በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን የጠየቁት መቼ ነበር?

የማቴዎስ ወንጌል ‘ከምሥራቅ የመጡ ጠቢባን’ ስጦታ ይዘው በማምጣት ኢየሱስን እንደጠየቁት ይናገራል። (ማቴዎስ 2:1-12) ሕፃኑን ኢየሱስን ለማየት የመጡት እነዚህ ጠቢባን ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች ምን ያህል እንደነበሩ የተገለጸ ነገር የለም። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ በቁጥር ሦስት እንደነበሩ የሚነገረውን ሐሳብ የሚደግፍ ጠንካራ ማስረጃ ካለመኖሩም በላይ ስማቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም።

ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ስተዲ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ማቴዎስ 2:11⁠ን አስመልክቶ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “በተለምዶ ከሚነገረው በተቃራኒ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን የጠየቁት እረኞቹ እንዳደረጉት በተወለደበት ምሽት በግርግም ውስጥ ሳለ አልነበረም። የመጡት ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሲሆን በመጡበት ወቅት ‘ከፍ ያለ ልጅ’ የነበረው ኢየሱስ ‘ቤት’ ውስጥ ነበር።” ሄሮድስ፣ ልጁ እንዲሞት ፈልጎ ስለነበረ በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ ባሉ መንደሮች ውስጥ ያሉ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆናቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ ማዘዙ ይህን ሐቅ ያረጋግጥልናል። ሄሮድስ በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆች እንዲገደሉ የወሰነው ከኮከብ ቆጣሪዎቹ ‘የተረዳውን ዘመን’ መሠረት አድርጎ ነው።—ማቴዎስ 2:16 የ1954 ትርጉም

ከዚህም በተጨማሪ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወርቅና ሌሎች ውድ ስጦታዎችን በማምጣት ኢየሱስን የጠየቁት በተወለደበት ምሽት ቢሆን ኖሮ ማርያም ኢየሱስን ከ40 ቀን በኋላ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ በወሰደችው ጊዜ ሁለት ዋኖሶችን ብቻ አታቀርብም ነበር። (ሉቃስ 2:22-24) በሕጉ ውስጥ ይህ ዝግጅት የተደረገው የበግ ጠቦት ማምጣት ለማይችሉ ድሃ ሰዎች ነበር። (ዘሌዋውያን 12:6-8) ይሁን እንጂ የኢየሱስ ወላጆች በጥሩ ጊዜ ላይ ያገኙት ይህ ውድ ስጦታ ግብጽ ውስጥ በቆዩበት ወቅት ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን በእጅጉ ሳይጠቅማቸው አልቀረም።—ማቴዎስ 2:13-15

ኢየሱስ አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ለመድረስ አራት ቀን የፈጀበት ለምን ነበር?

በመሠረቱ ኢየሱስ ይህን ያደረገው ሆን ብሎ ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ በዮሐንስ ምዕራፍ 11 ላይ ያለውን ዘገባ እንመርምር።

በቢታንያ የሚኖረውና የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር በጠና ሲታመም እህቶቹ ለኢየሱስ መልእክት ላኩበት። (ቁጥር 1-3) በወቅቱ ኢየሱስ ከቢታንያ የሁለት ቀን ገደማ መንገድ በሚያስኬድ ቦታ ላይ ይገኝ ነበር። (ዮሐንስ 10:40) አልዓዛር እንደታመመ የሚገልጸው መልእክት ኢየሱስ ጆሮ በደረሰበት ወቅት አልዓዛር ሞቶ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ኢየሱስ “በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን” ከቆየ በኋላ ወደ ቢታንያ ጉዞ ጀመረ። (ቁጥር 6, 7) ኢየሱስ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ካሳለፈ በኋላ ለሁለት ቀናት ተጉዞ አልዓዛር በሞተ በአራተኛው ቀን የተቀበረበት ቦታ ደረሰ።—ቁጥር 17

ኢየሱስ ቀደም ሲል ሁለት ሰዎችን ከሞት አስነስቶ ነበር። አንደኛውን ያስነሳው ግለሰቡ እንደሞተ ወዲያው ሲሆን ሌላውን ደግሞ በሞተበት ቀን ትንሽ ቆየት ብሎ ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 7:11-17፤ 8:49-55) ይሁንና ኢየሱስ ከሞተ አራት ቀን የሆነውንና አካሉ መፈራረስ የጀመረን ሰው ማስነሳት ይችላል? (ቁጥር 39) የሚገርመው፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ አይሁዳውያን “አንድ ሰው ከሞተ አራት ቀን ከሆነው” ምንም ተስፋ የለውም የሚል እምነት እንደነበራቸው ይናገራል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በአራተኛ ቀኑ ላይ አስከሬኑ መፈራረሰ የሚጀምር ሲሆን ለሦስት ቀናት በአስከሬኑ ላይ ታንዣብባለች ተብላ የምትታሰበው ነፍሱም በዚህ ጊዜ ሄዳለች።”

አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ከመጡት ሰዎች መካከል የአልዓዛርን መነሳት የሚጠራጠር ካለ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን የማየት አጋጣሚ ያገኛል። ኢየሱስ በተከፈተው መቃብር ፊት ቆሞ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ተጣራ። በዚህ ጊዜ ‘የሞተው ሰው ወጣ።’ (ቁጥር 43, 44) ብዙዎች ከሞት በኋላ ነፍስ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች የሚል የተሳሳተ እምነት አላቸው፤ ሆኖም ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ ይህ ሳይሆን ትንሣኤ ነው።—ሕዝቅኤል 18:4፤ ዮሐንስ 11:25