በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጠና የታመሙ ሰዎችን ማጽናናት

በጠና የታመሙ ሰዎችን ማጽናናት

በጠና የታመሙ ሰዎችን ማጽናናት

“የእናቴ በሽታ የማይድን መሆኑን ስሰማ ሁኔታውን ማመን አዳጋች ሆነብኝ። በጣም የምወዳት እናቴ ልትሞት እንደሆነ ስገነዘብ ነገሩን መቀበል ስለከበደኝ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጬ ነበር።”—ግሬስ፣ ካናዳ

በጠና የታመመ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ያላቸው ሰዎች የሚወዱት ሰው ሊሞት እንደሆነ ሲሰሙ በከፍተኛ ጭንቀት ሊዋጡና ምን እንደሚያደርጉ ግራ ሊገባቸው ይችላል። አንዳንዶች ‘ሁኔታውን በተመለከተ እውነቱን ፍርጥርጥ አድርጌ ለታማሚው መንገር ይኖርብኝ ይሆን’ የሚለው ነገር ያሳስባቸዋል። ሌሎች ደግሞ የሚወዱት ሰው ሲሠቃይ ምናልባትም በሕመሙ ምክንያት የዋጋ ቢስነት ስሜት ሲሰማው መመልከት የሚያሳድርባቸውን ጭንቀት መቋቋም ይችሉ እንደሆነ እርግጠኞች አይደሉም። በርካታ ሰዎች፣ ግለሰቡ ሞት አፋፍ ላይ ሲደርስ ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አለማወቃቸው ያስጨንቃቸዋል።

እንዲህ ያለ አሳዛኝ ዜና ስትሰማ ከምትወስደው እርምጃ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ማወቅ ያስፈልግሃል? በዚህ አስጨናቂ ወቅት እውነተኛ “ወዳጅ” መሆን እንዲሁም ማጽናኛና ድጋፍ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?—ምሳሌ 17:17

ተፈጥሯዊ ስሜት

ማንኛውም ሰው የሚወደው ግለሰብ በጠና ታምሞ ሲሠቃይ መመልከቱ እንደሚያስጨንቀው የታወቀ ነው። በየጊዜው ሰዎች ሲሞቱ የሚመለከቱት እንዲሁም ከሕሙማን ጋር ስለ ሞት የሚነጋገሩት ሐኪሞችም እንኳ የማይድን በሽታ ለያዘው አንድ ሰው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት የሚጠይቅ ነገር ሲገጥማቸው አብዛኛውን ጊዜ ይረበሻሉ አልፎ ተርፎም አቅም እንደሌላቸው ይሰማቸዋል።

አንተም፣ የምትወደው ሰው ሲሠቃይ ስሜትህን መቆጣጠር ይሳንህ ይሆናል። በጠና የታመሙ እህት የነበራቸው በብራዚል የሚኖሩ ሆዛ የተባሉ አንዲት አረጋዊት፣ “እጅግ የምትወዱት ሰው ያለማቋረጥ በሕመም ሲሠቃይ መመልከት በጣም ከባድ ነገር ነው” በማለት ተናግረዋል። ታማኝ የነበረው ሙሴ እህቱ በለምጽ በተመታችበት ወቅት “አምላክ ሆይ፤ እባክህ ፈውሳት” በማለት ጮዃል!—ዘኍልቍ 12:12, 13

ርኅሩኅ በሆነው አምላካችን በይሖዋ አምሳል ስለተፈጠርን አንድ የምንወደው ሰው በጠና ሲታመም መጨነቃችን አይቀርም። (ዘፍጥረት 1:27፤ ኢሳይያስ 63:9) ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው ሥቃይ ምን ይሰማዋል? የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀው ኢየሱስ ምን እንደተሰማው ልብ በል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ በበሽታ ለሚሠቃዩ ሰዎች ‘ራርቶላቸዋል።’ (ማቴዎስ 20:29-34፤ ማርቆስ 1:40, 41) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ የወዳጁ የአልዓዛር ሞት፣ በወዳጅ ዘመዶቹ ላይ ያሳደረውን ስሜት ሲመለከት በጣም ከማዘኑ የተነሳ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:32-35) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን እንደ ጠላት አድርጎ የሚገልጸው ሲሆን በቅርቡ በሽታና ሞት ፈጽሞ የማይኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣም ተስፋ ይሰጣል።—1 ቆሮንቶስ 15:26፤ ራእይ 21:3, 4

የምትወደው ሰው ለሞት በሚያደርስ በሽታ ስለመያዙ የሚገልጸውን አሳዛኝ ዜና ስትሰማ አንድን ሰው ተወቃሽ ልታደርግ እንደምትችል ግልጽ ነው። ይሁንና ማርታ ኦርቲስ የተባሉ ሐኪም፣ በማይድን በሽታ ለተያዙ ሰዎች የሚደረገውን እንክብካቤ አስመልክተው ባዘጋጁት የመመረቂያ ጽሑፍ ላይ የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- “ታማሚው ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት የሕክምና ቡድኑን፣ ነርሶችን ወይም ራስህን አትውቀስ። እንዲህ ማድረግህ ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ከማሻከርና ሰዎች አንገብጋቢ በሆነው ነገር ላይ እንዳያተኩሩ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ታማሚው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት ነው።” ታዲያ የምትወደው ሰው፣ የመዳን ተስፋ እንደሌለው ማወቁ የሚያስከትልበትን ጭንቀትም ሆነ ሕመሙን እንዲቋቋም ለመርዳት ምን ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

በሕመሙ ሳይሆን በግለሰቡ ላይ ትኩረት አድርግ

ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ሕመምተኛው በደረሰበት አካላዊ ጉዳት ላይ ሳይሆን በእሱ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ሣራ የተባለች አንዲት ነርስ እንዲህ ብላለች:- “ታማሚው ጤነኛ በነበረበት ወቅት የተነሳቸውን ፎቶግራፎች በቁም ነገር እመለከታለሁ። ከዚህ ቀደም ስላሳለፋቸው ነገሮች ሲያጫውተኝ በጥሞና አዳምጠዋለሁ። እንዲህ ማድረጌ ደግሞ ግለሰቡ አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የቀድሞ ሕይወቱን እንዲሁም ያሳለፈውን ታሪክ መለስ ብዬ ማስታወስ እንድችል ረድቶኛል።”

አን-ካትሪን የተባለች ሌላ ነርስ ደግሞ በግለሰቡ ላይ በሚታየው አካላዊ ጉዳት ላይ ብቻ ትኩረት እንዳታደርግ የረዳት ምን እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “የሕመምተኛውን ዓይን ትክ ብዬ በመመልከት ሁኔታውን ለማሻሻል ማድረግ ስለምችላቸው ነገሮች አስባለሁ።” ዘ ኒድስ ኦቭ ዘ ዳይንግ—ኤ ጋይድ ፎር ብሪንጊንግ ሆፕ፣ ኮምፈርት፣ ኤንድ ላቭ ቱ ላይፍስ ፋይናል ቻፕተር የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “አንድ የምትወዱት ሰው በበሽታ አሊያም በአደጋ ምክንያት አካላዊ ጉዳት ሲደርስበት በእጅጉ እንደምትረበሹ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ወቅት ልታደርጉት የምትችሉት ከሁሉ የተሻለ ነገር በሽታው በግለሰቡ ላይ ያስከተለውን ለውጥ ችላ በማለት በማንነቱ ላይ ማተኮር ነው።”

እርግጥ ነው፣ እንዲህ ማድረግ ራስን መግዛትና ሐሞተ ኮስታራ መሆንን ይጠይቃል። በጠና የታመሙ ሰዎችን አዘውትሮ የሚጠይቀው ዦርዥ የተባለ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች “የምንወደው ሰው ያለበት በሽታ፣ እሱን ከመርዳት ወደኋላ እንድንል እንዳያደርገን ለግለሰቡ ልባዊ ፍቅር ሊኖረን ይገባል” በማለት ተናግሯል። በሕመሙ ላይ ሳይሆን በግለሰቡ ላይ ማተኮርህ አንተንም ሆነ ሕመምተኛውን ይጠቅማል። በካንሰር የተያዙ ልጆችን የምትንከባከበው ኢቮን “ታማሚዎቹ ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት እንዳያጡ ልትረዳቸው እንደምትችል ማወቅህ ሰውነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጎዳ መሄዱ የሚያሳድርብህን ስሜት እንድትቋቋም ይረዳሃል” ብላለች።

ለማዳመጥ ዝግጁ ሁን

አንዳንድ ሰዎች፣ ግለሰቡን በጣም የሚወዱት ቢሆንም እንኳ ሞት አፋፍ ላይ በሚደርስበት ወቅት እሱን ለመጠየቅ ሊያቅማሙ ይችላሉ። ለምን? ምክንያቱም ‘ምን እለዋለሁ’ የሚለው ሐሳብ ያስጨንቃቸዋል። በማይድን በሽታ የተያዘች ጓደኛዋን በቅርቡ ያስታመመችው አን-ካትሪን፣ ዝምታ ያለውን ጥቅም እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “አንድን ሰው የምናጽናናው በምንናገረው ቃላት ብቻ ሳይሆን ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜትና በምናደርገው ድርጊት ጭምር ነው። ለእነዚህ ሰዎች እንደምናስብላቸው ከሚያሳዩት ነገሮች መካከል፣ ወንበር አምጥተን አጠገባቸው መቀመጥና እጃቸውን ደበስበስ ማድረግ ይገኙበታል፤ እንዲሁም ምን እንደሚሰማቸው ሲነግሩን ውስጣችን ከተረበሸ እንባችንን ለመቆጣጠር መታገል አይኖርብንም።”

የታመመው ሰው እውነተኛ ስሜቱን በግልጽ ሊነግርህ ይፈልግ ይሆናል። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ሕመምተኛው፣ ወዳጆቹ ስለሚጨነቁ ከበድ ያሉ የግል ጉዳዮች አንስተው ከእሱ ጋር ከመነጋገር እንደሚቆጠቡ ያውቃል። የታማሚው ጓደኞችና የቤተሰቡ አባላት እሱን የመርዳት ፍላጎት ይኖራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታማሚውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን አንስተው ከእሱ ጋር ባለማውራት ሌላው ቀርቶ ከጤንነቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን በመደበቅ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራሉ። እንዲህ ያሉትን መረጃዎች መደበቅ ምን ውጤት ያስከትላል? በማይድን በሽታ የተያዙ ሰዎችን የሚረዱ አንዲት ሐኪም እንደገለጹት ከሆነ እውነታውን ለመደበቅ የሚደረገው ጥረት፣ ሕመምተኛው በሽታውን መቀበልና ስለ ሕመሙ በግልጽ ማውራት እንዳይችል ያደርገዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ እሱን መንከባከብ የሚፈልጉት ወዳጆቹ ኃይላቸውን ሕመምተኛውን ለመርዳት እንዳያውሉት እንቅፋት ይሆንባቸዋል። በመሆኑም የታመመው ሰው፣ ስለራሱ ሁኔታና እንደሚሞት ማወቁ ስላሳደረበት ስሜት በግልጽ መናገር እስከፈለገ ድረስ ሊከለከል አይገባውም።

በጥንት ጊዜ የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ከሞት ጋር በተፋጠጡበት ጊዜ የተሰማቸውን ፍርሃት ለይሖዋ አምላክ ከመንገር ወደኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል፣ የ39 ዓመቱ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሊሞት እንደሆነ ሲያውቅ የተሰማውን ከፍተኛ ጭንቀት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 38:9-12, 18-20) በተመሳሳይም በማይድን በሽታ የተያዙ ሰዎች ሕይወታቸው ሊቀጭ መሆኑን በማወቃቸው የተሰማቸውን ሐዘን እንዳይገልጹ ሊከለከሉ አይገባም። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ቦታዎችን ለመጎብኘት፣ ቤተሰብ ለመመሥረት፣ የልጅ ልጆቻቸው አድገው ለማየት ወይም አምላክን በተሟላ መንገድ ለማገልገል የነበራቸው ሕልም እንደማይሳካ ማወቃቸው እንዲያዝኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ ‘ወዳጅ ዘመዶቻችን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቃቸው ይሸሹናል’ የሚል ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። (ኢዮብ 19:16-18) እነዚህ ሰዎች ‘በሽታው የሚያስከትልብኝን ሥቃይ እችለው ይሆን’ ወይም ‘ሰውነቴን እንደልቤ ማዘዝ ያቅተኝ ይሆን’ በሚለው ፍርሃት አሊያም እንደሚሞቱ ማወቃቸው በሚያስከትልባቸው ጭንቀት ብቻ እንኳ አእምሯቸው ሊወጠር ይችላል።

አን-ካትሪን እንዲህ ብላለች:- “ታማሚው የተሰማውን ሲነግርህ ጣልቃ ባለመግባት ወይም በእሱ ላይ ባለመፍረድ አሊያም የሚፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ባለመናገር የሚልህን ማዳመጥህ በጣም አስፈላጊ ነው። የግለሰቡን ትክክለኛ ስሜት ለማወቅና ምኞቱን፣ ስጋቱን እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን አመለካከት ለመረዳት የሚያስችልህ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህ ነው።”

አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ነገሮች መረዳት

ወዳጅህ የተሰጠው ከባድ ሕክምናም ይሁን ሕክምናው ያስከተለበት የጎንዮሽ ጉዳት ሥቃዩን እንዳባባሰበት ስትመለከት በጣም ከመረበሽህ የተነሳ የሕመምተኛውን መሠረታዊ ፍላጎት ይኸውም የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው ትዘነጋ ይሆናል።

በአንዳንድ ማኅበረሰብ፣ የታመመ የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች ሕመምተኛው ስላለበት ሁኔታ እውነቱን ባለመናገር አልፎ ተርፎም የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት በተመለከተ የራሱን ውሳኔ እንዳያደርግ አጋጣሚውን በመንፈግ ታማሚውን እንደጠቀሙት ሆኖ ይሰማቸዋል። በሌላ ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ ሌላ ችግር ይስተዋላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዤሪ የተባለ አንድ ነርስ “አንዳንድ ጊዜ ታማሚውን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች፣ ግለሰቡ አጠገባቸው የሌለ ይመስል ስለ እሱ ማውራት ይቀናቸዋል” ሲል ተናግሯል። እንዲህ ያሉት ልማዶች የታማሚውን መብት ይጋፋሉ።

ሌላው አስፈላጊ ነገር ደግሞ ተስፋ ነው። ጥሩ ሕክምና በሚሰጥባቸው አገሮች ውስጥ ተስፋ ብዙውን ጊዜ የሚያያዘው ውጤታማ ሕክምና ከማግኘት ጋር ነው። የካንሰር ሕመም ለሦስት ጊዜ ያህል ያገረሸባቸውን እናቷን ያስታመመችው ሚሼል እንደሚከተለው ብላለች:- “እናቴ ሌላ ዓይነት ሕክምና የማግኘት ወይም ሌላ ሐኪም የማማከር ሐሳብ ካላት ፍላጎቷን ለማሟላት ጥረት አደርጋለሁ። እውነታውን መቀበል እንዳለብኝ ሆኖም እናቴን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ላለመናገር መጠንቀቅ እንደሚገባኝ ተገንዝቤያለሁ።”

የታመመው ሰው ምንም የመዳን ተስፋ ባይኖረውስ? በማይድን በሽታ የተያዙ ሰዎች ስለ ሞት በግልጽ መነጋገር እንደሚፈልጉ አትዘንጋ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዦርዥ የተባለው ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል:- “ለሕመምተኛው በቅርቡ እንደሚሞት በግልጽ መንገር በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለው እርምጃ ግለሰቡ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ ያስችለዋል።” ሕመምተኛው ይህን ዝግጅት ማድረጉ ከመሞቱ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ለማስተካከል የሚያስችለው ከመሆኑም ባሻገር በሌሎች ላይ ሸክም ሆኜ ይሆን ከሚለው ጭንቀት ይገላግለዋል።

እርግጥ ነው፣ እነዚህን ነገሮች አንስቶ መነጋገሩ ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ እንዲህ ያለው ግልጽ ውይይት የልብህን አውጥተህ ለመናገር የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ይሰጥሃል። ሞት አፋፍ ላይ ያለው ሰው ከዚህ በፊት የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት፣ መጸጸቱን ለመግለጽ ወይም ይቅርታ ለመጠየቅ ይፈልግ ይሆናል። ይህ ውይይት ከዚህ ሰው ጋር የነበራችሁን ዝምድና ይበልጥ ያጠናክረዋል።

በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ማጽናኛ መስጠት

ሊሞት ለተቃረበ ሰው ማጽናኛ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው? ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ኦርቲስ እንዲህ ብለዋል:- “የታመመው ግለሰብ እንድታደርጉለት የሚፈልገው ነገር ካለ እንዲጠይቃችሁ አድርጉ። ከዚያም በትኩረት አዳምጡት። የሚቻል ከሆነ የሚፈልገውን ነገር አሟሉለት፤ ካልሆነ ደግሞ በግልጽ ንገሩት።”

ሞት አፋፍ ላይ ያለ ሰው፣ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጠገቡ እንዲሆኑለት ይፈልግ ይሆናል። ዦርዥ፣ “ታማሚው አቅም በማጣቱ ምክንያት ብዙ መናገር ባይችልም እንኳ እነዚህ ሰዎች ከአጠገቡ እንዳይርቁ በማድረግ እርዱት” ብሏል። ከታማሚው ጋር የሚገናኙት በስልክ ብቻ ቢሆንም እንኳ ይህ አጋጣሚ እርስ በርስ ለመበረታታትና አብረው ለመጸለይ ያስችላል። የምትወዳቸውን ሦስት ሰዎች በተከታታይ በሞት የተነጠቀችው ክርስቲና የተባለች አንዲት ካናዳዊት ሴት፣ “ሕይወታቸው የሚያልፍበት ሰዓት እየተቃረበ በሄደ መጠን ክርስቲያን ወዳጆቻቸው በሚያቀርቡት ጸሎት ይበልጥ ይታመኑ ነበር” በማለት ተናግራለች።

በሕመምተኛው ፊት ማልቀስ ሊያሳፍርህ ይገባል? በፍጹም። በታመመው ሰው ፊት ማልቀስህ ወዳጅህ አንተን እንዲያጽናናህ አጋጣሚውን ይሰጠዋል። ዘ ኒድስ ኦቭ ዳይንግ የተባለው መጽሐፍ “ሞት አፋፍ ላይ ያለ ሰው ሌሎችን ሲያጽናና መመልከት በጣም ልብ የሚነካ ነው፤ ይህ ደግሞ ለሰውየው እጅግ አስፈላጊ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ከፍተኛ እንክብካቤ ሲደረግለት የቆየው ይህ ግለሰብ ሌሎችን በሚያጽናናበት ወቅት እንደ አሳቢ ጓደኛ፣ አባት ወይም እናት በመሆን እንደቀድሞው ሌሎችን የመንከባከብ አጋጣሚ ያገኛል።

ታማሚው ሞት አፋፍ ላይ በሚደርስበት ወቅት አብረኸው እንዳትሆን የሚያደርጉህ አንዳንድ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ሆኖም የታመመው ሰው የተኛው ሆስፒታልም ይሁን ቤት፣ አብረኸው ለመሆን የምትችልበት ሁኔታ ካለ እስከ ሕይወቱ ማብቂያ ድረስ ከጎኑ ባትለይ ጥሩ ይሆናል። ይህ የመጨረሻ ሰዓት ከዚያ በፊት በቃላት ያልገለጽከውን ስሜትህን አውጥተህ ለመናገር የምትችልበትን አጋጣሚ ይሰጥሃል። ሞት አፋፍ ላይ ያለው ሰው ምንም መናገር ባይችል እንኳ እሱን ከመሰናበት እንዲሁም ፍቅርህንና በትንሣኤ እንደምታገኘው ያለህን ተስፋ ከመግለጽ ወደኋላ አትበል።—ኢዮብ 14:14, 15፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

እነዚህን የመጨረሻ ደቂቃዎች በሚገባ ከተጠቀምክባቸው የኋላ ኋላ ሊሰማህ ከሚችለው ጸጸት ትድናለህ። እንዲያውም ያለህን ጥልቅ ስሜት የገለጽክባቸውን እነዚህን አጋጣሚዎች ባስታወስክ ቁጥር መጽናናት ትችላለህ። እንዲህ በማድረግ “ለክፉ ቀን” የተወለደ እውነተኛ ወዳጅ መሆንህን ታስመሠክራለህ።—ምሳሌ 17:17

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሕመሙ ላይ ሳይሆን በግለሰቡ ላይ ማተኮርህ አንተንም ሆነ ሕመምተኛውን ይጠቅማል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ ታማሚ ያሉትን መብቶች ማክበር የሚቻልበት መንገድ

የመዳን ተስፋ የሌላቸው ሕሙማን ዕድሜያቸውን ለማራዘም በሚደረግ ጥረት ብዙ ሳይንገላቱ በሰላም የመሞት መብታቸው እንዲከበርላቸው ለማድረግ በበርካታ አገሮች ውስጥ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። የታማሚውን ፍላጎት የሚገልጽ በጽሑፍ የሰፈረ ሰነድ መኖሩ ከላይ የተጠቀሰውን መብት በማክበር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፤ እንዲሁም ታማሚው በቤቱ አሊያም በማይድን በሽታ ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ በሚሰጥበት ተቋም ውስጥ ለመሞት ያለውን ፍላጎት ያስከብርለታል።

የታማሚውን ፍላጎት የሚገልጽ አስቀድሞ የተዘጋጀ ሰነድ መኖሩ የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት:-

• በሐኪሞችና በታማሚው ዘመዶች መካከል የሚኖረውን የሐሳብ ልውውጥ ቀላል ያደርገዋል

• የታማሚው ቤተሰብ ለግለሰቡ የሚሰጠውን ሕክምና በሚመለከት ‘ምን ውሳኔ እናድርግ’ ብሎ እንዳይጨነቅ ይረዳል

• አላስፈላጊና ፋይዳ የሌለው እንዲሁም ከባድና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሕክምና የመስጠት አጋጣሚን ይቀንሳል

የታማሚውን ፍላጎት የሚገልጽ አስቀድሞ የተዘጋጀ ሰነድ ይበልጥ ጠቀሜታ እንዲኖረው ከተፈለገ ቢያንስ ከዚህ በታች የተገለጹትን ነገሮችን ማካተት ይኖርበታል:-

• ከምትወስደው ሕክምና ጋር በተያያዘ በአንተ ቦታ ሆኖ ውሳኔ ሊያደርግልህ የሚችለው ግለሰብ ስም

• የጤንነትህ ሁኔታ ምንም የመዳን ተስፋ ከሌለው የምትወስዳቸውና የማትወስዳቸው የሕክምና ዓይነቶች ዝርዝር

• ከተቻለ፣ የምትመርጣቸውን የሕክምና ዓይነቶች የሚያውቅ ሐኪም ስም

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታማሚው አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በነበረው ሕይወት እንዲሁም ባሳለፈው ታሪክ ላይ ትኩረት አድርግ