በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

3 ስለ ኢየሱስ እውነቱን ተማር

3 ስለ ኢየሱስ እውነቱን ተማር

3 ስለ ኢየሱስ እውነቱን ተማር

“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

እንቅፋት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶች ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው አይደለም ብለው ሊያሳምኑህ ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ በሕይወት እንደኖረ ይቀበላሉ፤ ሆኖም ከረጅም ጊዜ በፊት የሞተ አንድ ተራ ሰው ነበረ ይላሉ።

እንቅፋቱን እንዴት ልትወጣው ትችላለህ? የደቀ መዝሙሩን የናትናኤልን ምሳሌ ተከተል። * ጓደኛው ፊልጶስ መሲሑን ማለትም “የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስ” እንዳገኘው ነገረው። ናትናኤል ግን ፊልጶስ የተናገረውን ዝም ብሎ አልተቀበለም። እንዲያውም “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ሲል ጠየቀው። ናትናኤል ጥርጣሬ ያደረበት ቢሆንም ፊልጶስ “መጥተህ እይ” በማለት ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል። (ዮሐንስ 1:43-51) አንተም ብትሆን ኢየሱስን በተመለከተ ያሉትን ማስረጃዎች ራስህ ብትመረምር ትጠቀማለህ። በዚህ ረገድ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ኢየሱስ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን የሚያሳዩትን ታሪካዊ ማስረጃዎች መርምር። ጆሴፈስና ታሲተስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ የታወቁ ታሪክ ጸሐፊዎች ሲሆኑ ሁለቱም ክርስቲያኖች አልነበሩም። እነዚህ ሰዎች በጻፏቸው ታሪኮች ውስጥ ኢየሱስን መጥቀሳቸው፣ ኢየሱስ በታሪክ ዘመን የነበረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣል። ታሲተስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ኔሮ በ64 ዓ.ም. በሮም ለተከሰተው ቃጠሎ ክርስቲያኖችን የወነጀለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ኔሮ አደጋውን በአቋማቸው ምክንያት በሮማውያን ይጠሉና በብዙኃኑ ዘንድ ክርስቲያን ተብለው ይጠሩ በነበሩት ሰዎች ላይ ያሳበበ ሲሆን ይህ ነው የማይባል ሥቃይም አድርሶባቸዋል። ክርስቲያን ለሚለው ስም መገኛ የሆነው ክራይስቱስ [ክርስቶስ] በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ከአስተዳዳሪዎቻችን አንዱ በነበረው በጳንጥዮስ ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ ቅጣት ተቀብሏል።”

በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስና ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተናገሩትን ሐሳብ በተመለከተ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ በ2002 እትሙ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በጥንት ዘመን የነበሩ የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ኢየሱስ በእርግጥ በታሪክ የነበረ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ እነዚህ ገለልተኛ የታሪክ ዘገባዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው ስለ መሆኑ ያለበቂ ምክንያት መከራከር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመንና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።” በ2002 ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በአምላክ መኖር ከማያምኑ አንዳንድ ምሁራን በስተቀር አብዛኞቹ ምሁራን የናዝሬቱን ኢየሱስን በታሪክ እንደነበረ ሰው አድርገው ተቀብለውታል።”

ኢየሱስ ትንሣኤ እንዳገኘ የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ተመልከት። ኢየሱስ በጠላቶቹ በተያዘበት ጊዜ የቅርብ ጓደኞቹና ተከታዮቹ ጥለውት ሸሹ፤ ወዳጁ የነበረው ጴጥሮስም ከመፍራቱ የተነሳ እንደማያውቀው ተናገረ። (ማቴዎስ 26:31, 55, 56, 69-75) ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ በከፍተኛ ትጋት መንቀሳቀስ ጀመሩ። ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስን ባስገደሉት ሰዎች ፊት ቀርበው በድፍረት ተናገሩ። ደቀ መዛሙርቱ በከፍተኛ ቅንዓት ተነሳስተው የኢየሱስን ትምህርቶች በመላው የሮም ግዛት አዳረሱ፤ አቋማቸውን ከማላላት ሞትን ይመርጡ ነበር።

በደቀ መዛሙርቱ አመለካከት ላይ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለው አንዱ ምክንያት ምን ነበር? ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳና ‘ለኬፋ [ለጴጥሮስ] ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ እንደታየ’ ገልጿል። ጳውሎስ አክሎ “በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች [እንደታየ]” ተናግሯል። ጳውሎስ ይህን በጻፈበት ወቅት አብዛኞቹ የዓይን ምሥክሮች በሕይወት ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 15:3-7) ለክርስቶስ ትንሣኤ የዓይን ምሥክር የሆኑት ሰዎች አንድ ወይም ሁለት ብቻ ቢሆኑ ኖሮ ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች ቃላቸውን ሊያጣጥሉት ይችሉ ነበር። (ሉቃስ 24:1-11) ይሁንና የዓይን ምሥክር የሆኑት ሰዎች ከአምስት መቶ በላይ መሆናቸው ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ይሆናል።

ምን በረከት ያስገኛል? በኢየሱስ የሚያምኑና ትምህርቶቹን የሚታዘዙ ሰዎች ኃጢአታቸው ይቅር የሚባልላቸው ከመሆኑም ሌላ ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። (ማርቆስ 2:5-12፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19፤ 1 ጴጥሮስ 3:16-22) ቢሞቱ እንኳ ኢየሱስ “በመጨረሻው ቀን” እንደሚያስነሳቸው ቃል ገብቷል።—ዮሐንስ 6:40

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * ከተባለው መጽሐፍ ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 4⁠ንና “ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” የሚለውን ምዕራፍ 5⁠ን ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ የተባሉት የወንጌል ጸሐፊዎች ናትናኤልን በርቶሎሜዎስ በሚል ስም የጠሩት ይመስላል።

^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናትናኤል እንዳደረገው አንተም ኢየሱስን በተመለከተ ያሉትን ማስረጃዎች መርምር