በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ ይናገር የነበረው በየትኛው ቋንቋ ነው?

ምሑራን፣ ኢየሱስ ይናገር የነበረውን ቋንቋ አስመልክተው የሚሰጡት ሐሳብ የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የዕብራይስጥና የአረማይክ ቋንቋ ሳይናገር አልቀረም። ኢየሱስ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት በመጣ ጊዜ ወደ ምኩራብ በመግባት ከኢሳይያስ ትንቢት አንብቦ ነበር። ይህ ትንቢት በዕብራይስጥ እንደተጻፈ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ይህን ምንባብ ወደ አረማይክ ስለመተርጎሙ የሚገልጸው ነገር የለም።—ሉቃስ 4:16-21

ፕሮፌሰር ኧርነስት ራይት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ በፓለስቲና ምድር ይነገሩ ስለነበሩ ቋንቋዎች አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “የአብዛኞቹ ሰዎች ቋንቋ ግሪክኛና አረማይክ እንደነበር ጥርጥር የለውም . . . ሮማውያን ወታደሮችና ባለሥልጣናት በላቲን ሲነጋገሩ፣ አክራሪ አይሁዳውያን ደግሞ በዘመኑ ይነገር በነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ሲያወሩ ሊደመጡ ይችሉ ነበር።” ጲላጦስ፣ ኢየሱስ በተሰቀለበት እንጨት ላይ በሦስት ቋንቋ ይኸውም በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክኛ መጻፉ ምንም አያስገርምም።—ዮሐንስ 19:20

አለን ሚለርድ፣ ዲስከቨሪስ ፍሮም ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ሮማውያን ገዥዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ግሪክኛን ይጠቀሙ እንደነበር እሙን ነው። በመሆኑም፣ ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ጲላጦስ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ይሰጥ የነበረው በግሪክኛ ሳይሆን አይቀርም።” መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ባይናገርም፣ ኢየሱስና ጲላጦስ በሚነጋገሩበት ጊዜ አስተርጓሚ ስለመጠቀማቸው የሚገልጸው ነገር አለመኖሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—ዮሐንስ 18:28-40

ፕሮፌሰር ራይት እንዳሉት ከሆነ “[ኢየሱስ] ግሪክኛ ወይም ላቲን ይናገር እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎችን ሲያስተምር አብዛኛውን ጊዜ የአረማይክ ወይም የአረማይክ ቋንቋ ተጽዕኖ ባሳደረበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ሳይጠቀም አልቀረም።”—ቢብሊካል አርኪኦሎጂ፣ 1962 ገጽ 243

በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የተገነባባቸው ድንጋዮች ምን ያህል ትልቅ ነበሩ?

ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው ቤተ መቅደስ ለኢየሱስ ሲነግረው “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ” አለው። (ማርቆስ 13:1) ከእነዚህ ድንጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ምን ያህል ትልቅ ነበሩ?

ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ፣ ከፍ ተደርጎ የተሠራውን ቤተ መቅደሱ ያረፈበትን ስፍራ በሰሎሞን ጊዜ ከነበረው በእጥፍ አስፍቶት ነበር። ይህ ስፍራ በጥንት ዘመን ከተሠሩት ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን 480 ሜትር በ280 ሜትር ስፋት ነበረው። አንዳንዶቹ ድንጋዮች 11 ሜትር ርዝመት፣ 5 ሜትር ወርድ እንዲሁም 3 ሜትር ውፍረት ነበራቸው። የተወሰኑት ድንጋዮች እያንዳንዳቸው ከ500 ኩንታል በላይ ይመዝኑ ነበር። እንዲያውም አንዱ ድንጋይ 4000 ኩንታል ያህል ይመዝን የነበረ ሲሆን አንድ ምሑር እንዳሉት ከሆነ ይህ ድንጋይ “በጥንት ዘመን ከነበሩት ጥርብ ድንጋዮች መካከል የሚተካከለው አልነበረም።”

ኢየሱስ፣ ደቀ መዝሙሩ ላነሳው ሐሳብ መልስ ሲሰጥ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። (ማርቆስ 13:2) ከእነዚህ ትላልቅ ድንጋዮች አብዛኞቹ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ወታደሮች በጣሏቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ድረስ ይታያሉ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቤተ መቅደሱ ውጪ የተጣሉ ድንጋዮች፣ ኢየሩሳሌም