በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት መሠረት በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሾሉ እንጨቶች ቅጥር ተሠርቷል?

ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት ዙሪያሽን ቅጥር ቀጥረውና ከበውሽ ከሁሉም አቅጣጫ አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል።” (ሉቃስ 19:43) በ70 ዓ.ም. በቲቶ የሚመራው የሮም ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሾለ እንጨት ቅጥር በሠራበት ወቅት ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። ቲቶ ቅጥሩን የሠራው አይሁዳውያን እንዳይሸሹ ለመከልከል፣ ሕዝቡ እጃቸውን እንዲሰጡ ለማስገደድ እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ረሃብ ጠንቶባቸው እንዲማረኩ ለማድረግ ነበር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገረው ከሆነ በከተማዋ ዙሪያ ቅጥር እንዲሠራ ሲወሰን የሮም ሠራዊት የተለያዩ ክፍለ ጦሮች እንዲያጥሩ የተመደበላቸውን ቦታ ቀድመው ለመጨረስ ይሽቀዳደሙ ነበር። ወታደሮቹ በከተማዋ አካባቢ ያለውን ደን እስከ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መንጥረው ባመጧቸው ዛፎች በመጠቀም በኢየሩሳሌም ዙሪያ 7 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚያህል ቦታ የሚሸፍን ቅጥር ለመሥራት የፈጀባቸው 3 ቀን ብቻ ነበር። በዚህ ወቅት “ለአይሁዳውያን ከከተማዋ ማምለጥ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር” እንደነበር ጆሴፈስ ተናግሯል። በከተማዋ ውስጥ ረሃብ የተስፋፋ ከመሆኑም ሌላ መሣሪያ የታጠቁ የተለያዩ አንጃዎች እርስ በርስ ይዋጉ ጀመር፤ በመሆኑም ከአምስት ወራት ገደማ በኋላ ከተማዋ በወራሪዎቿ እጅ ወደቀች።

በእርግጥ ንጉሥ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ቦይ አስቆፍሮ ነበር?

በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መገባደጃ አካባቢ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በይሁዳና የዓለም ኃያል መንግሥት በነበረችው በአሦር መካከል ግጭት ተነስቶ ነበር። ሕዝቅያስ ኢየሩሳሌምን ከጥቃት ለመጠበቅና በጦርነት ወቅት ከተማዋ አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት እንዲኖራት ለማድረግ ሲል ብዙ ሥራ እንዳከናወነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ወደ ከተማዋ ውኃ ለማስገባት ሲል ያስቆፈረው 533 ሜትር ርዝመት ያለው ቦይ የሚጠቀስ ነው።—2 ነገሥት 20:20፤ 2 ዜና መዋዕል 32:1-7, 30

በ19ኛው መቶ ዘመን እንዲህ ዓይነት ቦይ የተገኘ ሲሆን የሕዝቅያስ ቦይ ወይም የሰሊሆም ቦይ ተብሎ ተጠራ። የቦዩ የመጨረሻ ክፍል ስለተቆፈረበት መንገድ የሚያብራራ ጽሑፍ በቦዩ ግድግዳ ላይ ተቀርጾ ተገኘ። አብዛኞቹ ምሑራን ይህ ጽሑፍ የተጻፈባቸውን ፊደላት ቅርጽ ሲመለከቱ ጽሑፉ በግድግዳው ላይ የተቀረጸው በሕዝቅያስ ዘመን ነው ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። ይሁንና ከአሥር ዓመት በፊት አንዳንዶች ይህ ቦይ የተቆፈረው ቀደም ሲል ከታሰበው ጊዜ 500 ዓመት በኋላ እንደሆነ ገለጹ። በመሆኑም ቦዩ የተቆፈረበትን ትክክለኛ ጊዜ ለማወቅ አንድ የእስራኤል ሳይንቲስቶች ቡድን ጥናት ማድረግ ጀመረ፤ ይህ ቡድን የደረሰበትን ውጤት በ2003 አሳትሟል። ምሑራኑ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰው ይሆን?

በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር አሞጽ ፍረምኪን እንዲህ ብለዋል፦ “ካርቦን-14 በሚባለው የጥንታዊ ነገሮችን ዕድሜ ለማወቅ የሚያስችል ዘዴ በመጠቀም በሰሊሆም ቦይ ግድግዳ ላይ ተለጥፈው የተገኙትን ነገሮች በመመርመርና በቦዩ ውስጥ ተጣብቀው ያገኘናቸውን ድንጋዮች ዩሬኒየም-ቶሪየም በተባለው ዘዴ በማጥናት ያገኘነው ውጤት ቦዩ የተቆፈረው በሕዝቅያስ ዘመን እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።” ኔቸር በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል፦ “በሦስት የተለያዩ ማስረጃዎች ማለትም ራዲዮሜትሪክ በተባለው የጥንታዊ ነገሮችን ዕድሜ ለማስላት የሚረዳ ዘዴ፣ በጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት እንዲሁም በታሪካዊ ዘገባዎች አማካኝነት ያገኘነው ውጤት [ቦዩ የተቆፈረው] በ700 ዓ.ዓ. ገደማ እንደሆነ ይጠቁማል። በዚህም የተነሳ የብረት ዘመን በሚባለው ጊዜ ከተሠሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱና እስካሁን ከታወቁ ግንባታዎች ሁሉ የተሠራበት ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የተረጋገጠው የሰሊሆም ቦይ ነው።”