በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ፍቅር እናት ለልጇ ባላት ፍቅር ላይ ይንጸባረቃል

የአምላክ ፍቅር እናት ለልጇ ባላት ፍቅር ላይ ይንጸባረቃል

የአምላክ ፍቅር እናት ለልጇ ባላት ፍቅር ላይ ይንጸባረቃል

“እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን [አ]ልረሳሽም።”—ኢሳይያስ 49:15

አንዲት እናት በእቅፏ ያለውን ሕፃን ስታጠባ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህ ሁኔታ እናት ለልጇ ርኅራኄና ፍቅር ከምታሳይባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ፓም የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ትላለች:- “ለመጀመሪያ ጊዜ ልጄን ሳቅፍ ሆዴ ስፍስፍ አለ፤ ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለብኝም ተሰማኝ።”

በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሐቅ ቢሆንም እንኳ የእናት ፍቅር በልጇ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቶች አረጋግጠዋል። በዓለም የጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ዘርፍ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከእናታቸው ተለይተው ያደጉ ሕፃናት ደስታ የራቃቸውና በጭንቀት የተዋጡ እንደሚሆኑ፣ አንዳንዴም ከፍተኛ የፍርሃት ስሜት እንደሚያድርባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።” ይኸው ጽሑፍ አንድን ጥናት ጠቅሶ እንደተናገረው፣ ከልጅነታቸው አንስቶ ፍቅርና ትኩረት ያገኙ ልጆች ችላ ከተባሉት ይልቅ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ አላቸው።

ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ዩ ሲ ኤል ኤ የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት አለን ሾር፣ የእናት ፍቅር ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ልጅ በሕፃንነቱ ከእናቱ ጋር የሚያሳልፋቸው ጊዜያት በኋለኛው ሕይወቱ ከሌሎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ያሳድራል።”

የሚያሳዝነው ግን የመንፈስ ጭንቀት፣ ሕመም ወይም ሌሎች ጫናዎች አንዲትን እናት ልጇን ችላ እንድትል አልፎ ተርፎም ‘የምታጠባውን ልጇን እንድትረሳ’ ሊያደርጓት ይችላሉ። (ኢሳይያስ 49:15) እርግጥ ነው፣ ይህ ሁኔታ የተለመደ አይደለም። እንዲያውም እናቶች ልጆቻቸውን መውደዳቸው ተፈጥሯዊ ነው። ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ፣ እናቶች በወሊድ ጊዜ ኦክሲቶሲን የተባለ ሆርሞን በከፍተኛ መጠን የሚያመነጩ ሲሆን ይህም የተለጠጠው ማሕፀን ወደ ቦታው እንዲመለስ ከማድረጉም ሌላ ወተት በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሚያመነጩት ይህ ሆርሞን እናት ለልጇ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንድታሳይ ይገፋፋታል ተብሎም ይታመናል።

የፍቅር ምንጭ ማን ነው?

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች፣ ሰዎች በእናትና በልጅ መካከል ያለውን ዓይነት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት የጀመሩት በአጋጣሚ እንደሆነና ይህንን ባሕርይ የሚያንጸባርቁትም ዝርያቸው እንዳይጠፋ ስለሚረዳቸው እንደሆነ ያስተምራሉ። ለአብነት ያህል፣ ማዘሪንግ ሜጋዚን የተባለ መጽሔት በኢንተርኔት ባስተላለፈው ዘገባ ላይ እንደሚከተለው ብሏል:- “በደረታቸው ከሚሳቡት እንስሳት በወረስነው አንጎል ላይ የተጨመረው ሊምቢክ ሲስተም ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው የአንጎል ክፍል ስሜቶቻችን የሚፈልቁበት ቦታ ነው። እናቶች ከልጆቻቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርገው ይኸው የአንጎላችን ክፍል ነው።”

እርግጥ ነው፣ ሊምቢክ ሲስተም የተባለው የአንጎላችን ክፍል ከስሜቶቻችን ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ‘እናት ለልጇ ያላት ፍቅር የተሳቢ እንስሳት አንጎል በአጋጣሚ በመሻሻሉ የተገኘ ነው’ መባሉ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል?

እስቲ ከዚህ የተለየ ሐሳብ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ መልክ መሆኑን ይናገራል፤ ይህም ሲባል የተፈጠርነው የአምላክን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ተደርገን ነው ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:27) የአምላክ ዋነኛው ባሕርይ ፍቅር ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም” በማለት ጽፏል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አምላክ ፍቅር አለው እንደማይል ልብ በል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ራሱ ፍቅር ነው። የፍቅር ምንጭ እሱ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል። ፍቅር ከቶ አይወድቅም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) ታዲያ ከሁሉ የላቀው ይህ ባሕርይ እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ ነው ቢባል ምክንያታዊ ይሆናል?

አንተስ ምን ይሰማሃል?

ከላይ ባለው አንቀጽ ላይ ስለ ፍቅር ምንነት የተሰጠውን መግለጫ ስታነብ አንድ ሰው ይህን የመሰለውን ፍቅር እንዲያሳይህ ሳትጓጓ አልቀረህም። እንዲህ ቢሰማህ ምንም አያስደንቅም። ለምን? ምክንያቱም እኛ ‘የአምላክ ልጆች ነን።’ (የሐዋርያት ሥራ 17:29) ሌሎችን የመውደድም ሆነ በሌሎች ዘንድ የመወደድ ፍላጎት እንዲኖረን ተደርገን ተፈጥረናል። እንዲሁም አምላክ ለእኛ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ፣ አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እናት ለልጇ ካላት ፍቅር ይበልጥ ጥልቅና ዘላቂ መሆኑን ያሳያል!

ይሁን እንጂ እንዲህ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል:- ‘አምላክ ጥበበኛ፣ ኃያልና አፍቃሪ ከሆነ የሰው ልጆች የሚደርስባቸውን መከራ የማያስወግደው ለምንድን ነው? ልጆች በአጭሩ እንዲቀጩ፣ የፍትሕ መጓደል እንዲኖር እንዲሁም ቸልተኛና ስግብግብ የሆኑ ሰዎች ምድርን እንዲያበላሹ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚያሻቸው ናቸው።

የአግኖስቲክ ፍልስፍና አራማጆች ከሚሉት በተቃራኒ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ይቻላል። በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችለዋል። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች አንተም ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ግብዣ ያቀርቡልሃል። የአምላክን ቃል በማጥናት እንዲሁም የፍጥረት ሥራዎቹን በመመልከት ስለ እሱ ያለህ እውቀት እንዲጨመር ባደረግህ መጠን አምላክ ከእኛ የራቀና ሊታወቅ የማይችል እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። እንዲያውም አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆንህ አይቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 17:27

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እናት ለልጇ ካላት ፍቅር ይበልጥ ዘላቂ ነው