በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገበያ ስፍራ መመሥከር

በገበያ ስፍራ መመሥከር

በገበያ ስፍራ መመሥከር

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በአቴና ከተማ በነበረበት ወቅት ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ለመስበክ በየቀኑ ወደ ገበያ ስፍራ ይሄድ ነበር። (ሥራ 17:17) ጳውሎስ በዚህ ቦታ መስበክን የመረጠው የአቴና ነዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በገበያ ስፍራ ስለነበረ ነው።

ከ2,000 ዓመታት ገደማ በኋላም የይሖዋ ሕዝቦች ወደ ገበያ ቦታዎች በመሄድ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ይሰብካሉ። ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚሄዱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በርካታ ሰዎችን በዚያ ያገኛሉ። በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች የሚሸምቱት በትላልቅ የገበያ ማዕከሎች ውስጥ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ከገበያ ማዕከሉ ኃላፊ ወይም ባለቤት ፈቃድ ካገኙ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ገበያተኞች እንዲመለከቷቸው ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣሉ።

ለምሳሌ በኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ትልቅ የገበያ ማዕከል ውስጥ ጽሑፎች የሰዎችን ትኩረት በሚስብ መንገድ ተደርድረው ነበር። በጠረጴዛው ላይ “በቤተሰብ ውስጥ መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚል ጽሑፍ ተቀምጦ ነበር። ምን ውጤት ተገኘ? በስድስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ 153 ጽሑፎችን በአንድ ቀን ውስጥ ማበርከት ተችሏል።

አንዲት ሴት ጽሑፎች ወደተደረደሩበት ጠረጴዛ ቀረብ ብላ ስለ ጽሑፎቹ ማብራሪያ ትሰጥ የነበረችውን የይሖዋ ምሥክር በጥሞና ማዳመጥ ጀመረች። ሴትየዋ በግልም ሆነ በቤተሰብ ሕይወታችን ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ከግምት ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን እንደምትስማማ ገልጻለች። ከዚያም ከታላቁ አስተማሪ ተማር፣ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባሉትን መጻሕፍት ወስዳለች።

የዚያን ቀን ከሰዓት በኋላ ጽሑፎቹ ከተደረደሩበት ጠረጴዛ አጠገብ ወደሚገኘው ሱቅ እየገባ የነበረ አንድ ሰው የወጣቶች ጥያቄ የተባለውን መጽሐፍ ሲያይ ትኩረቱ ተሳበ። ጠረጴዛው አጠገብ ቆማ የነበረችው እህት ሰውየውን የማረከው ነገር እንዳለ ከአስተያየቱ ማወቅ ስለቻለች “የወደድከው መጽሐፍ አለ?” በማለት ጠየቀችው። ሰውየውም ራሱን በመነቅነቅ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጣት በኋላ የወጣቶች ጥያቄ የተባለውን መጽሐፍ ሲጠቁማት እህት መጽሐፉን ሰጠችው። ሰውየው ሦስት ልጆች እንዳሉትና በሳምንት አንድ ጊዜ ውይይት የሚያደርጉበት ፕሮግራም እንዳላቸው ነገራት። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቹ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ይገኛሉ። ሰውየው መጽሐፉን እያገላበጠ ከተመለከተ በኋላ ከቤተሰቡ ጋር በሚያደርገው ውይይት ላይ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፉን እንደ መመሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት እንደሚችል ተናግሯል። አስፋፊዋ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የሚለውን መጽሐፍም ለሰውየው በማሳየት እሱም ሆነ ባለቤቱ ከቤተሰቡ ሕይወት ጋር በተያያዘ ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት የሚረዷቸው በጣም ጠቃሚ ምክሮችን ከዚህ መጽሐፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ጠቆመችው። ግለሰቡ፣ እህት ለሰጠችው ሐሳብ ምስጋናውን በመግለጽ ለጽሑፎቹ የገንዘብ መዋጮ ከማድረጉም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች እሱንና ቤተሰቡን መጥተው እንዲጠይቋቸው የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል።

በዚያን ዕለት በገበያ ማዕከሉ ሲሰብኩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ተሰምቷቸው ይሆን? አንዲት እህት “እኔ በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱን የስብከት ዘዴ ወድጄዋለሁ፤ ይህ ለእኔ ልዩ አጋጣሚ ነበር!” ብላለች። ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ፣ ምሥራቹ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንደሚሰበክ ተናግሯል። በዛሬው ዕለት በፐራመስ፣ ኒው ጀርሲ ይህ የምሥራች የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን ልብ ሲነካ መመልከት ችያለሁ። በገበያ ማዕከል ውስጥ ለመስበክ በተደረገው ዝግጅት መካፈል መቻል በጣም የሚያስደስት ነው። በዚህ ሥራ የተሳተፉት ሁሉ ደስተኞች ነበሩ። አመሻሹ ላይ ማናችንም ወደ ቤት መመለስ አልፈለግንም ነበር።”

አንተስ ምሥራቹን ለመስበክ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ትችል ይሆን? የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዋነኛነት የምንሰብከው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ነው። (ሥራ 20:20) ይሁንና በገበያ ስፍራ ወይም በገበያ ማዕከል ውስጥ ለመመሥከርስ ለምን አትሞክርም?