በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ አምላክ መንግሥት

ስለ አምላክ መንግሥት

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

ስለ አምላክ መንግሥት

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት መላውን ምድር የሚገዛ መስተዳድር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ . . . ‘መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።’”—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ዳንኤል 2:44

የአምላክ መንግሥት ገዥዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ የተወለደው የአምላክ መንግሥት ገዥ እንዲሆን ነው። አንድ መልአክ ለኢየሱስ እናት “ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለዘላለም ይነግሣል” በማለት ነግሯት ነበር። (ሉቃስ 1:30-33) ከዚህ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ከተከታዮቹ መካከል የተወሰኑት ከእሱ ጋር እንዲገዙ መርጧል። ሐዋርያቱን እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ።” (ሉቃስ 22:28, 29፤ ዳንኤል 7:27) በአጠቃላይ 144,000 የሚሆኑ የኢየሱስ ተከታዮች አብረውት ይገዛሉ።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1

መንግሥቱ የሚገዛው የት ሆኖ ነው?

የአምላክ መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል:- “[ወደ ሰማይ] የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። . . . ወደ አብ [እሄዳለሁ።]”—ዮሐንስ 14:2, 3, 12፤ ዳንኤል 7:13, 14

የአምላክ መንግሥት ክፋትን ምን ያደርጋል?

ኢየሱስ ክፉ ሰዎችን ከምድር ላይ የሚያጠፋ ሲሆን እንደሚከተለው ሲል ተናግሮ ነበር:- “የሰው ልጅ [ኢየሱስ] ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ . . . ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤ . . . ‘[ክፉዎች] ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።’”—ማቴዎስ 25:31-34, 46

የመንግሥቱ ተገዥዎች በመሆን በምድር ላይ የሚኖሩት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5፤ መዝሙር 37:29፤ 72:8) ወደፊት ምድር እርስ በርስ በሚዋደዱ ሰዎች ትሞላለች። ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸዋል:- “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35

የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ላሉ የሰው ዘሮች ምን ያደርግላቸዋል?

ኢየሱስ የሰው ልጆችን ከማንኛውም በሽታ ይፈውሳል። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለሕዝቡ ‘ስለ አምላክ መንግሥት የነገራቸው ሲሆን ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈውሷቸው ነበር።’ (ሉቃስ 9:11) ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን በራእይ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ . . . ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ ‘እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ . . . እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት [አይኖርም]።’”—ራእይ 21:1-4

የአምላክ መንግሥት ምድርን ገነት ያደርጋል። ከኢየሱስ ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” በማለት የጠየቀው ሲሆን ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል።—ሉቃስ 23:42, 43፤ ኢሳይያስ 11:4-9

ለተጨማሪ ማብራሪያ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።