በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እኛንም ‘ይታደገናል’

ይሖዋ እኛንም ‘ይታደገናል’

ይሖዋ እኛንም ‘ይታደገናል’

‘ይሖዋ ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም።’—መዝ. 37:40

1, 2. ስለ ይሖዋ የትኛውን እውነት ማወቃችን የመጽናናትና የብርታት ምንጭ ይሆንልናል?

በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት የሚፈጠረው ጥላ ምድር ስትዞር ሁልጊዜ ቦታውን ይቀይራል። የምድርና የፀሐይ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ግን ምንጊዜም አይለወጥም። (ሚል. 3:6) መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ . . . ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም” ይላል። (ያዕ. 1:17 NW) ስለ ይሖዋ ይህንን እውነት ማወቃችን በጣም የሚያጽናና እንዲሁም የሚያበረታታ ነው፤ በተለይ ደግሞ ከባድ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይህንን እውነት ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል።’ (መዝ. 70:5) ይሖዋ የማይለወጥ አምላክ ከመሆኑም ባሻገር ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አምላኪዎቹ ‘እንደሚረዳቸውና እንደሚታደጋቸው’ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አላቸው። (መዝ. 37:40) ይሖዋ በዘመናችን ያሉ አገልጋዮቹን የታደጋቸው እንዴት ነው? ለእኛስ በግለሰብ ደረጃ ታዳጊ የሚሆንልን እንዴት ነው?

ከተቃዋሚዎች ያድነናል

3. ተቃዋሚዎች፣ የይሖዋ ሕዝቦች ምሥራቹን እንዳይሰብኩ ማገድ እንደማይችሉ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ሰይጣን ምንም ያህል ተቃውሞ ቢያስነሳም የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ እንዳያቀርቡ ሊያግዳቸው አይችልም። የአምላክ ቃል፣ ‘በእናንተ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከሳችሁንም አንደበት ሁሉ ትረታላችሁ’ የሚል ዋስትና ይሰጠናል። (ኢሳ. 54:17) ተቃዋሚዎች፣ የአምላክ ሕዝቦች ምሥራቹን እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ እንዳይወጡ ለማገድ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

4, 5. በ1918 የይሖዋ ሕዝቦች ምን ዓይነት ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር? ውጤቱስ ምን ሆነ?

4 በ1918 ቀሳውስት፣ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ለማስቆም ስለፈለጉ ከባድ ስደት አስነስተውባቸው ነበር። በዚሁ ዓመት ግንቦት 7 ቀን የፌደራሉ መንግሥት፣ ወንድም ራዘርፎርድን ጨምሮ በዋናው መሥሪያ ቤት ያገለግሉ የነበሩ የተወሰኑ ወንድሞች እንዲታሰሩ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በወቅቱ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በበላይነት የሚከታተለው ወንድም ራዘርፎርድ ነበር። ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወንድም ራዘርፎርድና ሌሎቹ ወንድሞች አድማ አነሳስተዋል በሚል በሐሰት ተከሰው የረጅም ጊዜ እስራት ተበየነባቸው። ይህ መሆኑ ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤት በመጠቀም የስብከቱን ሥራ ለዘለቄታው ማስቆም እንደቻሉ የሚያሳይ ነው? በጭራሽ!

5 ይሖዋ ‘በእናንተ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ [ሁሉ] ይከሽፋል’ በማለት ቃል እንደገባ እናስታውስ። ወንድም ራዘርፎርድና ሌሎቹ ወንድሞች እስራት ከተፈረደባቸው ከዘጠኝ ወራት በኋላ መጋቢት 26, 1919 ባልታሰበ መንገድ ሁኔታዎች በመቀያየራቸው እነዚህ ወንድሞች በገንዘብ ዋስትና ተለቀቁ። በቀጣዩ ዓመት ግንቦት 5, 1920 ቀደም ሲል ከቀረበባቸው ክስ ነፃ ተደረጉ። እነዚህ ወንድሞች ባገኙት ነፃነት በመጠቀም የስብከቱን ሥራ ማከናወናቸውን ቀጠሉ። ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ እድገት ታይቷል! ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ‘ታዳጊያችን’ የሆነው ይሖዋ ነው።—1 ቆሮ. 3:7

6, 7. (ሀ) በናዚ አገዛዝ ወቅት በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ምን ለማድረግ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር? ውጤቱስ ምን ነበር? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ የትኛውን እውነታ ያረጋግጣል?

6 አሁን ደግሞ ሁለተኛውን ምሳሌ እንመልከት። በ1934 ሂትለር በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን በሙሉ ለማጥፋት ዝቶ ነበር። ይህ እንዲያው ተራ ዛቻ አልነበረም። ብዙም ሳይቆይ በርካቶች ተይዘው ታሰሩ። በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት የደረሰባቸው ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተገድለዋል። ታዲያ ሂትለር የይሖዋ ምሥክሮችን ለማጥፋት ያካሄደው ዘመቻ ተሳክቶለት ይሆን? በጀርመን የሚካሄደውን የስብከት ሥራ ሙሉ በሙሉ ማስቆምስ ችሎ ነበር? በፍጹም! በዚህ የስደት ወቅት ወንድሞቻችን በድብቅ መስበካቸውን ቀጥለው ነበር። የናዚ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ ደግሞ ባገኙት ነፃነት በመጠቀም መስበካቸውን ቀጥለዋል። በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ከ165,000 በላይ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይገኛሉ። አዎን፣ ‘ታዳጊያችን’ የሆነው ይሖዋ ‘በእናንተ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል’ በማለት የገባውን ቃል ጠብቋል።

7 የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ እንደሚያሳየው ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ በቡድን ደረጃ እንዲጠፉ ፈጽሞ አይፈቅድም። (መዝ. 116:15) ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃስ ጥበቃ ያደርግልናል? ይሖዋ እያንዳንዳችንን የሚታደገን እንዴት ነው?

አካላዊ ጥበቃስ ያደርግልናል?

8, 9. (ሀ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አካላዊ ጥበቃ ለማድረግ ቃል እንዳልገባ እንዴት እናውቃለን? (ለ) አካላዊ ጥበቃ ማግኘትን በተመለከተ ምን መገንዘብ ይኖርብናል?

8 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በግለሰብ ደረጃ አካላዊ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ቃል እንዳልገባ እናውቃለን። ንጉሥ ናቡከደነፆር ላሠራው የወርቅ ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ ያልነበሩት ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያን የነበራቸው ዓይነት አቋም አለን። ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው እነዚህ ወጣቶች ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አካላዊ ጥበቃ ያደርግልናል የሚል አመለካከት አልነበራቸውም። (ዳንኤል 3:17, 18ን አንብብ።) በእርግጥ ይሖዋ ከሚንበለበለው የእቶን እሳት አድኗቸዋል። (ዳን. 3:21-27) ሆኖም በጥንት ዘመንም እንኳ ቢሆን ይሖዋ ሕዝቦቹን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ያዳናቸው ሁልጊዜ አልነበረም። በርካታ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በተቃዋሚዎቻቸው ተገድለዋል።—ዕብ. 11:35-37

9 በዛሬው ጊዜስ? ይሖዋ ‘ታዳጊ’ እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦችን ከአደገኛ ሁኔታዎች ማዳን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ይሖዋ በአንዳንድ ሁኔታዎች ጣልቃ እንደገባ ወይም እንዳልገባ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን? አንችልም። ያም ቢሆን ከአደገኛ ሁኔታ የዳነ አንድ ሰው ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እንደረዳው ይሰማው ይሆናል። ሌሎች ሰዎች የዚህን ሰው አመለካከት መቃወማቸው ያለ ቦታቸው መግባት ይሆንባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በናዚ አገዛዝ ወቅት እንደሆነው ሁሉ በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች በደረሰባቸው ስደት ምክንያት እንደሞቱ መገንዘብ ይኖርብናል። ሌሎች ደግሞ በተለያዩ አሳዛኝ ሁኔታዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። (መክ. 9:11) እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎችን ስናስብ ‘እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሕይወታቸው በአጭሩ የተቀጨው እሱ ስላልታደጋቸው ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።

10, 11. የሰው ልጅ ራሱን ከሞት ማዳን የማይችለው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሞትን ምን ያደርገዋል?

10 “ራሱን ከሲኦል [ወይም ከሐዴስ ማለትም ከመቃብር] እጅ ማዳን” የሚችል ማንም ሰው እንደሌለ እናስታውስ። (መዝ. 89:48) ይሖዋስ ሊያድነን ይችላል? ሽብር ከነገሠበት የናዚ አገዛዝ በሕይወት የተረፈች አንዲት እህት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የምትወዳቸውን ሰዎች በሞት ባጣችበት ወቅት፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቷ እሷን ስታጽናናት “የሞቱ ሰዎች ሞተው የሚቀሩ ከሆነ ሞት ከአምላክ የበለጠ ኃይል ሊኖረው ነው ማለት ነው” ብላት እንደነበር ታስታውሳለች። ሞት፣ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ኃያል አምላክ የበለጠ ኃይል እንደሌለው ምንም ጥርጥር የለውም! (መዝ. 36:9) ይሖዋ በሲኦል ወይም በሐዴስ ያሉትን ሁሉ የሚያስታውሳቸው ሲሆን እያንዳንዳቸውንም ይታደጋቸዋል።—ሉቃስ 20:37, 38፤ ራእይ 20:11-14

11 በዛሬው ጊዜም ቢሆን ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹን ለመርዳት ጣልቃ ይገባል። ይሖዋ እኛን ‘የሚታደግባቸውን’ ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል

12, 13. መንፈሳዊ ጥበቃ ማግኘት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

12 ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን ሲሆን ይህም ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአሁኑ ጊዜ ካለን ሕይወት የበለጠ ውድ የሆነ ነገር እንዳለ እንገነዘባለን። ከምንም በላይ ውድ የሆነው ሀብታችን በግላችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ነው። (መዝ. 25:14፤ 63:3) እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ከሌለን በአሁኑ ጊዜ የምንመራው ሕይወት ትርጉም የለሽ ይሆናል፤ ለወደፊቱ ጊዜም ተስፋ አይኖረንም።

13 ደስ የሚለው፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር የመሠረትነውን የቅርብ ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት የሚያስችለንን እርዳታ ይሰጠናል። በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ይረዳናል። ታዲያ ከእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል ትጋት በተሞላበት መንገድ አዘውትረን በማጥናት እምነታችንን ማጠንከርና ተስፋችን ብሩኅ ሆኖ እንዲታየን ማድረግ እንችላለን። (ሮሜ 15:4) አምላክ፣ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን አጥብቀን በመጸለይ አጠያያቂ በሆኑ ተግባሮች እንድንካፈል የሚደርስብንን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እናገኛለን። (ሉቃስ 11:13) ታማኝና ልባም ባሪያ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ በመከተል “በተገቢው ጊዜ” ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ‘ምግብ’ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ማቴ. 24:45) በእነዚህ ዝግጅቶች ከተጠቀምን መንፈሳዊ ጥበቃ የምናገኝ ከመሆኑም በላይ ወደ አምላክ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን።—ያዕ. 4:8

14. ይሖዋ፣ መንፈሳዊ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

14 ይሖዋ፣ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት እንደሆነ ለመረዳት እንድንችል ቀደም ባለው ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትን ወላጆች እንደ ምሳሌ እንመልከት። ልጃቸው ቴሬዛ እንደጠፋች ከተነገራቸው ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ቴሬዛ መገደሏን የሚገልጽ አሳዛኝ ዜና ሰሙ። * አባቷ እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋ እንዲጠብቃት ጸሎት አቅርቤ ነበር። ሕይወቷ በሰው እጅ ሲያልፍ ‘ጸሎቴ ያልተሰማልኝ ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን በግለሰብ ደረጃ በተአምራዊ መንገድ ለመጠበቅ ቃል እንዳልገባ አውቃለሁ። ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ ስል ሳልታክት ጸሎት አቀረብኩ። ይሖዋ ሕዝቦቹን ይጠብቃል ሲባል የሚጠብቀው በመንፈሳዊ መሆኑን ይኸውም ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዳይበላሽ ለማድረግ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን ማወቄ እንድጽናና ረድቶኛል። ይህ ዓይነቱ ጥበቃ ከዘላለማዊ ደህንነታችን ጋር የተያያዘ በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ቴሬዛ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት ታገለግለው ስለነበር ይሖዋ በዚህ በኩል ጥበቃ አድርጎላታል ማለት ነው። ወደፊት ሕይወት የማግኘቷ ጉዳይ አፍቃሪ በሆነው አምላካችን እጅ ያለ መሆኑን ማወቄ እፎይታ አስገኝቶልኛል።”

በሕመም ወቅት ይንከባከበናል

15. ከባድ ሕመም በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ በየትኞቹ መንገዶች ሊረዳን ይችላል?

15 ይሖዋ ለዳዊት እንዳደረገለት ሁሉ እኛንም ‘ታመን ባለንበት ዐልጋ ላይ ሊንከባከበን’ ይችላል። (መዝ. 41:3) ምንም እንኳ ይሖዋ በዘመናችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባይታደገንም የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በቃሉ ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሕክምናና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዱን ይችላሉ። (ምሳሌ 2:6) ያለብንን የጤና ችግር በተመለከተ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ከሚወጡት ርዕሶች ጠቃሚ ሐሳቦችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮች ማግኘት እንችል ይሆናል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመንም፣ ይሖዋ ያለብንን ችግር መቋቋምና ታማኝነታችንን ጠብቀን መመላለስ እንድንችል በመንፈሱ አማካኝነት “እጅግ ታላቅ ኀይል” ሊሰጠን ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7) እንዲህ ያለው እርዳታ በሕመማችን ላይ ከመጠን በላይ በማተኮር መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንዳንስት ይረዳናል።

16. አንድ ወንድም ሕመሙ ያስከተለበትን ሁኔታ መቋቋም የቻለው እንዴት ነው?

16 ቀደም ባለው ርዕስ መግቢያ ላይ ተጠቅሶ የነበረውን ወጣት ወንድም እንመልከት። በ1998 ይህ ወንድም ኤማያትሮፊክ ላተራል ስክለሮስስ የተባለ በሽታ እንዳለበት የተነገረው ሲሆን ከጊዜ በኋላ በሽታው ሙሉ በሙሉ ሽባ አደረገው። * ይህ ወንድም በሽታው ያስከተለበትን ሁኔታ መቋቋም የቻለው እንዴት ነው? እንዲህ ይላል:- “ከሥቃዬ መገላገል የምችለው ስሞት ብቻ እንደሆነ ሳስብ ከፍተኛ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ይሰማኝ ነበር። በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ ይሖዋ ሦስት ነገሮችን እንዲያደርግልኝ እለምነዋለሁ:- ልቤ እንዲረጋጋ፣ ትዕግሥተኛ መሆን እንድችልና እንድጸና እንዲረዳኝ እጠይቀዋለሁ። ይሖዋም ለጸሎቴ መልስ እንደሰጠኝ ይሰማኛል። ልቤ መረጋጋቱ በሚያጽናኑ ሐሳቦች ላይ እንዳሰላስል አስችሎኛል፤ መራመድ፣ ጣፋጭ ምግቦችን መመገብ እንዲሁም ከቤተሰቦቼ ጋር መጨዋወት የምችልበት አዲሱ ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል በአእምሮዬ ለመሳል እሞክራለሁ። ታጋሽ መሆኔ እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻል የሚያስከትላቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ለመቋቋም አስችሎኛል። ጽናት ደግሞ በታማኝነት እንድቀጥል እንዲሁም መንፈሳዊ ሚዛኔን እንዳልስት ረድቶኛል። በእርግጥም ይሖዋ ታምሜ ባለሁበት አልጋ ላይ እንደተንከባከበኝ ስለሚሰማኝ የዳዊትን ስሜት እጋራለሁ።”—ኢሳ. 35:5, 6

የዕለት ምግባችንን ይሰጠናል

17. ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል? የገባልን ቃል ምን ትርጉም አለው?

17 ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። (ማቴዎስ 6:33, 34ን እና ዕብራውያን 13:5, 6ን አንብብ።) ይህ ሲባል ግን የሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደሚሟሉልን መጠበቅ ወይም ደግሞ ሳንሠራ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ እንችላለን ማለት አይደለም። (2 ተሰ. 3:10) ከዚህ ይልቅ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ካስቀደምንና ለመተዳደሪያ የሚሆነንን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞች ከሆንን ይሖዋ ለኑሮ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች እንድናገኝ እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን ማለት ነው። (1 ተሰ. 4:11, 12፤ 1 ጢሞ. 5:8) ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ባልጠበቅነው መንገድ ሊያሟላልን ይችላል፤ ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቁሳዊ ነገሮችን እንዲሰጠን ወይም ሥራ እንድናገኝ እንዲረዳን ሊያነሳሳው ይችላል።

18. ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

18 ቀደም ባለው ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችውን ነጠላ እናት እናስታውስ። ከትንሽ ልጇ ጋር በመሆን ወደ ሌላ አካባቢ በተዛወረችበት ወቅት ሥራ ለማግኘት ተቸግራ ነበር። ይህች እህት እንዲህ ብላለች:- “ጠዋት ጠዋት አገልግሎት የምወጣ ሲሆን ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሥራ ለማግኘት ጥረት አደርግ ነበር። አንድ ቀን ወተት ለመግዛት ወደ አንድ ሱቅ ገባሁ። እዚያም አትክልቶችን ብመለከትም አንዱንም ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አልነበረኝም። በሕይወቴ እንደዚያን ቀን ተሰምቶኝ አያውቅም። የዚያን ቀን ወደ ቤት ስመለስ ከቤቴ ጀርባ ባለው በረንዳ ላይ በተለያዩ አትክልቶች የተሞሉ ከረጢቶችን አገኘሁ። ይህ ለወራት የሚበቃን ምግብ ነበር። እንባዬ በጉንጮቼ እየወረደ ይሖዋን አመሰገንኩት።” ይህን ስጦታ ያመጣላቸው በግቢው ውስጥ አትክልቶችን የሚያለማ በጉባኤያቸው የሚገኝ አንድ ወንድም መሆኑን እህት በኋላ ላይ አወቀች። ከጊዜ በኋላ ለዚህ ወንድም እንዲህ ስትል ጽፋለታለች:- “የዚያን ዕለት በጣም ያመሰገንኩህ ቢሆንም ይሖዋ በአንተ ደግነት ተጠቅሞ ፍቅሩን ስላሳየኝ እሱንም አመስግኜዋለሁ።”—ምሳሌ 19:17

19. በታላቁ መከራ ወቅት የይሖዋ አገልጋዮች ምን እንደሚያገኙ መተማመን ይችላሉ? በአሁኑ ጊዜ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

19 ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ በጥንት ጊዜያትም ሆነ በዘመናችን ያደረጋቸው ነገሮች ዛሬም እንደሚረዳን ለመተማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ይሆኑናል። በቅርቡ በሰይጣን ዓለም ላይ ታላቁ መከራ ሲመጣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ያም ቢሆን የይሖዋ አገልጋዮች አምላካቸው እንደሚረዳቸው ሙሉ በሙሉ መተማመን ይችላሉ። መዳናቸው እንደቀረበ ስለሚያውቁ ራሳቸውን ቀና ማድረግና መደሰት ይችላሉ። (ሉቃስ 21:28) እስከዚያው ድረስ ግን ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን የማይለወጠው አምላካችን በእርግጥም ‘ታዳጊያችን’ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በእሱ ላይ እምነታችንን ለመጣል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ ሕይወታቸው በአጭሩ ለተቀጨ ሰዎች ታዳጊ የሚሆንላቸው እንዴት ነው?

• መንፈሳዊ ጥበቃ ማግኘት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚሰጠን የገባው ቃል ምን ትርጉም አለው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ራዘርፎርድና ሌሎቹ ወንድሞች በ1918 ታስረው የነበረ ቢሆንም ከቀረበባቸው ክስ ከጊዜ በኋላ ነፃ ተደርገዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ‘ታመን ባለንበት ዐልጋ ላይ ሊንከባከበን’ ይችላል