በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሐሳቡን ይለውጣል?

አምላክ ሐሳቡን ይለውጣል?

አምላክ ሐሳቡን ይለውጣል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም” ይላል። በተጨማሪም አምላክ ራሱ ‘እኔ ይሖዋ አልለወጥም’ በማለት አረጋግጦልናል። (ያዕቆብ 1:17፤ ሚልክያስ 3:6) ይሖዋ አምላክ፣ አሥር ጊዜ ሐሳባቸውን የሚለዋውጡ በመሆናቸው የተነሳ እነሱን ማስደሰትም ሆነ ማመንን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት የሰው ልጆች ምንኛ የተለየ ነው!

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች ‘አምላክ ሐሳቡን ለውጦ ይሆን?’ ብለው ይጠይቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ይሖዋ አምላክ ለክርስቲያኖች ተአምር የመፈጸም ችሎታ ሰጥቷል፤ አሁን ግን ተአምር ለመሥራት የሚያስችል ኃይል አይሰጥም። በጥንት ጊዜያት ከአንድ በላይ ማግባትን ፈቅዶ ነበር፤ አሁን ግን ይህን ልማድ ከልክሏል። ይሖዋ፣ በሙሴ ሕግ ውስጥ ሕዝቡ ሰንበትን እንዲጠብቅ አዟል፤ አሁን ግን ይህን ሕግ እንድናከብር አይጠበቅብንም። ታዲያ እነዚህ ምሳሌዎች አምላክ ሐሳቡን እንደለወጠ የሚያሳዩ አይደሉም?

በመጀመሪያ ደረጃ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን፦ አምላክ የፍቅርና የፍትሕ መሥፈርቶቹን ፈጽሞ አይለውጥም። ከዚህም በተጨማሪ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት የሰው ልጆችን ለመባረክ ያለው “ዘላለማዊ ዓላማ” በፍጹም አልተለወጠም። (ኤፌሶን 3:11) ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ሰው ባሕርይ ብዙ ጊዜ እንደጠበቅከው ሳይሆን በመቅረቱ ለእሱ ያለህን አመለካከት ልትለውጥ እንደምትችል ሁሉ ይሖዋም የሁኔታዎች መለወጥ ሁኔታዎቹን በሚይዝበት መንገድ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሳዋል።

አምላክ አገልጋዮቹ ያሉበትን ሁኔታና በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት የሚሰጣቸውን መመሪያም ይለውጣል። ይህ ደግሞ ሊያስገርመን አይገባም። ለምሳሌ፣ አንድ ጎበዝ አስጎብኚ መንገዱ ላይ አደገኛ ሁኔታ ሊያጋጥመው እንደሚችል ቢያስተውል ምን የሚያደርግ ይመስልሃል? ከአደጋው ለመሸሽ እንዲችሉ በሌላ መንገድ እንደሚወስዳቸው ለሚያስጎበኛቸው ሰዎች ይነግራቸዋል። ይህ ሲባል ግን አስጎብኚው መጀመሪያ ሊሄዱበት ያሰቡትን ቦታ በተመለከተ ሐሳቡን ቀይሯል ማለት ነው? አይደለም። እስቲ አንዳንድ ሰዎችን ግራ የሚያጋቧቸውን ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ምሳሌዎች እንመርምር።

ተአምር ማድረግ የቀረው ለምንድን ነው?

አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተአምር እንዲፈጽሙ ኃይል የሰጣቸው ለምን ነበር? አምላክ እስራኤላውያንን የተመረጡ ሕዝቦቹ አድርጎ ይመለከታቸው በነበረበት ጊዜ ከእነሱ ጋር መሆኑን ለማሳየት በተደጋጋሚ ጊዜያት ተአምራት መፈጸሙን ሳታውቅ አትቀርም። አምላክ በሙሴ አማካኝነት እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲያወጣና በምድረ በዳ እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲያስገባቸው ታላቅ ኃይሉን አሳይቷል። የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በተደጋጋሚ በአምላክ ላይ እምነት እንደሌላቸው አሳይተዋል። በመጨረሻም ይሖዋ እስራኤላውያንን በመተው የክርስቲያን ጉባኤን ሲያቋቁም ለሐዋርያትና ለሌሎች ክርስቲያኖች ተአምራት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን ሰው ፈውሰዋል፤ እንዲሁም ጳውሎስ አንድን ሰው ከሞት አስነስቷል። (የሐዋርያት ሥራ 3:2-8፤ 20:9-11) እነዚህ ሐዋርያት የፈጸሟቸው ተአምራት የክርስትና እምነት በብዙ አገሮች እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ተአምር ማድረግ የቀረው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በምሳሌ ሲያስረዳ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) ወላጆች አንድን ሕፃን የሚይዙበት መንገድ አንድን ትልቅ ልጅ ከሚይዙበት መንገድ የተለየ እንደሆነ ሁሉ ይሖዋም የክርስቲያን ጉባኤ “ሕፃን” መሆኑ ሲያበቃ ጉባኤውን የሚይዝበትን መንገድ ለውጧል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በልሳን እንደ መናገር ወይም እንደ መተንበይ ያሉ ተአምራዊ ስጦታዎች ‘እንደሚቀሩ’ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 13:8

ከአንድ በላይ ማግባት የተፈቀደው ለምን ነበር?

ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት “ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሎ ሲናገር ለጋብቻ መሥፈርት ማውጣቱ እንደነበር ኢየሱስ አመልክቷል። (ማቴዎስ 19:5) የአምላክ ዓላማ፣ ጋብቻ ሁለት ሰዎች የሚመሠርቱት ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ ባደራጀበትና ሕጉን በሰጠበት ጊዜ ከአንድ በላይ ማግባት የተለመደ ነገር ሆኖ ነበር። በመሆኑም ከአንድ በላይ የማግባትን ልማድ ያስጀመረው አምላክ ባይሆንም ወይም እንዲህ ያለውን ድርጊት ባያበረታታም ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎችን ሰጥቷል። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ግን የአምላክ ቃል ከአንድ በላይ ማግባትን በግልጽ ከልክሏል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2

ይሖዋ አምላክ ሁኔታዎችን የሚያስተካክልበት የራሱ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ አንዳንድ ነገሮችን ይታገሳል። (ሮም 9:22-24) ይሖዋ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ተገቢ ያልሆኑ ልማዶችን ለጊዜው ‘የፈቀደው’ የእስራኤላውያንን ‘ልበ ደንዳናነት’ በማየት መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:8፤ ምሳሌ 4:18

ሰንበትን ማክበር የቀረው ለምንድን ነው?

አምላክ ሳምንታዊው ሰንበት እንዲከበር ያዘዘው እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ ነው። በኋላም ይህን ሕግ ለብሔሩ በሰጠው ሕግ ውስጥ እንዲካተት አደረገ። (ዘፀአት 16:22-30፤ 20:8-10) ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ‘ትእዛዛትንና ድንጋጌዎችን የያዘውን ሕግ አስወግዷል’ እንዲሁም ‘በእጅ የተጻፈውን ሰነድ ደምስሷል።’ (ኤፌሶን 2:15፤ ቆላስይስ 2:14) ‘ከተወገዱት’ እንዲሁም ‘ከተደመሰሱት’ ሕግጋት መካከል የሰንበት ሕግም ይገኝበታል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ የወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ረገድ ማንም ሰው አይፍረድባችሁ” ይላል። (ቆላስይስ 2:16) ታዲያ አምላክ የሰንበትን ሕግ የሚያካትተውን የሙሴን ሕግ ለእስራኤላውያን የሰጠው ለምን ነበር?

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል። አሁን ግን ያ እምነት ስለመጣ በሞግዚት ሥር መሆናችን አብቅቷል።” (ገላትያ 3:24, 25) አምላክ ሐሳቡን ከመለወጥ ይልቅ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በሚቆየው የሰንበት ሕግ አማካኝነት ሰዎች በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ዘወትር ጊዜ መመደብ እንዳለባቸው ሕዝቡን አስተምሯል። የሰንበት ሕግ ለጊዜው ብቻ የተሰጠ ቢሆንም አምላክ ወደፊት ያዘጋጀውንና የሰው ልጆች ከአካላዊ ችግሮቻቸውና በመንፈሳዊነታቸው ላይ ከሚሰነዘር ጥቃት ለዘላለም እረፍት የሚያገኙበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው።—ዕብራውያን 4:10፤ ራእይ 21:1-4

እምነት የሚጣልበትና አፍቃሪ አምላክ

ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች፣ ይሖዋ አምላክ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መመሪያዎችንና ትእዛዛትን እንደሰጠ ያሳያሉ። ይህ ሲባል ግን አምላክ ሐሳቡን ለውጧል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሕዝቦቹ ያሉበትን የተለያዩ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳደረገላቸው ያሳያል፤ ይህንንም ያደረገው ለጥቅማቸው ሲል ነበር። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ይሖዋ መሥፈርቶቹን ስለማይለውጥ እሱን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለብን መቼም ቢሆን ማወቅ እንችላለን። ከዚህም በላይ አምላክ ተስፋ የሰጣቸው ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ “ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ . . . የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ ያቀድሁትን እፈጽማለሁ” ብሏል።—ኢሳይያስ 46:10, 11

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ የፍቅርና የፍትሕ መሥፈርቶቹን ፈጽሞ አይለውጥም

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጳውሎስ፣ ከጊዜ በኋላ ተአምራዊ ስጦታዎች ‘እንደሚቀሩ’ ተናግሯል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ ዓላማ፣ ጋብቻ ሁለት ሰዎች የሚመሠርቱት ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ነበር