በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጻድቃን አምላክን ለዘላለም ያወድሱታል

ጻድቃን አምላክን ለዘላለም ያወድሱታል

ጻድቃን አምላክን ለዘላለም ያወድሱታል

“ጻድቅ ሰው ሲታወስ ይኖራል። . . . ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል።”—መዝ. 112:6, 9

1. (ሀ) አምላክ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች በሙሉ ምን አስደሳች ተስፋ ይጠብቃቸዋል? (ለ) በዚህ ረገድ ምን የሚል ጥያቄ ይነሳል?

አምላክ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች በሙሉ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት ተጨማሪ እውቀት በመቅሰም ለዘላለም ተደስተው ይኖራሉ። ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ብዙ እያወቁ በሄዱ መጠን ልባቸው በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። እንዲህ የመሰለውን ታላቅ ተስፋ ለማግኘት ቁልፉ “ጽድቅ” ሲሆን መዝሙር 112 ደግሞ ይህን ባሕርይ ያጎላል። ይሁንና ቅዱስና ጻድቅ አምላክ የሆነው ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን እንዴት እንደ ጻድቅ አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል? ትክክል የሆነውን ለማድረግ ምንም ያህል ብንጥርም ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የምንሠራቸው ስህተቶች በጣም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ።—ሮም 3:23፤ ያዕ. 3:2

2. ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ያከናወናቸው ሁለት ተአምራት የትኞቹ ናቸው?

2 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ፍጹም መፍትሔ አዘጋጅቷል። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በሰማይ የሚኖረው የሚወደው ልጁ ፍጹም ሰው ሆኖ መወለድ እንዲችል ሕይወቱን ወደ አንዲት ድንግል ማህፀን በተአምር በማዛወር ነው። (ሉቃስ 1:30-35) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ በጠላቶቹ እጅ ከተገደለ በኋላ ይሖዋ ሌላ አስደናቂ ተአምር ፈጸመ። አምላክ ኢየሱስን ክብር የተጎናጸፈ መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ ከሞት አስነስቶታል።—1 ጴጥ. 3:18

3. አምላክ ለልጁ ሰማያዊ ሕይወት በመስጠት ወሮታ የከፈለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ፣ ልጁ ሰው ከመሆኑ በፊት ያልነበረውን ነገር ይኸውም በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት በመስጠት ወሮታ ከፍሎታል። (ዕብ. 7:15-17, 28) ኢየሱስ ከባድ መከራዎች ባጋጠሙት ጊዜ ፍጹም አቋሙን ስለጠበቀ ይሖዋ እንዲህ በማድረጉ ደስተኛ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት በፍቅር ተነሳስተው ሳይሆን በራስ ወዳድነት ስሜት ነው ሲል ሰይጣን ላቀረበው የሐሰት ክስ አባቱ ከሁሉ የተሻለና አጥጋቢ መልስ መስጠት እንዲችል አድርጓል።—ምሳሌ 27:11

4. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ለእኛ ሲል ምን አድርጓል? ይሖዋስ ምን ተሰማው? (ለ) ይሖዋና ኢየሱስ ያደረጉልህ ነገር ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

4 ኢየሱስ በሰማይ ሌሎች ነገሮችንም አከናውኗል። “የገዛ ራሱን ደም” ዋጋ ይዞ ‘ስለ እኛ በአምላክ ፊት ለመታየት’ ቀርቧል። በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን የኢየሱስን ውድ መሥዋዕት “ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት” አድርጎ በደስታ ተቀብሎታል። ከዚህም የተነሳ ‘በንጹሕ ሕሊና ሕያው ለሆነው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ’ እንችላለን። ይህ ዝግጅት “ሕዝቦች ሆይ፣ ያህን አወድሱ” የሚሉትን የ⁠መዝሙር 112 የመክፈቻ ቃላት እንድናስተጋባ የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት ነው!—ዕብ. 9:12-14, 24፤ 1 ዮሐ. 2:2

5. (ሀ) በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ይዘን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይገባናል? (ለ) መዝሙር 111 እና መዝሙር 112 የተቀናበሩት በምን መንገድ ነው?

5 በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ይዘን ለመቀጠል በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን መኖር ይገባናል። ይሖዋ ላሳየን ታላቅ ፍቅር ሳናመሰግነው አንድም ቀን ሊያልፍብን አይገባም። (ዮሐ. 3:16) በተጨማሪም የአምላክን ቃል ማጥናታችንንና ከመልእክቱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ለመኖር የሚቻለንን ሁሉ ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። መዝሙር 112 በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘው መኖር ለሚፈልጉ ሁሉ ግሩም ምክር ይዟል። ይህ መዝሙር ከመዝሙር 111 ጋር የተያያዘ ነው። ሁለቱም መዝሙሮች የሚጀምሩት “ሕዝቦች ሆይ፣ ያህን አወድሱ!” ወይም “ሃሌ ሉያ!” በሚለው መግለጫ ነው፤ መዝሙሮቹ 22 ስንኞች ያሏቸው ሲሆን እያንዳንዱ ስንኝ የሚጀምረው ከ22ቱ የዕብራይስጥ ፊደላት በአንዱ ነው። *

ለደስታ የሚሆን ምክንያት

6. በ⁠መዝሙር 112 ላይ የተገለጸው አምላክን የሚፈራ ሰው የተባረከው እንዴት ነው?

6 “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] የሚፈራ፣ በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ የተባረከ ነው። ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።” (መዝ. 112:1, 2) መዝሙራዊው በመጀመሪያ ‘ይሖዋን ስለሚፈራ’ አንድ ሰው የጠቀሰ ሲሆን ከዚያም በቁጥር 2 የመጨረሻ ስንኝ ላይ በብዙ ቁጥር በመናገር “ቅኖች” የሚለውን ቃል እንደተጠቀመ ልብ በል። ከዚህ ሁኔታ መረዳት እንደምንችለው መዝሙር 112 ብዙ ግለሰቦችን ስላቀፈ አንድ ቡድን የሚናገር ይመስላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ፣ መዝሙር 112:9⁠ን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች ጋር አያይዞ መጠቀሙ ይህን ሐሳብ ይደግፋል። (2 ቆሮንቶስ 9:8, 9ን አንብብ።) ይህ መዝሙር በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮች ደስተኞች መሆን እንደሚችሉ በሚገባ ይገልጻል!

7. የአምላክ አገልጋዮች ለእሱ ጤናማ ፍርሃት ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው? አምላክ ለሰጠን ትእዛዛት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል?

7 በ⁠መዝሙር 112:1 ላይ እንደተገለጸው እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ይሖዋን እንደሚፈሩ’ በአኗኗራቸው የሚያሳዩ ከሆነ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። እሱን ላለማሳዘን እንዲጠነቀቁ የሚያደርጋቸው ይህ ጤናማ ፍርሃት የሰይጣንን ዓለም መንፈስ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል። ደግሞም የአምላክን ቃል በማጥናትና ትእዛዛቱን በማክበር ‘እጅግ ደስ ይሰኛሉ።’ ከትእዛዛቱ መካከል በመላው ምድር የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኮ ይገኝበታል። በአንድ በኩል ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚጣጣሩ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ የፍርድ ቀን መድረሱን በተመለከተ ለክፉዎች ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ።—ሕዝ. 3:17, 18፤ ማቴ. 28:19, 20

8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ለአምላክ ያደሩ ሰዎች፣ ላሳዩት ቅንዓት ወሮታ ያገኙት እንዴት ነው? (ለ) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ወደፊት ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል?

8 በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች እነዚህን ትእዛዛት በማክበራቸው ቁጥራቸው ወደ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ሊደርስ ችሏል። የአምላክ ሕዝቦች “በምድር ላይ ኀያል” መሆናቸውን ማን ሊክድ ይችላል? (ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9, 14) አምላክ ወደፊት ዓላማውን ዳር በሚያደርስበት ጊዜ ምንኛ ‘ይባረካሉ!’ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ‘ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ምድር’ ለመመሥረት በቡድን ደረጃ “ታላቁን መከራ” በሕይወት ያልፋሉ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከአርማጌዶን በሕይወት የተረፉ ሰዎች ሌሎች ‘በረከቶችንም’ ያገኛሉ። ከሞት የሚነሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የመቀበል መብት ይኖራቸዋል። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! በመጨረሻም በአምላክ ትእዛዛት ‘እጅግ ደስ የሚሰኙ’ ሰዎች ወደ ፍጽምና የሚደርሱ ከመሆኑም ሌላ “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” በማግኘት ለዘላለም ይደሰታሉ።—2 ጴጥ. 3:13፤ ሮም 8:21

በሀብታችን በጥበብ መጠቀም

9, 10. እውነተኛ ክርስቲያኖች ያገኙትን መንፈሳዊ ብልጽግና የተጠቀሙበት እንዴት ነው? ጽድቃቸው ለዘላለም የሚኖረውስ እንዴት ነው?

9 “ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። ቸር፣ ርኅሩኅና ጻድቅ እንደ መሆኑ፣ ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል።” (መዝ. 112:3, 4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በቁሳዊ ሀብታቸው የታወቁ ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ በቁሳዊ መንገድ ባይሆንም እንኳ እውነተኛ ብልጽግና ያገኙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸው ሰዎችም አሉ። በኢየሱስ ዘመን እንደታየው በአምላክ ፊት በትሕትና ለመመላለስ የሚመርጡ አብዛኞቹ ሰዎች ድሆችና የተናቁ ሊሆኑ ይችላሉ። (ሉቃስ 4:18፤ 7:22፤ ዮሐ. 7:49) ይሁንና አንድ ሰው ያለው ቁሳዊ ሀብት ብዙም ሆነ ጥቂት በመንፈሳዊ ባለጸጋ ሊሆን ይችላል።—ማቴ. 6:20፤ 1 ጢሞ. 6:18, 19፤ ያዕቆብ 2:5ን አንብብ።

10 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ የእምነት አጋሮቻቸው ያገኙትን መንፈሳዊ ብልጽግና ለራሳቸው ብቻ ይዘው አይቀመጡም። ከዚህ ይልቅ ጨለማ በዋጠው የሰይጣን ዓለም ውስጥ ለሚገኙ ‘ቅን ሰዎች እንደ ብርሃን’ ያበራሉ። ይህን የሚያደርጉት ሌሎች ሰዎች ውድ መንፈሳዊ ሀብት ከሆነው ከጥበብና ከአምላክ እውቀት እንዲጠቀሙ በመርዳት ነው። ተቃዋሚዎች የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማስቆም ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። እንዲያውም የዚህ የጽድቅ ሥራ ፍሬ “ለዘላለም ይኖራል።” የአምላክ አገልጋዮች በጽድቅ ጎዳና በጽናት መመላለሳቸውን ከቀጠሉ ‘ለዘላለም የመኖር’ ዋስትና ይኖራቸዋል።

11, 12. የአምላክ አገልጋዮች ቁሳዊ ሀብታቸውን ለየትኞቹ ዓላማዎች ያውሉታል?

11 የአምላክ አገልጋዮች ባጠቃላይ ይኸውም በመንፈስ የተቀባው የባሪያው ክፍልም ሆነ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ቁሳዊ ነገሮችን በመስጠት ለጋስ መሆናቸውን አሳይተዋል። መዝሙር 112:9 “በልግስና ለድኾች ሰጠ” ይላል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ሌላው ቀርቶ በችግር ላይ ላሉ ሌሎች ሰዎችም እንኳ ቁሳዊ እርዳታ ያበረክታሉ። በተጨማሪም የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ቁሳዊ ሀብታቸውን ተጠቅመው ለሚደረገው የእርዳታ እንቅስቃሴ ድጋፍ ይሰጣሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው እንዲህ ማድረግ ደስታ ያስገኛል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35ንና 2 ቆሮንቶስ 9:7ን አንብብ።

12 ከዚህም ባሻገር ይህን መጽሔት በ172 ቋንቋዎች ለማተም የሚወጣውን ወጪ አስብ፤ መጽሔቱ በቋንቋቸው ከሚዘጋጅላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአንጻራዊ ሁኔታ ድሆች ናቸው። በተጨማሪም ይህ መጽሔት መስማት ለተሳናቸው በምልክት ቋንቋ፣ ማየት ለተሳናቸው ደግሞ በብሬል እንደሚዘጋጅ መዘንጋት አይኖርብንም።

ደግና ፍትሐዊ የሆነ

13. በደግነት በመስጠት ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተዉልን እነማን ናቸው? የእነሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

13 “ደግና ለሌሎች የሚያበድር ሰው ጥሩ ሰው ነው።” (መዝ. 112:5 NW) ለሌሎች እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት ሁልጊዜ በደግነት ተነሳስተው ነው ሊባል እንደማይችል ሳታስተውል አትቀርም። አንዳንዶች የሚሰጡት ለታይታ ብለው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ቅር እያላቸው ሊሆን ይችላል። የበታችነት ስሜት እንዲያድርብህ አሊያም ችግር ፈጣሪ ወይም ሸክም እንደሆንክ እንዲሰማህ ከሚያደርግ ሰው እርዳታ መቀበል አያስደስትም። በአንጻሩ ደግሞ የደግነት ባሕርይ ካለው ሰው እርዳታ መቀበል በጣም ያስደስታል። ይሖዋ በደግነትና በደስታ በመስጠት ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምሳሌያችን ነው። (1 ጢሞ. 1:11፤ ያዕ. 1:5, 17) ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ ያሳየውን የደግነት ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ማር. 1:40-42) በመሆኑም በአምላክ ፊት እንደ ጻድቅ ለመቆጠር በደስታና በደግነት መስጠት የሚኖርብን ሲሆን በተለይ በመስክ አገልግሎት ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ስንጥር እንዲህ ማድረግ ያስፈልገናል።

14. ‘የምንሠራቸውን ነገሮች በፍትሕ ማከናወን’ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

14 “ሥራውን በፍትሕ ያከናውናል።” (መዝ. 112:5 NW) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው የታማኙ መጋቢ ክፍል ከይሖዋ ፍትሕ ጋር በሚስማማ መንገድ የጌታን ንብረቶች በጥንቃቄ ይይዛል። (ሉቃስ 12:42-44ን አንብብ።) ይህ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የተፈጸሙ ከባድ ኃጢአቶችን መመልከት የሚኖርባቸው ሽማግሌዎች በተሰጣቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ላይ ተንጸባርቋል። በተጨማሪም የባሪያው ክፍል ሁሉም ጉባኤዎች፣ የሚስዮናውያን መኖሪያዎችና የቤቴል ቤቶች ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ ከሚሰጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ማየት እንደሚቻለው ማንኛውም ጉዳይ የሚያዘው ፍትሕ በሚንጸባረቅበት ሁኔታ ነው። ፍትሕ ማሳየት የሚጠበቅባቸው ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም፤ ሌሎች ክርስቲያኖችም ንግድ ነክ ጉዳዮችን ጨምሮ እርስ በርሳቸውም ሆነ አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ማንኛውም ግንኙነት ይህን ባሕርይ እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል።—ሚክያስ 6:8, 11ን አንብብ።

ጻድቃን የሚያገኟቸው በረከቶች

15, 16. (ሀ) በዓለም ላይ የሚሰሙት መጥፎ ዜናዎች በጻድቃን ላይ ምን ስሜት ያሳድራሉ? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች በየትኛው ሥራ ለመቀጠል ቆርጠዋል?

15 “ለዘላለም ከስፍራው አይናወጥምና፤ ጻድቅ ሰው ሲታወስ ይኖራል። ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤ ልቡ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] በመተማመን የጸና ነው። ልቡ የጸና ነው፤ አይፈራምም፤ በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል።” (መዝ. 112:6-8) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ስለ ጦርነት፣ ስለ ሽብርተኝነት፣ ከዚህ በፊት ስለማይታወቁና በአዲስ መልክ ስለሚያገረሹ በሽታዎች፣ ስለ ወንጀል፣ ስለ ድህነት እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትሉ ብክለቶች የሚናገሩ ክፉ ወሬዎችን ወይም መጥፎ ዜናዎችን መስማት የተለመደ ነው። አምላክ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥራቸው ሰዎች እነዚህ ዜናዎች ከሚያሳድሩባቸው መጥፎ ስሜቶች ማምለጥ ባይችሉም እንኳ በፍርሃት አይሽመደመዱም። አምላክ በቅርቡ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ስለሚያውቁና የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት ስለሚጠባበቁ ልባቸው “የጸና” ነው። አንድ ዓይነት አደጋ ቢከሰት እንኳ ይሖዋ እንደሚረዳቸው ስለሚተማመኑ ሁኔታውን መቋቋም የሚችሉበት የተሻለ አቅም አላቸው። ይሖዋ ጻድቅ አገልጋዮቹ ‘እንዲናወጡ’ አይፈቅድም፤ እንዲያውም እንዲጸኑ የሚያስችላቸውን እርዳታና ኃይል ይሰጣቸዋል።—ፊልጵ. 4:13

16 በተጨማሪም የአምላክ ጻድቅ አገልጋዮች ጥላቻንና ተቃዋሚዎች የሚያናፍሱባቸውን የሐሰት ወሬ ችለው መኖር ያለባቸው ቢሆንም ይህ ሁኔታ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ዝም ሊያሰኛቸው አልቻለም፤ ወደፊትም ዝም አያሰኛቸውም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ አገልጋዮች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩ እንዲሁም ለመልእክቱ በጎ ምላሽ የሰጡትን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ በጽናትና በትጋት ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። ፍጻሜው እየቀረበ በሄደ መጠን ጻድቃን የሚደርስባቸው ተቃውሞ እያየለ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። ሰይጣን ዲያብሎስ የማጎጉ ጎግ ሆኖ በዓለም ዙሪያ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት ይህ ጥላቻ የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ከዚያ በኋላ ጠላቶቻችን በአሳፋሪ ሁኔታ ድል በሚመቱበት ጊዜ ‘ውድቀታቸውን እናያለን።’ የይሖዋ ስም ሙሉ በሙሉ ከነቀፋ ነፃ ሆኖ ማየት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ሕዝ. 38:18, 22, 23

“በክብር ከፍ ከፍ ይላል”

17. ጻድቃን ‘በክብር ከፍ ከፍ የሚሉት’ እንዴት ነው?

17 ዲያብሎስና እሱ የሚገዛው ዓለም የሚሰነዝሩት ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ይሖዋን በኅብረት ማወደስ ምንኛ ያስደስት ይሆን! በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ይዘው የሚኖሩ ሁሉ ይህን ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ። ይሖዋ የጻድቃን ‘ቀንድ በክብር ከፍ ከፍ ይላል’ የሚል ተስፋ ስለሰጠ ውርደትና ሽንፈት ተከናንበው አንገታቸውን አይደፉም። (መዝ. 112:9) የይሖዋ ጻድቅ አገልጋዮች የእሱን ሉዓላዊነት የሚቃወሙ ሁሉ ለውድቀት ሲዳረጉ በሚያዩበት ጊዜ ከፍተኛ የድል አድራጊነት ስሜት ያድርባቸዋል።

18. በ⁠መዝሙር 112 መደምደሚያ ላይ የሚገኙት ሐሳቦች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው?

18 “ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤ ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤ የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች።” (መዝ. 112:10) በቅርቡ፣ የአምላክን ሕዝብ መቃወማቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ከሚያድርባቸው የምቀኝነትና የጥላቻ ስሜት የተነሳ ‘እየመነመኑ ይጠፋሉ።’ ሥራችን ቆሞ ለማየት ያላቸው ፍላጎት ከፊታችን ባለው “ታላቅ መከራ” ወቅት አብሯቸው ይጠፋል።—ማቴ. 24:21

19. ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

19 ይህ ታላቅ ድል በሚገኝበት ወቅት በሕይወት ከሚተርፉት ደስተኛ ሰዎች መካከል ትገኝ ይሆን? አሊያም ደግሞ የሰይጣን ዓለም ከማብቃቱ በፊት በበሽታ ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ በሞት ብታንቀላፋ ትንሣኤ ከሚያገኙት “ጻድቃን” ጋር ትነሳ ይሆን? (ሥራ 24:15) በ⁠መዝሙር 112 ላይ በተገለጸው ጻድቅ ሰው እንደተወከሉት ሰዎች አንተም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ማሳደርህንና የይሖዋን ባሕርያት መኮረጅህን ከቀጠልክ ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች አዎ የሚል መልስ መስጠት ትችላለህ። (ኤፌሶን 5:1, 2ን አንብብ።) ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎች ተረስተው እንዲቀሩ ሳይሆን ‘ሲታወሱ’ እንዲኖሩና የጽድቅ ሥራቸውም በቸልታ እንዳይታለፍ ያደርጋል። ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሖዋ ያስታውሳቸዋል እንዲሁም ይወዳቸዋል።—መዝ. 112:3, 6, 9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 እነዚህ ሁለት መዝሙሮች የተያያዙ መሆናቸውን ከተዋቀሩበት መንገድም ሆነ ከይዘታቸው ማየት ይቻላል። መዝሙር 111:3, 4⁠ን ከ⁠መዝሙር 112:3, 4 ጋር በማወዳደር ማየት እንደሚቻለው በ⁠መዝሙር 112 ላይ የተጠቀሰው አምላክን የሚፈራ ሰው በ⁠መዝሙር 111 ላይ ጎላ ተደርገው የተገለጹትን የአምላክ ባሕርያት አንጸባርቋል።

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

• ድምፃችንን ከፍ አድርገን “ሃሌ ሉያ” እንድንል የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

• እውነተኛ ክርስቲያኖች በጣም እንዲደሰቱ ያደረጋቸው በዘመናችን የታየው የትኛው እድገት ነው?

• ይሖዋ የሚወደው ምን ዓይነት የልግስና መንፈስ ያለውን ሰው ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ይዘን ለመቀጠል በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት ማሳደር ይገባናል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፈቃደኝነት የሚሰጡ መዋጮዎች ለመልሶ ማቋቋም ሥራና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማሰራጨት ድጋፍ ይሰጣሉ