በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዝናብ በመኖሩ አመስጋኝ ሁን

ዝናብ በመኖሩ አመስጋኝ ሁን

ዝናብ በመኖሩ አመስጋኝ ሁን

ዝናብ ባይኖር ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? እውነት ነው፣ በጣም ኃይለኛ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም ሌላ ቀዝቃዛና ዝናባማ የአየር ንብረት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ዝናብ ሊያማርራቸው ይችላል። (ዕዝራ 10:9) ይሁንና በጣም ሞቃትና ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ስለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች ከብዙ ጊዜ በኋላ ዝናብ ሲያገኙ በእጅጉ ይደሰታሉ!

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው በሚገኙት አገሮች የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፤ ከእነዚህ መካከል ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊነት ያገለገለበት የትንሿ እስያ መካከለኛ ክፍል ይገኝበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እዚያ በነበረበት ወቅት ለጥንቶቹ ሊቃኦንያውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል፦ “[አምላክ] መልካም ነገሮች በማድረግ ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት የተትረፈረፈ ምግብ ያቀርብላችኋል፣ ልባችሁንም በደስታ ይሞላዋል።” (የሐዋርያት ሥራ 14:17) እዚህ ላይ ጳውሎስ በመጀመሪያ ዝናብን መጥቀሱ ሊስተዋል የሚገባው ነው፤ ዝናብ ከሌለ ምንም ነገር ሊበቅልና “ፍሬያማ ወቅቶች” ሊኖሩ አይችሉም።

መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ስለ ዝናብ ይናገራል። ዝናብን ለማመልከት የተሠራባቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። አስደናቂ ስለሆነው ስለዚህ ስጦታ ይበልጥ ማወቅ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ስለመሆኑ ያለህን እምነት ማጠናከር ትፈልጋለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዝናብ ምን ይላል?

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ለዝናብ መኖር በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ጠቅሶ ነበር። ኢየሱስ “አባታችሁ . . . በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል” ብሏል። (ማቴዎስ 5:45) እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለ ዝናብ ከመናገሩ በፊት ፀሐይን እንደጠቀሰ አስተዋልክ? ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ፀሐይ ዕፅዋት ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ኃይል መስጠት ብቻ ሳይሆን ለምድር የውኃ ዑደትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። በየዓመቱ 400,000 ኪሎ ሜትር ኩብ የባሕር ውኃ ተኖ ጨው አልባ ወደሆነ እንፋሎት የሚለወጠው ከፀሐይ በሚመነጨው ሙቀት ነው። ፀሐይን የፈጠረው ይሖዋ አምላክ በመሆኑ ዝናብን ለማዝነብ ውኃን ወደ ላይ ያተናል መባሉ ተገቢ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የውኃ ዑደትን እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል፦ “[አምላክ] የውሃን ነጠብጣብ ወደ ላይ ያተናል፤ መልሶም በዝናብ መልክ በጅረቶች ላይ ያወርዳል፤ ደመናት ጠል ያንጠባጥባሉ፤ ዶፍም በሰው ላይ ይወርዳል።” (ኢዮብ 36:26-28) ሳይንሳዊ ድጋፍ ያለው ይህ ሐሳብ ከተጻፈ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፈ በመሆኑ የሰው ልጅ የውኃን ዑደት ለማጥናት የሚያስችል ሰፊ ጊዜ ነበረው። ይሁንና በ2003 የተዘጋጀው ዋተር ሳይንስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ የተባለ መማሪያ መጽሐፍ “በአሁኑ ጊዜ . . . የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት አይታወቅም” በማለት ገልጿል።

የሳይንስ ሊቃውንት የሚያውቁት ነገር ቢኖር የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት በዓይን በማይታዩ ቅንጣቶች እንደሆነ ነው፤ እነዚህ ቅንጣቶች በደመና ውስጥ በጣም ትናንሽ ጠብታዎች እንዲፈጠሩ መሠረት ሆነው ያገለግላሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትናንሽ ጠብታዎች ተጠራቅመው አንድ የዝናብ ጠብታ ይፈጥራሉ። ይህ ደግሞ በርካታ ሰዓታትን የሚፈጅ ውስብስብ የሆነ ሂደት ነው። ሃይድሮሎጂ ኢን ፕራክቲስ የተባለ የሳይንስ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “በደመና ውስጥ ያሉ ትናንሽ ጠብታዎች ወደ ዝናብ ጠብታዎች የሚቀየሩት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ። እንዲህ ያሉ ጽንሰ ሐሳቦች አሁንም ቢሆን የበርካታ ተመራማሪዎችን ትኩረት በመሳብ ላይ ይገኛሉ።”

ዝናብ እንዲገኝ የሚያደርገውን የውኃ ዑደት የፈጠረው አምላክ አገልጋዩን ኢዮብን እንደሚከተሉት ያሉ ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ የሚገፋፉ ጥያቄዎች ጠይቆት ነበር፦ “ዝናብ አባት አለውን? የጤዛን ጠብታ ማን ወለደው? . . . ደመናትን ለመቍጠር ጥበብ ያለው ማን ነው? የሰማያትንስ የውሃ ገንቦ ዘንበል ማድረግ ማን ይችላል?” (ኢዮብ 38:28, 38) ይህ ከሆነ 3,500 ዓመታት ቢያልፉም የሳይንስ ሊቃውንት ለእነዚህ ከባድ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት አልቻሉም።

የውኃ ዑደት የሚከናወነው በምን መንገድ ነው?

የግሪክ ፈላስፎች፣ የወንዝ ውኃ የሚገኘው ከዝናብ ሳይሆን ከባሕር እንደሆነ ያስተምሩ ነበር፤ እንደ እነሱ አባባል ከሆነ የባሕር ውኃ በሆነ መንገድ በምድር ውስጥ ለውስጥ ሄዶ ወደ ተራሮች አናት ከወጣ በኋላ ንጹሕ የምንጭ ውኃ ሆኖ ይፈሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ፣ ሰለሞን እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንደነበረው አድርጎ ይናገራል። ሰለሞን በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት፦ “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።” (መክብብ 1:7) በእርግጥ ሰለሞን፣ የባሕር ውኃ በሆነ መንገድ ውስጥ ለውስጥ ሄዶ ወደ ተራራ ከወጣ በኋላ ወንዝ ሆኖ ይፈሳል ማለቱ ነበር? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እስራኤላውያን ወገኖቹ ስለ ውኃ ዑደት ምን ብለው ያምኑ እንደነበር እንመልከት። የጥንት እስራኤላውያን የውኃ ዑደትን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው?

ሰለሞን ከኖረ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ኤልያስ የተባለው የአምላክ ነቢይ የተናገረው ነገር፣ ዝናብ የሚገኘው ከየት እንደሆነ ያውቅ እንደነበር ያሳያል። በኤልያስ ዘመን ከሦስት ዓመት በላይ የቆየ ከባድ ድርቅ ተከስቶ ነበር። (ያዕቆብ 5:17) ይሖዋ አምላክ በሕዝቦቹ ላይ ይህን መቅሰፍት ያመጣው እሱን ትተው የከነዓናውያን የዝናብ አምላክ የሆነውን በኣልን ማምለክ በመጀመራቸው ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የኤልያስን ምክር ሰምተው ንስሐ በመግባታቸው ኤልያስ በምድሪቱ ላይ ዝናብ እንዲመጣ ጸለየ። ኤልያስ እየጸለየ ሳለ አገልጋዩን “ወደ ባሕሩ ተመልከት” አለው። አገልጋዩ “የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች” መሆኑን ሲነግረው ኤልያስ ጸሎቱ ምላሽ እንዳገኘ ተገነዘበ። ወዲያውኑ “ሰማዩ በጥቍር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱ ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብ ጣለ።” (1 ነገሥት 18:43-45) ይህ ዘገባ ኤልያስ ስለ ውኃ ዑደት እውቀት እንደነበረው ያሳያል። ከባሕሩ በላይ ደመና እንደሚፈጠርና ወደ ምሥራቅ በሚነፍሰው ነፋስ እየተገፋ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚወሰድ ያውቅ ነበር። እስከ አሁን ድረስ ምድሪቱ ዝናብ የምታገኘው በዚህ መንገድ ነው።

ኤልያስ ዝናብ እንዲመጣ ከጸለየ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አሞጽ የተባለ አንድ ገበሬ የውኃን ዑደት አስመልክቶ ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ ገልጿል። እስራኤላውያን፣ ድሆችን በመጨቆናቸውና የሐሰት አማልክትን በማምለካቸው ቅጣት እንደሚደርስባቸው አምላክ በአሞጽ በኩል ትንቢት አስነግሮ ነበር። አምላክ እንዳያጠፋቸው አሞጽ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።” ከዚያም አሞጽ፣ ይሖዋ “የባሕሩንም ውሃ ጠርቶ፣ በገጸ ምድር ላይ የሚያፈስ” ፈጣሪ በመሆኑ መመለክ የሚገባው እሱ ብቻ እንደሆነ ገለጸላቸው። (አሞጽ 5:6, 8) ቆየት ብሎ አሞጽ የውኃ ዑደት የሚከናወንበትን ሂደት አስመልክቶ ይህን አስደናቂ እውነታ በድጋሚ ተናግሯል። (አሞጽ 9:6) በዚህ መንገድ አሞጽ የዝናብ ዋነኛ ምንጭ ውቅያኖስ እንደሆነ አመልክቷል።

በ1687 ኤድመንድ ሃሊ ይህን ሐቅ በሳይንስ አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ሃሊ ያቀረቡት ማስረጃ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ኦንላየን እንዲህ ይላል፦ “የውኃ ዑደት የሚከናወነው በምድር ውስጥ ሲሆን የባሕር ውኃ ወደ ተራራ ከወጣ በኋላ [ወንዝ ሆኖ] ይፈሳል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እስከ 18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ተቀባይነት ነበረው።” በዛሬው ጊዜ፣ የውኃ ዑደት የሚከናወንበትን መንገድ ማንኛውም ሰው ያውቀዋል። ይኸው ኢንሳይክሎፒዲያ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ከባሕር ላይ ውኃ ይተንና በአየር ውስጥ ወደ ፈሳሽነት ይለወጣል ከዚያም ዝናብ ሆኖ ወደ ምድር ይወርዳል፤ በመጨረሻም ውኃው ወደ ወንዞች ይገባና ወደ ባሕር ይመለሳል።” ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰለሞን በ⁠መክብብ 1:7 ላይ ስለ ዝናብ ዑደት የተናገረው ሐሳብ ይህንኑ ሂደት የሚያመለክት ነው።

ይህን ማወቅህ ምን እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል?

የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የውኃን ዑደት በትክክል መግለጻቸው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጅ ፈጣሪ በሆነው በይሖዋ አምላክ መንፈስ መሪነት መጻፉን ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እርግጥ ነው፣ የሰው ልጆች የምድርን የተፈጥሮ ሀብት አላግባብ መጠቀማቸው የአየር ንብረቱ እንዲዛባና በአንዳንድ አካባቢዎች ኃይለኛ ጎርፍ፣ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ሆኖም የውኃን ዑደት የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን እንደሚያጠፋ’ ከረጅም ጊዜ በፊት ቃል ገብቷል።—ራእይ 11:18

ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ለዝናብም ሆነ ለሌሎቹ የአምላክ ስጦታዎች ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና የተማርከውን ተግባር ላይ በማዋል ይህን ማድረግ ትችላለህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አምላክ ወደፊት የሚያመጣውን አዲስ ዓለም መውረስና በአምላክ ስጦታዎች እየተደሰትክ ለዘላለም መኖር ትችላለህ። በእርግጥም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ዝናብን ከፈጠረው ከይሖዋ አምላክ ነው።—ያዕቆብ 1:17

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዝናብ

ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ ተን

ከተክሎች የሚወጣ ተን

ትነት

ጎርፍ

መሬት ውስጥ ያለ ውኃ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ እየጸለየ ሳለ አገልጋዩን “ወደ ባሕሩ ተመልከት” ብሎት ነበር