በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በኅብረት የምናቀርብለት ውዳሴ ይገባዋል

ይሖዋ በኅብረት የምናቀርብለት ውዳሴ ይገባዋል

ይሖዋ በኅብረት የምናቀርብለት ውዳሴ ይገባዋል

“ሕዝቦች ሆይ፣ ያህን አወድሱ!”—መዝ. 111:1 NW

1, 2. “ሃሌ ሉያ” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው? በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበትስ እንዴት ነው?

“ሃሌ ሉያ!” በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይህን አባባል መስማት የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ ሰዎች በዕለታዊ ንግግራቸው ውስጥ አጽንዖት መስጠት የሚፈልጉት ነገር ሲኖር በዚህ አባባል በብዛት ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ይህ አባባል በውስጡ የያዘውን ጥልቅ ትርጉም የሚረዱት ጥቂቶች ሲሆኑ በዚህ አባባል የሚጠቀሙ ብዙዎች የሚከተሉት አኗኗር ደግሞ ለአምላክ ክብር አያመጣም። (ቲቶ 1:16) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “የተለያዩ መዝሙራትን የጻፉ ሰዎች፣ ሃሌ ሉያ የሚለውን ቃል ሁሉም ሰው አብሯቸው ይሖዋን እንዲያወድስ ለመጋበዝ ይጠቀሙበት ነበር” ሲል ገልጿል። እንዲያውም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን “ሃሌ ሉያ” የሚለው አባባል “ያህን [ማለትም] ይሖዋን አወድሱ” የሚል ትርጉም እንዳለው ጠቅሰዋል።

2 አዲስ ዓለም ትርጉም በ⁠መዝሙር 111:1 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ “ሕዝቦች ሆይ፣ ያህን አወድሱ!” ብሎ ተርጉሞታል፤ ይህም ትክክል ነው። ይህ አባባል በ⁠ራእይ 19:1-6 ላይ በግሪክኛ አገባቡ አራት ጊዜ የሚገኝ ሲሆን የተሠራበትም የሐሰት ሃይማኖት መጥፋቷን ተከትሎ የተገኘውን ደስታ ለመግለጽ ነው። የሐሰት ሃይማኖት በምትጠፋበት ጊዜ እውነተኛ አምላኪዎች “ሃሌ ሉያ” የሚለውን አባባል ክብር ባለው መንገድ የሚጠቀሙበት ልዩ ምክንያት ይኖራቸዋል።

የይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች

3. በየጊዜው የምንሰበሰብበት ዋናው ዓላማ ምንድን ነው?

3 የ⁠መዝሙር 111 አቀናባሪ ለይሖዋ በኅብረት ውዳሴ ማቅረባችን ተገቢ የሆነባቸውን በርካታ ምክንያቶች ጠቅሷል። ቁጥር 1 እንዲህ ይላል፦ “በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።” በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። በየጉባኤዎቻችንም ሆነ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በየጊዜው አንድ ላይ የምንሰበሰብበት ዋናው ዓላማ ይሖዋን ለማወደስ ነው።

4. ሰዎች የይሖዋን ሥራ መፈለግ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 “የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፣ ደስ በሚሰኙባት ሁሉ ዘንድ የተፈለገች ናት።” (መዝ. 111:2 የ1954 ትርጉም) “የተፈለገች ናት” የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው ይህ ጥቅስ በአምላክ ሥራ ላይ “ትኩረት አድርገው በተመስጦ የሚያሰላስሉና የሚያጠኑ” ሰዎችን ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል ብሏል። የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች አስደናቂ የሆኑ በርካታ ነገሮች እንዲከናወኑ ያስችላሉ። ይሖዋ ለፀሐይ፣ ለምድርና ለጨረቃ ቦታ የመደበላቸው ሲሆን እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሁሉም ቦታቸውን እንዲጠብቁ በማስቻል ምድራችን ሙቀትና ብርሃን እንድታገኝ፤ ሌሊትና ቀን እንዲሁም ወቅቶች እንዲፈራረቁ ብሎም በውኃ አካላት ላይ እንቅስቃሴ እንዲከሰት አድርጓል።

5. ሰዎች ስለ አጽናፈ ዓለም ያላቸው ግንዛቤ እያደገ መሄዱ ምን አስገኝቷል?

5 የሳይንስ ሊቃውንት በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ምድር ስለምትገኝበት ቦታ እንዲሁም በትክክለኛ ሁኔታ የተሠራችው ግዙፏ ጨረቃ ስላላት ምኅዋር፣ መጠንና ክብደት ብዙ እውቀት አካብተዋል። እነዚህ የሰማይ አካላት የተደራጁበት መንገድም ሆነ በመካከላቸው ያለው ዝምድና ጊዜውን ጠብቆ የሚከሰት ግሩም የሆነ የወቅቶች መፈራረቅ እንዲኖር አስችሏል። በተጨማሪም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ኃይሎች ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተስተካክለው የተሠሩ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች ተገኝተዋል። በመሆኑም የሜካኒካል ምሕንድስና ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ ምሑር “አንዳች ዝንፍ ሳይል የተሠራ አጽናፈ ዓለም” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጽሑፍ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት አጽናፈ ዓለም በራሱ መጣ ብሎ ማሰብ ከፍተኛ እምነት ይጠይቃል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፤ በመሆኑም ባለፉት 30 ዓመታት [ሊቃውንቱ] የአመለካከት ለውጥ ያደረጉበትን ምክንያት መረዳት አዳጋች አይሆንም። በጥንቃቄ የተሠራችውን መኖሪያችንን ይበልጥ እያወቅናት በመጣን መጠን የማስተዋል ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ አለ ብለን ለማመን እንገደዳለን።”

6. አምላክ ሰውን ስለሠራበት መንገድ ምን ይሰማሃል?

6 የአምላክ የፍጥረት ሥራ አስደናቂ መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ነገር እሱ እኛን የሠራበት መንገድ ነው። (መዝ. 139:14) አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር አእምሮ፣ አስፈላጊ የሰውነት ክፍሎች የተሟሉለት አካል እንዲሁም ሥራ የመሥራት ችሎታና አቅም ሰጥቷቸዋል። አምላክ ከሰጠን የመናገርና የማዳመጥ እንዲሁም የመጻፍና የማንበብ ችሎታ ጋር በተያያዘ የሚታየውን ተአምር እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ብዙ ሰዎች እነዚህ ችሎታዎች አሏቸው። በተጨማሪም ቀጥ ብሎ መቆም የሚችለው ሰውነትህ አስደናቂ የሆነ የምሕንድስና ሥራ የተንጸባረቀበት ነው። ሰውነትህ ያለው ቅርጽም ሆነ በተመጣጠነ ሁኔታ የተሠራ መሆኑ እንዲሁም በውስጡ የሚካሄደው ሥራ ብሎም መንቀሳቀስና የተለያዩ ሥራዎች ማከናወን መቻልህ በግርምት እንድትዋጥ ያደርግሃል። ከዚህም በላይ አእምሮህና የስሜት ሕዋሳትህ መሥራት እንዲችሉ የሚያደርጉት አስደናቂ የሆኑት የነርቭ አውታሮች፣ የሳይንስ ሊቃውንት ከሠሯቸው ከየትኞቹም ነገሮች ጋር ፈጽሞ ሊወዳደሩ አይችሉም። ደግሞም ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን መሥራት እንዲችሉ ያደረጋቸው ብቸኛው ምክንያት አእምሮና የስሜት ሕዋሳት ኖሯቸው መፈጠራቸው ነው። ከፍተኛ ሥልጠና ያገኘና የላቀ ችሎታ ያለው መሐንዲስ እንኳ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የተሠሩትን የጣቶችህን ያህል ውበትና ጠቃሜታ ያላቸው መሣሪያዎች መፈልሰፍ አይችልም። እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘አምላክ እንደፈለግነው የሚታዘዙልን ጣቶች ባይሰጠን ኖሮ አስደናቂ የሆኑ የሥነ ጥበብም ሆነ የግንባታ ሥራዎች ሊከናወኑ ይችሉ ነበር?’

የአምላክ ታላላቅ ሥራዎችና ባሕርያት

7. መጽሐፍ ቅዱስን ከአምላክ ታላላቅ ሥራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገን መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?

7 የይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች እሱ ለሰው ልጆች ሲል ያደረጋቸውን ሌሎች ድንቅ ነገሮችም የሚጨምሩ ሲሆን እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነው፤ በውስጡ ያሉት የተለያዩ ክፍሎች እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸውም ያስገርማል። ከሌላ ከማንኛውም መጽሐፍ በተለየ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ለማስተማር የሚጠቅም ነው።’ (2 ጢሞ. 3:16) ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ አምላክ በኖኅ ዘመን ክፋትን ከምድር ገጽ እንዴት እንዳስወገደ ይገልጻል። ከዘፍጥረት ቀጥሎ የሚገኘው የዘፀአት መጽሐፍ ደግሞ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ በማውጣት አምላክነቱን እንዴት እንዳረጋገጠ ያሳያል። መዝሙራዊው የሚከተለውን የተናገረው እነዚህን ነገሮች በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም፦ [ይሖዋ] ሥራው ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ቸር፣ ርኅሩኅም ነው።” (መዝ. 111:3, 4) በአንተ የሕይወት ዘመን የተከናወኑትን ጨምሮ ይሖዋ በታሪክ ዘመናት በሙሉ ያደረጋቸው ነገሮች የእሱ ‘ክብርና ግርማ’ ሲታወስ እንዲኖር ያደርጋሉ ቢባል አትስማማም?

8, 9. (ሀ) የአምላክ ሥራዎች ሰዎች ካከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች የተለዩ የሆኑት በምን መንገዶች ነው? (ለ) አንተ በግልህ የምታደንቃቸው አንዳንዶቹ የአምላክ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

8 መዝሙራዊው እንደ ጽድቅ፣ ቸርነትና ርኅራኄ ያሉትን የይሖዋን ግሩም ባሕርያት ጎላ አድርጎ እንደገለጸም ልብ በል። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የሚያደርጉት ነገር አብዛኛውን ጊዜ በጽድቅ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃለህ። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ አድራጎታቸው ከስግብግብነት፣ ከምቀኝነትና ከትዕቢት የሚመነጭ ነው። የዚህን እውነተኝነት፣ ለሚያካሂዱት ጦርነትና የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከሚያመርቷቸው አሰቃቂ እልቂት የሚያስከትሉ መሣሪያዎች ማየት ይቻላል። እነዚህ መሣሪያዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎችን ለአስከፊ ሰቆቃና ለከፍተኛ ስጋት ዳርገዋል። በተጨማሪም ሰዎች የሠሯቸው አብዛኞቹ ሥራዎች የተከናወኑት ድሆችን መጠቀሚያ በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ ብዙ ሰዎች በባሪያዎች ጉልበት የተገነቡትን ፒራሚዶች እንደ ምሳሌ ይጠቅሱ ይሆናል። እነዚህ ፒራሚዶች በዋነኝነት ያገለገሉት ለኩሩዎቹ ፈርዖኖች የመቃብር ቦታ ሆነው ነበር። ከዚህም በላይ በዛሬ ጊዜ ሰዎች የሚያከናውኗቸው አብዛኞቹ ሥራዎች በሰዎች ላይ ጭቆና የሚያስከትሉ ከመሆናቸውም ሌላ “ምድርን እያጠፉ” ናቸው።—ራእይ 11:18ን አንብብ።

9 ምንጊዜም ትክክል በሆነ ነገር ላይ የተመሠረቱት የይሖዋ ሥራዎች ከዚህ ምንኛ የተለዩ ናቸው! ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ለማዳን ያደረገው ምሕረት የተንጸባረቀበት ዝግጅት ከሥራዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው። አምላክ የቤዛውን ዝግጅት በማድረግ ‘የራሱን ጽድቅ አሳይቷል።’ (ሮም 3:25, 26) በእርግጥም ‘ጽድቁ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል!’ አምላክ ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን በትዕግሥት በመያዙ ቸርነቱ ሊታይ ችሏል። ሰዎች ጎጂ ከሆነው መንገዳቸው ተመልሰው ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉ በሚማጸናቸው ጊዜ በደግነት ይዟቸዋል።—ሕዝቅኤል 18:25ን አንብብ።

የገባውን ቃል በታማኝነት ይጠብቃል

10. ይሖዋ ለአብርሃም ከገባው ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

10 “ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።” (መዝ. 111:5) መዝሙራዊው እዚህ ላይ እየጠቀሰ ያለው የአብርሃምን ቃል ኪዳን ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ የአብርሃምን ዘር እንደሚባርከው እንዲሁም ዘሮቹ የጠላቶቻቸውን ደጅ እንደሚወርሱ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍ. 22:17, 18፤ መዝ. 105:8, 9) እነዚህ የተስፋ ቃሎች የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ባገኙበት ወቅት የአብርሃም ዘር ሆኖ የተገኘው የእስራኤል ብሔር ነበር። ይህ ብሔር ለብዙ ዓመታት በግብፅ በባርነት ሥር የቆየ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ‘አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማሰብ’ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው። (ዘፀ. 2:24) ይሖዋ እነሱን የያዘበት መንገድ ምን ያህል ቸር እንደሆነ ያሳያል። ለሰውነታቸው የሚያስፈልግ ምግብ፤ ለአእምሯቸውና ለልባቸው ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ ይሰጣቸው ነበር። (ዘዳ. 6:1-3፤ 8:4፤ ነህ. 9:21) ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዓመታት አምላክ ወደ እሱ እንዲመለሱ ለማሳሰብ ነቢያትን ቢልክላቸውም እንኳ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ በአምላክ ላይ ፊታቸውን ያዞሩ ነበር። አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ ካወጣቸው ከ1,500 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከ። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ኢየሱስን አልተቀበሉትም፤ እንዲያውም እንዲገደል አሳልፈው ሰጥተውታል። ከዚያ በኋላ ይሖዋ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክን እስራኤል’ አቋቋመ። ይህ ብሔር ከክርስቶስ ጋር በመሆን የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር ሆነ። ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመባረክ በዚህ ዘር እንደሚጠቀም አስቀድሞ ተናግሯል።—ገላ. 3:16, 29፤ 6:16

11. ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባውን ‘ኪዳን እንደሚያስብ’ እያሳየ ያለው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ‘ኪዳኑን የሚያስብ’ ከመሆኑም ሌላ በገባው ቃል አማካኝነት እንደሚመጡ የተናገራቸውን በረከቶች ያስታውሳል። በዛሬው ጊዜ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ነው። ከዚህም ሌላ “የዕለቱን ምግባችንን ለዕለቱ የሚያስፈልገንን ያህል ስጠን” ከሚለው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ ሰብዓዊ ፍላጎቶቻችን እንዲሟሉልን ለምናቀርበው ልመና መልስ መስጠቱን ቀጥሏል።—ሉቃስ 11:3፤ መዝ. 72:16, 17፤ ኢሳ. 25:6-8

የይሖዋ እጅግ ታላቅ ኃይል

12. የጥንቶቹ እስራኤላውያን ‘የአሕዛብ ርስት የተሰጣቸው’ በምን መንገድ ነው?

12 “ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣ የአሠራሩን ብርታት አሳይቶአል።” (መዝ. 111:6) መዝሙራዊው እንዲህ ሲል በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ክንውኖች አንዱን ይኸውም ከግብፅ በተአምር የወጡበትን ሁኔታ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ በፈቀደላቸው ጊዜ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ያሉትን መንግሥታት ድል ማድረግ ችለው ነበር። (ነህምያ 9:22-25ን አንብብ።) አዎን፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን “የአሕዛብን ርስት” ሰጥቷቸዋል። አምላክ ኃይሉን የገለጠበት እንዴት ያለ አስደናቂ ክንውን ነው!

13, 14. (ሀ) መዝሙራዊው፣ አምላክ ከባቢሎናውያን ጋር በተያያዘ ኃይሉን የገለጸበትን የትኛውን ሁኔታ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል? (ለ) ይሖዋ ሕዝቦቹን ነፃ ለማውጣት ሲል ያከናወናቸው ሌሎች ታላላቅ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

13 ሁላችንም በሚገባ እንደምናውቀው፣ ይሖዋ ብዙ ነገር ያደረገላቸው ቢሆንም እንኳ እስራኤላውያን ለእሱም ሆነ ቅድመ አያቶቻቸው ለሆኑት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አክብሮት ሳያሳዩ ቀርተዋል። አምላክ ባቢሎንን ተጠቅሞ በግዞት እንዲወሰዱ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን በዓመፅ ጎዳና መመላለሳቸውን ገፍተውበት ነበር። (2 ዜና 36:15-17፤ ነህ. 9:28-30) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን እንደሚሉት የመዝሙር 111 አቀናባሪ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ በሕይወት ኖሮ ከሆነ ይሖዋን ለታማኝነቱና ለኃይሉ የሚያወድስበት ተጨማሪ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። አምላክ ታማኝነቱንና ኃይሉን ያሳየው በምርኮ የያዘቻቸውን ሰዎች ከግዛቷ እንዳይወጡ የማድረግ ደንብ ትከተል ከነበረችው የባቢሎን ግዛት አይሁዳውያንን ነፃ በማውጣት ነው።—ኢሳ. 14:4, 17

14 ከአምስት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ ይሖዋ ንስሐ የገቡትን የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ በማውጣት ኃይሉን እጅግ በላቀ ሁኔታ አሳይቷል። (ሮም 5:12) ይሖዋ እንዲህ ማድረጉ ካስገኛቸው ውጤቶች አንዱ 144,000 ሰዎች በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ መንገድ የተከፈተ መሆኑ ነው። በ1919 ይሖዋ የእነዚህን የተቀቡ ክርስቲያኖች ጥቂት ቀሪዎች ከሐሰት ሃይማኖት ምርኮ ነፃ ለማውጣት ኃይሉን ተጠቅሟል። ቅቡዓኑ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ያከናወኗቸውን ሥራዎች መፈጸም የቻሉት በአምላክ ኃይል ብቻ ነው። እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን ካስመሠከሩ በሰማይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆነው ምድርን ይገዛሉ፤ ይህም ንስሐ ለገቡት የሰው ዘሮች በረከት ያስገኝላቸዋል። (ራእይ 2:26, 27፤ 5:9, 10) ከጥንቶቹ እስራኤላውያን በተለየ መልኩ ስፋት ባለው ሁኔታ ምድርን ይወርሳሉ።—ማቴ. 5:5

እምነት የሚጣልባቸውና ዘላለማዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች

15, 16. (ሀ) ከአምላክ የእጅ ሥራዎች መካከል የትኞቹ ይገኙበታል? (ለ) አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ምን መመሪያዎችን ሰጥቶ ነበር?

15 “የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤ ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤ ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤ በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።” (መዝ. 111:7, 8) ከይሖዋ ‘የእጅ ሥራዎች’ መካከል ለእስራኤላውያን የተሰጡትን አሥር ዋና ዋና ሕግጋት የያዙት ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ይገኙበታል። (ዘፀ. 31:18) እነዚህ ሕጎችም ሆኑ በሙሴ ሕግ ውስጥ የታቀፉት ሌሎች ደንቦች እምነት በሚጣልባቸውና ዘላለማዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

16 ለምሳሌ ያህል፣ በጽላቶቹ ላይ ከሰፈሩት መመሪያዎች ወይም ሕጎች መካከል አንዱ ‘እኔ ይሖዋ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ’ ይላል። ሕጉ በመቀጠል ይሖዋ ‘ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ፍቅርን የሚያሳይ’ እንደሆነ ይገልጻል። የድንጋይ ጽላቶቹ የሌሎችን ንብረት መመኘት የሚከለክለውን ጥልቅ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ሕግ ጨምሮ “አባትህንና እናትህን አክብር” እና “አትስረቅ” እንደሚሉት ያሉ ጊዜ የማይሽራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችም ይዘዋል።—ዘፀ. 20:5, 6, 12, 15, 17

ቅዱስና የተፈራ አዳኛችን

17. እስራኤላውያን የአምላክን ስም በቅድስና እንዲይዙ የሚያደርጓቸው ምን ምክንያቶች ነበሯቸው?

17 “ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።” (መዝ. 111:9) በዚህ ጊዜም ቢሆን መዝሙራዊው ይህን የተናገረው ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል በታማኝነት እንደፈጸመ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ይሖዋ ሕዝቡን በመጀመሪያ በጥንቷ ግብፅ ባሮች ሆነው እንዲቀሩ አላደረገም፣ በኋላም በባቢሎን ምርኮኞች ሆነው ሕይወታቸውን በዚያው እንዲገፉ አልተዋቸውም። በሁለቱም ወቅቶች አምላክ ሕዝቡን አድኗል። እነዚህ ሁለት ክንውኖች ብቻ እንኳ እስራኤላውያን የአምላክን ስም በቅድስና እንዲይዙ ሊያደርጓቸው ይገባ ነበር።—ዘፀአት 20:7ንና ሮም 2:23, 24ን አንብብ።

18. የአምላክን ስም መሸከም መብት እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

18 መውጫ የሌለው ከሚመስለው ከኃጢአትና ከሞት ባርነት የዳኑት በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖችም ስሙን በቅድስና የሚይዙበት ምክንያት አላቸው። በናሙና ጸሎቱ ላይ ከተጠቀሰው “ስምህ ይቀደስ” ከሚለው የመጀመሪያው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። (ማቴ. 6:9) ታላቅ ክብር ባለው በዚህ ስም ላይ ማሰላሰላችን በውስጣችን አምላካዊ ፍርሃት ሊያሳድርብን ይገባል። የ⁠መዝሙር 111 ጸሐፊ “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው” ብሎ መናገሩ ለአምላካዊ ፍርሃት ትክክለኛ አመለካከት እንደነበረው ያሳያል።—መዝ. 111:10

19. በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንማራለን?

19 ለአምላክ ያለን ጤናማ ፍርሃት ለመጥፎ ነገር ጥላቻ እንድናዳብር ያስችለናል። በተጨማሪም በ⁠መዝሙር 112 ላይ የተገለጹትን የአምላክን ግሩም ባሕርያት እንድንኮርጅ ይረዳናል። በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ይህን መዝሙር እንመረምራለን። ይህ መዝሙር አምላክን ለዘላለም ከሚያወድሱት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ለመቆጠር ምን ማድረግ እንዳለብን ያሳያል። በእርግጥም ይሖዋ ሰዎች የሚያቀርቡለት ውዳሴ ይገባዋል። “ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።”መዝ. 111:10

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

• ለይሖዋ፣ በኅብረት ውዳሴ ልናቀርብለት ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?

• በሥራዎቹ ላይ የተንጸባረቁት የይሖዋ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

• የአምላክን ስም የመሸከም መብት በማግኘትህ ምን ይሰማሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየጊዜው አንድ ላይ የምንሰበሰብበት ዋናው ዓላማ ይሖዋን ለማወደስ ነው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሕጎች በሙሉ እምነት በሚጣልባቸውና ዘላለማዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው