በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለዝምታ ጊዜ አለው”

“ለዝምታ ጊዜ አለው”

“ለዝምታ ጊዜ አለው”

“መናገር ብር ነው፤ ዝምታ ወርቅ ነው” የሚል አንድ የቆየ የምሥራቃውያን አባባል አለ። ብሪወርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ፍሬዝ ኤንድ ፌብል የተሰኘው መጽሐፍ “ቃል አንድ ሰቅል ቢመዝን፣ ዝምታ ደግሞ ሁለት ሰቅል ይመዝናል” የሚል ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የዕብራይስጥ አባባል እንዳለ ገልጿል። የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰለሞንም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ . . . ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።”—መክ. 3:1, 7

ታዲያ ከመናገር ይልቅ ዝም ማለት ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው? “ጸጥ” እና “ዝም” ማለት የሚሉት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ቃላት በተጠቀሱባቸው ቦታዎች ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች ስንመለከት፣ ዝም ማለት ተገቢ የሚሆኑባቸው ቢያንስ ሦስት ዘርፎች እንዳሉ እንገነዘባለን። ዝም ማለት የአክብሮት መግለጫና የአስተዋይነት ምልክት የሆነው እንዲሁም ጸጥታ ለማሰላሰል የሚረዳው እንዴት እንደሆነ አንድ በአንድ እንመልከት።

ዝምታ የአክብሮት መግለጫ ነው

ዝምታ፣ አክብሮት ማሳየት የሚቻልበት አንዱ መንገድ ነው። ነቢዩ ዕንባቆም “እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፣ ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል” ብሏል። (ዕን. 2:20) በተጨማሪም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ‘የይሖዋን ማዳን፣ ዝም ብለው ተስፋ እንዲያደርጉ’ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ሰቆ. 3:26) መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ዘምሯል፦ “በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት . . . ሰው ልብህ አይሸበር።”—መዝ. 37:7

ታዲያ አንድም ቃል ሳንናገር ይሖዋን ማወደስ እንችላለን? አንዳንድ ጊዜ፣ በፍጥረት ላይ የሚታየውን ውበት ስንመለከት በአድናቆት ከመሞላታችን የተነሳ ስሜታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል። በዚህ መልኩ ውብ ስለሆነው ተፈጥሮ ማሰባችን ፈጣሪን በልባችን የምናወድስበት አንድ መንገድ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት አንዱን መዝሙሩን የጀመረው “አምላክ ሆይ፣ በጽዮን በአንተ ፊት ውዳሴና ዝምታ አለ፤ የተሳልነውን ለአንተ እንሰጣለን” በሚሉት ቃላት ነበር።—መዝ. 65:1 NW

ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት እንዳለብን ሁሉ እሱ ለሚናገራቸው ነገሮችም አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ በሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ ለእስራኤል ብሔር ንግግር ባቀረበበት ወቅት እሱና ካህናቱ እንዲህ ብለው ነበር፦ “ጸጥ ብለህ አድምጥ! . . . አምላክህን እግዚአብሔርን ታዘዝ።” እስራኤላውያን የአምላክ ሕግ በሚነበብበት ቦታ ሲሰበሰቡ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ በትኩረት እንዲያዳምጡ ይጠበቅባቸው ነበር። ሙሴ “ይማሩ ዘንድ፣ . . . ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችን . . . ሰብስብ” በማለት ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።—ዘዳ. 27:9, 10፤ 31:11, 12

በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችም የአውራጃ ስብሰባዎችን ጨምሮ በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች በአክብሮት ማዳመጣቸው ተገቢ ነው። ከመድረክ ጠቃሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ፣ ሳያስፈልግ ከሌሎች ጋር ማውራት ለአምላክ ቃልና ለድርጅቱ አክብሮት እንደጎደለን የሚያሳይ አይደለም? ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ ዝም ብለን ማዳመጥ ይኖርብናል።

ከአንድ ሰው ጋር በምንነጋገርበት ጊዜም ጥሩ አዳማጭ መሆናችን ለግለሰቡ አክብሮት እንዳለን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ በሐሰት የወነጀሉትን ወዳጆቹን “አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ” ብሏቸው ነበር። ኢዮብ እነሱ ሲናገሩ ዝም ብሎ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነበር። እሱ መናገር ሲፈልግ ደግሞ “ዝም በሉ፤ እኔ ልናገር” ብሏቸዋል።—ኢዮብ 6:24፤ 13:13

ዝምታ የአስተዋይነት ምልክት ነው

መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን የሚገታ . . . ጠቢብ ነው” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም “አስተዋይ . . . አንደበቱን ይገዛል” ይላል። (ምሳሌ 10:19፤ 11:12) ኢየሱስ ዝም በማለት ጠቢብና አስተዋይ መሆኑን ግሩም በሆነ መንገድ እንዴት እንዳሳየ ተመልከት። በአንድ ወቅት፣ ኢየሱስ በጣም ይጠሉት ለነበሩት ሰዎች መልስ መስጠት ምንም ፋይዳ እንደሌለው ስላስተዋለ ‘ዝም ማለትን’ መርጧል። (ማቴ. 26:63) በኋላም ተከሶ ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ጊዜ “ምንም መልስ አልሰጠም።” እሱ ከሚናገር ይልቅ ተግባሩ ራሱ እንዲናገርለት በመምረጥ አስተዋይ መሆኑን አሳይቷል።—ማቴ. 27:11-14

እኛም በተለይ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመን አንደበታችንን መግታታችን አስተዋይነት ነው። የምሳሌ መጽሐፍ “ታጋሽ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤ ግልፍተኛ ሰው ግን ቂልነትን ይገልጣል” ይላል። (ምሳሌ 14:29) ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን በችኮላ መልስ የምንሰጥ ከሆነ ‘ምነው ምላሴን በቆረጠው’ እንድንል የሚያደርገንን ያልታሰበበት ነገር ልንናገር እንችላለን። በዚህ ወቅት የተናገርነው ነገር ቂልነት የተንጸባረቀበትና በኋላ ላይ አእምሯችንን የሚረብሸን ሊሆን ይችላል።

ክፉ ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ አንደበታችንን መጠበቃችን አስተዋይነት ነው። በአገልግሎት ላይ ፌዘኛ ሰዎች ሲያጋጥሙን፣ የተሻለው መልስ ዝም ማለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አብረውን የሚማሩ ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦቻችን መጥፎ ቀልዶችንና የብልግና ቃላትን ሲናገሩ፣ በቀልዳቸው ወይም በንግግራቸው እንዳልተደሰትን ለማሳየት አንዳንድ ጊዜ ዝም ማለታችን አስተዋይነት ነው። (ኤፌ. 5:3) መዝሙራዊው “ክፉዎችም በእኔ ዘንድ እስካሉ ድረስ፣ ልጓም በአፌ አስገባለሁ” በማለት ጽፏል።—መዝ. 39:1

“አስተዋይ” ሰው የሌሎችን ሚስጥር አያወጣም። (ምሳሌ 11:12) አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን ጉዳዮች ለሌሎች ላለመንገር ይጠነቀቃል። በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሚስጥር በመጠበቅ ረገድ ጠንቃቆች መሆን አለባቸው፤ ይህም የጉባኤው አባላት በእነሱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዳያጡ ያደርጋቸዋል።

ዝምታ ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ሲድኒ ስሚዝ የተባለ በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረ እንግሊዛዊ ጸሐፊ፣ በእሱ ዘመን ስለኖረ አንድ ሰው ሲጽፍ “ከሰው ጋር ሲጫወት አልፎ አልፎ ዝም ብሎ የሚያዳምጥ መሆኑ ከእሱ ጋር መጨዋወት አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል” ብሏል። እርግጥ ነው፣ ሁለት ጓደኛሞች በየዕለቱ በሚያደርጉት ውይይት አንዱ ብቻ ተናጋሪ መሆን የለበትም፤ ሁለቱም ሐሳባቸውን መግለጽ አለባቸው። ይሁንና አንድ ሰው ከሌሎች ጋር በመጨዋወት ረገድ የተዋጣለት እንዲሆን ጥሩ አዳማጭ መሆን አለበት።

ሰለሞን “ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው” ሲል አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 10:19) በመሆኑም አንድ ሰው የሚናገረው ነገር ባነሰ መጠን ማሰተዋል የጎደለው ነገር የመናገሩ አጋጣሚም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል። እንዲያውም “አላዋቂ እንኳ ዝም ቢል ጠቢብ፣ አንደበቱንም ቢገዛ አስተዋይ ይመስላል።” (ምሳሌ 17:28) እንግዲያው እኛም ‘የከንፈሮቻችንን መዝጊያ እንዲጠብቅልን’ ይሖዋን በጸሎት እንጠይቀው።—መዝ. 141:3

ለማሰላሰል ይረዳል

መጽሐፍ ቅዱስ በጽድቅ ጎዳና ስለሚጓዝ ሰው ሲናገር ‘[የአምላክን] ሕግ በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል’ ይላል። (መዝ. 1:2) አንድ ሰው በዚህ መንገድ እንዲያሰላስል በጣም ምቹ የሚሆንለት እንዴት ያለ ሁኔታ ነው?

የአብርሃም ልጅ የሆነው ይስሐቅ ‘በመሸ ጊዜ ለማሰላሰል ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር።’ (ዘፍ. 24:63 የ1954 ትርጉም) ይስሐቅ ጸጥታ የሚሰፍንበትን ጊዜና ቦታ መርጦ ነበር። ንጉሥ ዳዊትም ያሰላስል የነበረው ሰው ሁሉ በሚተኛበትና ጸጥ ረጭ ባለው ሌሊት ነበር። (መዝ. 63:6) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ እንኳ ብቻውን የሚሆንበትና የሚያሰላስልበት ጊዜ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ ግርግር ከሚበዛበት አካባቢ ርቆ ወደ ተራራ፣ ወደ ምድረ በዳ ወይም ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ይሄድ ነበር።—ማቴ. 14:23፤ ሉቃስ 4:42፤ 5:16

ጸጥታ የሰፈነበት አካባቢ መንፈስን የሚያድስ መሆኑ አይካድም። እንዲህ ያለው አካባቢ ራሳችንን ለመመርመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል፤ ራሳችንን መመርመራችን ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ማሻሻያ ለማድረግ ከሚያስፈልጉን ወሳኝ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ጸጥታ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል። ጸጥታ በሚሰፍንበት ጊዜ ማሰላሰል፣ ልካችንን የማወቅና የትሕትና ባሕርይ በውስጣችን እንዲተከል የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል።

ዝምታ ጥሩ ነገር ቢሆንም “ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክ. 3:7) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች “በመላው ምድር” ላይ በመስበኩ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ነው። (ማቴ. 24:14) ለምሥራቹ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱም የአምላክ አገልጋዮች የሚያሰሙት የደስታ ጩኸት ከምንጊዜውም ይበልጥ እያስተጋባ ነው። (ሚክ. 2:12 የ1954 ትርጉም) እንግዲያው የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት ከሚያውጁትና ስለ አምላክ ድንቅ ሥራዎች ከሚናገሩት ሰዎች መካከል ለመቆጠር የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። በዚህ ጠቃሚ ሥራ እየተካፈልን አኗኗራችን ‘ዝምታ ወርቅ’ የሚሆንበት ጊዜ መኖሩን እንደምንገነዘብ የሚያሳይ ይሁን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ማዳመጥና መማር ይኖርብናል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎታችን ላይ ሰዎች ሲሰድቡን፣ የተሻለው መልስ ዝም ማለት ሊሆን ይችላል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸጥታ የሰፈነበት ሁኔታ ለማሰላሰል ይረዳል