በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ምክር ማግኘት የምትችልባቸው በርካታ ምንጮች አሉ። ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው መወጣት የሚችሉባቸውን ሐሳቦች የሚያቀርቡ በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት የተሠማሩበት የሥራ መስክ፣ በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። እንደ ላቲን አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ አሜሪካና ጃፓን ባሉ ተራርቀው በሚገኙ ቦታዎች ራስ አገዝ መጻሕፍት በገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። ሰዎችን ለመርዳት ታስበው የሚዘጋጁ ቪዲዮዎች፣ ሴሚናሮችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችም ተወዳጅነት እያተረፉ ነው። እነዚህ ዝግጅቶች ተወዳጅ እንዲሆኑ ያደረጋቸው፣ ሰዎች የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን ወይም የጋብቻ አማካሪዎችን አሊያም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ሳያማክሩ ችግሮቻቸውን ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የሚገልጹ መሆናቸው ነው። ታዲያ ምክር የሚሰጡት በየትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ነው?

ስኬታማ ስለ መሆን፣ የትዳር ጓደኛ ስለማግኘት እንዲሁም ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚናገሩት ርዕሰ ጉዳዮች በሰዎች ዘንድ በጣም ተፈላጊ ከሆኑት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የመንፈስ ጭንቀት፣ ሐዘንና የትዳር መፍረስ የሚያስከትሉትን ሥቃይ ከመቋቋም ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ሐሳቦችም በስፋት ይገኛሉ። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ከመጠን በላይ የመብላትና የመጠጣት ልማድን እንዲሁም የሲጃራ ሱስን ለማሸነፍ የሚረዳ ምክር ማግኘት ይፈልጋሉ። የሚያገኙት ምክር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው? አንዳንድ ጊዜ ሊሆን ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን ምክሩን በተግባር ማዋል ያስቸግራል። በመሆኑም “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማሳሰቢያ መከተል የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 14:15

ራስ አገዝ መጻሕፍት፣ የፎቶግራፍ ጥበብንና የሒሳብ አያያዝን እንዲሁም ቋንቋን ከሚያስተምሩ ጽሑፎች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። እንዲህ ያሉ ሙያዎችን የሚያስተምሩ ጽሑፎች፣ ሰዎች ብዙ ወጪ ሳያወጡ አንድን ሙያ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲማሩ ያስችሏቸዋል። ከሥራ፣ ከትዳር፣ ልጅን ከማሳደግ ወይም ከአእምሮ ጤንነት ጋር በተያያዘ የተዘጋጁ ራስ አገዝ መጻሕፍት ግን ከላይ ከተጠቀሱት ጽሑፎች የተለዩ ናቸው። ራስ አገዝ መጻሕፍት አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የተወሰነ የአኗኗር ዘይቤን ወይም ፍልስፍናን እንዲከተሉ ያበረታታሉ። ስለዚህ እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቃችን የጥበብ አካሄድ ነው፦ ‘ምክሩን የሰጠው ማን ነው? ምክሩን ለመስጠት የተጠቀመበትን መረጃ ያገኘው ከየት ነው?’

ራስ አገዝ መጻሕፍትን የሚያዘጋጁ ባለሙያዎች አብዛኛውን ጊዜ ሐሳብ የሚሰጡት በጥንቃቄ በተሰባሰበ መረጃ ላይ ተመርኩዘው አይደለም። አንዳንዶቹ ባለሙያዎች፣ ሰዎች መስማት የሚፈልጉትን ነገር በመናገር ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ስለሚያውቁ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ምክር ሊሰጡ ይችላሉ። የሚያስገርመው እንዲህ ያለ ምክር የሚሰጥበት የሥራ መስክ በአንድ አገር ውስጥ ብቻ እንኳ በዓመት ከስምንት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል!

ራስ አገዝ ጽሑፎች የሚሰጡት መመሪያ ተግባራዊ መሆን ይችላል?

ራስ አገዝ ጽሑፎችን የምትመለከተው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ፈልገህ ነው። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የምታገኘው ምክር በተግባር ለማዋል የሚያስቸግር ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ጽሑፎች እንደሚከተለው ያሉ ምክሮችን ይሰጡሃል፦ ‘አዎንታዊ አመለካከት ካዳበርክ ችግሮችህን መፍታት ትችላለህ። የምትፈልገው ነገር ገንዘብም ይሁን ጤንነት አሊያም የተሳካ ወዳጅነት አዎንታዊ አመለካከት ከያዝክ ልታገኘው ትችላለህ።’ እንዲህ ያለው ምክር ተግባራዊ መሆን የሚችል ነው? በገሃዱ ዓለም የሚያጋጥሙህን እውነታዎች ለመጋፈጥና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይረዳሃል?

በጣም ተወዳጅ ከሆኑት መካከል የሚጠቀሱትን ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነትና በትዳር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ መጻሕፍት ሰዎች ደስተኛና የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው አስችለዋል? እንደዚያ ማለት አይቻልም። በላቲን አሜሪካ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን ያተረፉና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ራስ አገዝ መጻሕፍትን ያዘጋጀ አንድ ደራሲ “ጤናማ የሆነ ወዳጅነት መመሥረትና በራስ የመተማመን መንፈስ መገንባት የሚቻልበትን መንገድ ለአንባቢዎች አቅርቧል” በማለት አንዲት ሃያሲ ተናግረዋል። ደራሲው በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደገለጸው ስኬታማ ያልሆነ ወዳጅነትን ይዞ መቀጠል ማንነትን እንደ መካድ ነው። ይህ ዓይነቱ ምክር ‘አንድ ሰው ያሉበትን ችግሮች ተገንዝቦ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ በዋነኝነት ሊያሳስበው የሚገባው የሚያስደስተውን ነገር ማድረጉ ነው’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

ራስ አገዝ መጻሕፍት አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን ሊይዙ እንደሚችሉ አይካድም። ያም ሆኖ ጎጂ የሆኑ ምክሮችንም ሊሰጡ ይችላሉ። አንድ ባለሙያ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ሊሰጥ ቢችልም በሌላ ርዕስ ላይ የሚሰጠው ምክር ግን ነገሮችን የሚያባብስ ሊሆን ይችላል። ራስ አገዝ መጻሕፍት ከሚሰጧቸው በርካታና አንዳንድ ጊዜም እርስ በርስ የሚጋጩ ምክሮች መካከል ጠቃሚ የሆነውን መምረጥ አዳጋች ይሆናል። ታዲያ እምነት ልትጥል የምትችለው ማን በሚሰጥህ ምክር ላይ ነው? እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ደራሲው ምክሩን የሰጠው ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ካደረገ በኋላ ነው? ወይስ በራሱ አመለካከት ላይ ተመርኩዞ? ደራሲው ሀብት ወይም ታዋቂነት ለማግኘት ያለው ፍላጎት በሚሰጠው ምክር ላይ ተጽዕኖ አድርጎበት ይሆን?’

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጊዜ የማይሽረው ምክር በመስጠት ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጽሐፍ እንደሆነ አስመሥክሯል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ራስ አገዝ መጻሕፍት በሚያነሷቸው በአብዛኞቹ ርዕሰ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ርዕሶች ላይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ይሰጣል። ይህ መጽሐፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚከተለውን ምክር በተግባር እንዲያውሉ አነሳስቷቸዋል፦ “አእምሯችሁን በሚያሠራው ኃይል እየታደሳችሁ መሄድ አለባችሁ፤ . . . አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌሶን 4:23, 24) መጽሐፍ ቅዱስ የችግሮቻችንን መንስኤ ማስተዋል እንድንችል የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ችግሮቹን እንዴት መቋቋም እንደምንችል ያስተምረናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚያነሳሱ አሳማኝና ጠንካራ ምክንያቶችን ይሰጣል። የሚቀጥለው ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።