በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የለምጽ በሽታ በዛሬው ጊዜ ምን ያመለክታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ለምጽ” የሚለው ቃል በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ የሚከሰተውን በባክቴሪያ የሚተላለፍ የሥጋ ደዌ በሽታንም ያመለክታል። ይህን ባክቴሪያ (ማይኮባክቲሪየም ሌፕሬ) በ1873 ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት ዶክተር ጌርሃርት ሃንሰን ናቸው። ተመራማሪዎች ይህ ባክቴሪያ ከሰውነት ውጪ በንፍጥ ውስጥ ሆኖ እስከ ዘጠኝ ቀን ድረስ በሕይወት መቆየት እንደሚችል ደርሰውበታል። ከዚህ በተጨማሪ ከሥጋ ደዌ በሽተኞች ጋር በቅርብ የሚገናኙ ሰዎች በበሽታው የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ እንደሆነና ባክቴሪያው ያለባቸው አልባሳትም ለበሽታው መዛመት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተረድተዋል። የዓለም የጤና ድርጅት በ2007 ብቻ የሥጋ ደዌ በሽታ እንዳለባቸው የታወቁ ሰዎች ቁጥር ከ220,000 በላይ መሆኑን ሪፖርት አድርጓል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የሥጋ ደዌ በሽታ ሰዎችን ያጠቃ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም። በመሆኑም የሙሴ ሕግ የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበት ሰው ተገልሎ እንዲቀመጥ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 13:3-5 የ1954 ትርጉም) ይሁን እንጂ “ለምጽ” ተብሎ የተተረጎመው ጻራት የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሚሠራበት በሰዎች ላይ የሚከሰተውን በሽታ ለማመልከት ብቻ አይደለም። ጻራት በልብስና በቤቶችም ላይ ሊወጣ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ለምጽ ከሱፍ ወይም ከበፍታ በተሠሩ ልብሶች ላይ ወይም ከቆዳ በተሠራ በማንኛውም ነገር ላይ ሊታይ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ለምጹ ልብሱን በማጠብ ሊጠፋ ይችላል፤ ሆኖም “አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት” እና አልለቅ ቢል ልብሱ ወይም ቆዳው መቃጠል ነበረበት። (ዘሌዋውያን 13:47-52) በአንድ ቤት ግድግዳ ላይ “ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት የሚያደላ የተቦረቦረ ነገር” ሲታይ ደዌው መከሰቱን ማወቅ ይቻላል። በዚህ ጊዜ በበሽታው የተለከፈውን ድንጋይ ማውጣት፣ ልስኑን ደግሞ መፈቅፈቅ እና ሰው ወደማይኖርበት አካባቢ ወስዶ መጣል ያስፈልግ ነበር። ለምጹ ተመልሶ ከተከሰተ ቤቱ መፍረስ ያለበት ከመሆኑም ሌላ የግንባታ ቁሳቁሶቹም መወገድ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 14:33-45) አንዳንዶች በልብሶች ወይም በቤቶች ላይ የሚወጣው ለምጽ በአሁኑ ጊዜ ሻጋታ ወይም ሽበት ተብሎ የሚጠራውን ሊያመለክት እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ያከናወነው ስብከት ብር አንጥረኞቹ ሁከት እንዲያስነሱ ያደረገው ለምንድን ነው?

በኤፌሶን የሚኖሩት ብር አንጥረኞች “የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች” በመሥራት ብዙ ገቢ ያገኙ ነበር። አርጤምስ የአደን፣ የመራባትና የወሊድ አምላክ እንዲሁም የኤፌሶን ከተማ ጠባቂ እንደሆነች ይታመን ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:24) ምስሏ “ከሰማይ” እንደወረደና በኤፌሶን በሚገኘው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደተቀመጠ ይነገር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:35) ይህ ቤተ መቅደስ በጥንት ጊዜ ከተሠሩ የዓለማችን ሰባት አስደናቂ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። በየዓመቱ መጋቢት/ሚያዝያ ላይ ለአርጤምስ ክብር በሚካሄደው በዓል ላይ ለመገኘት ብዙ አማኞች ወደ ኤፌሶን ይጎርፉ ነበር። ወደዚህ ስፍራ የሚጎርፉት ሰዎች ለአምልኮ የሚያገለግሉ ዕቃዎችን ማስታወሻ እንዲሆኗቸው፣ ከአደጋ እንዲጠብቋቸው፣ ወደመጡበት ቦታ በሚመለሱበት ጊዜ ቤተሰባቸው ለአምልኮ እንዲጠቀምባቸው ወይም በስጦታ መልክ ለአምላካቸው ለመስጠት ይፈልጓቸው ስለነበር ዕቃዎቹ ከፍተኛ ገበያ ነበራቸው። በኤፌሶን የተገኙ ጥንታዊ የተቀረጹ ጽሑፎች ከወርቅና ከብር የተሠሩ የአርጤምስ ምስሎች በብዛት ይመረቱ እንደነበር ይገልጻሉ፤ ሌሎች የተቀረጹ ጽሑፎችም በወቅቱ ስለነበረው የብር አንጥረኞች ማኅበር ለይተው ይጠቅሳሉ።

ጳውሎስ “በእጅ የተሠሩ” ምስሎች “አማልክት አይደሉም” በማለት አስተምሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:26) በመሆኑም ብር አንጥረኞቹ መተዳደሪያቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ስጋት ስላደረባቸው የጳውሎስን የስብከት እንቅስቃሴ በመቃወም ዓመፅ አነሳሱ። ከብር አንጥረኞቹ አንዱ የሆነው ድሜጥሮስ ያደረባቸውን ስጋት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “አሳሳቢ የሆነው ይህ የእኛ ሥራ መናቁ ብቻ ሳይሆን የታላቋ አምላክ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ዋጋ ቢስ ሆኖ ሊቀርና መላው የእስያ አውራጃም ሆነ ዓለም በሙሉ የሚያመልከው ገናናው ክብሯ ሳይቀር ሊገፈፍ መሆኑ ጭምር ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 19:27