በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰውን ሳይሆን አምላክን እንድንፈራ የሚያደርጉን አምስት ምክንያቶች

ሰውን ሳይሆን አምላክን እንድንፈራ የሚያደርጉን አምስት ምክንያቶች

ሰውን ሳይሆን አምላክን እንድንፈራ የሚያደርጉን አምስት ምክንያቶች

ወጣቱ በጣም የተደሰተ ከመሆኑም ሌላ ነገሩ አስገርሞታል። ያጋጠመው ሁኔታ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነበር። ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያደረገው ውይይት ዓይኑን ገልጦለታል። ‘አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ለብዙ ዓመታት ያስጨንቀው የነበረ ቢሆንም አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግልጽ መልስ አግኝቷል። ይህ ወጣት፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚና አስደሳች የሆነ መረጃ እንደያዘ አያውቅም ነበር።

ሲያነጋግሩት የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ከሄዱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ቤቱን ያከራየችው ሴት በሩን በርግዳ በመግባት “እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” በማለት በቁጣ ጠየቀችው።

የሴትየዋ ሁኔታ በጣም ያስገረመው ይህ ወጣት ምንም መልስ ሊሰጣት አልቻለም።

“እነማን እንደሆኑ አውቄያለሁ። ሁለተኛ እዚህ ቤት ድርሽ ካሉ ቤቱን ለቀህ መውጣት ትችላለህ!” በማለት ጮኸችበት።

ከዚያም በሩን በኃይል ዘግታው ሄደች።

የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው ያውቃሉ

ይህ ወጣት ያጋጠመው ሁኔታ እንግዳ ነገር አይደለም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) በጥቅሉ ሲታይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ አይደሉም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “እኛ ከአምላክ ወገን መሆናችንን እናውቃለን፤ መላው ዓለም ግን በክፉው ኃይል ሥር ነው” ብሏቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ” ተደርጎ ተገልጿል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) ሰውን መፍራት፣ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ውጤታማ የሆኑ መሣሪያዎች መካከል አንዱ ነው።

ለሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ያደረገውና ምንም ኃጢአት ያልሠራው ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ፌዝና ተቃውሞ ደርሶበታል። ኢየሱስ “ያለ ምክንያት ጠሉኝ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:25) ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንደሚከተለው በማለት ተከታዮቹን ለሚጠብቃቸው ነገር አዘጋጅቷቸዋል፦ “ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ። ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኳችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል።”—ዮሐንስ 15:18, 20

ብዙዎች ይህን ማስጠንቀቂያ በመፍራት ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ከመቆም ወደኋላ ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስን በመፈለግ ላይ ስለነበሩ ሰዎች ሲናገር “አይሁዳውያንን ይፈሩ ስለነበረ ስለ እሱ በግልጽ የሚናገር ሰው አልነበረም” ይላል። (ዮሐንስ 7:13፤ 12:42) በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ በክርስቶስ የሚያምን ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንደሚገለል በማስጠንቀቅ ሕዝቡን ያስፈራሩ ነበር። ስለሆነም ብዙዎች ሰውን መፍራታቸው ክርስቲያን እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:13

ክርስትና ከተቋቋመ በኋላ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ “ከባድ ስደት” እንደተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 8:1) እንዲያውም በመላው የሮም ግዛት ክርስቲያኖች ስደት ደርሶባቸው ነበር። በሮም የነበሩ ታዋቂ ሰዎች፣ ሐዋርያው ጳውሎስን “ስለዚህ ኑፋቄ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ [እናውቃለን]” ብለውታል። (የሐዋርያት ሥራ 28:22) አዎን፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በየቦታው ስደት ይደርስባቸው ነበር።

በዛሬው ጊዜም ሰይጣን ብዙዎች ሰውን በመፍራት የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ከመሆን ወደኋላ እንዲሉ ለማድረግ ይጥራል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ያሉ ቅን ሰዎች በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ወይም ከማኅበረሰቡ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል አሊያም ይፌዝባቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች፣ በሰዎች ዘንድ ያላቸውን ከበሬታ ብሎም ወዳጆቻቸውን እንደሚያጡ ወይም ሌሎች ቁሳዊ ድጋፍ እንደማያደርጉላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ገጠራማ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ገበሬዎች በመከር ወቅት ጎረቤቶቻቸው እንደማይረዷቸው ወይም ከብቶቻቸውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ በማሰብ ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። እንዲህ ያለ ፍራቻ ቢኖርም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ ለመታመንና የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ከአምላክ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም ይሖዋ ባርኳቸዋል።

ሰውን ሳይሆን አምላክን መፍራት ያለብን ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው” በማለት ሰውን ሳይሆን አምላክን እንድንፈራ ያሳስበናል። (መዝሙር 111:10) ይህ ዓይነቱ ፍርሃት የሚያርበደብድ ወይም የሚያሸብር ሳይሆን ሕይወት የሰጠንን አምላክ ላለማሳዘን ብለን የምናሳየው ጤናማ ፍርሃት ነው። አምላክን መፍራት ከፍቅር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ታዲያ ሰውን ሳይሆን አምላክን መፍራት ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አምስት ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።

1 ይሖዋ ከሁሉ በላይ ነው። ይሖዋ ከማንም ሰው የላቀ ኃይል አለው። አምላክን መፍራታችን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጎን እንደተሰለፍን ያሳያል፤ በእሱ ፊት “አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው።” (ኢሳይያስ 40:15) አምላክ ሁሉን ቻይ በመሆኑ ለእሱ ታማኝ በሆኑ ሰዎች ላይ ‘እንዲደገን የተበጀን መሣሪያ’ ሁሉ ለማክሸፍ የሚያስችል ኃይል አለው። (ኢሳይያስ 54:17) የዘላለም ሕይወት ማግኘት ያለበት ማን እንደሆነ የሚወስነው ይሖዋ ስለሆነ ስለ እሱ ከመማርና ፈቃዱን ከመፈጸም ምንም ነገር ወደኋላ እንዲያደርገን አለመፍቀዳችን ጥበብ ነው።—ራእይ 14:6, 7

2 አምላክ ይረዳናል እንዲሁም ይጠብቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ምሳሌ 29:25 ላይ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል” ይላል። በአምላክ ላይ ያለንን እምነት በግልጽ ከመናገር ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ስለሚችል ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው። አምላክ እንደሚከተለው በማለት እኛን ለማዳን ኃይል እንዳለው ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:10

3 አምላክ ወደ እሱ የሚቀርቡ ሰዎችን ይወዳቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተሉትን ልብ የሚነኩ ቃላት ጽፏል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።” (ሮም 8:37-39) በአምላክ የምንታመንና እሱን የምንታዘዝ ከሆነ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጽኑ ፍቅር ያሳየናል። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

4 አምላክ ያደረገልንን ነገሮች በሙሉ ከፍ አድርገን እንመለከታለን። ይሖዋ ሕይወት የሰጠን ፈጣሪያችን ነው። በተጨማሪም ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ሕይወት አስደሳችና እርካታ የሞላበት እንዲሆን የሚያደርጉ ነገሮችንም ሰጥቶናል። በእርግጥም አምላክ የመልካም ስጦታ ሁሉ ምንጭ ነው። (ያዕቆብ 1:17) አምላክ ያሳየውን ፍቅራዊ ደግነት ከፍ አድርጎ ይመለከት የነበረው ታማኙ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ . . . ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም።”—መዝሙር 40:5

5 ይቃወሙን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ይለወጡ ይሆናል። አቋምህን ከማላላት ይልቅ አምላክን ለመፍራትና እሱን ለመውደድ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ የሚቃወሙህን ሰዎች ልትረዳቸው ትችላለህ። የኢየሱስን ዘመዶች እንደ ምሳሌ ተመልከት። መጀመሪያ ላይ አላመኑበትም ነበር፤ እንዲያውም “አእምሮውን ስቷል” እስከ ማለት ደርሰዋል። (ማርቆስ 3:21፤ ዮሐንስ 7:5) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን ከዘመዶቹ መካከል ብዙዎቹ አማኞች ሆነዋል። አልፎ ተርፎም የኢየሱስ ወንድሞች የነበሩት ያዕቆብና ይሁዳ ከቅዱሳን መጻሕፍት መካከል የተወሰኑትን የመጻፍ መብት አግኝተዋል። ክርስቲያኖችን አጥብቆ ያሳድድ የነበረው ሳኦልም ተለውጦ ጳውሎስ የተባለ ሐዋርያ ሆኗል። በዛሬው ጊዜም ስደት የሚያደርሱብን አንዳንድ ሰዎች ያለንን ጽኑ አቋም ሲመለከቱ እውነት እኛ ጋር እንዳለ ሊያስተውሉ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 1:13

ለምሳሌ ያህል፣ በኢትዮጵያ የምትኖር አበራሽ የተባለች አንዲት ሴት እውነትን ለማግኘት ትጸልይ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር ከቤተሰቦቿ አባላትና ከሃይማኖት መሪዎች ከባድ ተቃውሞ አጋጠማት። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው የነበሩት አንዳንድ ዘመዶቿ በሰው ፍርሃት ተሸንፈው ጥናታቸውን አቆሙ። እሷ ግን አምላክ ብርታትና ጥንካሬ እንዲሰጣት አጥብቃ ትጸልይ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። መጽናቷ ምን ውጤት አስገኘ? ከዘመዶቿ መካከል ስምንቱ በእሷ አቋም ተበረታተው እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩ ሲሆን ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ ናቸው።

የሰውን ፍርሃት ማሸነፍ ትችላለህ

በሰው ፍርሃት እንዳትሸነፍ ለአምላክ ያለህን ፍቅር ለማጠናከር አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና እንደ ዕብራውያን 13:6 ባሉ ጥቅሶች ላይ በማሰላሰል ለአምላክ ያለህን ፍቅር ማጠናከር ትችላለህ። ጥቅሱ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ይላል። ሰውን ሳይሆን አምላክን መፍራት ትክክልና የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩትን ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች አትዘንጋ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርካቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋልህ የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች አስታውስ። በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ትችላለህ። እንዲሁም የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ታገኛለህ። በዛሬው ጊዜ ያሉት ሁኔታዎች ግራ የሚያጋቡ ቢሆኑም አስደሳች ተስፋ ይኖርሃል። በተጨማሪም በማንኛውም ጊዜ ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ በጸሎት መቅረብ ትችላለህ።

ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:17) በአሁኑ ጊዜ ጽኑ አቋም መያዝና አምላካዊ ፍርሃት ማዳበር ይኖርብናል። ሰውን በመፍራት እምነትህ እንዲዳከም ከመፍቀድ ይልቅ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት አምላክ ላቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ትችላለህ። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

አምላክ ለሚፈሩት ሰዎች የሚሰጠውን ነገር ማንም ሰው ሊሰጥህ እንደማይችል አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው” ይላል።—ምሳሌ 22:4

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አበራሽ በመጽናቷ ከዘመዶቿ መካከል ስምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን ቀጥለዋል