በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዳራችሁ “በሦስት የተገመደ” ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት አድርጉ

ትዳራችሁ “በሦስት የተገመደ” ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት አድርጉ

ትዳራችሁ “በሦስት የተገመደ” ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት አድርጉ

‘በሦስት የተገመደ ገመድ ቶሎ አይበጠስም።’—መክ. 4:12

1. የመጀመሪያዎቹን ሰዎች በጋብቻ ያጣመራቸው ማን ነው?

ይሖዋ አምላክ፣ ተክሎችንና እንስሳትን ከፈጠረ በኋላ የመጀመሪያ ሰው የሆነውን አዳምን ወደ ሕልውና አመጣው። ከዚያም አዳም ኃይለኛ እንቅልፍ እንዲወስደው በማድረግ ከጎድን አጥንቶቹ አንዱን ወስዶ ፍጹም የሆነች ረዳት አበጀለት። አዳም፣ ይሖዋ የሰጠውን ረዳት ሲመለከት “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለት ተናገረ። (ዘፍ. 1:27፤ 2:18, 21-23) ይሖዋም የመጀመሪያዋን ሴት ከፈጠረ በኋላ በሥራው እንደተደሰተ አሳይቷል፤ ይሖዋ፣ ሔዋን ለአዳም ተስማሚ ረዳት እንደሆነች ስላመነ እነዚህን ሰዎች በጋብቻ ካጣመራቸው በኋላ ባረካቸው።—ዘፍ. 1:28፤ 2:24

2. አዳምና ሔዋን ግንኙነታቸው እንዲበላሽ ሰይጣን ምን አድርጓል?

2 የሚያሳዝነው ግን የአምላክ ዝግጅት የሆነው ጋብቻ ብዙም ሳይቆይ ጥቃት ተሰነዘረበት። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ተብሎ የተጠራው አንድ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ሔዋንን በማታለል አምላክ እንዳይበሉ ከከለከላቸው ዛፍ እንድትበላ አደረጋት። አዳምም ከሚስቱ ጋር በመተባበር የአምላክን ትእዛዝ ጣሰ፤ እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ በማድረጋቸው ትክክለኛ በሆነው የአምላክ አገዛዝና አመራር ላይ ዓምፀዋል። (ዘፍ. 3:1-7) ይሖዋ እነዚህን ባልና ሚስት ስለፈጸሙት ጥፋት ሲጠይቃቸው የሰጡት መልስ ግንኙነታቸው እንደተበላሸ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። አዳም “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” በማለት ጥፋቱ የሚስቱ እንደሆነ ገለጸ።—ዘፍ. 3:11-13

3. አንዳንድ አይሁዳውያን ምን የተሳሳተ አመለካከት አዳብረው ነበር?

3 ከዚያ በኋላ ባሉት በርካታ መቶ ዘመናትም ሰይጣን በትዳር ጓደኛሞች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ የተለያዩ መሠሪ ዘዴዎችን ሲጠቀም ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የሃይማኖት መሪዎች ጋብቻን በተመለከተ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ ትምህርት እንዲያስፋፉ ያደረገባቸው ወቅቶች አሉ። አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ባሎች ጥቃቅን በሆኑ ስህተቶች እንኳ ሚስቶቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ በመግለጽ የአምላክን መሥፈርቶች አቃልለዋል። ለምሳሌ አንድ ባል፣ ሚስቱ ምግብ ላይ ጨው በማብዛቷ ብቻ ሊፈታት እንደሚችል ይገልጹ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” በማለት ተናግሯል።—ማቴ. 19:9

4. በዛሬው ጊዜ የጋብቻ ዝግጅት ጥቃት እየተሰነዘረበት ያለው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን በዛሬው ጊዜም ቢሆን የጋብቻን ጥምረት ለማፍረስ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመው ጥምረት፣ ያልተጋቡ ጥንዶች አብረው መኖራቸው እንዲሁም ትዳር በቀላሉ የሚፈርስ መሆኑ ሰይጣን የሚያደርገው ጥረት እንደተሳካለት የሚጠቁም ነው። (ዕብራውያን 13:4ን አንብብ።) እኛስ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ትዳርን በተመለከተ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው የተዛባ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ትዳር ደስታ የሰፈነበትና የሰመረ እንዲሆን የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

በትዳራችሁ ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው አድርጉ

5. “በሦስት የተገመደ ገመድ” የሚለው አገላለጽ ከትዳር ጋር በተያያዘ ምን ትርጉም አለው?

5 ትዳር የሰመረ እንዲሆን ከተፈለገ ባልና ሚስት በጋብቻቸው ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው ሊያደርጉ ይገባል። የአምላክ ቃል ‘በሦስት የተገመደ ገመድ ቶሎ አይበጠስም’ ይላል። (መክ. 4:12) “በሦስት የተገመደ ገመድ” የሚለው አገላለጽ ምሳሌያዊ ነው። ይህን አገላለጽ ወደ ትዳር ስናመጣው በሁለት ክሮች የተወከሉት ባልና ሚስት፣ መሃል ላይ በሚገኝ ሌላ ክር ማለትም በይሖዋ አምላክ አማካኝነት አንድ ላይ እንደተጣመሩ ወይም እንደተገመዱ ያሳያል። ባልና ሚስት ከአምላክ ጋር መጣመራቸው ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

6, 7. (ሀ) ክርስቲያኖች አምላክ በትዳራቸው ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንዲት እህት፣ ከባለቤታቸው ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ገልጸዋል?

6 ታዲያ ባልና ሚስት ትዳራቸው በሦስት እንደተገመደ ገመድ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? መዝሙራዊው ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 40:8) እኛም ለአምላክ ያለን ፍቅር በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው ያነሳሳናል። ባልና ሚስት ከይሖዋ ጋር ጠንካራ የግል ዝምድና ሊመሠርቱ እንዲሁም የእሱን ፈቃድ ማድረግ ሊያስደስታቸው ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ባልም ሆነ ሚስት የትዳር ጓደኛቸው ለአምላክ ያለው ፍቅር እንዲያድግ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 27:17

7 የአምላክ ሕግ በውስጣችን ካለ እንደ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር የመሳሰሉ ባሕርያትን የምናዳብር ሲሆን እነዚህ ባሕርያት ደግሞ የጋብቻችንን ጥምረት ያጠናክሩታል። (1 ቆሮ. 13:13) በትዳር ውስጥ 50 ዓመታት ያሳለፉ ሳንድራ የተባሉ አንዲት እህት እንዲህ ብለዋል:- “ባለቤቴ የሚሰጠኝን መንፈሳዊ መመሪያና ምክር እንዲሁም ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ፤ ባለቤቴ ከእኔ ይበልጥ ይሖዋን ይወዳል።” እናንት ባሎች፣ ሚስቶቻችሁ ስለ እናንተ እንዲህ ብለው እንዲናገሩ የሚገፋፋ ባሕርይ አላችሁ?

8. በትዳር ውስጥ “መልካም ውጤት” ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

8 በትዳራችሁ ውስጥ ለመንፈሳዊ ጉዳዮችና ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ትሰጣላችሁ? የትዳር ጓደኞቻችሁን ይሖዋን አብረዋችሁ እንደሚያገለግሉ አጋሮቻችሁ አድርጋችሁ ትመለከቷቸዋላችሁ? (ዘፍ. 2:24) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” በማለት ጽፏል። (መክ. 4:9) በእርግጥም ባልና ሚስት “መልካም ውጤት” እንዲያገኙ ማለትም ፍቅር የሰፈነበትና ዘላቂ የሆነ እንዲሁም ይሖዋ የባረከው ትዳር እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው።

9. (ሀ) ባሎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) በቈላስይስ 3:19 መሠረት አንድ ባል ሚስቱን እንዴት ሊይዛት ይገባል?

9 ባልና ሚስት ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚያደርጉት ጥረት በጋብቻቸው ውስጥ ለይሖዋ ቦታ እንደሰጡት ወይም እንዳልሰጡት ይጠቁማል። ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ነገር የማሟላት ኃላፊነት በዋነኝነት የተሰጠው ለባሎች ነው። (1 ጢሞ. 5:8) ከዚህም በላይ ባሎች ስለ ሚስቶቻቸው ስሜት እንዲያስቡ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ቈላስይስ 3:19 “ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” ይላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ‘መራራ መሆን’ የሚለው ሐሳብ “አጥንት የሚሰብር ነገር መናገርንና መማታትን እንዲሁም ለሚስቶች ፍቅር አለማሳየትን፣ የሚያስፈልጋቸውን አለማቅረብን ብሎም እንክብካቤ፣ ጥበቃና እገዛ አለማድረግን” እንደሚጨምር ገልጸዋል። በክርስቲያኖች ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ያሉ ባሕርያትን ማሳየት ተገቢ እንዳልሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስቱ ለእሱ መገዛት ቀላል ይሆንላታል።

10. ክርስቲያን ሚስቶች ለራስነት ሥልጣን ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

10 በትዳራቸው ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ የሚፈልጉ ክርስቲያን ሚስቶችም አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- ‘ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ። ክርስቶስ፣ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና።’ (ኤፌ. 5:22, 23) ሰይጣን፣ ከአምላክ ርቆ በራስ መመራት ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝ በመግለጽ ሔዋንን አታልሏታል። በዛሬው ጊዜ በብዙ ትዳሮች ውስጥ በራስ የመመራት መንፈስ ይታያል። አምላክ ለትዳር ያለው ዓይነት አመለካከት ያላት ሴት ግን አፍቃሪ ለሆነው ባሏ መገዛት የምትጠላው ነገር አይሆንም። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላት ሴት ይሖዋ፣ ሔዋንን ለባሏ “ረዳት” ወይም ማሟያ አድርጎ እንደሾማትና ይህንን ድርሻም የተከበረ አድርጎ እንደሚመለከተው ታስታውሳለች። (ዘፍ. 2:18) አምላክ የሰጣትን ይህንን ድርሻ በፈቃደኝነት የምትቀበል ክርስቲያን ሚስት ለባሏ እውነተኛ “ዘውድ” ናት።—ምሳሌ 12:4

11. አንድ ወንድም ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን የረዳቸውን ነገር ሲገልጹ ምን ብለዋል?

11 አምላክ በትዳር ውስጥ ቦታ እንዲኖረው የሚረዳው ሌላው ነገር ደግሞ ባልና ሚስት የአምላክን ቃል አብረው ማጥናታቸው ነው። በትዳር ዓለም 55 አስደሳች ዓመታት ያሳለፉት ወንድም ጄራልድ “ጋብቻ የሰመረ እንዲሆን የሚረዳው በጣም አስፈላጊ ነገር መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ማንበብና ማጥናት ነው” ብለዋል። አክለውም እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “የትዳር ጓደኛሞች አብረው መሥራታቸው በተለይም መንፈሳዊ ነገሮችን በአንድነት ማከናወናቸው እርስ በርሳቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲኖራቸው ያደርጋል።” ባልና ሚስት አንድ ላይ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው የይሖዋ መሥፈርቶች ምንጊዜም ከአእምሯቸው እንዳይጠፉ፣ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖራቸው እንዲሁም ቀጣይ የሆነ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

12, 13. (ሀ) ባለትዳሮች አብረው መጸለያቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ትዳር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የትኞቹ ናቸው?

12 ከዚህም በተጨማሪ አስደሳች ትዳር እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ባልና ሚስት አብረው ይጸልያሉ። አንድ ባል በትዳሩ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጥቀስ በአምላክ ፊት ‘ልቡን ማፍሰሱ’ የትዳሩን ጥምረት እንደሚያጠናክረው ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 62:8) ለምሳሌ ያህል፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መመሪያ እንዲሰጣችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሆናችሁ በጸሎት ከለመናችሁት በኋላ በመካከላችሁ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት መፍታት ቀላል ይሆናል። (ማቴ. 6:14, 15) ባልም ሆነ ሚስት የትዳር ጓደኛቸውን ለመርዳት እንዲሁም ‘እርስ በርስ ለመቻቻልና አንዳቸው በሌላው ላይ ቅር የተሰኙበት ነገር ካለ ይቅር ለመባባል’ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰዳቸው ተገቢ ነው። (ቈላ. 3:13) ወደ አምላክ መጸለያችሁ በእሱ የምትተማመኑ መሆናችሁን እንደሚያሳይ አስታውሱ። ንጉሥ ዳዊት “የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል” ብሏል። (መዝ. 145:15) ወደ አምላክ በመጸለይ እሱን በተስፋ የምንጠብቅ ከሆነ ጭንቀታችን ይቀልልናል፤ ምክንያቱም አምላክ ‘ስለ እኛ እንደሚያስብ’ እናውቃለን።—1 ጴጥ. 5:7

13 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና አብሮ ማገልገልም በትዳር ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ ይረዳል። ባለትዳሮች ሰይጣን ቤተሰብን ለመከፋፈል የሚጠቀምባቸውን ‘የተንኰል ሥራዎች’ እንዴት መዋጋት እንደሚችሉ በስብሰባዎች ላይ ይማራሉ። (ኤፌ. 6:11) አዘውትረው አንድ ላይ የሚያገለግሉ ባልና ሚስት ‘በምንም ነገር ሳይናወጡ ጸንተው መቆምን’ ይማራሉ።—1 ቆሮ. 15:58

ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ

14. በትዳር ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን ሊያደርጉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

14 ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሐሳቦች አዲስ እንዳልሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ያም ቢሆን እነዚህን ሐሳቦች ከትዳር ጓደኞቻችሁ ጋር ለምን በግልጽ አትወያዩባቸውም? እነዚህን ነጥቦች በትዳራችሁ ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ አንዳንድ ነገሮችን ማስተካከል ይኖርባችሁ እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። መጽሐፍ ቅዱስ በትዳራቸው ውስጥ አምላክ ቦታ እንዲኖረው ያደረጉ ሰዎችም እንኳ ‘ብዙ ችግር እንደሚገጥማቸው’ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:28) የሰው ልጆች ፍጹማን አለመሆናቸውና ይህ ክፉ ዓለም የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዲሁም የዲያብሎስ ወጥመዶች፣ ታማኝ በሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ትዳር ውስጥም እንኳ ውጥረት እንዲሰፍን ሊያደርጉ ይችላሉ። (2 ቆሮ. 2:11) ያም ቢሆን ይሖዋ እንዲህ ያለውን ውጥረት እንድቋቋም ይረዳናል። አዎን፣ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም ይቻላል። ታማኙ ኢዮብ ከብቶቹን፣ አገልጋዮቹንና ልጆቹን ቢያጣም “በዚህ ሁሉ፣ . . . አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።”—ኢዮብ 1:13-22

15. ሰዎች ውጥረት ሲያጋጥማቸው ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የትዳር ጓደኛችሁ ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢናገራችሁ ምን ማድረግ የተሻለ ነው?

15 በሌላ በኩል ግን የኢዮብ ሚስት “አሁንም ታማኝነትህን አልተውህምን? ይልቁን እግዚአብሔርን ርገምና ሙት!” ብላው ነበር። (ኢዮብ 2:9) በእርግጥም አሳዛኝ ሁኔታዎች ወይም ሌሎች አስቸጋሪ ነገሮች መከሰታቸው የሚፈጥረው ጭንቀት አንድ ሰው ማመዛዘን የጎደለው እርምጃ እንዲወስድ ሊያደርገው ይችላል። ጠቢቡ ሰሎሞን “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ተናግሯል። (መክ. 7:7 የ1954 ትርጉም) የትዳር ጓደኛችሁ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ስላጋጠመው ወይም “ግፍ” ስለደረሰበት በንዴት ገንፍሎ የሚጎዳ ነገር ቢናገራችሁ ለመረጋጋት ሞክሩ። እሱ በተናገረበት መንገድ ምላሽ መስጠት ከሁለት አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም ሁኔታውን የሚያባብስ ነገር እንድትናገሩ ሊያደርጋችሁ ይችላል። (መዝሙር 37:8ን አንብብ።) ስለዚህ የትዳር ጓደኛችሁ በመበሳጨቱ ወይም ተስፋ በመቁረጡ የተነሳ ‘ኀይለ ቃል’ ቢናገራችሁ ነገሩን ለማለፍ ሞክሩ።—ኢዮብ 6:3

16. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 7:1-5 ላይ የሰጠው ሐሳብ በትዳር ውስጥ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ሚዛናዊ መሆን በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ባለትዳሮች አንዳቸው ከሌላው በሚጠብቁት ነገር ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት፣ የትዳር ጓደኛቸው ጥሩ ያልሆነ ባሕርይ እንዳለው ይመለከቱና የትዳር ጓደኛቸውን ‘መለወጥ እንደሚችሉ’ ያስቡ ይሆናል። ፍቅርና ትዕግሥት በማሳየት የትዳር ጓደኞቻችሁ ቀስ በቀስ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ልትረዷቸው ትችሉ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን አንድ ነገር አትዘንጉ፤ ኢየሱስ የሌሎችን ጥቃቅን ጉድለቶች የሚለቃቅምን ሰው፣ በራሱ ዓይን ውስጥ ያለውን “ግንድ” ሳያይ በወንድሙ ዓይን ውስጥ ያለውን “ጉድፍ” ለማውጣት ከሚሞክር ሰው ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ” በማለት አሳስቦናል። (ማቴዎስ 7:1-5ን አንብብ።) ይህ ሲባል ግን ከበድ ያሉ ችግሮች በቸልታ መታለፍ ይኖርባቸዋል ማለት አይደለም። በትዳር ውስጥ ወደ 40 የሚጠጉ ዓመታትን ያሳለፉት ሮበርት እንዲህ ብለዋል:- “የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ግልጽ መሆናቸውና ትክክለኛ የሆኑ አስተያየቶችን በፈቃደኝነት መቀበላቸው የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ይሆናል።” ስለዚህ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። የትዳር ጓደኞቻችሁ እንዲኖሯቸው የምትፈልጓቸውን ባሕርያት እያሰባችሁ ከመበሳጨት ይልቅ አሁን ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ማድነቅንና በእነዚህ መደሰትን ተማሩ።—መክ. 9:9

17, 18. ችግሮች ሲፈጠሩ እርዳታ ከየት ማግኘት እንችላለን?

17 በሕይወታችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁ ለውጦች ፈተና ሊሆኑባችሁ ይችላሉ። አንድ ባልና ሚስት ልጆች መውለዳቸው ሁኔታዎች ፈታኝ እንዲሆኑባቸው ሊያደርግ ይችላል። ባል ወይም ሚስት አሊያም ልጆች በጠና ይታመሙ ይሆናል። ወይም ደግሞ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችሁ ለየት ያለ እንክብካቤ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ልጆች ሲያድጉ ከቤተሰቡ ርቀው ሊሄዱ ይችላሉ። ከቲኦክራሲያዊ መብቶችና ኃላፊነቶች ጋር በተያያዘም ሌሎች ለውጦች ሊመጡ ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ ለውጦች በትዳር ጓደኛሞች መካከል ውጥረት እንዲሰፍንና ጭንቀት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።

18 በትዳራችሁ ውስጥ በተፈጠረው ውጥረት የተነሳ ሁኔታዎች ከአቅማችሁ በላይ እንደሆኑ ከተሰማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? (ምሳሌ 24:10) ተስፋ አትቁረጡ! ሰይጣን ከአምላክ አገልጋዮች አንዱ ንጹሑን አምልኮ ሲተው ከማየት የበለጠ የሚያስደስተው ነገር የለም። ባልና ሚስት ይሖዋን ቢተዉ ደግሞ በጣም ይደሰታል። እንግዲያው ትዳራችሁ በሦስት የተገመደ ሆኖ እንዲቀጥል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም በታማኝነት ስለጸኑ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ታሪኮችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ዳዊት ‘አምላክ ሆይ፤ ሰዎች አስጨንቀውኛል’ በማለት ልቡን ለይሖዋ አፍስሷል። (መዝ. 56:1) እናንተስ “ሰዎች” እንዳስጨነቋችሁ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ለጭንቀታችሁ ምክንያት የሆኑት ሌሎች ሰዎችም ይሁኑ የሚቀርባችሁ ሰው፣ እናንተም እንደ ዳዊት ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ማግኘት እንደምትችሉ አስታውሱ። ዳዊት “እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ” ብሏል።—መዝ. 34:4

የምናገኘው በረከት

19. የሰይጣንን ጥቃት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

19 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የትዳር ጓደኛሞች “እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ፤ አንዱም ሌላውን ያንጽ” የሚለውን ምክር ሁልጊዜ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (1 ተሰ. 5:11) ሰይጣን፣ ‘ሰዎች ለይሖዋ ታማኝ የሚሆኑት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው’ የሚል አቋም እንዳለው አትርሱ። ሰይጣን ለአምላክ ታማኝ እንዳንሆን ለማድረግ ሲል ትዳርን ማፍረስን ጨምሮ ማንኛውንም ዘዴ ይጠቀማል። የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም እንድንችል በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን አለብን። (ምሳሌ 3:5, 6) ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵ. 4:13

20. በትዳር ውስጥ አምላክ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ ምን በረከት ያስገኛል?

20 በትዳር ውስጥ አምላክ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ ብዙ በረከቶችን ያስገኛል። ሃምሳ አንድ ዓመታት በጋብቻ ያሳለፉት ጆኤልና ባለቤታቸው ይህ እውነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወንድም ጆኤል እንዲህ ብለዋል:- “ባለቤቴን ስለሰጠኝ እንዲሁም በመካከላችን ስላለው አስደሳች ወዳጅነት ይሖዋን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። ጥሩ አጋር ሆናልኛለች።” እነዚህ ባልና ሚስት ትዳራቸው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? ጆኤል “አንዳችን ለሌላው ደግነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር ለማሳየት ምንጊዜም ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል። ማንኛችንም ብንሆን በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ እነዚህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ማንጸባረቅ አንችልም። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ለማዋል እንዲሁም በትዳራችን ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ልናደርግ ይገባል። እንዲህ ካደረግን ትዳራችን ‘በሦስት እንደተገመደ ገመድ [ስለሚሆን] ቶሎ አይበጠስም።’—መክ. 4:12

ታስታውሳለህ?

• በትዳር ውስጥ ይሖዋ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

• ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ የትዳር ጓደኛሞች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

• ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ለአምላክ ቦታ እንደሰጡት የሚያሳዩት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትዳር ጓደኛሞች አብረው መጸለያቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይረዳቸዋል