በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ይፈጸማል

ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ይፈጸማል

ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ይፈጸማል

“እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም። የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ።” (ኢሳይያስ 46:9, 10) ይህን የተናገረው ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል መተንበይ የሚችለው ይሖዋ ነው።

የሰው ልጅ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል መተንበይ እንደማይችል የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ እውነትን የሚፈልጉ ሁሉ ትንቢቶቹን ያጻፈው በእርግጥ አምላክ ስለመሆኑ እንዲመረምሩ ሊያነሳሳቸው ይገባል። እስቲ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመልከት።

በጥንት ጊዜ የነበሩ ብሔራት

አምላክ ባቢሎን፣ ኤዶም፣ ሞአብና አሞን ለዘላለም እንደሚጠፉ ትንቢት ተናግሯል። (ኤርምያስ 48:42፤ 49:17, 18፤ 51:24-26፤ አብድዩ 8, 18፤ ሶፎንያስ 2:8, 9) በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሕዝቦች ራሳቸውን የቻሉ ብሔራት ተደርገው መታየታቸው የቀረ መሆኑ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል ትክክለኛነት ያረጋግጣል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች ‘አንድ መንግሥት የቱንም ያህል ኃያል ቢሆን በመጨረሻ መጥፋቱ እንደማይቀር ማንኛውም ሰው አስቀድሞ ሊናገር ይችላል’ ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ይሁንና ይህ የመከራከሪያ ነጥብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በደፈናው ስለ አንድ ነገር ከመናገር አልፎ ዝርዝር መረጃዎችን የሚሰጥ መሆኑን ያላገናዘበ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ባቢሎን የምትጠፋው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ተዘግቧል። መጽሐፍ ቅዱስ ከተማይቱ በሜዶናውያን ድል እንደምትደረግ፣ የወራሪ ሠራዊቱ አዝማች ቂሮስ እንደሚባል እንዲሁም ለከተማይቱ እንደ መከላከያ አጥር የሆኑላት ወንዞች እንደሚደርቁ አስቀድሞ ተናግሯል።—ኢሳይያስ 13:17-19፤ 44:27 እስከ 45:1

መጽሐፍ ቅዱስ ድል የተደረጉ ብሔራት ሁሉ ለዘላለም እንደሚጠፉ አይናገርም። ለምሳሌ ያህል፣ ባቢሎናውያን ምርኮኞችን ነጻ የመልቀቅ ፖሊሲ ያልነበራቸው ቢሆንም፣ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እንደምትያዝ በሚናገረው ትንቢት ላይ አምላክ ከተማዋ ተመልሳ እንደምትገነባ ተናግሯል። (ኤርምያስ 24:4-7፤ 29:10፤ 30:18, 19) ይህ ትንቢት የተፈጸመ ሲሆን የአይሁድ ሕዝብም እስከ ዘመናችን ድረስ በብሔር ደረጃ አለ።

ከዚህም ባሻገር ይሖዋ ግብጽ የዓለም ኃያል መንግሥት መሆኗ እንደሚያከትም የተናገረ ቢሆንም ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ እንደምትሆን’ ተንብዮአል። ይህች የጥንት ኃያል መንግሥት ከጊዜ በኋላ ‘ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች።’ (ኤርምያስ 46:25, 26፤ ሕዝቅኤል 29:14, 15) ይህም ቢሆን በትክክል ተፈጽሟል። በተጨማሪም ይሖዋ ግሪክ የዓለም ኃያል መንግሥት መሆኗ እንደሚቀር ተንብዮአል። ይሁንና ይህች ብሔር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሕልውና ውጭ እንደምትሆን አልተናገረም። ይሖዋ ለዘላለም ይጠፋሉ ያላቸው በጥንት ዘመን የነበሩ ብሔራት ከሕልውና ውጭ መሆናቸውና ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደማይጠፉ ትንቢት የተናገረላቸው ብሔራት ደግሞ አሁንም ድረስ ያሉ መሆናቸው ምን ያስተምረናል? የአምላክ ቃል የያዛቸው ትንቢቶች ትክክለኛና እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ያስገነዝበናል።

አስደናቂ ዝርዝር መረጃዎችን የያዙ ትንቢቶች

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ የባቢሎንን አወዳደቅ በተመለከተ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ተናግሯል። በተመሳሳይም የሕዝቅኤል መጽሐፍ ስለ ጢሮስ አወዳደቅ ሲናገር ድንጋዮቿ፣ እንጨቶቿና የግንቦቿ ፍርስራሽ “ወደ ባሕር” እንደሚጣል ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 26:4, 5, 12) ይህ ትንቢት በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ፍጻሜውን አግኝቷል። የታላቁ እስክንድር ወታደሮች በየብስ ላይ የሚገኘውን የወደመውን ከተማ ፍርስራሽ ባሕሩ ውስጥ ደልድለው በደሴት ላይ ወደምትገኘው የከተማዋ ክፍል የሚወስድ መንገድ ከሠሩ በኋላ በደሴት ላይ የነበረችውን ከተማ ድል አደረጓት።

በዳንኤል 8:5-8, 21, 22 እና 11:3, 4 ላይ የሰፈረው ትንቢት ደግሞ እጅግ ታላቅ ስለሆነ አንድ “የግሪክ ንጉሥ” የሚገልጽ አስደናቂ ዝርዝር መግለጫ ይዟል። ይህ ገዥ እጅግ ገናና በሆነበት ወቅት እንደሚሞት እንዲሁም መንግሥቱ ለአራት እንደሚከፈልና ወራሾቹም ልጆቹ እንደማይሆኑ በትንቢት ተነግሯል። ትንቢቱ ከተጻፈ ከ200 ዓመት በኋላ ይህ ኃያል ንጉሥ ታላቁ እስክንድር ሆኖ ተገኘ። ታሪክ እንደሚነግረን ታላቁ እስክንድር ያለ ዕድሜው ሞቷል፤ መንግሥቱንም የተከፋፈሉት ልጆቹ ሳይሆኑ አራት ጄኔራሎቹ ናቸው።

አንዳንድ ሰዎች ይህ ትንቢት የተጻፈው ታሪኩ ካለፈ በኋላ ነው የሚል ትችት ይሰነዝራሉ። ይሁንና እስቲ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ከላይ የተጠቀሰውን ትንቢት በድጋሚ ልብ ብለህ ተመልከተው። ከትንቢት አንጻር ከተመለከትነው፣ የተሰጡት ዝርዝር መረጃዎች አስደናቂ ናቸው። ይሁንና ትንቢት እንዲመስል ተደርጎ የተጻፈ ታሪክ ነው ከተባለ ግን ብዙ ዝርዝር መረጃዎች እንደሚጎድሉት አይሰማህም? ከእስክንድር ዘመን በኋላ የኖረ አንድ አስመሳይ ጸሐፊ አንባቢዎቹን ለማስደመም እየሞከረ ከነበረ፣ እስክንድር እንደሞተ ሁለት ልጆቹ ንጉሥ ለመሆን እንደሚጥሩና በሰው እንደሚገደሉ ሳይጠቅስ የቀረው ለምንድን ነው? አራቱ ጄኔራሎች በተለያዩ የእስክንድር ግዛቶች ላይ መንግሥታቸውን የሚመሰርቱት ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ እንደሚሆን ያልጠቀሰው ለምንድን ነው? የዚህን ታላቅ ንጉሥና የአራቱን ጄኔራሎች ስም ያልተናገረውስ ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፉት ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ ነው የሚለው ትችት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በማስረጃ የተደገፈ አይደለም። ይህን ትችት የሚሰነዝሩት፣ ማስረጃዎቹን ከመመርመራቸው በፊት ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ አይቻልም ብለው የደመደሙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ስለማይቀበሉ ሁሉንም ነገር ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ለማብራራት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ አምላክ የትንቢቶቹ ምንጭ እሱ መሆኑን ለማስረገጥ የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን በመስጠት ጥበቡን አሳይቷል። *

በእያንዳንዱ ትንቢትና በአፈጻጸሙ ላይ ጊዜ ወስደህ የምታሰላስል ከሆነ እምነትህ ይጠናከራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለምን አታጠናም? በዚህ ረገድ “ቅዱሳን መጽሐፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና ጠቃሚ ናቸው” (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 343 እስከ 346 ላይ የሚገኘው ሠንጠረዥ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ። * ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ከወሰንክ ትንቢቶቹን የምታጠናው እምነትህን የመገንባት ግብ ይዘህ መሆን ይኖርበታል። አንቀጾቹን አንብበህ ለመጨረስ አትጣደፍ፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች በሙሉ በትክክል እንደሚፈጸሙ በሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ላይ አሰላስል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፉት ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ ነው የሚለው ትችት ትክክል አለመሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 106-111 ተመልከት።

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጠቅሙ መመሪያዎች

ልናሰላስልበት የሚገባን ሌላም ቁም ነገር አለ። የዓለም ኃያላን መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ በትክክል የተነበየው አምላክ ለዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጠቅሙ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችንም ሰጥቶናል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:-

ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል።​ገላትያ 6:7

ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።​የሐዋርያት ሥራ 20:35

ደስታ ማግኘት መንፈሳዊ ፍላጎትን በማርካት ላይ የተመካ ነው።​ማቴዎስ 5:3

እነዚህን መመሪያዎች በሕይወትህ የምትሠራባቸው ከሆነ ደስታና ስኬት እንደሚያስገኙልህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአምላክ ቃል አንዳንዶቹ ብሔራት ለዘላለም እንደሚጠፉ ተናግሯል

ኤዶም

ባቢሎን

አንዳንዶቹ ግን ለዘላለም እንደሚጠፉ አልተነበየም

ግሪክ

ግብጽ

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

WHO photo by Edouard Boubat

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቁ እስክንድር