስ ቀለዮጳና የጉዞ ጓደኛው ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ፈቅዶላቸዋል። ከዚያም ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት ገልጦ አስረዳቸው።’—ሉቃስ 24:13-27, 32

10. በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥምህ ሰው ስለ ሃይማኖት ያለውን አመለካከት ለማወቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

10 የምታነጋግረው ሰው ስለ ሃይማኖት ምን አመለካከት እንዳለው አታውቅ ይሆናል። አመለካከቱን ለማወቅ “ሰዎች ስለ ጸሎት ምን እንደሚሰማቸው ማወቅ ያስደስተኛል” ልትለው ትችላለህ። አክለህም “ጸሎታችንን የሚሰማ አንድ አካል አለ ብለው ያምናሉ?” የሚል ጥያቄ አቅርብለት። ለዚህ ጥያቄ የሚሰጥህ መልስ የግለሰቡን አመለካከትና ሃይማኖቱን እንድታውቅ ሊረዳህ ይችላል። ግለሰቡ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንዳለው ካስተዋልክ አመለካከቱን ይበልጥ ለማወቅ “አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች የሚሰማ ይመስልዎታል? ወይስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ጸሎቶች አሉ ብለው ያስባሉ?” በማለት ልትጠይቀው ትችላለህ። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጥሩ ውይይት ማድረግ እንድትችሉ ይረዳችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል ማሳየት ሲያስፈልግህ የሰውየውን እምነት ሳትነቅፍ በዘዴ እንዲህ ልታደርግ ትችላለህ። በውይይቱ ከተደሰተ ተመልሰህ እንድትጠይቀው ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ይሁንና መልሱን የማታውቀው አንድ ጥያቄ ቢጠይቅህስ? በጥያቄው ላይ የበለጠ ምርምር ካደረግህ በኋላ ተመልሰህ በመሄድ ‘ስለ ተስፋህ ለቀረበልህ ጥያቄ መልስ መስጠት’ ትችላለህ። ይህንንም ስታደርግ “በትሕትናና በአክብሮት” መሆን አለበት።—1 ጴጥሮስ 3:15

ኢየሱስ መማር የሚገባቸውን ሰዎች አስተምሯል

11. ምሥራቹን መማር የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት ምን ሊረዳህ ይችላል?

11 ፍጹም የነበረው ኢየሱስ መማር የሚገባቸውን ሰዎች ለማወቅ የሚያስችል የማስተዋል ችሎታ ነበረው። እኛ ግን “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎችን መለየት ይከብደናል። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) የኢየሱስ ሐዋርያትም ቢሆኑ እንዲህ ማድረጉን ቀላል ሆኖ አላገኙትም፤ በመሆኑም ኢየሱስ ‘ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው [“የሚገባው ማን እንደ ሆነ፣” የ1954 ትርጉም] ፈልጉ’ ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 10:11) ልክ እንደ ኢየሱስ ሐዋርያት አንተም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማዳመጥና ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን መፈለግ ይኖርብሃል። የምታነጋግራቸውን ሰዎች በሙሉ በጥሞና በማዳመጥና የእያንዳንዱን ግለሰብ ዝንባሌ በማጤን ምሥራቹን መማር የሚገባቸውን ሰዎች ልታገኝ ትችላለህ።

12. ለመንግሥቱ ምሥራች ፍላጎት ያሳየን ሰው መርዳትህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

12 ለመንግሥቱ ምሥራች የተወሰነ ፍላጎት ያሳየ ሰው ካገኘህ፣ ከግለሰቡ ጋር ከተለያያችሁ በኋላም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መማር ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ማሰብህ አስፈላጊ ነው። ከአንድ ሰው ጋር ባደረግኸው ውይይት ስለ ሰውየው የተረዳኸውን ነገር በማስታወሻህ ላይ መጻፍህ ቀጣይ የሆነ መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ያስችልሃል። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ስለ ሰውየው እምነት፣ አስተሳሰብ ወይም ስላለበት ሁኔታ ይበልጥ ለማወቅ እንድትችል በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብሃል።

13. አንድ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ምን ሊረዳህ ይችላል?

13 ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ያላቸውን አመለካከት እንዲነግሩህ ማበረታታት የምትችለው እንዴት ነው? በአንዳንድ አካባቢዎች “የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት አስቸጋሪ ይሆንብዎታል?” ብሎ መጠየቅ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ግለሰቡ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለውን አመለካከት ይጠቁማል። ሌላው መንገድ ደግሞ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብና “ይህ የሚፈጸም ይመስልዎታል?” ብሎ መጠየቅ ነው። ልክ እንደ ኢየሱስ ከሁኔታው ጋር ተስማሚ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ በአገልግሎትህ ስኬታማ ልትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ልታደርግበት የሚገባህ ነገር አለ።

ኢየሱስ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅሞባቸዋል

14. ሰዎችን በጥያቄ ሳታፋጥጥ አመለካከታቸውን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

14 ሰዎችን ሳታሸማቅቅ አመለካከታቸውን ለማወቅ ጥረት አድርግ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተጠቀመበትን ዘዴ ኮርጅ። ኢየሱስ ሰዎችን በጥያቄ አያፋጥጣቸውም ነበር። ከዚህ ይልቅ አድማጮቹን ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጓቸውን ጥያቄዎች ይጠይቅ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ቅን ለሆኑ ሰዎች እረፍት የሚሰጥና የመረጋጋት መንፈስ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ደግ አድማጭ ነበር። (ማቴዎስ 11:28) ሁሉም ዓይነት ሰዎች ወደ እሱ ቀርበው ችግራቸውን መንገር አይከብዳቸውም ነበር። (ማርቆስ 1:40፤ 5:35, 36፤ 10:13, 17, 46, 47) ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ስላሉት ሐሳቦች የሚሰማቸውን በነፃነት እንዲነግሩህ ከፈለግህ በጥያቄ አታፋጥጣቸው።

15, 16. ሰዎች ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች እንዲወያዩ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

15 ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ከመጠቀም በተጨማሪ ትኩረት የሚስብ አንድ ሐሳብ በመሰንዘርና ምላሻቸውን በማዳመጥ እንዲወያዩ ልታበረታታቸው ትችላለህ። ለምሳሌ ይህል፣ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሎት ነበር። (ዮሐንስ 3:3) ኒቆዲሞስ ይህ አባባል ስላስገረመው ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ለማወቅ በማሰብ ኢየሱስን ጥያቄ ለመጠየቅና የሚሰጠውን መልስ ለመስማት ተነሳስቷል። (ዮሐንስ 3:4-20) አንተም በዚህ መንገድ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ትችላለህ።

16 በዛሬው ጊዜ፣ በርካታ አዳዲስ ሃይማኖቶች የመፈጠራቸው ጉዳይ በአፍሪካ፣ በምሥራቅ አውሮፓና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ አካባቢዎች የመወያያ ርዕስ ሆኗል። በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ በአብዛኛው ውይይት ለመጀመር እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “የሃይማኖት መብዛት ያሳስበኛል። ሆኖም በቅርቡ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ አንድ እንደሚሆኑ እምነት አለኝ። ይህን ለማየት ይጓጓሉ?” ስለ ተስፋህ የሚያስደንቅ ነገር በመናገር ሰዎች ስለ ጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት እንዲገልጹ ማነሳሳት ትችላለህ። ሰዎች ለመመለስ የሚቀላቸው ሁለት አማራጭ መልስ ያለው ጥያቄ ሲቀርብላቸው ነው። (ማቴዎስ 17:25) የምታነጋግረው ሰው ላነሳኸው ጥያቄ መልስ ከሰጠህ በኋላ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ተጠቅመህ ራስህ መልሱን ስጥ። (ኢሳይያስ 11:9፤ ሶፎንያስ 3:9) በጥሞና በማዳመጥና የግለሰቡን ምላሽ በማስተዋል በሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ በምን ርዕስ ላይ ብትወያዩ እንደሚሻል ለመወሰን ትችላለህ።

ኢየሱስ ልጆችን ያዳምጥ ነበር

17. ኢየሱስ ለልጆች ትኩረት ይሰጥ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ለአዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ለልጆችም ትኩረት ይሰጥ ነበር። ልጆች ስለሚጫወቷቸው ጨዋታዎች እንዲሁም ስለሚናገሯቸው ነገሮች ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜም ወደ እሱ እንዲመጡ ይጋብዛቸው ነበር። (ሉቃስ 7:31, 32፤ 18:15-17) ኢየሱስን ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል በርካታ ልጆች ይገኙበት ነበር። ትናንሽ ልጆች መሲሑን ባወደሱበት ጊዜ ኢየሱስ ትኩረት ሰጥቶ የተመለከታቸው ከመሆኑም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍት በትንቢት የተናገሩት መሆኑን ገልጿል። (ማቴዎስ 14:21፤ 15:38፤ 21:15, 16) በዛሬው ጊዜም በርካታ ልጆች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እየሆኑ ነው። ታዲያ እነዚህን ልጆች እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?

18, 19. ልጅህ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?

18 ልጅህ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ለመርዳት ከፈለግህ ልታዳምጠው ይገባል። ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ አመለካከቶች ካሉት እነዚህን መረዳት ይኖርብሃል። ልጅህ የተናገረው ነገር ምንም ይሁን ምን በመጀመሪያ እሱን ማመስገንህ ጥበብ ይሆናል። ከዚያም ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያስተውል ለመርዳት ተስማሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ልትጠቀም ትችላለህ።

19 በዚህም ጊዜ ቢሆን ጥያቄዎች ጥሩ ሚና ይጫወታሉ። ልክ እንደ አዋቂዎች ልጆችም ቢሆኑ በጥያቄ የሚያፋጥጣቸው ሰው አይወዱም። ልጅህን ብዙ ከባድ ጥያቄዎች ጠይቀህ እንዲመልስልህ ከማስጨነቅ ይልቅ ስለ ራስህ አንድ አጠር ያለ ሐሳብ ብትነግረው የተሻለ አይሆንም? እየተወያያችሁ ካላችሁት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ልጅ ሳለህ ምን ይሰማህ እንደነበረና ለምን እንደዚያ እንደተሰማህ ልትገልጽለት ትችላለህ። ከዚያም “አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል?” በማለት ልትጠይቀው ትችላለህ። ልጅህ የሚሰጥህ ምላሽ ጠቃሚና የሚያበረታታ መንፈሳዊ ውይይት እንድታደርጉ በር ሊከፍት ይችላል።

ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን መምሰልህን ቀጥል

20, 21. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስትካፈል ጥሩ አድማጭ መሆን የሚገባህ ለምንድን ነው?

20 በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እየተወያየህ ያለኸው ከልጅህም ጋር ይሁን ከሌላ ሰው፣ ጥሩ አድማጭ መሆንህ በጣም አስፈላጊ ነው። በእርግጥም ማዳመጥ የፍቅር መግለጫ ነው። ማዳመጥህ ትሑት መሆንህን እንዲሁም ለተናጋሪው አክብሮት እንዳለህና ከልብ እንደምታስብለት ያሳያል። ማዳመጥ ግለሰቡ የሚናገራቸውን ነገሮች በትኩረት መከታተልን ይጠይቃል።

21 በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስትካፈል የምታነጋግረውን ሰው በጥሞና አዳምጥ። የሚናገረውን ነገር ትኩረት ሰጥተህ የምታዳምጥ ከሆነ ይበልጥ ስሜቱን ሊማርክ የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የትኛው እንደሆነ ለማስተዋል ትችላለህ። ከዚያም የኢየሱስን የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች በመጠቀም ግለሰቡን ለመርዳት ጣር። ይህን ስታደርግ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተወዳዳሪ የሌለውን ታላቁን አስተማሪ ትኮርጃለህ። ይህም ደስታና እርካታ ያስገኝልሃል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ሌሎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ያበረታታው እንዴት ነው?

• ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ሰዎች ያዳምጥ የነበረው ለምንድን ነው?

• በአገልግሎትህ ላይ ጥያቄዎችን መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

• ልጆች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምትሰብክበት ጊዜ ጥሩ አድማጭ ሁን

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆችን ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመረዳት ስንጥር ኢየሱስን እንኮርጃለን