በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቱ እንደሚያፈራ አታውቁም!

የቱ እንደሚያፈራ አታውቁም!

የቱ እንደሚያፈራ አታውቁም!

“ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ . . . የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።”—መክ. 11:6

1. አንድ ተክል እድገት የሚያደርግበት መንገድ የሚያስገርም እንዲሁም ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ የሚገፋፋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

አንድ ገበሬ ታጋሽ መሆን ይኖርበታል። (ያዕ. 5:7) ገበሬው ዘሩን ከዘራ በኋላ መብቀል እስኪጀምርና እስኪያድግ ድረስ መጠበቅ አለበት። ዘሩ ለመብቀል የሚያስፈልጉት ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ቀስ በቀስ ከመሬት ውስጥ ብቅ በማለት ቅጠል ማውጣት ይጀምራል። ከዚያም ቡቃያው አድጎ ያሽታል። በመጨረሻም ሰብሉ ለአጨዳ ይደርሳል። አንድ ተክል እድገት የሚያደርግበት መንገድ እንዴት የሚያስደንቅ ነው! እንደዚህ ያለው እድገት እንዲካሄድ የሚያደርገው ማን እንደሆነ ማወቁ ደግሞ ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ የሚገፋፋ ነው። ሰዎች ዘሩን በመንከባከቡም ሆነ ውኃ በማጠጣቱ ሥራ መካፈል ይችሉ ይሆናል። ዘሩን ሊያሳድገው የሚችለው ግን አምላክ ብቻ ነው።—ከ1 ቆሮንቶስ 3:6 ጋር አወዳድር።

2. ቀደም ባለው ርዕስ ውስጥ በተመለከትናቸው ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ ስለ መንፈሳዊ እድገት ምን ትምህርት ሰጥቷል?

2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ፣ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩን ሥራ ዘር ከመዝራት ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች በተናገረው ምሳሌ ላይ ገበሬው መልካም ዘር ቢዘራም እንኳ ዘሩ አድጎ ፍሬ የሚያፈራ ተክል መሆን አለመሆኑ የተመካው በግለሰቡ የልብ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማር. 4:3-9) ኢየሱስ ስለሚተኛው ዘሪ በተናገረው ምሳሌ ላይ ደግሞ ገበሬው ዘሩ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ እንደማይረዳው ገልጿል። ይህ የሆነው ዘሩ የሚያድገው በሰዎች ጥረት ሳይሆን በአምላክ ኃይል በመሆኑ ነው። (ማር. 4:26-29) እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ የተናገራቸውን ሌሎች ሦስት ምሳሌዎች እንመልከት፤ እነሱም ስለ ሰናፍጭ ዘር፣ ስለ እርሾውና ስለ መረቡ የተናገራቸው ምሳሌዎች ናቸው። *

የሰናፍጩ ዘር ምሳሌ

3, 4. ስለ ሰናፍጭ ዘር የሚገልጸው ምሳሌ የአምላክን መንግሥት መልእክት በተመለከተ የትኞቹን ነገሮች ጎላ አድርጎ ይገልጻል?

3 በማርቆስ ምዕራፍ 4 ላይ ስለ ሰናፍጭ ዘር የሚናገር ምሳሌም የሚገኝ ሲሆን ምሳሌው ሁለት ነገሮችን ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- አንደኛው፣ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መልእክቱን የሚቀበሉት ሰዎች ጥበቃ ማግኘታቸው ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትላልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”—ማር. 4:30-32

4 ይህ ምሳሌ ‘የአምላክ መንግሥት’ የሚያደርገውን እድገት የሚያመለክት ነው፤ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ጀምሮ የመንግሥቱ መልእክት መሰራጨቱና የክርስቲያን ጉባኤ መስፋፋቱ ‘የአምላክ መንግሥት’ እድገት ማድረጉን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የሰናፍጭ ዘር በጣም ትንሽ ሲሆን አነስተኛ የሆነን ነገር ለማመልከት ይሠራበታል። (ከሉቃስ 17:6 ጋር አወዳድር።) ውሎ አድሮ ግን የሰናፍጭ ተክል ከ3 እስከ 5 ሜትር የሚደርስ ቁመት ሊኖረውና ጠንካራ ቅርንጫፎች ሊያወጣ ስለሚችል እንደ ዛፍ ሊቆጠር ይችላል።—ማቴ. 13:31, 32

5. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ምን ዓይነት እድገት አድርጎ ነበር?

5 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ 120 ያህል ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ በተቀቡበት ወቅት የክርስቲያን ጉባኤ ከዚህ ትንሽ ቁጥር ተነስቶ እድገት ማድረግ ጀመረ። አነስተኛ ጅምር ያለው ይህ ጉባኤ በአንጻራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድገት በማድረግ በሺህ የሚቆጠሩ አማኞችን የሚያካትት ሆነ። (የሐዋርያት ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 5:28፤ 6:7፤ 12:24፤ 19:20ን አንብብ።) በሦስት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የመከሩ ሠራተኞች ቁጥር ከፍተኛ እድገት በማሳየቱ ሐዋርያው ጳውሎስ በቈላስይስ ለሚገኘው ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ [እንደተሰበከ]” መግለጽ ችሏል። (ቈላ. 1:23) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ እድገት ነው!

6, 7. (ሀ) ከ1914 ጀምሮ ምን ዓይነት እድገት እየታየ ነው? (ለ) ወደፊት ምን ተጨማሪ እድገት ይኖራል?

6 የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሰናፍጩ “ዛፍ” ቅርንጫፎች ከተጠበቀው በላይ ተንሰራፍተዋል። የአምላክ ሕዝቦች “ከአንቺ ታናሽ የሆነው ሺህ፣ ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት ቃል በቃል ሲፈጸም ተመልክተዋል። (ኢሳ. 60:22) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ይካፈሉ የነበሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን፣ በ2008 ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይህንን ሥራ እንደሚያከናውኑ አልገመቱም ነበር። ይህ በእርግጥም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ከተገለጸው የሰናፍጭ ዘር ጋር የሚመሳሰል አስገራሚ እድገት ነው!

7 ይሁን እንጂ እድገቱ በዚህ ያቆማል? በፍጹም። ከጊዜ በኋላ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች መላዋን ምድር ይሞሏታል። የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች በሙሉ ከምድር ገጽ ይወገዳሉ። ይህ የሚሆነው በሰው ልጆች ጥረት ሳይሆን ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ከምድር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ስለሚወስድ ነው። (ዳንኤል 2:34, 35ን አንብብ።) “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች” በማለት ኢሳይያስ የተናገረው ሌላ ትንቢት በዚያ ወቅት የመጨረሻ ፍጻሜውን ሲያገኝ እንመለከታለን።—ኢሳ. 11:9

8. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተገለጹት ወፎች እነማንን ያመለክታሉ? (ለ) በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ከየትኞቹ ነገሮች ጥበቃ አግኝተናል?

8 ኢየሱስ፣ በአምላክ መንግሥት ጥላ ሥር የሰማይ ወፎች እንደሚያርፉ በምሳሌው ላይ ተናግሯል። እነዚህ ወፎች ግን በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ስለዘራው ዘሪ በሚናገረው ምሳሌ ላይ እንደተገለጹት መልካሙን ዘር የሚለቅሙ ወፎች፣ የአምላክን መንግሥት ጠላቶች የሚያመለክቱ አይደሉም። (ማር. 4:4) ከዚህ ይልቅ በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለጹት ወፎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጥበቃ ለማግኘት የሚፈልጉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በዚህ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት በመንፈሳዊ የሚያቆሽሹ ልማዶችና ርኩስ ድርጊቶች ጥበቃ አግኝተዋል። (ከኢሳይያስ 32:1, 2 ጋር አወዳድር።) ይሖዋም መሲሐዊውን መንግሥት ከዛፍ ጋር በማመሳሰል እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል:- “ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፤ ቅርንጫፎች ያወጣል፤ ፍሬ ያፈራል፤ ያማረም ዝግባ ይሆናል። የወፍ ዐይነት ሁሉ መኖሪያውን በዚያ ያደርጋል፤ በቅርንጫፎቹም ጥላ ሥር ያርፋል።”—ሕዝ. 17:23

የእርሾው ምሳሌ

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ስለ እርሾው በተናገረው ምሳሌ ላይ ያጎላው ነጥብ ምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ አብዛኛውን ጊዜ ምንን ለማመልከት ተሠርቶበታል? ኢየሱስ እርሾን ከመጥቀሱ ጋር በተያያዘ የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?

9 እድገት በሰብዓዊ ዓይን ሁልጊዜ ላይታይ ይችላል። ኢየሱስ ቀጥሎ በሰጠው ምሳሌ ላይ ይህንን ነጥብ የሚያጎላ ሐሳብ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” (ማቴ. 13:33) እዚህ ላይ የተጠቀሰው እርሾ ምን ያመለክታል? እርሾው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርገው እድገት ጋር የሚዛመደውስ እንዴት ነው?

10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ አብዛኛውን ጊዜ ኃጢአትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በጥንቷ የቆሮንቶስ ጉባኤ የነበረ አንድ ኃጢአተኛ ስላሳደረው መጥፎ ተጽዕኖ ሲገልጽ እርሾን በዚህ መንገድ ተጠቅሞበታል። (1 ቆሮ. 5:6-8) ታዲያ ኢየሱስ ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ እርሾን የጠቀሰው መጥፎ የሆነ ነገር እድገት ስለማድረጉ ለመናገር ነበር?

11. እርሾ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው እንዴት ነበር?

11 ለዚህ ጥያቄ መልስ ከማግኘታችን በፊት ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችን ልብ ማለት ያስፈልገናል። አንደኛ፣ ይሖዋ የፋሲካ በዓል ሲከበር ሕዝቡ በእርሾ እንዳይጠቀም የከለከለ ቢሆንም በሌሎች ጊዜያት እርሾ የተጨመረባቸው መሥዋዕቶችን ተቀብሏል። እርሾ፣ ለምስጋና ከሚቀርበው የኅብረት መሥዋዕት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ይውል ነበር፤ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው ይሖዋ ለሰጠው በረከቶች አመስጋኝ መሆኑን በሚያሳይ መንፈስ ስጦታውን በፈቃደኝነት ያቀርባል። ይህም በማዕዱ ለሚካፈሉ ሁሉ ደስታ ያስገኝላቸው ነበር።—ዘሌ. 7:11-15

12. መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌያዊ አነጋገር ስለሚጠቀምበት መንገድ ምን ግንዛቤ አግኝተናል?

12 ሁለተኛ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ነገር አንዳንድ ጊዜ በአሉታዊ መንገድ ቢሠራበትም በሌላ ጊዜ ደግሞ ያው ነገር በጥሩ ጎኑ ሊሠራበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ ሰይጣን፣ አደገኛና ጨካኝ መሆኑን ለማመልከት በአንበሳ ተመስሏል። ራእይ 5:5 ደግሞ ኢየሱስን ከአንበሳ ጋር በማመሳሰል “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” ይለዋል። ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ አንበሳ፣ ድፍረት የተሞላበት ፍትሕን ያመለክታል።

13. ኢየሱስ ስለ እርሾ የተናገረው ምሳሌ ከመንፈሳዊ እድገት ጋር በተያያዘ ምን ያመለክታል?

13 ሦስተኛ፣ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እርሾው ሊጡን በሙሉ እንዳበላሸውና ከጥቅም ውጭ እንዳደረገው አልተናገረም። እዚህ ላይ ኢየሱስ የተለመደውን የዳቦ አዘገጃጀት መግለጹ ነበር። ሴትየዋ እርሾውን ከዱቄቱ ጋር የቀላቀለችው ሆን ብላ ሲሆን ጥሩ ውጤትም አስገኝቶላታል። እርሾው በዱቄቱ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር። በመሆኑም እርሾው፣ ሊጡ እንዲቦካ የሚያደርግበት መንገድ ከሴትየዋ እይታ የተሰወረ ነበር። ይህ ምሳሌ፣ ዘር ዘርቶ ሌሊት የሚተኛውን ሰው ያስታውሰናል። ኢየሱስ “[ሰውየው] ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል” በማለት ተናግሯል። (ማር. 4:27) አንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ማየት እንደማይቻል የሚገልጽ እንዴት ያለ ቀላል ምሳሌ ነው! መጀመሪያ ላይ ግለሰቡ የሚያደርገውን እድገት መመልከት አንችል ይሆናል፤ ውሎ አድሮ ግን ውጤቱ በግልጽ ይታያል።

14. እርሾው ሊጡን በሙሉ እንዲቦካ ማድረጉ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ያመለክታል?

14 ይህ እድገት የሚካሄድበት መንገድ በሰብዓዊ ዓይን የማይታይ ከመሆኑም ባሻገር እድገቱ የሚከናወነው በመላው ምድር ላይ ነው። ይህም ስለ እርሾው በሚናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሌላው ነጥብ ነው። እርሾው ‘ሦስት መስፈሪያ ዱቄት’ የሚሆነው ሊጥ በሙሉ እንዲቦካ አድርጓል። (ሉቃስ 13:21 የ1954 ትርጉም) የደቀ መዛሙርት ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ፣ ልክ እንደ እርሾ በጣም ስለተስፋፋ በአሁኑ ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” እየተሰበከ ነው። (ሥራ 1:8፤ ማቴ. 24:14) ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ ለተገኘው ለዚህ አስደናቂ እድገት አስተዋጽኦ ማድረጋችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

የመረቡ ምሳሌ

15, 16. (ሀ) ስለ መረቡ የሚናገረውን ምሳሌ በአጭሩ ግለጽ። (ለ) መረቡ ምን ያመለክታል? ይህ ምሳሌ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ ከሰጡት ሰዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ የትኛውን ነጥብ በተዘዋዋሪ ይገልጻል?

15 የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ከሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር መብዛት ይልቅ አስፈላጊ የሆነው ነገር እነዚህ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለመሆናቸው ነው። ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ ከሰጡት ሰዎች ቁጥር መጨመር ጋር የተያያዘውን ይህንን ነጥብ ኢየሱስ ስለ መረብ የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ በተናገረበት ወቅት በተዘዋዋሪ ጠቅሷል። ኢየሱስ “ደግሞም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር ተጥሎ የዓሣ ዓይነቶችን የያዘ መረብ ትመስላለች” ብሏል።—ማቴ. 13:47

16 የአምላክን መንግሥት የስብከት ሥራ የሚያመለክተው መረብ ሁሉንም የዓሣ ዓይነቶች ይዟል። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ዓሣ አጥማጆቹ መረቡ ሲሞላላቸው ጎትተው ወደ ባሕሩ ዳር አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በቅርጫት ውስጥ ጨመሩ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻም ልክ እንደዚሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን በመለየት፣ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።”—ማቴ. 13:48-50

17. ስለ መረቡ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው የመለየት ሥራ የሚከናወነው በየትኛው ጊዜ ውስጥ ነው?

17 ኢየሱስ በክብሩ በሚገኝበት ጊዜ በበጎችና በፍየሎች ላይ የመጨረሻ ፍርድ እንደሚበይን ተናግሮ ነበር፤ ታዲያ ከላይ የተገለጸው የመለየት ሥራ ይህንን የሚያመለክት ነው? (ማቴ. 25:31-33) አይደለም። ይህ የመጨረሻ ፍርድ የሚበየነው ኢየሱስ በታላቁ መከራ ወቅት ሲመጣ ነው። ከዚህ በተለየ መልኩ፣ ስለ መረቡ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው የመለየት ሥራ የሚከናወነው ‘የዓለም መጨረሻ’ ወይም የዚህ ሥርዓት መደመደሚያ ተብሎ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ነው። * ይህ ደግሞ በታላቁ መከራ የሚደመደመውን የምንኖርበትን ዘመን ያመለክታል። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ያለው እንዴት ነው?

18, 19. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል? (በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻም ተመልከት።)

18 በዘመናችን ከሰው ዘር ባሕር ውስጥ የወጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምሳሌያዊ ዓሣዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ቃል በቃል እየተሳቡ ነው። አንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ ሌሎች ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ ይገኛሉ፤ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንኳ ፈቃደኞች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ናቸው ማለት ይቻላል? ዓሣ አጥማጆቹ እነዚህን ሰዎች፣ ‘ወደ ባሕሩ ዳር አውጥተዋቸው’ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በቅርጫት ወደተመሰሉት የክርስቲያን ጉባኤዎች የሚሰበሰቡት ‘ጥሩዎቹ’ ብቻ እንደሆኑ ኢየሱስ ተናግሯል። በመጥፎዎቹ ዓሣዎች የተመሰሉት ሰዎች የሚጣሉ ሲሆን በመጨረሻም፣ ወደፊት የሚመጣውን ጥፋት ወደሚያመለክተው ምሳሌያዊ እቶን እሳት ይወረወራሉ።

19 መጥፎ በመሆናቸው ምክንያት እንደተጣሉት ዓሣዎች ሁሉ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ የነበሩ በርካታ ሰዎችም ማጥናታቸውን አቁመዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን የሆኑ ወላጆች ያሏቸው አንዳንዶች የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል እውነተኛ ፍላጎት የላቸውም። እነዚህ ግለሰቦች ይሖዋን ለማገልገል መወሰን አይፈልጉም፤ ሌሎቹ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ይሖዋን ሲያገለግሉት ከቆዩ በኋላ እሱን ማገልገላቸውን አቁመዋል። * (ሕዝ. 33:32, 33) ይሁን እንጂ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የመጨረሻው የፍርድ ቀን ከመምጣቱ በፊት በቅርጫት ወደተመሰሉት ጉባኤዎች መሰብሰባቸውና ጥበቃ በሚያገኙበት ቦታ መቆየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው።

20, 21. (ሀ) ኢየሱስ እድገት ማድረግን በተመለከተ የተናገራቸውን ምሳሌዎች በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል? (ለ) አንተስ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

20 ኢየሱስ እድገት ማድረግን በተመለከተ የተናገራቸውን ምሳሌዎች በአጭሩ በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል? አንደኛ፣ የሰናፍጩ ዘር ካደረገው እድገት ጋር በሚመሳሰል መልኩ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። የይሖዋ ሥራ እንዳይከናወን ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም! (ኢሳ. 54:17) ከዚህም በተጨማሪ በዛፉ ‘ጥላ ሥር ለመስፈር’ የፈለጉ ሁሉ መንፈሳዊ ጥበቃ አግኝተዋል። ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ የሚያሳድገው አምላክ መሆኑ ነው። ዱቄት ውስጥ የተሸሸገው እርሾ ሊጡን በሙሉ እንዲቦካ እንዳደረገው ሁሉ ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የተከናወነውን እድገትም ሁልጊዜ ማስተዋል ወይም መረዳት ባንችልም እድገቱ ግን እየተካሄደ ነው! ሦስተኛ፣ ለመንግሥቱ ምሥራች ምላሽ የሰጡ ሰዎች ሁሉ ጥሩ ዓሣዎች ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንዶች በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሱት መጥፎ ዓሣዎች ሆነዋል።

21 ያም ቢሆን ይሖዋ፣ በርካታ ጥሩ ዓሣዎችን ሲስባቸው መመልከት እንዴት የሚያበረታታ ነው! (ዮሐ. 6:44) ይህ ደግሞ በተለያዩ አገሮች አስደናቂ እድገት እንዲኖር አድርጓል። ለዚህ ሁሉ እድገት መመስገን የሚገባው ይሖዋ ነው። ሁላችንም ይህንን እድገት መመልከታችን ከበርካታ ዘመናት በፊት የተጻፈውን የሚከተለውን ምክር እንድንታዘዝ ሊገፋፋን ይገባል:- “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ . . . ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።”—መክ. 11:6

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ማብራሪያዎች ቀደም ሲል በሰኔ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-22 እንዲሁም በጥቅምት 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 589-608 (እንግሊዝኛ) ላይ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረጉ ማስተካከያዎች ናቸው።

^ አን.17 ማቴዎስ 13:39-43 ከመንግሥቱ ስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ስለ ሌላ ነጥብ የሚገልጽ ቢሆንም ይህ ምሳሌ የሚፈጸምበት ጊዜ ስለ መረቡ የተሰጠው ምሳሌ ከሚፈጸምበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሁለቱም ምሳሌዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ‘የዓለም መጨረሻ’ ወይም የዚህ ሥርዓት መደመደሚያ ተብሎ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ነው። የመዝራቱና መከሩን የመሰብሰቡ ሥራ የሥርዓቱ መደምደሚያ በተባለው ጊዜ ውስጥ ያለማቋረጥ እንደሚከናወን ሁሉ ምሳሌያዊውን ዓሣ የመለየቱ ሥራም ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው።—የጥቅምት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25-26እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ ገጽ 178-181 አንቀጽ 8-11

^ አን.19 ይህ ሲባል ታዲያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ወይም መሰብሰብ ያቆሙትን ሰዎች በሙሉ መላእክት እንደ መጥፎ ዓሣዎች በመቁጠር ጥለዋቸዋል ማለት ነው? አይደለም! አንድ ሰው ከልቡ ወደ ይሖዋ ለመመለስ ከፈለገ እሱ ይቀበለዋል።—ሚል. 3:7

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ስለ ሰናፍጭ ዘር የተናገረው ምሳሌ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ ስለሰጡት ሰዎች ቁጥር መጨመር ምን ያስተምረናል? እነዚህ ሰዎች ስለሚያገኙት መንፈሳዊ ጥበቃስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

• ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው እርሾ ምን ያመለክታል? ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ ከሚሰጡት ሰዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ኢየሱስ የትኛውን ነጥብ ጎላ አድርጎ ገልጿል?

• ኢየሱስ ስለ መረቡ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ከአምላክ መንግሥት እድገት ጋር በተያያዘ የትኛውን ነጥብ ገልጿል?

• “በቅርጫት ውስጥ” ካሉት መካከል ሆነን ለመቀጠል ምን ማድረግ አለብን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ሰናፍጭ ዘር የሚገልጸው ምሳሌ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ ስለሰጡት ሰዎች ቁጥር መጨመር ምን ያስተምረናል?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እርሾው ከሚገልጸው ምሳሌ ምን እንማራለን?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩዎቹን ዓሣዎች ከመጥፎዎቹ ዓሣዎች የመለየቱ ሥራ ምን ትርጉም አለው?