በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ፈራጅ

ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ፈራጅ

ወደ አምላክ ቅረብ

ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ፈራጅ

ዘፍጥረት 18:22-32

ፍትሕሚዛናዊነትና አለማዳላት። እንዲህ ያሉ ግሩም ባሕርያት አይማርኩህም? ሰዎች ስንባል በተፈጥሯችን ሌሎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙን እንፈልጋለን። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ የፍትሕ መጓደል በእጅጉ ተስፋፍቷል። ይሁንና ልንተማመንበት የሚገባ አንድ ፈራጅ አለ፤ እሱም ይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ነገር ትክክል ነው። ዘፍጥረት 18:22-32 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይሖዋና አብርሃም ያደረጉት ውይይት ይህን በግልጽ ያሳያል። *

ይሖዋ ለአብርሃም በሰዶምና ገሞራ ያለውን ሁኔታ ለመመርመር እንዳሰበ ሲነግረው አብርሃም የአጎቱ ልጅ የሆነውን ሎጥን ጨምሮ በዚያ የሚኖሩት ጻድቃን ደኅንነት አሳስቦት ነበር። በመሆኑም ይሖዋን እንዲህ በማለት ጠየቀው፦ “በእርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ . . . በውስጧ ለሚገኙ አምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን አትምርምን?” (ቁጥር 23, 24) አምላክ 50 ጻድቃን ቢገኙ ከተማዋን እንደማያጠፋት ገለጸለት። አብርሃምም ቁጥሩ አሥር እስኪደርስ ድረስ ይሖዋን አምስት ጊዜ ጠይቆታል። አምላክ፣ አብርሃም በጠየቀው ቁጥር ያን ያህል ጻድቃን ካሉ ከተማዋን እንደማያጠፋት ነገረው።

በዚህ ወቅት አብርሃም አምላክን እየተሟገተ ነበር? በፍጹም! ቢሟገት ኖሮ የትዕቢት መንፈስ እንዳንጸባረቀ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ሆኖም የአብርሃም አነጋገር አክብሮታዊ ፍርሃትና ትሕትና እንደነበረው ያሳያል። እንዲያውም ራሱን “ትቢያና ዐመድ” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም “እባክህ” በማለት አክብሮት በተሞላበት መንገድ ተናግሯል። (ቁጥር 27, 30-32) ከዚህም በላይ የአብርሃም አነጋገር ይሖዋ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንደሚፈርድ ያለውን እምነት ያሳያል። አብርሃም፣ አምላክ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር ያጠፋል ማለት “ፈጽሞ የማይታሰብ” [NW] እንደሆነ ከአንዴም ሁለቴ ተናግሯል። ታማኙ የእምነት አባት “የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን [እንደሚፈርድ]” ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል።—ቁጥር 25

አብርሃም የተናገራቸው ነገሮች ትክክል ነበሩ? መልሱ በአንድ በኩል አዎን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አይደለም የሚል ነው። በሰዶምና ገሞራ ቢያንስ አሥር ጻድቃን ሊገኙ ይችላሉ ብሎ ማሰቡ ስህተት ሲሆን አምላክ ‘ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንደማያጠፋ’ መናገሩ ግን ትክክል ነበር። በኋላም አምላክ እነዚህን በክፋት የተሞሉ ከተሞችን ሲያጠፋ ጻድቁ ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ በመላእክት እርዳታ በሕይወት ተርፈዋል።—2 ጴጥሮስ 2:7-9

ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመመርመር እንዳሰበ ለአብርሃም በመንገር ሐሳቡን እንዲገልጽ መንገድ ከፍቶለታል። ከዚያም ወዳጁ አብርሃም ያስጨነቀውን ነገር ሲናገር በትዕግሥት አዳምጦታል። (ኢሳይያስ 41:8) ይህ ታሪክ፣ ይሖዋ በምድር ላይ ያሉትን አገልጋዮቹን የሚያከብር ትሑት አምላክ እንደሆነ ያስተምረናል። በተጨማሪም ምንጊዜም ትክክለኛ ፍርድ በሚሰጠው በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ የምንታመንበት በቂ ምክንያት እንዳለን ያሳያል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.1 በዚህ ወቅት ይሖዋን ወክሎ አብርሃምን ያነጋገረው አንድ መልአክ ነው። ሌላ ምሳሌ ለማግኘት ዘፍጥረት 16:7-11, 13⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም ሰዶምና ገሞራን አስመልክቶ ይሖዋን ጠይቆታል