በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚገዙት ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎች ይጠቀማሉ

የሚገዙት ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎች ይጠቀማሉ

የሚገዙት ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎች ይጠቀማሉ

ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ አምላክ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች ከሰው ልጆች መካከል በመምረጥ እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። በእነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚከሰተው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የአምላክ ቃል ሁኔታውን እንደ አዲስ ከመወለድ ጋር አመሳስሎታል። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች እንደ አዲስ የተወለዱበት ዓላማ በሰማይ ገዥዎች እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:12) በሰማይ እንዲገዙ ደግሞ ከሞት ተነስተው በሰማይ ሕይወት ያገኛሉ። (ሮም 6:3-5) በዚያም ከክርስቶስ ጋር ‘ነገሥታት ሆነው በምድር ላይ ይገዛሉ።’—ራእይ 5:10፤ 11:15

የአምላክ ቃል ዳግመኛ ከተወለዱት ክርስቲያኖች በተጨማሪ ሌሎችም ዘላለማዊ መዳን እንደሚያገኙ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ (በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት) ውስጥ አምላክ በሁለት ቡድን የተከፈሉ ሰዎችን የማዳን ዓላማ እንዳለው ተገልጿል። አንደኛው ቡድን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን በሰማይ ሆነው የሚገዙ ሰዎች ያቀፈ ሲሆን ሌላው ቡድን ደግሞ በምድር የሚኖሩ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተገዢዎች ያካትታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ዳግመኛ ለተወለዱት የእምነት ባልንጀሮቹ የጻፈውን ሐሳብ ልብ በል። ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት ነው፤ ሆኖም ለእኛ [አነስተኛ ሰዎችን ላቀፈው ቡድን] ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ [ብዙ ሰዎችን ላቀፈው ቡድን] ኃጢአት ጭምር ነው።”—1 ዮሐንስ 2:2

በተመሳሳይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ፍጥረት [ብዙ ሰዎችን ያቀፈው ቡድን] የአምላክን ልጆች [አነስተኛ ሰዎችን ያቀፈውን ቡድን] መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።” (ሮም 8:19-21) ሐዋርያው ዮሐንስና ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፉትን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? በዚህ መንገድ ልንረዳው ይገባናል፦ ዳግመኛ የተወለዱት ክርስቲያኖች በሰማይ ያለው አገዛዝ ክፍል ይሆናሉ። ለምን? በምድር ላይ ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ዘላለማዊ በረከቶችን ለማምጣት ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚከተለው ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው በዚህ ምክንያት ነው፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።”—ማቴዎስ 6:10

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም መዳን የሚያገኙት በሁለት ቡድን የተከፈሉ ሰዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የኢየሱስ ቅድመ አያት ለሆነው ለአብርሃም “የምድር ሕዝቦች ሁሉ [ብዙ ሰዎችን ያቀፈው ቡድን] በዘርህ [አነስተኛ ሰዎችን ባቀፈው ቡድን] ይባረካሉ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 22:18) አዎን፣ በአብርሃም “ዘር” አማካኝነት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ።

ይህ “ዘር” ማን ነው? ይህ “ዘር” ኢየሱስ ክርስቶስንና አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸውን ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ” ብሏል። (ገላትያ 3:16, 29) ታዲያ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዚህ “ዘር” አማካኝነት የሚያገኟቸው በረከቶች ምንድን ናቸው? በአምላክ ፊት ተቀባይነት የማግኘትና ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ይሰጣቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ተንብዮአል።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18፤ ራእይ 21:1-5

እውነት ነው፣ በሰማይ የመግዛት መብት ያገኙት ጥቂቶች ናቸው፤ ይህ አገዛዝ ከሚያስገኘው በረከት የሚጠቀሙት ይኸውም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወትና ሌሎች ብዙ በረከቶችን የሚያገኙት ግን ብዙዎች ናቸው። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ የአምላክ መንግሥት ከሚያስገኛቸው ዘላለማዊ በረከቶች ተቋዳሽ እንድትሆኑ እንመኛለን።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። አንተስ ከእነሱ መካከል ትሆን ይሆን?