በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ምሕረት አሳይቶኛል

አምላክ ምሕረት አሳይቶኛል

አምላክ ምሕረት አሳይቶኛል

ቦልፌንክ ሞክኒክ እንደተናገረው

“አሁን ጠንካራ መሆን አለብህ።” እነዚህ ቃላት እናቴ በችኮላ አቅፋ ስትሰናበተኝ በአጽንኦት የተናገረቻቸው ናቸው። ከዚያም ወታደሮች ከእናቴ ለይተው ችሎት ፊት አቀረቡኝ። በመጨረሻም የአምስት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። ብዙ ሰዎች የተበየነባቸውን ፍርድ ሲሰሙ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ይዋጡ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ እኔ የአእምሮ ሰላም ያገኘሁት በዚህ ወቅት ነበር። እንዲህ ያልኩት ለምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

ይህ ሁኔታ የተከሰተው በ1952 ስሎቬኒያ ውስጥ ነበር። * እርግጥ ታሪኩ የሚጀምረው ይህ ከመሆኑ ከ20 ዓመታት በፊት ማለትም በ1930 ነው። በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአገራችን ብዙ ሰዎችን በአንድ ቀን ለማጥመቅ ዝግጅት አድርገው ነበር። ወላጆቼ በርታ እና ፍራንትስ ሞክኒክ ከሚጠመቁት መካከል ነበሩ። በዚያን ጊዜ የስድስት ዓመት ልጅ ስሆን እህቴ ማይዳ ደግሞ አራት ዓመቷ ነበር። በማሪቦር ከተማ በሚገኘው ቤታችን ውስጥ በርካታ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ ነበር።

በ1933 አዶልፍ ሂትለር በጀርመን ሥልጣን የያዘ ሲሆን በይሖዋ ምሥክሮች ላይም ስደት ማድረስ ጀመረ። በዚህ ጊዜ በርካታ ጀርመናውያን የይሖዋ ምሥክሮች፣ የስብከቱን ሥራ ለማገዝ ወደ ዩጎዝላቪያ ተዛወሩ። ወላጆቼ እነዚህን ታማኝ ሰዎች በእንግድነት መቀበል ያስደስታቸው ነበር። ከእነዚህ እንግዶች መካከል አንዱ የሆነውን ወንድም ማርቲን ፖትጺንገርን በደንብ አስታውሰዋለሁ፤ ይህ ወንድም በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ለዘጠኝ ዓመት ታስሯል። ይህ ከሆነ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወንድም ማርቲን ከ1977 አንስቶ በሞት እስካንቀላፋበት እስከ 1988 ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል።

ወንድም ማርቲን ወደ ቤታችን ሲመጣ የሚተኛው እኔ አልጋ ላይ ሲሆን እኔና እህቴ ደግሞ ከወላጆቻችን ጋር እንተኛ ነበር። ወንድም ማርቲን፣ በኪስ የምትያዝ አነስተኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ነበረችው። ልጅ ሳለሁ ይህችን የምታምር መጽሐፍ ማገላበጥ ያስደስተኝ ነበር።

ከባድ ስደት የነበረበት ጊዜ

ሂትለር ይበልጥ ኃያል በሆነበት በ1936 ወላጆቼ በሉሰርን፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው ታሪካዊ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። አባቴ ጥሩ ድምፅ ስለነበረው በዚህ አጋጣሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን ሲያነብ እንዲቀዳ ተጋበዘ። ከጊዜ በኋላ በመላው ስሎቬኒያ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች እነዚህን ንግግሮች አዳምጠዋቸዋል። ይህ የማይረሳ ስብሰባ ከተካሄደ ብዙም ሳይቆይ በአውሮፓ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከባድ ስደት ደረሰባቸው። ብዙዎቹ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ሥቃይ የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ፤ ሚያዝያ 1941 ደግሞ የጀርመን ወታደሮች ዩጎዝላቪያን በከፊል ተቆጣጠሩ። በዚህ ወቅት በስሎቬኒያ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ተዘጉ። ከቤት ውጭ በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እንዳናወራም ተከለከልን። የይሖዋ ምሥክሮች ከማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኞች ስለነበሩ ጦርነቱን ለመደገፍ ፈቃደኞች አልሆኑም። * በዚህም የተነሳ ብዙዎች የታሰሩ ሲሆን በደንብ አውቀው የነበረውን ፍራንትስ ድሮዝግ የተባለውን ወጣት ጨምሮ አንዳንዶቹ ተገደሉ። የናዚ ወታደሮች ከቤታችን መቶ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ ሰዎችን ይረሽኑ ነበር። እናቴ ተኩሱን ላለመስማት ጆሮዋን በጨርቅ ለመድፈን ስትጥር የነበረውን ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። ፍራንትስ በጣም ለሚቀርበው ጓደኛው የላከውን የስንብት ደብዳቤ የደመደመው “በአምላክ መንግሥት እንገናኝ” በሚሉት ቃላት ነበር።

እጅግ የተጸጸትኩበት ውሳኔ

በዚያን ወቅት የ19 ዓመት ወጣት ነበርኩ። ፍራንትስ የነበረውን ጽኑ አቋም ባደንቅም እኔ ግን የፍርሃት ስሜት አደረብኝ። ‘እኔንም ይገድሉኝ ይሆን?’ የሚለው ሐሳብ ያስጨንቀኝ ነበር። እምነቴ ጠንካራ ካለመሆኑም በላይ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና አልነበረኝም። በዚህ ጊዜ ለውትድርና ተጠራሁ። ፍርሃቴን ለመቋቋም የሚያስችል እምነት ስላልነበረኝ ለቀረበልኝ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠሁ።

ከዚያም ከሩሲያ ጋር ውጊያ ወደሚካሄድበት የጦር ግንባር ተላክሁ። ብዙም ሳይቆይ በአጠገቤ ያሉት ጓደኞቼ ሲረፈረፉ ተመለከትኩ። ጦርነቱ በጣም አሰቃቂ ነበር። ሕሊናዬ ይበልጥ ይወቅሰኝ ጀመር። ይሖዋ ይቅር እንዲለኝና በትክክለኛው መንገድ ለመጓዝ የሚያስችለኝን ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ለመንኩት። በተሰነዘረብን ከባድ ጥቃት የተነሳ በሠራዊታችን ውስጥ ግር ግር ሲፈጠር ማምለጫ ቀዳዳ አገኘሁ።

እርግጥ ከተያዝኩ እንደምገደል አውቅ ነበር። በቀጣዮቹ ሰባት ወራት በተለያዩ ቦታዎች ስደበቅ ቆየሁ። በዚህ ወቅት ለማይዳ፣ “አሠሪዬን ተሰናብቼ ሌላ ቦታ እየሠራሁ ነው” የሚል መልእክት የያዘ ፖስት ካርድ ለመላክ ችዬ ነበር። እንዲህ ያልኩት አምላክን ለማገልገል መወሰኔን ልገልጽላት ፈልጌ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ የተወሰኑ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጎኝ ነበር።

የሕብረ ብሔሩ ጦር ጀርመንን ድል ካደረገ ከሦስት ወራት በኋላ በነሐሴ 1945 ወደ ማሪቦር ተመለስኩ። የሚገርመው ነገር አባቴ፣ እናቴና እህቴ ከዚህ አስከፊ ጦርነት በሕይወት ተርፈው ነበር። በወቅቱ አገሪቷን የተቆጣጠሩት ኮሚኒስቶች ቢሆኑም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ያደርሱ ነበር። የስብከቱ ሥራ በይፋ ቢታገድም የይሖዋ ምሥክሮች በድብቅ ሥራቸውን ያካሂዱ ነበር።

የካቲት 1947 ሩዶልፍ ካሊ፣ ዱሻን ሚኪች እና ኤድመንት ስትሮፕኒክ የተባሉ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሞት ተፈረደባቸው። ይሁንና በኋላ ላይ የሞት ፍርዱ ወደ 20 ዓመት እስራት ተለወጠላቸው። የመገናኛ ብዙኃን ስለዚህ ሁኔታ በሰፊው የዘገቡ ሲሆን በርካታ ሰዎችም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ኢፍትሐዊ ድርጊት እየተፈጸመ እንዳለ ማወቅ ችለዋል። እኔም እነዚህን የዜና ዘገባዎች ሳነብ በጸጸት ስሜት ተዋጥኩ። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

መንፈሳዊ ጥንካሬ አገኘሁ

በሕይወቴ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከደረሱብኝ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በጥብቅ መከተል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ፤ በመሆኑም በድብቅ በሚካሄደው የስብከት ሥራ ለመካፈል የቻልኩትን ያህል ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናቴ እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ መጥፎ ልማዶችን ለማስወገድ የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አገኘሁ።

በ1951 ራሴን ለአምላክ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ፤ ስለሆነም ከአሥር ዓመታት ገደማ በፊት ትቼው ወደነበረው የክርስትና ሕይወት ተመለስኩ። በመጨረሻም ይሖዋ፣ ታማኝና ፍቅሩ የማይቀዘቅዝ እውነተኛ አባት እንደሆነ ተገነዘብኩ። በወጣትነቴ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ አድርጌ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ይቅር ባይ ስለመሆኑ የሚናገረው ሐሳብ አጽናንቶኛል። አምላክ ልክ እንደ አፍቃሪ አባት ‘በፍቅር ሰንሰለት ስቦኛል።’—ሆሴዕ 11:4

በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት በይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በድብቅ እናካሂድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንሰብክ ነበር። ከተጠመቅኩ ዓመት ሳይሞላኝ ተያዝኩ። ወደ ችሎት ከመግባቴ በፊት ከእናቴ ጋር ለአጭር ጊዜ ተገናኝተን ነበር። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት እናቴ ካቀፈችኝ በኋላ “አሁን ጠንካራ መሆን አለብህ” አለችኝ። የአምስት ዓመት እስራት እንደተፈረደብኝ ስሰማ አልተረበሽኩም።

በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ከሦስት ሰዎች ጋር ታሰርኩ፤ በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሌላ መንገድ ሊሰሙ ለማይችሉት ለእነዚህ ሰዎች የመናገር አጋጣሚ አገኘሁ። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ባይኖሩኝም እንኳ ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በግሌ ሳጠና ያነበብኳቸውን ጥቅሶች ከነማብራሪያቸው ማስታወስ መቻሌ በጣም አስገርሞኝ ነበር። አብረውኝ ለታሰሩት ሰዎች ‘በእስር ቤት ውስጥ ለአምስት ዓመት መቆየት ቢኖርብኝ እንኳ ይሖዋ ብርታት ይሰጠኛል’ በማለት ደጋግሜ እነግራቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ከዚያ ቀደም ብሎ እንድፈታ ይፈቅድ ይሆናል። ‘እሱ ካለ ደግሞ ማን ሊከለክለው ይችላል?’ እያልኩ አስብ ነበር።

የተወሰነ ነፃነት አገኘን

በኅዳር 1953 መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ምሕረት ማድረጉን በይፋ አሳወቀ። በመሆኑም በእስር ቤት የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ነፃ ወጡ። ከእስር ስፈታ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ከሁለት ወራት በፊት እንደተነሳ ተገነዘብኩ። ከዚያም ወዲያውኑ ጉባኤዎችንና የስብከቱን ሥራ ማደራጀት ጀመርን። መሃል ማሪቦር በሚገኝ አንድ ሕንፃ ምድር ቤት ውስጥ መሰብሰቢያ ቦታ ያገኘን ሲሆን በግድግዳውም ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች—የማሪቦር ጉባኤ” የሚል ምልክት ለጠፍንበት። በዚህ መንገድ ይሖዋን በነፃነት ማገልገል በመቻላችን ልባችን በአድናቆት ተሞላ።

በ1961 መጀመሪያ ላይ አቅኚ ሆኜ በሙሉ ጊዜ ማገልገል ጀመርኩ። ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ በዩጎዝላቪያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ይህ ቢሮ የሚገኘው በዛግሬብ፣ ክሮኤሽያ ነበር። በወቅቱ ቅርንጫፍ ቢሮ ሆኖ ያገለግል የነበረው አንድ ትንሽ ክፍል ሲሆን በዚያም ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ይሠሩ ነበር። በአቅራቢያው የነበሩ ክርስቲያኖችም የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በአገሪቱ ቋንቋ ስናዘጋጅ ቀን ቀን እየመጡ ይረዱን ነበር።

በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያን ሴቶች ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን ያግዙን ነበር። ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል መጽሔቶችን መስፋት ይገኝበታል። እኔም ማጣሪያ ንባብ ማድረግን፣ መተርጎምን፣ መላላክንና ሪፖርት ማጠናቀርን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን አከናውን ነበር።

የምድብ ለውጥ

በ1964 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ይህ ደግሞ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች አዘውትሮ መጎብኘትንና በመንፈሳዊ እንዲጠናከሩ መርዳትን ይጨምራል። ይህን ሥራ በጣም እወደው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ጉባኤ ወደ ቀጣዩ ጉባኤ የምጓዘው በአውቶቡስ ወይም በባቡር ነበር። በትናንሽ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት አብዛኛውን ጊዜ በብስክሌት ወይም በእግሬ እሄድ የነበረ ሲሆን አንዳንዴም እስከ ቁርጭምጭሚቴ በሚደርስ ማጥ ውስጥ መጓዝ ነበረብኝ።

አንዳንድ ጊዜ የሚያስቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት አንድ ክርስቲያን ወንድም ቀጥሎ ወደምጎበኘው ጉባኤ በጋሪ ይዞኝ እየሄደ ሳለ ጋሪው መንገጫገጭ ጀመረ። ከዚያም አንደኛው ጎማ ወለቀና ሁለታችንም መሬት ላይ ተንደባለልን። መሬት ላይ ሳለን ፈረሱን ቀና ብለን ስናየው እሱም በመገረም ዓይኑን አፍጥጦ ተመለከተን። ዓመታት ካለፉ በኋላም ሁኔታው ትዝ ባለን ቁጥር እንስቃለን። በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩት ወዳጆቻችን ያሳዩን ከግብዝነት የራቀ ፍቅር እጅግ የሚያስደስት ነበር።

ኖቪ ሳድ ከተማ ውስጥ ማሪካ ከተባለች አቅኚ ጋር ተዋወቅሁ። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላት ፍቅርና በአገልግሎት ቀናተኛ መሆኗ እጅግ ማረከኝ፤ በመሆኑም ላገባት ፈለግሁ። ከተጋባን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ጉባኤዎችን ማገልገል ጀመርን።

ቤተሰቦቼ በእገዳው ወቅት የተለያዩ ችግሮች ደርሶባቸዋል። አባቴ በጦርነቱ ወቅት ከጠላት ጋር ተባብረሃል ተብሎ ከሥራው ተባረረ። ወደ ሥራው ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ ቢጥርም ልፋቱ ከንቱ ሆነ፤ በመሆኑም ተስፋ ቆረጠ። ለጊዜው እምነቱ የተዳከመ ቢሆንም ከመሞቱ በፊት መንፈሳዊ ጥንካሬ ማግኘት ችሎ ነበር። በ1984 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በጉባኤ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ትሑትና ታማኝ የሆነችው እናቴ የሞተችው አባቴ ከመሞቱ ቀደም ብሎ በ1965 ነበር። ማይዳ ደግሞ በማሪቦር በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ በማገልገል ላይ ትገኛለች።

በኦስትሪያ ማገልገል

በ1972 እኔና ማሪካ ወደ ኦስትሪያ በመዛወር በዚያ ለሚገኙ የዩጎዝላቪያ ስደተኞች እንድንሰብክ ግብዣ ቀረበልን። ወደ ዋናው ከተማ ቪየና ስንደርስ ይህ ቋሚ የአገልግሎት ምድባችን ይሆናል ብለን አላሰብንም ነበር። ቀስ በቀስ በዩጎዝላቪያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች በመላው ኦስትሪያ ተቋቋሙ።

ከጊዜ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆንኩ ሲሆን ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን በመላው አገሪቱ የሚገኙ እነዚህን ጉባኤዎችና ቡድኖች መጎብኘት ጀመርኩ። ቆየት ብሎም በጀርመንና በስዊዘርላንድ የሚገኙ በእነዚህ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎችን እንድንጎበኝ ግብዣ ቀረበልን። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎችን በማደራጀት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት ችያለሁ።

አንዳንድ ጊዜ የበላይ አካል አባላት በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር፤ በአንድ ወቅት ከወንድም ማርቲን ፖትጺንገር ጋር ተገናኘን። ከ40 ዓመታት ገደማ በፊት በተደጋጋሚ ቤታችን በእንግድነት በሚመጣበት ወቅት ስለነበሩት ሁኔታዎች አንስተን ተጫወትን። እኔም “በኪስህ የምትይዛትን ያችን ኢንሳይክሎፒዲያ ማገላበጥ እንዴት ያስደስተኝ እንደነበር ታስታውሳለህ?” ብዬ ጠየቅኩት።

ወንድም ማርቲን፣ “አንዴ ቆየኝ” ብሎኝ ከነበርንበት ክፍል ወጣ። ከዚያም መጽሐፏን ይዞ መጣና ሰጠኝ። “ይህ ከአንድ ጓደኛህ የተሰጠህ ስጦታ ነው” አለኝ። ይህ መጽሐፍ በጣም ከምወዳቸው መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ነው።

የጤንነት ችግር እያለም በአገልግሎት መቀጠል

በ1983 ካንሰር እንዳለብኝ ታወቀ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሕይወት መቀጠል የምችለው ለጥቂት ጊዜ እንደሆነ ተነገረኝ። ይህ ወቅት በተለይ ለማሪካ በጣም አስጨናቂ ነበር፤ ይሁን እንጂ በምታደርግልኝ ፍቅራዊ እንክብካቤና በርካታ ወንድሞች በሚሰጡኝ ድጋፍ ደስተኛ ሕይወት መምራት ችያለሁ።

በአሁኑ ጊዜ እኔና ማሪካ በቪየና ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈልን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጠዋት ጠዋት ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የትርጉም ሥራ ሳከናውን ማሪካ ደግሞ በስብከቱ ሥራ በትጋት ትካፈላለች። በኦስትሪያ የሚገኙ የዩጎዝላቪያ ዜግነት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከትንሽ ቡድን ተነስቶ ከ1,300 በላይ መድረሱን መመልከቴ በጣም አስደስቶኛል። እኔና ማሪካ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳት በመቻላችን ትልቅ መብት አግኝተናል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ሪፑብሊክ በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የውሰና ፕሮግራም ላይ የመገኘት መብት አግኝቻለሁ። በ1999 በክሮኤሽያ፣ በ2006 ደግሞ በስሎቬኒያ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተወስነዋል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከ70 ዓመታት ገደማ በፊት የስብከቱ ሥራ የጀመረው እንዴት እንደሆነ እንዲናገሩ ከተጠየቁት ወንድሞች መካከል አንዱ ነበርኩ።

በእርግጥም ይሖዋ ድክመቶቻችንንና ስህተቶቻችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ አፍቃሪ አባት ነው። ይሖዋ ኃጢአትን የማይቆጥር በመሆኑ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! (መዝሙር 130:3) በእርግጥም ይሖዋ ደግነትና ምሕረት አሳይቶኛል። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በዚያን ጊዜ በዩጎዝላቪያ ሥር ስሎቬኒያን ጨምሮ ስድስት ሪፑብሊኮች ነበሩ።

^ አን.9 የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ለመመልከት በዚህ መጽሔት በገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።

^ አን.39 ወንድም ቦልፌንክ ሞክኒክ ይህ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እያለ ሚያዝያ 11, 2008 አርፈዋል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ:- ወላጆቼ በርታ እና ፍራንትስ ሞክኒክ፣ ማይዳና እኔ በማሪቦር፣ ስሎቬኒያ በ1940ዎቹ የተነሳነው ፎቶ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከማሪካ ጋር