በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ቀኔ አልደረሰም”

“ቀኔ አልደረሰም”

“ቀኔ አልደረሰም”

የአንድ ትልቅ የቆሻሻ መኪና ሾፌር መኪናውን መቆጣጠር ስላቃተው መንገዱን ስቶ በመውጣት በአካባቢው የነበሩ ሦስት እግረኞችን ገጨ። በኒው ዮርክ ሲቲ የሚታተም ጋዜጣ እንደዘገበው፣ አብረው ሲሄዱ የነበሩት ወንድና ሴት በአደጋው ወዲያውኑ የሞቱ ሲሆን አንድ የ23 ዓመት ወጣት ደግሞ ራሱን ሳተ። ወጣቱ ራሱን ካወቀ በኋላ፣ የተፈጠረውን አደጋ ሲመለከት ‘እኔ አላምንም፤ ይህ በእኔ ላይ ደረሰ ማለት ነው? አምላክ ሆይ እባክህ እርዳኝ’ ብሎ አሰበ። ከዚያም “ቀኔ አልደረሰም” በማለት ተናገረ።

አንተም ተመሳሳይ ነገር ሲባል ሳትሰማ አልቀረህም። ብዙዎች፣ አንድ ግለሰብ ከአደጋ ለጥቂት እንዳመለጠ ሲመለከቱ ‘ቀኑ አልደረሰም’ ይላሉ፤ ባልተጠበቀ አደጋ ሲሞት ግን ‘ቀኑ ደርሶ ነው’ ወይም ‘የአምላክ ፈቃድ ስለሆነ ነው’ ይላሉ። ሰዎቹ ለደረሰው ሁኔታ መንስኤው ዕድልም ነው ይበሉ የአምላክ ፈቃድ፣ መሠረታዊ ሐሳቡ አንድ ነው። ብዙዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥማቸው ማንኛውም ነገር አስቀድሞ እንደተወሰነ ስለሚያምኑ ይህን ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ይህ ዓይነቱ እምነት ከጥንትም የነበረ ነው። ከዚህም በላይ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት የሚያንጸባርቁት ሞት ወይም ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥማቸው ብቻ አይደለም።

ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን የኖሩት ባቢሎናውያን የከዋክብት እንቅስቃሴ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያምኑ ነበር። በመሆኑም ዕድላቸውን ለማወቅ የሰማይ አካላትን ይመለከታሉ። ግሪኮችና ሮማውያን ደግሞ የዕድል አማልክትን ያመልኩ ነበር፤ እነዚህ እንስት አማልክት ሰዎች ጥሩም ሆነ መጥፎ ሁኔታ እንዲያጋጥማቸው በማድረግ ረገድ ያላቸው ኃይል ዋና አማልክት ከሆኑት ከዙስ እና ከጁፒተር እንኳ እንደሚበልጥ ይታሰብ ነበር።

በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ደግሞ ሂንዱዎችና ቡድሂስቶች፣ አንድ ሰው ከአሁን በፊት በነበረው ሕልውና ያደረጋቸው ነገሮች በአሁኑ ሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እንዲሁም አሁን የሚያደርጋቸው ነገሮች ወደፊት በሚኖረው ሕልውና ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ያምናሉ። በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርትም የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን እምነት እንደሚደግፉ ያሳያል።

በመሆኑም ሰዎች በማስረጃ በተደገፉ ነገሮች ብቻ እንደሚያምኑ በሚታሰብበት በዚህ ዘመን እንኳ ብዙዎች የሕይወት ዕጣቸው፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዲሁም ዕድላቸው አስቀድሞ እንደተወሰነ እና ይህን ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ማመናቸው ምንም አያስገርምም። አንተስ እንደዚህ ታስባለህ? በእርግጥ የሰው ልጆች የሚያጋጥማቸው ነገር፣ በሕይወታቸው ስኬታማ መሆን አለመሆናቸው ሌላው ቀርቶ መወለድና መሞት እንኳ አስቀድሞ የተወሰነ ነገር ነው? ሕይወትህን የሚቆጣጠረው ዕድል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Ken Murray/New York Daily News