በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለንጹሑ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

ለንጹሑ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ለንጹሑ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

ኤልያስ ሕዝቡ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሲያዘግም አሻግሮ ተመለከተ። ገና ጎህ መቅደዱ ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ በረሃብና በችግር የተጎሳቆለ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ለሦስት ዓመት ተኩል የዘለቀው ድርቅ በሕዝቡ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሏል።

ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ከሚጓዙት ሰዎች መካከል በትዕቢት የተሞሉትና የይሖዋ ነቢይ የሆነው ኤልያስን ክፉኛ የሚጠሉት 450 የበኣል ነቢያት ይገኙበታል። ንግሥት ኤልዛቤል በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችን ያስገደለች ቢሆንም ኤልያስ ግን የበኣልን አምልኮ በጽናት ከመቃወም ወደኋላ አላለም። ግን እስከ መቼ? የበኣል ካህናት ይህ ሰው ብቻውን ሊቋቋማቸው እንደማይችል ሆኖ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (1 ነገሥት 18:3, 19, 20) ንጉሥ አክዓብም በሠረገላው ሆኖ ወደ ተራራው ይጓዛል። እሱም ቢሆን ኤልያስን አይወደውም ነበር።

ከንጹሑ አምልኮ ጎን ብቻውን የቆመው ኤልያስ በዚያን ቀን በሕይወቱ አጋጥሞት የማያውቅ አንድ አስደናቂ ክንውን ሊመለከት ነው። ይህ ነቢይ መልካምና ክፉ በሆኑ ኃይሎች መካከል አስደናቂ ግድድር የሚታይበት መድረክ ሲዘጋጅ ይመለከታል። ሰዎች ከዚያን ጊዜ በፊት ይህን የመሰለ ግድድር አይተው አያውቁም። ኤልያስ ጎህ መቅደድ ሲጀምር ምን ተሰምቶት ይሆን? ኤልያስ ‘እንደ እኛው ሰው’ ስለሆነ የፍርሃት ስሜት ሳይሰማው አይቀርም። (ያዕቆብ 5:17) ሌላው ቢቀር፣ ኤልያስ እምነት የለሽ በሆነው ሕዝብ፣ በከዳተኛ መሪያቸውና እሱን ከመግደል ወደኋላ በማይሉት የበኣል ነቢያት መከበቡ የብቸኝነት ስሜት እንዳሳደረበት ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ነገሥት 18:22

ይሁን እንጂ እስራኤላውያንን ወደ ችግር የመራቸው ምን ነበር? ይህን ታሪክ ማወቅህስ ለምን ይጠቅምሃል? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችን ታሪክ በጥልቀት እንድንመረምርና ‘በእምነታቸው እንድንመስላቸው’ ይመክረናል። (ዕብራውያን 13:7) እስቲ የኤልያስን ታሪክ ተመልከት።

ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ግድድር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ

ኤልያስ በአብዛኛው የሕይወቱ ዘመን፣ የሚኖርበት ምድርም ሆነ የሕዝቡ ማንነት ልዩ መገለጫ የነበረው ንጹሕ አምልኮ ችላ ሲባልና ሲረገጥ ተመልክቷል። በወቅቱ እስራኤል ውስጥ በንጹሑና በሐሰተኛው ሃይማኖት ማለትም በይሖዋ አምልኮና በአካባቢያቸው የነበሩት ሕዝቦች በሚያመልኳቸው ጣዖታት መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግድድር ነበር። በኤልያስ ዘመን ይህ ግድድር ይበልጥ ተፋፋመ።

ንጉሥ አክዓብ የሲዶን ንጉሥ ልጅ የሆነችውን ኤልዛቤልን አግብቶ ነበር። ኤልዛቤል ደግሞ የበኣልን አምልኮ በእስራኤል ምድር ለማስፋፋትና የይሖዋን አምልኮ ለማጥፋት ቆርጣ ተነስታ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አክዓብ በሚስቱ ተጽዕኖ ሥር ወደቀ። ለበኣል ቤተ ጣዖትና መሠዊያ የሠራ ከመሆኑም ሌላ የዚህ ባዕድ አምላክ ቀንደኛ አምላኪ ሆነ። በዚህም ይሖዋን በእጅጉ አስቆጣው።—1 ነገሥት 16:30-33 *

የበዓል አምልኮ ይህን ያህል አስከፊ የሆነው ለምንድን ነው? አብዛኞቹን ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ እንዲርቁ በማባበል እስራኤልን አስቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች አስጸያፊ ነገሮችንና የጭካኔ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ያበረታታ ነበር። ይህም ወንዶችና ሴቶች በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጽሙትን ዝሙት፣ ልቅ የጾታ ብልግናን እንዲሁም ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ይጨምራል። ይሖዋ ነቢዩ የረሃቡን መቆም እስኪናገር ድረስ የሚዘልቅ ድርቅ በሕዝቡ ላይ እንደሚመጣ እንዲነግረው ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከው። (1 ነገሥት 17:1) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኤልያስ ሕዝቡንና የበኣልን ነቢያት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበስባቸው ለአክዓብ ነገረው።

ይሁንና ይህ ግድድር ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አንዳንዶች በአሁኑ ጊዜ የበኣል ቤተ ጣዖቶችና መሠዊያዎች ስለሌሉ ስለ በኣል አምልኮ የሚናገረው ታሪክ ለእኛ ጥቅም የለውም ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እንዲያው በታሪክነት እንዲወሳ ብቻ ተብሎ የተጻፈ አይደለም። (ሮሜ 15:4) “በኣል” የሚለው ቃል “ባለቤት” ወይም “ጌታ” የሚል ፍቺ አለው። ይሖዋ ሕዝቡ እሱን “በኣል” ወይም እንደ ባል አድርገው እንዲመርጡት ነግሯቸዋል። (ኢሳይያስ 54:5) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎችም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሳይሆን ሌሎች የተለያዩ ጌቶችን እያገለገሉ ነው ቢባል አትስማማም? እውነት ነው፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የሚሰጡት ለገንዘብ፣ ለሰብዓዊ ሥራ፣ ለመዝናኛ ወይም የጾታ ፍላጎትን ለማርካት አሊያም በይሖዋ ምትክ የሚመለኩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አማልክትን ለማምለክ ከሆነ እነዚህ ነገሮች ጌቶቻቸው እንዲሆኑ መርጠዋል ማለት ነው። (ማቴዎስ 6:24፤ ሮሜ 6:16) በመሆኑም የበኣል አምልኮ ዋነኛ ገጽታዎች በዛሬው ጊዜም ተስፋፍተዋል። ከዚህም የተነሳ በጥንት ዘመን በይሖዋና በበኣል መካከል የነበረውን ግድድር ማወቃችን ማንን ማገልገል እንዳለብን በጥበብ እንድንመርጥ ይረዳናል።

‘የዋለሉት’ እንዴት ነበር?

አንድ ሰው ነፋሻማ በሆነው የቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሆኖ መላውን የእስራኤል ምድር ማለትም ከታላቁ ባሕር (የሜድትራኒያን ባሕር) በታች ከሚገኘው የቂሶን ወንዝ ሸለቆ አንስቶ በሰሜን አቅጣጫ ርቀው እስከሚገኙት የሊባኖስ ተራሮች ድረስ ማየት ይችላል። * ይሁንና በዚህ ወሳኝ ቀን ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ የእስራኤልን ምድር የሚያይ ሰው ምድሪቱ በድርቅ የተጎዳች መሆኗን ማወቅ አይሳነውም። በአንድ ወቅት በለምነቷ ትታወቅ የነበረችውና ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች የሰጣት ይህች ምድር የሞት ጥላ አጥልቶባታል። የአምላክ ሕዝቦች በመረጡት የሞኝነት አካሄድ ምክንያት ምድሪቱ በፀሐይ ሐሩር ተጠብሳለች። ኤልያስ ወደ ተራራው ወደሚወጣው ሕዝብ ቀረብ ብሎ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አላቸው።—1 ነገሥት 18:21

ኤልያስ ‘በሁለት ሐሳብ ትዋልላላችሁ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ሕዝቡ ከይሖዋ ወይም ከበኣል አምልኮ አንዱን መምረጥ እንዳለበት አልተገነዘበም ነበር። ሁለቱንም አንድ ላይ ቀላቅለው ማምለክ እንደሚችሉ ማለትም በአንድ በኩል አስጸያፊ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም የበኣልን ልብ ደስ ማሰኘት በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ አምላክን እርዳታ መጠየቅ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ምናልባትም ይህን ያደረጉት በኣል እርሻቸውንና ከብቶቻቸውን ሲባርክላቸው ‘የሰራዊት አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ደግሞ በጦርነት ላይ እንደሚረዳቸው አስበው ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙኤል 17:45) እነዚህ ሰዎች በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙዎች የሚዘነጉትን አንድ ሐቅ ይኸውም ይሖዋ አምልኮን ከማንም ጋር የማይጋራ መሆኑን ሳያስተውሉ ቀርተው ነበር። ይሖዋ፣ ሰዎች እሱን ብቻ እንዲያመልኩት ይፈልጋል፤ ደግሞም አምልኮ ይገባዋል። ይሖዋንና ሌሎች አማልክትን በአንድ ላይ ማምለክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ አስጸያፊ ተግባር ነው!—ዘፀአት 20:5

በመሆኑም እስራኤላውያን በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት እንደሚሞክር ሰው ‘ይዋልሉ’ ነበር። በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ስህተት እየሠሩ ነው! እነዚህ ሰዎች “በኣልን” የመሰሉ ነገሮች የሕይወታቸው ክፍል እንዲሆኑ በመፍቀዳቸው አምላክን ከማምለክ ወደኋላ ብለዋል። በመሆኑም ኤልያስ እስራኤላውያን ከመዋለል እንዲቆጠቡ ያቀረበላቸው ጥሪ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ስለያዙት ነገሮችና ስለ አምልኳችን መለስ ብለን እንድንመረምር ይረዳናል።

አስገራሚ ፈተና

በመቀጠል ኤልያስ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ፈተና አቀረበ። ፈተናው በጣም ቀላል ነበር። የበኣል ካህናት መሠዊያ ይሠሩና በላዩ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ከዚያም መሥዋዕቱን በእሳት እንዲያቀጣጥል አምላካቸውን ይለምኑታል። ኤልያስም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። ኤልያስ “በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው” ሲል ነገራቸው። ኤልያስ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ አሳምሮ ያውቅ ነበር። እጅግ ጠንካራ እምነት ስለነበረው የበኣል ነቢያት ቅድሚያውን ወስደው እንዲሞክሩ ፈቀደላቸው። ከዚህም ባሻገር ለመሥዋዕት የሚቀርበውን ወይፈን እንዲመርጡና ወደ አምላካቸው ወደ በኣል በቅድሚያ ጸሎት እንዲያቀርቡ እንዲሁም ተቃዋሚዎቹ ያስፈልገናል ያሉትን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ አጋጣሚውን ሰጣቸው። *1 ነገሥት 18:24, 25

የምንኖረው ተአምራት በሚፈጸሙበት ዘመን ላይ አይደለም። ይሁንና ይሖዋ አልተለወጠም። እኛም ልክ እንደ ኤልያስ በእሱ ልንተማመን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማማ ነገር ሲናገሩ እነሱን በመፍራት ያሻቸውን እንዲናገሩ አንፈቅድላቸውም። ልክ እንደ ኤልያስ፣ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ እውነተኛውን አምላክ እንጠይቃለን። ይህንንም የምናደርገው በራሳችን ሳይሆን ነገሮችን “ለማቅናት” ተብሎ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል በመታመን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የበኣል ነቢያት መሥዋዕታቸውን አዘጋጅተው አምላካቸውን መጥራት ጀመሩ። “በኣል ሆይ ስማን” በማለት ደጋግመው ጮኹ። በዚህ ሁኔታ ብዙ ሰዓታት አለፉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም” በማለት ይናገራል። እኩለ ቀን ላይ ኤልያስ፣ በኣል ሥራ በዝቶበት ወይም በሐሳብ ተውጦ ሊሆን ይችላል፤ ተኝቶም ከሆነ የሚቀሰቅሰው ሰው ያስፈልገዋል እያለ በካህናቱ ላይ ያፌዝባቸው ጀመር። ኤልያስ እነዚህን አስመሳዮች “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ!” አላቸው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኤልያስ የበኣል አምልኮ እንዲሁ ሰዎችን ለማታለል ተብሎ የተፈጠረ ልብ ወለድ መሆኑን ስለተገነዘበ የአምላክ ሕዝቦችም የበኣል አምልኮ ሐሰተኛ መሆኑን እንዲያስተውሉ ፈልጎ ነበር።—1 ነገሥት 18:26, 27

ሁኔታው ያበሳጫቸው የበኣል ካህናትም ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ‘እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ማቁሰል’ ጀመሩ። ይህ ሙከራቸውም ቢሆን ከንቱ ነበር! “አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።” (1 ነገሥት 18:28, 29) በእርግጥም በኣል ሕያው አምላክ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የፈጠረው የሐሰት አምላክ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ ከይሖዋ ሌላ ጌታ መምረጥ ለሐዘን ብሎም ለውርደት ይዳርጋል።—መዝሙር 25:3፤ 115:4-8

ፈተናው ምላሽ አገኘ

በመጨረሻም፣ አመሻሹ ላይ የኤልያስ ተራ ደረሰ። ኤልያስ ፈርሶ የነበረውን የይሖዋ መሠዊያ በድጋሚ ሠራ፤ ይህን መሠዊያ ያፈረሱት የንጹሕ አምልኮ ጠላቶች መሆናቸው እሙን ነው። ኤልያስ መሠዊያውን ለመሥራት 12 ድንጋዮችን የተጠቀመ ሲሆን ይህም አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ቀደም ሲል ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተሰጣቸውን ሕግ የመታዘዝ ግዴታ እንዳለባቸው ለማስታወስ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ከዚያም መሥዋዕቱን በመሠዊያው ላይ ካኖረ በኋላ አካባቢው በውኃ እንዲጥለቀለቅ አደረገ። ውኃው የተገኘው በአቅራቢያው ከነበረው የሜድትራኒያን ባሕር ሊሆን ይችላል። ከዚህም ባሻገር በመሠዊያው ዙሪያ ጉድጓድ እንዲቆፈርና በውኃ እንዲሞላ አደረገ። የበዓል ነቢያት ያስፈልገናል ያሉትን ሁሉ እንዲያደርጉና ምቹ አጋጣሚ እንዲያገኙ ፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም በራሱ ላይ ግን ሁኔታዎቹ ይበልጥ ከባድ እንዲሆኑ አደረገ። ይህ በአምላክ ላይ ትልቅ እምነት እንደነበረው ያሳያል።—1 ነገሥት 18:30-35

ሁሉም ነገር ከተዘጋጀ በኋላ ኤልያስ ጸሎት አቀረበ። ኤልያስ ያቀረበው ልብ የሚነካ አጭር ጸሎት በጣም ያሳስበው የነበረው ነገር ምን መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኤልያስ ሕዝቡ “የእስራኤል አምላክ” ይሖዋ እንጂ በኣል እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ፈልጎ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሕዝቡ እሱ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን እንዲረዳና ክብርም ሆነ ምሥጋና ሊሰጥ የሚገባው ለአምላክ መሆኑን እንዲያውቅ ፈልጓል። በመጨረሻም ይሖዋ ‘ልባቸውን እንዲመልስላቸው’ በመጠየቅ ለሕዝቡ እንደሚያስብ አሳይቷል። (1 ነገሥት 18:36, 37) ምንም እንኳ እስራኤላውያን የተከተሉት እምነት የለሽ አካሄድ ብዙ ችግሮችን ያስከተለ ቢሆንም ኤልያስ ይወዳቸው ነበር። እኛስ ለአምላክ በምናቀርበው ጸሎት ላይ የስሙ ጉዳይ እንደሚያሳስበን መግለጽ እንዲሁም ወደ አምላክ በትሕትና መቅረብና ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ርኅራኄ እንዳለን ማሳየት እንችል ይሆን?

ኤልያስ ጸሎት ከማቅረቡ በፊት ሕዝቡ ‘ይሖዋም ልክ እንደ በኣል ሐሰተኛ አምላክ ይሆን እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከጸሎቱ በኋላ እንዲህ ስላለው ነገር ለማሰብ የሚያስችል ጊዜ እንኳ አልነበራቸውም። ዘገባው ስለ ሁኔታው ሲገልጽ “ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች” ይላል። (1 ነገሥት 18:38) እንዴት ያለ አስደናቂ መልስ ነው! ታዲያ ሕዝቡ ምን ተሰማው?

ሕዝቡም ይህን ሲመለከቱ “አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” በማለት ጮኹ። (1 ነገሥት 18:39) በመጨረሻ፣ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ተገነዘቡ። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እምነት እንዳላቸው አላሳዩም ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ፣ ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ከሰማይ እሳት ልኮ መልስ መስጠቱን ካዩ በኋላ እውነተኛ አምላክ መሆኑን መናገራቸው፣ እምነት ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም ኤልያስ እምነታቸውን በሌላ መንገድ እንዲያሳዩ ጠየቃቸው። ከበርካታ ዓመታት በፊት ሊያደርጉት ይገባ የነበረውን ማለትም የይሖዋን ሕግ እንዲታዘዙ ነገራቸው። የአምላክ ሕግ ሐሰተኛ ነቢያትና ጣዖት አምላኪዎች መገደል እንዳለባቸው ይናገራል። (ዘዳግም 13:5-9) እነዚህ የበኣል ነቢያት የይሖዋ አምላክ ቀንደኛ ጠላቶች የነበሩ ሲሆን የአምላክን ዓላማ ሆነ ብለው ይቃወሙ ነበር። ምሕረት ይገባቸው ይሆን? ካህናቱ ምንም የማያውቁ ሕፃናትን ከነሕይወታቸው ለበኣል መሥዋዕት ሲያደርጓቸው የርኅራኄ ስሜት ታይቶባቸው ነበር? (ምሳሌ 21:13፤ ኤርምያስ 19:5) በፍጹም፣ እነዚህ ሰዎች ምሕረት አይገባቸውም ነበር። በመሆኑም ኤልያስ ሕዝቡ የበኣልን ነቢያት እንዲገድሏቸው ያዘዘ ሲሆን እነሱም የታዘዙትን ፈጽመዋል።—1 ነገሥት 18:40

በዛሬው ጊዜ፣ አንዳንድ ተቺዎች በቀርሜሎስ ተራራ የቀረበው ፈተና በዚህ መንገድ መደምደሙ ትክክል እንዳልነበር ይናገራሉ። እንዲያውም አክራሪ ሰዎች በሃይማኖት ስም የሚፈጽሙት የዓመጽ ድርጊት ተቀባይነት እንዳለው ለማስረዳት ይህን ታሪክ እንደ ማስረጃ አድርገው ሊጠቅሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው። በዛሬው ጊዜ ደግሞ የዓመጽ ድርጊት የሚፈጽሙ በርካታ አክራሪ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ። ሆኖም ኤልያስ አክራሪ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን በመወከል የአምላክን የጽድቅ ፍርድ አስፈጽሟል። ከዚህም በላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በክፉዎች ላይ ሰይፍ በማንሳት ረገድ የኤልያስን ዓይነት አካሄድ ሊከተሉ እንደማይችሉ ያውቃሉ። መሲሑ ከመጣ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሊከተሉት የሚገባው መመሪያ ኢየሱስ ለጴጥሮስ እንደሚከተለው ሲል የተናገረው ነው:- “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።” (ማቴዎስ 26:52) ወደፊት ይሖዋ መለኮታዊውን የጥፋት ፍርድ ለማስፈጸም በልጁ ይጠቀማል።

ከአንድ እውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቀው በአምላክ ላይ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ መኖር ነው። (ዮሐንስ 3:16) ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ደግሞ እንደ ኤልያስ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን የእምነት ምሳሌ መከተል ነው። ኤልያስ ይሖዋን ብቻ ያመለከ ሲሆን ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታቷል። ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የሚጠቀምበትን የሐሰት ሃይማኖት በድፍረት አጋልጧል። በራሱ ችሎታና እሱ በፈለገው መንገድ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ በይሖዋ ይታመን ነበር። በእርግጥም ኤልያስ ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል። እኛም በእምነቱ እንምሰለው!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ኤልያስ ከአክዓብ ጋር ስለነበረው የቀድሞ ግንኙነት ይበልጥ ለማወቅ በሚያዝያ 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የኤልያስን የመሰለ እምነት አለህን?” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.13 የቀርሜሎስ ተራራ ከበታቹ ካለው ባሕር ከሚነፍሰው እርጥበት አዘል አየር በቂ ዝናብና ጠል ስለሚያገኝ አብዛኛውን ጊዜ ለምለም ነበር። ዝናብ የሚያዘንበው በኣል እንደሆነ ተደርጎ ይታመን ስለነበር ይህ ተራራ የበኣል አምልኮ ማዕከል እንደነበር ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ባዶና ጠፍ የሆነው የቀርሜሎስ ተራራ የበኣል አምልኮ ሐሰት መሆኑን ለማጋለጥ ተስማሚ ቦታ ነበር።

^ አን.17 ኤልያስ በመሠዊያው ላይ “እሳት አታንድዱበት” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ጣዖት አምላኪዎች አንዳንዴ ከመሠዊያው በታች ቀዳዳ ያበጁና ከሥር ሆነው እንጨቱን በመለኮስ እሳቱ የመጣው ከሰው ኃይል በላይ ከሆነ አካል እንደሆነ አድርገው ይናገሩ ነበር።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከይሖዋ ሌላ ጌታ መምረጥ ለሐዘን ይዳርጋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ነው!