በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች—እድገታችሁ በግልጽ እንዲታይ አድርጉ

ወጣቶች—እድገታችሁ በግልጽ እንዲታይ አድርጉ

ወጣቶች—እድገታችሁ በግልጽ እንዲታይ አድርጉ

“እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።” —1 ጢሞ. 4:15

1. አምላክ፣ ወጣቶች ምን እንዲያገኙ ይፈልጋል?

“አንተ ወጣት በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ያሰኝህ።” (መክ. 11:9) እንዲህ በማለት የጻፈው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰለሞን ነው። ሰለሞን እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ ያነሳሳው ይሖዋ አምላክ ነበር፤ እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋ በወጣትነታችሁ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም ጭምር ደስተኞች እንድትሆኑ ይፈልጋል። ይሁንና ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ዕድሜያቸው የሚሠሯቸው ስህተቶች የወደፊት ደስታቸውን ሊያበላሹባቸው ይችላሉ። ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ እንኳ ‘በወጣትነቱ የሠራው ኀጢአት’ ባስከተለበት መዘዝ አዝኗል። (ኢዮብ 13:26) ክርስቲያን የሆነ አንድ ወጣት በጉርምስና ዕድሜውና ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከባድ ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርበታል። በዚህ ወቅት የተሳሳተ ውሳኔ ማድረጉ ከባድ የስሜት ጠባሳ የሚያስከትልበት ከመሆኑም ሌላ በቀሪ ሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮች ሊፈጥር ይችላል።—መክ. 11:10

2. ወጣቶች ከባድ ስህተት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የሚረዳቸው የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው?

2 ወጣቶች ማስተዋል የታከለበት ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር ልብ በል፦ “በማስተዋል ችሎታችሁ እንደ ልጆች አትሁኑ፤ . . . በማስተዋል ችሎታችሁ የጎለመሳችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮ. 14:20) ወጣቶች፣ እንደ ጎልማሳ ሰው የማሰብና ነገሮችን የማመዛዘን ችሎታ እንዲያዳብሩ የተሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ከባድ ስህተት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል።

3. ጎልማሳ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

3 ወጣት ከሆንክ ጎልማሳ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግህ መገንዘብ ይኖርብሃል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ማንም ሰው ወጣትነትህን እንዲንቅ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን። . . . በሕዝብ ፊት ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። . . . እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።” (1 ጢሞ. 4:12-15) ክርስቲያን ወጣቶች እድገት ማድረግ እንዲሁም እድገታቸው በሌሎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ ይገባቸዋል።

እድገት ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

4. መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

4 እድገት ማድረግ ሲባል “መሻሻል፣ ጥሩ ለውጥ ማድረግ” ማለት ነው። ጢሞቴዎስ በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና እንዲሁም አገልግሎቱን በሚያከናውንበት መንገድ እድገት ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ እንዲጥር ጳውሎስ መክሮታል። ጢሞቴዎስ አኗኗሩ ለሌሎች አርዓያ እንዲሆን መጣር ነበረበት። በሌላ አባባል መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን ሊቀጥል ይገባ ነበር።

5, 6. (ሀ) የጢሞቴዎስ እድገት በግልጽ መታየት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች እድገት በማድረግ ረገድ የጢሞቴዎስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ ከላይ ያለውን ምክር የጻፈው ከ61 እስከ 64 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን በወቅቱ ጢሞቴዎስ ተሞክሮ ያካበተ የጉባኤ ሽማግሌ ነበር። ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ መጀመሩ አልነበረም። ጢሞቴዎስ በ49 ወይም በ50 ዓ.ም. በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ አሊያም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ የነበረ ይመስላል፤ በዚያ ወቅት መንፈሳዊ እድገቱን ያስተዋሉ ‘በልስጥራና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች በመልካም ምግባሩ መሥክረውለት ነበር።’ (ሥራ 16:1-5) በዚያን ጊዜ ጳውሎስ በሚስዮናዊነት አብሮት እንዲያገለግል ጢሞቴዎስን ወሰደው። ጳውሎስ፣ ይህ ወጣት በቀጣዮቹ ወራት የበለጠ እድገት ማድረጉን ካስተዋለ በኋላ በተሰሎንቄ ያሉትን ክርስቲያኖች እንዲያበረታታቸውና እንዲያጸናቸው ወደዚያች ከተማ ላከው። (1 ተሰሎንቄ 3:1-3, 6ን አንብብ።) ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው ጢሞቴዎስ፣ እድገቱ በሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የጀመረው ገና ወጣት እያለ ነበር።

6 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያላችሁ እናንት ወጣቶች፣ በክርስቲያናዊ አኗኗራችሁና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ችሎታችሁ የምታደርጉት እድገት በግልጽ እንዲታይ አስፈላጊ የሆኑትን መንፈሳዊ ባሕርያት ለማዳበር አሁኑኑ ጥረት ማድረግ ይገባችኋል። ኢየሱስ ከ12 ዓመቱ ጀምሮ “በጥበብ እያደገ” ይሄድ ነበር። (ሉቃስ 2:52) እንግዲያው ከሚከተሉት ሦስት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ እድገት ማድረጋችሁን በግልጽ ማሳየት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፦ (1) ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ፣ (2) ትዳር ለመመሥረት በምትዘጋጁበት ጊዜ እንዲሁም (3) “ጥሩ አገልጋይ” ለመሆን ጥረት ስታደርጉ።—1 ጢሞ. 4:6

“ጤናማ አእምሮ” በመያዝ ችግሮችን ተቋቋሙ

7. ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉ?

7 ካሮል የተባለች የ17 ዓመት ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ስሜቴ በጣም ከመደቆሱ እንዲሁም አእምሮዬና አካሌ እጅግ ከመዛሉ የተነሳ ጠዋት ላይ ባልነጋ ብዬ እመኝ ነበር።” * ካሮል የዚህን ያህል በጭንቀት የተዋጠችው ለምን ነበር? የአሥር ዓመት ልጅ ሳለች ወላጆቿ በፍቺ የተለያዩ ሲሆን እሷም ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አክብሮት ከሌላት እናቷ ጋር ለመኖር ተገደደች። አንተም እንደ ካሮል በጣም የሚያስጨንቁና ብዙም መሻሻል የማይችሉ ሁኔታዎች አጋጥመውህ ይሆናል።

8. ጢሞቴዎስ የትኞቹን ችግሮች መቋቋም ነበረበት?

8 ጢሞቴዎስም መንፈሳዊ እድገት ያደርግ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ችግሮችን መቋቋም አስፈልጎት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ‘በተደጋጋሚ የሚነሳ [የሆድ] ሕመም’ ነበረበት። (1 ጢሞ. 5:23) እንዲሁም ጳውሎስ፣ የሐዋርያነት ሥልጣኑን የማይቀበሉ ሰዎች የፈጠሯቸውን አንዳንድ ችግሮች እንዲያስተካክል ጢሞቴዎስን ወደ ቆሮንቶስ በላከው ጊዜ በመካከላቸው “ያለ ፍርሃት” ማገልገል እንዲችል ጢሞቴዎስን እንዲተባበሩት የጉባኤውን አባላት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 4:17፤ 16:10, 11) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ጢሞቴዎስ አይናፋር የነበረ ይመስላል።

9. ጤናማ አእምሮ ምንድን ነው? ከፍርሃት መንፈስ የሚለየውስ እንዴት ነው?

9 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ለመርዳት ሲል እንዲህ ብሎታል፦ “አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም።” (2 ጢሞ. 1:7) “ጤናማ አእምሮ” ሲባል ማስተዋል በታከለበት መንገድ ማሰብና ነገሮችን ማመዛዘን ማለት ነው። ሁኔታዎች እንዳሰብከው ባይሆኑም እንኳ ያጋጠሙህን ችግሮች ተቋቁመህ መኖርንም ይጨምራል። ክርስቲያናዊ ጉልምስናን ያላዳበሩ አንዳንድ ወጣቶች አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የፍርሃት መንፈስ ሲያንጸባርቁ ይታያሉ፤ እነዚህ ወጣቶች ጊዜያቸውን በእንቅልፍ በማሳለፍ ወይም ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ዕፆች በመውሰድና የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ በመጠጣት፣ አዘውትረው ጭፈራ ቤት በመሄድ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸም ካጋጠማቸው ችግር ለመሸሽ ይጥራሉ። እኛ ክርስቲያኖች ግን “አምላካዊ ያልሆነ ምግባርንና ዓለማዊ ምኞቶችን ክደን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” ተመክረናል።—ቲቶ 2:12

10, 11. ጤናማ አስተሳሰብ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ “ወጣት ወንዶች ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” ያበረታታል። (ቲቶ 2:6) አንተም ችግሮች ሲያጋጥሙህ በጸሎት ወደ አምላክ በመቅረብና አምላክ በሚሰጥህ ብርታት በመተማመን ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 4:7ን አንብብ።) በዚህ መንገድ “አምላክ በሚሰጠው ኃይል” ሙሉ በሙሉ የመተማመን ስሜት ታዳብራለህ።—1 ጴጥ. 4:11

11 ከላይ የጠቀስናት ካሮል፣ ጤናማ አስተሳሰብ ማዳበሯና ወደ አምላክ መጸለይዋ ያጋጠማትን ችግር እንድትቋቋም ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ የምትከተለውን ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር በመቃወም አቋሜን ማሳወቅ በሕይወቴ ውስጥ ካደረግኳቸው ከባድ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ረገድ ጸሎት በጣም ረድቶኛል። ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሆነ ስለማውቅ ከእንግዲህ የሚያስፈራኝ ነገር የለም።” የሚያጋጥሙህ ችግሮች የተሻልክ ሰው እንደሚያደርጉህና እንደሚያጠናክሩህ አትዘንጋ። (መዝ. 105:17-19፤ ሰቆ. 3:27) ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምህ አምላክ ፈጽሞ አይጥልህም። ይሖዋ ‘እንደሚረዳህ’ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳ. 41:10

የተሳካ ትዳር ለመመሥረት መዘጋጀት

12. ትዳር ለመመሥረት የሚያስብ ክርስቲያን በምሳሌ 20:25 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው?

12 አንዳንድ ወጣቶች ደስታ ሲያጡ፣ በብቸኝነት ሲዋጡ፣ ሕይወት ሲሰለቻቸው እንዲሁም ቤት ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ለዚህ ሁሉ መፍትሔው ጋብቻ እንደሆነ በማሰብ ቸኩለው ትዳር ይመሠርታሉ። ይሁንና የጋብቻ ቃል ኪዳን በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ለአምላክ ስእለት ሲሳሉ ምን እንደሚጠበቅባቸው ሳያስተውሉ በችኮላ ይሳሉ ነበር። (ምሳሌ 20:25ን አንብብ።) አንዳንድ ጊዜ ወጣቶችም፣ ካገቡ በኋላ ምን እንደሚጠበቅባቸው በቁም ነገር ሳያስቡበት ወደ ትዳር ዓለም ይገባሉ። በኋላ ላይ ግን ትዳር ካሰቡት በላይ ብዙ ኃላፊነት እንደሚያስከትል ይገነዘባሉ።

13. ለጋብቻ ለመጠናናት የሚያስቡ ሁሉ የትኞቹን ጥያቄዎች ሊያስቡባቸው ይገባል? በዚህ ረገድ ምን ጠቃሚ ምክር ማግኘት ይችላሉ?

13 እንግዲያው መጠናናት ከመጀመራችሁ በፊት እንዲህ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ማግባት የምፈልገው ለምንድን ነው? ከትዳር ለማግኘት የምጠብቀው ምንድን ነው? ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል? ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ዝግጁ ነኝ?’ በዚህ ረገድ ማስተዋል በታከለበት መንገድ ሁኔታችሁን መመርመር እንድትችሉ ለመርዳት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር የሚያብራሩ ጽሑፎች አውጥቷል። * (ማቴ. 24:45-47) በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ይሖዋ እንደሰጣችሁ ምክር አድርጋችሁ በመመልከት በጥሞና መርምሩት እንዲሁም በሕይወታችሁ ተግባራዊ አድርጉት። “ማስተዋል እንደሌላቸው፣ እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።” (መዝ. 32:8, 9) ትዳር መመሥረት የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች በመረዳት ረገድ የጎለመሳችሁ መሆን ያስፈልጋችኋል። ለጋብቻ ለመጠናናት ዝግጁ እንደሆናችሁ ከተሰማችሁ “በንጽሕና አርዓያ” መሆን እንደሚኖርባችሁ ምንጊዜም አትዘንጉ።—1 ጢሞ. 4:12

14. መንፈሳዊ ጉልምስና ትዳር ከመሠረትክ በኋላም የሚረዳህ እንዴት ነው?

14 መንፈሳዊ ጉልምስና ካገባችሁ በኋላም ትዳራችሁ የሰመረ እንዲሆን ይረዳችኋል። የጎለመሰ ክርስቲያን “ክርስቶስ ወዳለበት የሙላት ደረጃ [ለመድረስ]” ይጥራል። (ኤፌ. 4:11-14) የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት ለማዳበር ተግቶ ይሠራል። ምሳሌያችን የሆነው “ክርስቶስ . . . ራሱን አላስደሰተም።” (ሮም 15:3) የትዳር ጓደኛሞችም የራሳቸውን ሳይሆን የሌላውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ከሆነ ትዳራቸው ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ ይሆናል። (1 ቆሮ. 10:24) እንደዚህ ባለው ትዳር ውስጥ ባል ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያል፤ ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ እንደተገዛ ሁሉ ሚስትም ለባሏ ትገዛለች።—1 ቆሮ. 11:3፤ ኤፌ. 5:25

“አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም”

15, 16. በአገልግሎት ረገድ እድገትህ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስ በተሰጠው አስፈላጊ ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲህ ብሏል፦ “በአምላክ ፊት እንዲሁም . . . በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አጥብቄ አሳስብሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፣ . . . በጥድፊያ ስሜት አገልግል።” አክሎም “የወንጌላዊን ሥራ አከናውን እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም” ብሎታል። (2 ጢሞ. 4:1, 2, 5) ጢሞቴዎስ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ‘የእምነትን ቃሎች በሚገባ መመገብ’ ያስፈልገው ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 4:6ን አንብብ።

16 አንተስ ‘የእምነትን ቃሎች በሚገባ መመገብ’ የምትችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በሕዝብ ፊት ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። . . . በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።” (1 ጢሞ. 4:13, 15) እድገት ለማድረግ ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት ማድረግ ይኖርብሃል። “ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን” የሚለው ሐሳብ በአንድ ነገር ሙሉ በሙሉ መመሰጥን ያመለክታል። የጥናት ልማድህ ምን ይመስላል? “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” ሙሉ ትኩረት ሰጥተህ ትመረምራለህ? (1 ቆሮ. 2:10) ወይስ ስለ እነዚህ ነገሮች ለማወቅ ብዙም ጥረት አታደርግም? በምታጠናው ነገር ላይ ማሰላሰልህ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንድትነሳሳ ያደርግሃል።—ምሳሌ 2:1-5ን አንብብ።

17, 18. (ሀ) የትኞቹን ችሎታዎች ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያስፈልግሃል? (ለ) የጢሞቴዎስ ዓይነት አመለካከት ማዳበርህ በአገልግሎትህ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

17 ሚሼል የተባለች አንዲት ወጣት አቅኚ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን እንድችል ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም እንዲኖረኝ አደርጋለሁ፤ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ። ይህም መንፈሳዊ እድገት ማድረጌን እንድቀጥል ረድቶኛል።” በእርግጥም አቅኚ ሆኖ ማገልገል በአገልግሎት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጠቀም ችሎታህን እንድታሻሽል እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ ይረዳሃል። ጥሩ አንባቢ ለመሆን ጥረት አድርግ፤ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ይኑርህ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ሲሰጥህ ከተመደበልህ ጽሑፍ ሳትወጣ ሌሎችን ሊያስተምር በሚችል መንገድ ክፍልህን በመዘጋጀት በመንፈሳዊ የጎለመስህ ወጣት መሆንህ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ ትችላለህ።

18 ‘የወንጌላዊን ሥራ ማከናወን’ ሲባል በአገልግሎትህ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲሁም ሰዎች መዳን እንዲያገኙ መርዳት ማለት ነው። ይህንንም ለማድረግ ‘የማስተማር ጥበብን’ ማዳበር ያስፈልግሃል። (2 ጢሞ. 4:2) ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር በመሥራት እንደተማረው ሁሉ አንተም ልምድ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር በአገልግሎት በመካፈል እነሱ የሚጠቀሙበትን የማስተማር ዘዴ መኮረጅ ትችላለህ። (1 ቆሮ. 4:17) ጳውሎስ በመንፈሳዊ ስለረዳቸው ሰዎች በጻፈበት ወቅት የአምላክን ምሥራች ብቻ ሳይሆን ‘የገዛ ነፍሱን’ ጭምር እንደሰጣቸው ወይም ሕይወቱን እነሱን ለመርዳት እንዳዋለ ተናግሯል፤ ይህንን ያደረገው በጣም ይወዳቸው ስለነበር ነው። (1 ተሰ. 2:8) አንተም በአገልግሎትህ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ከፈለግህ ለሌሎች ከልቡ ይጨነቅ እንዲሁም ‘ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ እንደ ባሪያ ያገለግል’ እንደነበረው እንደ ጢሞቴዎስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይኖርብሃል። (ፊልጵስዩስ 2:19-23ን አንብብ።) በአገልግሎትህ እንዲህ ያለውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ታሳያለህ?

እድገት ማድረግ እውነተኛ እርካታ ያስገኛል

19, 20. መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ደስታ ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?

19 መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል በትዕግሥት ጥረት የምታደርግ ከሆነ ከጊዜ በኋላ በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘ብዙዎችን ባለጸጋ ማድረግ’ ትችላለህ፤ እነሱም ‘ደስታህ ወይም የሐሴትህ አክሊል’ ይሆናሉ። (2 ቆሮ. 6:10፤ 1 ተሰ. 2:19) ፍሬድ የተባለ አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንዲህ ብሏል፦ “ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጊዜዬን የማሳልፈው ሌሎችን በመርዳት ነው። ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል የሚለው አባባል እውነት መሆኑን ተመልክቻለሁ።”

20 ዳፍኒ የተባለች አንዲት ወጣት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅሁ መጠን ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ችያለሁ። አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ይሖዋን ስታስደስተው እውነተኛ ደስታና ከፍተኛ እርካታ ታገኛለህ!” መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን ሰዎች የሚያስተውሉት ሁልጊዜ ባይሆንም ይሖዋ ግን የምታደርገውን እድገት ሁልጊዜ ያየዋል እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብ. 4:13) እናንት ወጣት ክርስቲያኖች፣ በሰማይ ለሚኖረው አባታችሁ ክብርና ውዳሴ ማምጣት እንደምትችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። እድገታችሁ በሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ ጥረት በማድረግ ልቡን ደስ ማሰኘታችሁን ቀጥሉ።—ምሳሌ 27:11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.13 “ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?” ግንቦት 2007 ንቁ!“የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚረዳ መለኮታዊ መመሪያ” ግንቦት 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ፤ “በአሥራዎቹ ዕድሜ እያሉ ትዳር መመሥረት የጥበብ እርምጃ ነው?” መስከረም 22, 1983 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እንዲሁም “ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?” ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 (እንግሊዝኛ)።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

• በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ እድገትህ በሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ችግሮች ሲያጋጥሙህ፣

ትዳር ለመመሥረት በምትዘጋጅበት ጊዜ፣

በአገልግሎት

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎት ያጋጠሟችሁን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳችኋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣት አስፋፊዎች ውጤታማ የሆነ የማስተማር ችሎታ ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?